Tuesday, February 23, 2016

ቃል ኪዳን!


“ከመረጥኹት ጋራ ቃል ኪዳኔን አደረግኹ” (መዝ. 88/89፥3)።
በዚህ ቃል ሽፋንነት የገባው የስሕተት ትምህርት፥ የክርስቶስን የመካከለኛነት ስፍራ ለፍጡራን አሰጥቷል። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን ከተለያዩ ቅዱሳን ጋር ስለ ልዩ ልዩ ጕዳዮች የገባውን ቃል ኪዳን መነሻ በማድረግና፥ “ከመረጥኹት ጋራ ቃል ኪዳኔን አደረግኹ” የሚለውን ቃል በመታከክ፥ በዐዲስ ኪዳንም ኀጢአተኞች ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡበትን የተለያየ ቃል ኪዳን ለቅዱሳን ሰጥቷል የሚሉ አሉ።
በቅዱሳን ስም በተደረሱት ገድላትና ድርሳናት ውስጥ፥ ከራስ ዐልፈው ሰባትና ከዚያም በላይ ያለውን ትውልድ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያስገቡ ቃል ኪዳኖች እንዳሉ ተገልጧል። ቃል ኪዳኖቹ የተመሠረቱትም በቅዱሳን ስም የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነው። ሌላው ቀርቶ የአንዱን ቅዱስ ገድል የጻፈ፥ ያጻፈ፥ ያነበበ፥ የተረጐመ፥ የሰማ፥ ያሰማ እንኳ መንግሥተ ሰማያትን እንደሚወርስ ተስፋ የሚሰጡ ገድላት በርካታ ናቸው። ይህም በራእ. 1፥3 ላይ፥ “ዘመኑ ቀርቧልና፥ የሚያነብበው የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው” ከሚለው የተኰረጀ ሊኾን ይችላል።
በመዝሙረ ዳዊት 88/89፥3 ላይ የተገለጠው፥ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንጂ ሌሎችን አይወክልም። በቍጥር 4 ላይ፥ “ለባሪያዬ ለዳዊት ማልኹ፤ ዘርኽን ለዘላለም አዘጋጃለኹ፤ ዙፋንኽንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለኹ” ማለቱም ይህንኑ ያስረዳል። ቃል ኪዳን የገባው የማይዋሽ እግዚአብሔር በመኾኑ፥ “ኪዳኔንም አላረክስም፤ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም። ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልኹ። ዘሩ ለዘለዓለም፥ ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሓይ ይኖራል። ለዘለዓለም እንደ ጨረቃ ይጸናል። ምስክርነቱ በሰማይ የታመነ ነው” ብሎ ነገሩን እንዳጻናለት ይናገራል (ቍጥር 34-37)።
ይህ ስለ ዙፋኑ መጽናት የተገባው ቃል ኪዳን ለጊዜው ጥላነቱ በሰሎሞን ሲታይ፥ በክርስቶስ ግን ተፈጽሟል (2ሳሙ. 7፥12-16፤ ሉቃ. 1፥32፤ ዕብ. 1፥5፡8፤ ራእ. 22፥11)። እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታማኝ አምላክ በመኾኑ፥ ዳዊት ከሞተ በኋላ ልጁ ሰሎሞን በቃል ኪዳኑ ውስጥ የነበረውን ውል አፍርሶ በመገኘቱ መንግሥቱ መቀደድ ቢኖርበትም፥ እግዚአብሔር ግን ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን ዐስቦ ይህን በሰሎሞን ዘመን አላደረገበትም (ዳን. 9፥4፤ 1ነገ. 9፥5-7፤ 11፥1-13)።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ (በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት) ቃል ኪዳን ከተገባላቸው መካከል ዋናዎቹ፥ አዳም፥ ኖኅ፥ አብርሃም፥ ሙሴና ዳዊት ናቸው። ለአዳም የተሰጠው ቃል ኪዳን መልካሙንና ክፉውን በሚያስታውቀው ዛፍ ምልክትነት፥ ዘላለማዊ ሕይወትን የሚያስገኝ ተስፋን የያዘ ነበር። የቃል ኪዳኑ ተቀባዮች አዳምና ሔዋን በኪዳኑ ስላልጸኑ ሞት ገዛቸው (ዘፍ. 2፥8-17፤ ሆሴ. 6፥7)።
ከአዳም ቀጥሎ ቃል ኪዳን የተሰጠው ለኖኅ ሲኾን፥ ምድር ዳግመኛ በጥፋት ውሃ እንዳትጠፋ የቆመ ኪዳን ነው። ይህ በምድር ላይ የመኖርን ተስፋ የያዘው ኪዳን፥ በቀስተ ደመና ምልክትነት ተገልጦ ለዓለም ሕዝብ ኹሉ ያገለግላል (ዘፍ. 9፥1-17)።
እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን፥ በብሉይ ኪዳን ጐላ ያለ ስፍራ ከተሰጣቸውና በዐዲስ ኪዳን ፍጻሜ ካገኙት ቃል ኪዳኖች መካከል ይጠቀሳል። የቃል ኪዳኑ ተቀባዮች ለጊዜው ምድራዊቱን ከነዓንን የወረሱት አብርሃምና በይሥሐቅ በኩል የተቈጠሩት ዘሮቹ ኹሉ ሲኾኑ፥ ፍጻሜው ግን አይሁድ፥ አሕዛብ ሳይባል አብርሃምን በእምነት በመምሰላቸው የአብርሃም ልጆች የኾኑት ኹሉ ናቸው (ገላ. 3፥7-9፡29፤ ሮሜ 4፥11-12፤ 9፥7-8)። የዚህ ቃል ኪዳን ምልክት ግዝረት፥ የቃል ኪዳኑ ተስፋ ደግሞ በዘሩ የአሕዛብ መባረክና ከነዓንን መውረስ ነው (ዘፍ. 17፥1-21፤ ሮሜ 4፥11)።
የምድር አሕዛብ ኹሉ የተባረኩበት የአብርሃም ዘር ክርስቶስ፥ የምድራዊቱ ከነዓን አማናዊት የኾነችውን ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን የሚያወርስ በመኾኑ፥ ለቃል ኪዳኑ ፍጻሜን ሰጥቷል (ገላ. 3፥16)። እግዚአብሔር በክርስቶስ ያደረገው ኹሉ ለአብርሃም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት መኾኑንም ቅዱሳን መስክረዋል (ሉቃ. 1፥54፡73)።
በመቀጠል ደግሞ ለሙሴ የተሰጠውን ቃል ኪዳን እናገኛለን (ዘፀ. 19፥5-6፤ 24፥7-8)። የቃል ኪዳኑ ተቀባዮች የኾኑት ሕዝበ እስራኤል፥ የአብርሃምን የቃል ኪዳን ምልክት ተከትለው ሰንበታቱን መጠበቃቸው ለዚህ ቃል ኪዳን ምልክት ኾኗል (ዘፀ. 31፥13፤ ሕዝ. 20፥10-17)። በቃል ኪዳኑ የተሰጣቸው ተስፋ በአገራቸው ሕይወትን ማግኘት ነው። ይህንም ገና ከምድረ ግብጽ ሳይወጡ በነበረው ዕለት ምሽት ላይ ያረዱት የፋሲካ መታሰቢያ በግ ደም አረጋግጦላቸዋል (ዘፀ. 12፥21-28)።
ከግብጽ ምድር ወጥተው ወደ ሲና ተራራ ሲደርሱ፥ ሕጉን በድንጋይ ጽላት ጽፎ ይጠብቁትና በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል ቃል ኪዳን ይኾን ዘንድ ለሙሴ ሰጠው። ይህም ብሉይ ኪዳን ተብሎ የተጠራው ነው (ዘፀ. 19፥20፤ 31፥18፤ 20፥1-17፤ 34፥28፤ ዘዳ. 4፥13)። በእንሰሳት ደም የቆመው ብሉይ ኪዳን ወደ ፊት ለሚመጣው ዐዲስ ኪዳን መንገድ ጠራጊ እንጂ በራሱ ቋሚነት አልነበረውም። የጽላቱ ተሰብረው መተካታቸው፥ የማደሪያው ድንኳን ሰሎሞን በሠራው ቤተ መቅደስ መተካቱ፥ የመሥዋዕት መደጋገምና የመሳሰሉት ኹኔታዎች ለጊዜያዊነቱ ምልክቶች ተደርገው ይወሰዳሉ። ይበልጥ ደግሞ ትንቢቱ ይህን አረጋግጧል (ዘዳ. 18፥15፤ ኤር. 31፥31)።
ቃል ኪዳን የሚጸናው ኹለቱም ወገኖች ሲጠብቁት ብቻ ነው። ከኹለቱ አንዱ ጠብቆ ሌላው ቢያፈርሰው ቃል ኪዳን መኾኑ ይቀራል። ብሉይ ኪዳን ጊዜያዊነቱ ሳያንስ ሕዝቡ ሊጠብቀው ባለመቻሉ ቃል ኪዳንነቱ ቀረ። እግዚአብሔርም ከዚህ በብዙ መንገድ የተሻለውን ዐዲስ ቃል ኪዳን እንደሚገባ ተናገረ (ኤር. 31፥31-34)። ይህም ስለ ዐዲስ ኪዳን የተነገረ ትንቢት በመኾኑ፥ በዕብራውያን 8 ላይ ተፈጻሚ ኾኖ ተጠቀሰ። ዐዲስ ኪዳን የተሻለና የበለጠ ኪዳን በመኾኑ ብሉይ ኪዳን ከነጓዙ ፍጻሜ አግኝቶ እንደሚቀርና የሚጠቀምበት ቀርቶ የሚያስበው እንኳ እንደማይኖር እግዚአብሔር በአጽንዖት ተናገረ (ኤር. 3፥16)።
እግዚአብሔር እስከዚህ ድረስ ለተለያዩ ቅዱሳንና ለአጠቃላዩ የእስራኤል ሕዝብ ገብቶ የነበረውን ቃል ኪዳን ኹሉ በመጠቅለል፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ዐዲስና ለዘላለም የማይፈርስ፥ ተጨማሪ የማያስፈልገው ቃል ኪዳን ገባ። እርሱም በገዛ ደሙ የመሠረተው ዐዲስ ኪዳን ነው (ሉቃ. 22፥19-20፤ ኢሳ. 42፥6-7)። ይህ ኪዳን በክርስቶስ ለሚያምኑ ኹሉ የተሰጠ ሲኾን፥ የዘላለም ሕይወትን ተስፋ የያዘ ቃል ኪዳን ነው። የተስፋው ምልክቶችም ጥምቀትና ቅዱስ ቍርባን ናቸው (ማር. 16፥16፤ 1ቆሮ. 11፥23-26፤ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 1972፣ ገጽ 80)።
ዐዲስ ኪዳን ብሉይ ኪዳንን በከፊል ሳይኾን ሙሉ በሙሉ ተክቷል። ዐዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ክብሩ የጸናበት፥ ኹሉ የተፈጸመበት ታላቅ ቃል ኪዳን መኾኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍትም መስክረዋል፤ “ወበምክረ ዚኣከ ወልድከ ዋሕድ ኢየሱስ ዘተሰቅለ በእንተ መድኀኒትነ ዘበቃለ ኪዳንከ ቦቱ ገበርከ ሠሚረከ ቦቱ። - ለድኅነታችን በተሰቀለው በአንድያ ልጅኽ በኢየሱስ በባሕርይኽ ምክር ደስ ተሰኝተኽበት ቃል ኪዳንኽን ኹሉ በእርሱ አድርገኻል” (መጽሐፈ ቅዳሴ 1984፣ ገጽ 65)።  
እንዲሁም በእልመስጦአግያ፥
“ከመ ታእምሩ ፈቃዶ ለኢየሱስ ክርስቶስ ወትሌብዉ ምስጢረ መድኀኒትክሙ ኦ አንትሙ እደው ወአንስት ቅዱሳት እለ ሀሎክሙ ውስተ ተመክሖ በክርስቶስ፥ ወኩኑ አሐደ ምስለ ብእሲ ዘውስጥ አንትሙኬ እለ አጽንዐ እግዚአብሔር ኪዳኖ ምስሌክሙ ወሤመ መንፈሶ ውስቴትክሙ፡፡”
ትርጓሜ፥ “የኢየሱስ ክርስቶስን ፈቃድ ታውቁ ዘንድና የደኅንነታችኹን ምስጢር ታስተውሉ ዘንድ፥ በክርስቶስ ትምክሕት ያላችኹ እናንተ ወንዶችና ቅዱሳት ሴቶች ሆይ፥ ከውስጣዊ ሰውነት ጋር አንድ ኹኑ፤ እግዚአብሔር ኪዳኑን ከእናንተ ጋር ያጸና መንፈሱንም በውስጣችኹ ያሳደረ እናንተ ናችኹ እኮ” (ሃይማኖተ አበው 1986፣ ገጽ 24)።
የእግዚአብሔር የባሕርይ ምክርና ሐሳቡ ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜም በክርስቶስ በኩል በገባው ዐዲስ ኪዳን በኩል ተፈጽሟል። እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር ባለው ታሪክ የገባው የመጨረሻው ቃል ኪዳን ዐዲስ ኪዳን ብቻ ነው። በዚህ ኪዳን ያልተፈጸመለት ወይም የቀረው ነገር ኖሮ፥ በሌላ ቃል ኪዳን ለመፈጸም በማሰብ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባ ሌላ ቃል ኪዳን ገብቷል የሚለው ትምህርት ልብ ወለድ ከመኾን አይዘልም፤ ምክንያቱም የዘመን ፍጻሜ በኾነው ባለንበት ዘመን፥ እግዚአብሔር ለማድረግ ያሰበው፥ ነገሮችን ኹሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል እንጂ ሌላ ቃል ኪዳን ለመግባት አይደለም (ኤፌ. 1፥10)።
ከላይ ለማሳየት እንደ ተሞከረው፥ ለቀደሙት አበው የገባው ቃል ኪዳን፥ ከወቅቱ ኹኔታ ጋር በተያያዘ መንገድ፥ ወይም ስለ ወደ ፊቱ ተስፋ ነበር እንጂ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባ ቃል ኪዳን አልነበረም፤ እንዲህ ያለውን ቃል ኪዳን ከማንም ፍጡር ጋር አልገባም። ምናልባት ለአዳም የገባው ቃል ኪዳን በአዳም ባይፈርስ ኖሮ፥ ለዘላለም በሕይወት መኖርን የሚያስገኝ ቃል ኪዳን ይኾን ይኾናል። ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ ወደ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበትን ቃል ኪዳን የገባው ግን በክርስቶስ በኩል ብቻ ነው።
በሐሰት ለቅዱሳን በዐዲስ ኪዳን ተገባ በሚባለው ቃል ኪዳን መሠረት፥ እንዲህና እንዲያ ያደረገ ይህንና ያን ያገኛል የሚል ተስፋ በብዙ አዋልድ መጻሕፍት በስፋት ተጽፎ እናነባለን። አብዛኛው ቃል ኪዳን ተሰጠ ተብሎ የሚተረከው ቅዱሳኑ ሊሞቱ ሲሉ በመጨረሻዋ ሰዓት ላይ ነው። እንዲህ ከኾነ ታዲያ በዐዲስ ኪዳን መጥምቁ ዮሐንስ፥ ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ፥ እና ያዕቆብ በግፍ የተገደሉ ቅዱሳን ናቸው፤ ሊሞቱ ሲሉም ኾነ ከዚያ በፊት ቃል ኪዳን እንደ ተገባላቸው በሐዲስ ኪዳን ውስጥ አናገኝም (ማቴ. 14፥10-12፤ ሐ.ሥ. 7፥6 12፥2)። ለነዚህ ቅዱሳን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ሰዎች ከልባቸው አንቅተው (አመንጭተው) በደረሱላቸው ድርሰትና ገድላት ውስጥ ግን፥ የተለያዩ ቃል ኪዳኖችን ጻጽፈው ሊያስነብቡን ቢከጅሉም አንድም እውነትነት የለውም።
ዛሬ ብዙዎቹ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባልኾነ ቃል ኪዳን ተታለዋል። ስለዚህ በክርስቶስ አዳኝነት አምነው ከመጽደቅና በእርሱ ኖረው መልካም የሥራ ፍሬን ከማፍራት ይልቅ፥ በኀጢአት ላይ ኀጢአትን በመጨመር ከእግዚአብሔር ባልኾነው ቃል ኪዳን እየተኵራሩ፥ ‘በእገሌ ቃል ኪዳን መሠረት እንዲህ ካደረግኹ አልኰነንም’ ብለው ራሳቸውን ይሸነግላሉ። የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ይላቸዋል፤ “ለዐመፀኞች ልጆች ወዮላቸው፥ ይላል እግዚአብሔር። ከእኔ ዘንድ ያልኾነ ምክር ይመከራሉ። ኀጢአትንም በኀጢአት ላይ ይጨምሩ ዘንድ ከመንፈሴ ዘንድ ያልኾነውን ቃል ኪዳን ያደርጋሉ።” (ኢሳ. 30፥1)።
ምንጭ፦ የተቀበረ መክሊት 3ኛ ገጽ 106