Friday, November 27, 2015

ፖሊስ መምህር ግርማ ወንድሙን በተጨማሪነት በግድያ ወንጀል መጠርጠሩን ገለፀ።

ፖሊስ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መምህር ግርማ ወንድሙ በተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል የተፈቀደው ዋስትና ላይ የመርማሪ ፖሊስ ይግባኝ ውድቅ ተደረገ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የምርመራ ቡድን ከተጠርጣሪው ቤት ያገኘሁት ስምንት ሲም ካርድ ላይ እንዲጣራ ለኢትዮ ቴሌኮም ልኬ ውጤት እየጠበኩ ነው፤ ሌላ ተጠርጣሪም ስላለ ያን ለመያዝ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ቢልም የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተጠየቀው የምርመራ ስራ ተጠርጣሪውን ዋስትና የሚያስከለክል አይደለም በማለት ዋስትና መፍቀዱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ መርማሪ ቡድኑ ይግባኝ ጠይቆ ዋስትናውን በማሳገድ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ተከራክሯል።

ችሎቱ የሁለቱን ወገን ክርክር መርምሮ ፖሊስ የተሰጠው ጊዜ በቂ ነው፤ ቀሪ ምርመራውን ለማድረግም ተጠርጣሪውን ዋስትና የሚያስከለክል አይደለም ሲል የተፈቀደውን ዋስትና አጽንቶታል።

በዚህም መምህር ግርማ በተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል በ50 ሺህ ብር፣ በሀሰተኛ ሰነድ በመገልገል ደግሞ በ40 ሺህ ብር በጠቅላላው የ90 ሺህ ብር ዋስትና ተፈቅዶላቸዋል።

በተያያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን መምህር ግርማ መንድሙን ከዚህ በፊት ከተጠረጠሩበት ወንጀል በተጨማሪ በግድያ ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ሲል አመልክቷል።

የምርመራ ቡድኑ ጉዳዩን ለፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ያመለከተ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠረጠረበትን የግድያ ወንጀል ዝርዝር እና የምርመራ ሂደቱን ለችሎቱ እንዲያቀርብ ለህዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

ከፖሊስ ባገኘነው መረጃ መሰረት መምህር ግርማ ወንድሙ እስከ ህዳር 20 2008 ዓ.ም ድረስ በእስር የሚቆዩ ይሆናል።







በሀይለኢየሱስ ስዩም  

- See more at: http://www.fanabc.c