“የሊቀ ጳጳሱ ልጅ ነኝ” በሚል የቀረበን ጥያቄ ውድቅ አደረገው።

(መማሌት ኪዳነወልድ)
የፍርድ ቤት ክርክሩ ከ3 ዓመት በላይ ፈጅቷል      የሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ሚካኤል፤ በነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ከሞቱ በኋላ ነው፤ “የሊቀ ጳጳሱ ልጅ ነኝ” የሚል የወራሽነት አቤቱታ ለፍ/ቤት የቀረበው፡፡ “የሟች ልጅ ነኝ” የሚል አቤቱታ ያቀረቡት አቶ ዮሐንስ ተክለሚካኤል፤ ጳጳሱ እንዳሳደጓቸው በመግለጽና ተወላጅነቴን ያስረዱልኛል ያሏቸውን ሰነዶች በማያያዝ፣ የሰዎችን ምስክርነት ለፍ/ቤት አሰምተዋል፤ ፍ/ቤቱም ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም የልጅነት ማረጋገጫ ውሳኔውን አሳወቀ፡፡ ጉዳዩ ግን በዚሁ አልተቋጨም፡፡ የሊቀ ጳጳሱ እኅት፤ የፍ/ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ጠይቀዋል፡፡ በአቶ ዮሐንስ የቀረበው የልደትና የጥምቀት ወረቀቶች በአግባቡ የተረጋገጡ አይደሉም፤ ልጅነቱ በሳይንሳዊ መንገድ በዲኤንኤ መረጋገጥ አለበት በማለት መቃወሚያ አቅርበዋል - የጳጳሱ እኅት ወ/ሮ በላይነሽ ዓባይ፡፡ “ሊቀ ጳጳሱ አሳድገውኛል ከማለት ውጪ፣ ሊቀ ጳጳሱ በልጅነት እንደተቀበሉት የሚያሳይ ማስረጃ አልቀረበም፤” ያሉት ወ/ሮ በላይነሽ፤ በተጨማሪም በቀረበው የጥምቀትና የልደት ካርድ ላይ የአባት ስም የተቀየረው ሊቀ ጳጳሱ ከሞቱ በኋላ ነው፤” ብለዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ በሰጡት መልስ፣ “ወ/ሮ በላይነሽ የጳጳሱ እኅት መሆናቸውን አላውቅም፡፡ በሕይወት እያሉ እኅት አለኝ አላሉኝም፤” ብለዋል፡፡ “የአባቱን ስም ቀይሯል” ለሚለው ተቃውሞ አቶ ዮሐንስ ምላሽ ሲሰጡም፤ በሟች አባቴና በእናቴ ስምምነት፤ እናቴ ቤተሰቦችጋ ነው ያደግሁት፡፡ በዚህ ምክንያት፣ በእናቴ አባት ስም ስጠራ ቆይቻለሁ፤” ብለዋል፡፡ “ከልደትና ከጥምቀት ወረቀት ውጭ፤ የሰው ምስክሮች አስደምጫለሁ፡፡ ከምስክሮቹ አንዷም እናቴ ናት፤” በማለትም ተከራክረዋል፡፡ የይግባኝ ክርክሩን የዳኘው ከፍተኛ ፍ/ቤት፤ በአቶ ዮሐንስ ቀረበው የልደት የምስክር ወረቀት ሕጋዊነት እንደሌለው ገልፆ፤ በክሊኒክ የተመዘገበ የወሊድ መረጃዎችንም ጠቅሷል፡፡ በክሊኒኩ የተመዘገበው የወላጅ እናት አድራሻ የተሳሳተ እንደሆነ ፍ/ቤቱ ጠቅሶ፤ የወላጅ እናት ዕድሜ ተብሎ የተመዘገበው መረጃም፤ ከዮሐንስ እናት ዕድሜ ጋር በሰፊው ይራራቃል፤ ብሏል፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እስከ መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም ጉዳዩን ሲመረምር ከቆየ በኋላ በሰጠው ውሳኔ፣ አቶ ዮሐንስ “የሊቀ ጳጳሱ ልጅ አይደሉም፤” በማለት የሥር ፍ/ቤትን ውሳኔ ሽሯል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግ፣ ለማዕርገ ጵጵስና የሚመረጡት በሥርዓተ ምንኩስና በድንግልና መንኩሰው በክህነት ቤተክርስቲያኒቱን የሚያገለግሉ ሲሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱም ይህንኑ በማረጋገጥ በጣልቃ ገብ መከራከሯን የፍርድ ሐተታው ያመለክታል፡፡     
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
December 7, 2015 at 11:55 PM

የአባ ሰላማ (አባ ዲያብሎስ) እና የአንተ ውሸትና ስም ማጥፋት ገደል ገባ በለኛ። ልክ እኮ አንሶላ ያጋፈፉችሁ ነበር የምትመስሉት።

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger