በቤተ ክርስቲያን ድክመትና የቁልቁሊት ጉዞ ትልቁን
ድርሻ የሚወስደው ከውስጥ የሚነሳው ሽኩቻ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል። ከኬልቄዶን ጉባዔ አንስቶ በየዘመናቱ ሂደት በየክፍልፋይ አብያተ
ክርስቲያናት ውስጥ ሲታይ የቆየው መለያየትና መናቆር መነሻው በመንፈሳዊ ሥልጣን ላይ በሚቀመጡ መሪዎችና ሊቅ ነን በሚሉ ሹመኞች
እንደሆነ ብዙ ዋቢ ማቅረብ ይቻላል። ተመሪው ሕዝብም በሚናቆሩ መሪዎች ሁለት ወገን ቆሞ ለአንዱ ወገን አሸናፊነት የቤተክርስቲያኒቱን
ግድግዳ እየነቀለ የማፍረሱን ሂደት ማፋጠኑ ሌላው ጉዳት ነው። ሥልጣኑ መንፈሳዊ ሆኖ ሳለ ሽኩቻው ወደሥጋዊ ሕይወት በማድላቱ በመደማመጥ
መፍትሄ ለማምጣት ባለመቻሉ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን እየተዳከመች በመሄድ ላይ ትገኛለች። በዚያው አንጻር ያሉባትን ተግዳሮቶችና
ጊዜውን የዋጀ ክህሎት ያለው ብቁ አመራር በመፍጠር ስላልተቻለ ችግሩ እንዳለ ሊቆይ ችሏል። በዓለም ላይ ካሉ አብያተ ክርስቲያናት
ውስጥ አንዷ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም አንዷ የችግሩ ሰላባ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን መካድ አይቻልም።
የሩቁን ትተን የራሷን ቤተ ክርስቲያን ላዕላይ
መዋቅር ራሷ መምራት ከጀመረችበት ከ1950ቹ አንስቶ ብንመለከት ችግሮች እየገዘፉ እንጂ እንየቀነሱ አለመሄዳቸው አስገራሚ ነው።
በተለይም ከአፄው ስርወ መንግሥት መውደቅ ጀምሮ አሁን እስካለው እስከ ዘመነ ኢህአዴግ ድረስ ቤተክርስቲያን በአስተዳደሯ ተዳክማ፤
በተከታዮቿ አሽቆልቁላ መሄዷገሃዳዊ እውነት ነው። ጳጳሳቶቿ ፓትርያርካቸውን ከሰው በላው ደርግ ጋር ወግነው የበሉት ሥልጣን እናገኛለን
ብለው ካልሆነ ስለእውነትና ስለቤተ ክርስቲያን ዝም ማለታቸው ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ደርግ ፓትርያርክ ሲሾምላቸው አሜን ብለው
መቀበላቸው ሥጋዊ ፍርሃት አሸንፏቸው ካልሆነ በስተቀር ለቤተ ክርስቲያን ልዕልናና ስለክርስቶስ ወንጌል ግድ ብሏቸው ሊሆን አይችልም።
እንዲያም ሆኖ ከነፈሰው ጋር የሚነፍሱት ጳጳሳት «ብፁዕ ወቅዱስ» ሲሉ በነበሩት ፓትርያርክ ላይ ሌላ ፓትርያርክ ለመሾም ሰላማዊ
ሰልፍ በመውጣት ወደምርጫ የገቡት ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እድገት ተጨንቀው አለመሆኑንም አስረግጦ መናገር ይቻላል።
በዘመነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፕትርክና
የተሻለ አስተዳደርና የልማት ምልክቶች የታየበት ጊዜ ቢሆንም ዘመኑን የዋጀ መዋቅራዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ የሰውና የሀብት ብክነቱ
ግን ወደር ያልተገኘለት ሆኖ አልፏል። በሌላ መልኩም ከታዩት ስህተቶች
ውስጥ ደግሞ ወደመንፈሳዊ ሥልጣን እንዲመጡ የተደረጉት ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ለለውጥ ሳይሆን ለውድቀት በር የከፈተ መሆኑ ሌላው ጉዳይ
ነው። እንኳን ለሊቀ ለሊቀጳሳትነት ይቅርና ለደላላነት የማይመጥኑ ሰዎች በአፈፋ በገፈፋ መሾማቸው በአሳፋሪነቱ ወደር የለውም። ጳጳሳቱ
የታወቀና ያልታወቀ የግል ኃጢአታቸው በአደባባይ የተነበበት እንዲሁም በዘረኝነት፤ በጎጠኝነት፤ በአፍቅሮ ንዋይ ፤ በሥልጣን ጥመኝነት፤
በአድመኝነት ራሳቸውን በተግባር ያሳወቁበት ጊዜ መሆኑ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ድክመት ትልቁን ድርሻ መውሰዱን መሸፈን ከእውነታው ማፈግፈግ
ይሆናል።
እነዚሁ ጳጳስ የተባሉት ሰዎች ከማኅበረ ቅዱሳን
ጋር አብ’ረው ለነውራቸው መሸፈኛ ያገኙ መስሏቸው ቤተክርስቲያኒቱን ሲያምሱ መገኘታቸው ለወንጌል አገልግሎት መዳከምና እረኛ አልቦ የሆኑ ተከታዮቿ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲኮበልሉ የሆነበትም
ዘመን ነበር። አስቀድሞ በተደረገ ፖለቲካዊ ምርጫ ወደፓትርያርክነት የመጡት አባ ማትያስም ከነበረው የተሻለ አስተዳደር ለመፍጠር
ይቅርና የነበረውን ለማስቀጠል አለመቻላቸው ሌላው የቀጣይ ውድቀት አንዱ ማሳያ ነው።
የመሻሻል ምልክት የሌለውንና የጅምላ ሹመኞቹን
የጳጳሳት ጉባዔ በርዕሰ መንበርነት የሚመሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንዴት አድርገው ቤተክርስቲያኒቱን ወደአንድ የአመራር
ከፍታ ሊያሳድጉ ይችላሉ? በጭራሽ አይችሉም! ምክንያቱም ፓትርያርክ ከመሆናቸው በፊት ያልነበራቸውን ችሎታ ዛሬ ከወዴት ያገኙታል?
በብዙ ሚዛን አሁን ካለበት ሁኔታ የተሻለ የነበረውን የአቡነ ጳውሎስን አስተዳደር በምኒልክና አስኳል ጋዜጣ ላይ በመተቸት ይታወቁ
የነበሩት አቡነ ማትያስ የሥልጣኑ ሉል እጃቸው ላይ ሲወድቅ ወሬውን በተግባር ከማሳየት ይልቅ ለባለጉዳዮች «ተኝቷል በሉልኝ» በማለት
በር ዘግተው መደበቅን ምርጫቸው ማድረጋቸው በሰፊው ይወራል።
ከዚህ በፊት በዚሁ መካነ ጦማር ላይ የሙስና
ታሪኩን በቅጽል ስሙ ያወጣነውና ማኅበረ ካህናቱ «ኑረዲን» የሚሉት(ንቡረእድ) ማንም እንዳይገባ በሩን ዘግቶ ለፓትርያርኩ የብቃት
ጉድለት ተጨማሪ ድርሻ የወሰደ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በሩ ቢከፈትስ ፓትርያርኩ መፍትሄ የመስጠት ብቃት አላቸው ወይ? ብለው የሚጠይቁ
ብዙዎች ናቸው። አንድ ሰሞን ትኩስ በሚሆንና ቆይቶ በሚባረድ ስሜት
ውስጥ ሆነው ፈታኝ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ችግር መፍታት አይቻልም። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ትኩስም፤ በራድም በመሆን የለውጥ
ሰው መሆን አይችሉም። አንዱን መያዝ የግድ ይላል። በር እየዘጉ መደበቅም ችግሮቹንና ሸክሙን ከሚያበዛ በስተቀር እንከኖችን ሊሰውር
የሚችል የምትሃት መንገድ አይደለም። መደበቅን እንደምርጫ ከወሰዱ ደግሞ ሲመተ ፓትርያርኩን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች ሰጥተው
ወደገዳም መሄድ ይሻላል።
ሌላው የቤተ ክርስቲያኒቱ የአመራር ጉድለት
«ቋሚ» የሚባለው ነገር ቋሚ ያልሆነው ተለዋዋጭ ሲኖዶስ ጉዳይ ነው። ጳጳሳት ስለሚገኙት ብቻ «ቋሚ» ሊባል አይችልም። በየ3 ወሩ
በሚደረግ መለዋወጥ «ቋሚ» የሆነ አመራር ሊሰጥ የሚችለው በምን መለኪያ ነው? የሲኖዶስ ውሳኔዎች አፈጻጸም የሚዘገዩት ወይም ለችግሮች
አፋጣኝ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በውዝፍ እየተተወ የሚቀረው 3 ወራት ለሥራ በቂ ጊዜ ባለመሆኑ የተነሳ እንደሆነም መዘንጋት የሌለበት
ነጥብ ነው። ቢያንስ ለአንድ ዓመት የሚቆይና ቋሚ ሊያሰኝ የሚችል ሥራ መፈጸም የሚችል የቋሚ ሲኖዶስ ያስፈልጋል። በየ3 ወራት መቀያየር
ያስፈለገው ጳጳሳቱ ከአዲስ አበባ ውጪ መቆየቱ ስለሚሰለቻቸው እንደእረፍት ጊዜ የመለዋወጫ መንገድ የወሰዱበት ዘዴ ሊሆን ይችላል
እንጂ ሥራ ለመስራት አይደለም። ለዚያውም መሥራት የማይችሉ ሠራተኞች አድርገው አድርገን ከቆጠርናቸው ነው። ከራሱና ከዘር ጉዳይወጥቶ የቤተ ክርስቲያን ችግር ግድ የሚለው ጳጳስ ከቶውኑ
አለን? እነ አባ ማቴዎስ አሁን ባሉበት ሥልጣን እየሰሩ ያለው ሲታይ ለፓትርያርክነት መወዳደራቸው በራሱ ቤተ ክርስቲያኒቱን ራስ
ዳሽንን ከሚያክል የተራራ ሸክም ገላገላት የሚያሰኝ ነው። ዛሬ ካሉት ጳጳሳት መካከል ጵጵስና ከመሾማቸው በፊት የጵጵስና የክብር
ልብስ በማሰፋት በጉጉት ሲጠባበቁ የቆዩ እንደነበሩ እናውቃለን። አንዳንዶቹም ጳጳስ ሳይሆኑ በፊት የጵጵስናውን ድስት አጥልቀው ፎቶ
ተነስተውም ታይተዋል። ዘመቻና ዲናር የሲመት መስፈርት በመሆኑ የተነሳ የተሻለ የአስተዳደር ለውጥ አልታየም፤ ወደፊትም አይታይምም።
አንድ ጳጳስ፤ «በኛ ጊዜ ይሄን ያህል ገንዘብ ያስከፍል ነበር» ሲሉ ሰምተን አፍረንባቸዋል።
ከዚህ በታች የምንመለከተው ፎቶ ግራፍም የዚያ የሹመት ስካር ውጤት ነው። አባ
ገ/ሚካኤል ይባላል። ከዚህ በፊት በቃሲም ሥላሴ ሰባኬ ወንጌል ነበር። ከዚያም ኬንያ ከተላከ በኋላ ፈርጥጦ ከአፈንጋጩ ሲኖዶስ የተቀላቀለ
ነው። አሁን ደግሞ ሳይሾም በፊት የሲመት አራራውን እየተወጣው ይገኛል። ነገ ደግሞ ወይም በፈርጣጩ ሲኖዶስ አለያም በዘመቻ መልክ
በሀገር ቤቱ ልማት የለሽ ሲኖዶስ ሊሾም ይችል ይሆናል።
ጳጳስ ከሆኑት መካከልም እንደዚሁ ሲያደርጉ የነበሩ ተሹመው ታይተዋል። ነገ
ስላለመሆኑ ማረጋገጫ የለም። የጵጵስናውን ሹመት በተስፋ የሚጠባበቁትም ልብሱ ብል እስኪበላው ድረስ አሰፍተው ጥቅምትና ግንቦትን
በህልም ይቋምጣሉ።
ቤተ ክርስቲያን ግን እያሽቆለቆለች፤ አስተዳደሯ
እየሞተ ነው። እየገደላት ያለው ማነው?