Sunday, November 5, 2017

እውነቱን ፈልፍለን ለማግኘት መጸሐፎቹን እንመርምር!


መነሻ ሃሳብ «ገመና ዘ81ዱ» መጽሐፍ (ጽሑፉ በድጋሚ ተስተካክሎና ረዘም ተደርጎ የቀረበ ስለሆነ በትዕግስት እንዲያነቡ ይጠየቃሉ።)

ሀተታ፤
በኦርቶዶክሳውያን ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከታች ጀምሮ እስከላይኛው እርከን ድረስ ያለው ሰው ስህተት ይኖርብናል ወይም ልንሳሳት እንችላለን ብሎ የሚያስብ ሰው ማግኘት ከባድ ነው። በክርስቶስ ደም የተመሰረተችው ቤተክርስቲያን ፍጽምትና ንጽሕት መሆኗን በመቀበል  መሪውና ተመሪውም በዚያው ዓይን ራሱን እያየ እኛ ፍጹማንና ንጹሐን ነን፣ የስህተት አስተምህሮ አይነካካንም በሚል ሰውኛ ተመካሂነት ራሱን በማስጠለል፤ ስህተትን አምኖ ለመቀበል አይፈልግም። ነገር ግን ትውልዱ አንባቢ፣ ጠያቂ፣ ስንዴውን ከእንክርዳዱ በመለየት ንጹሑን ቃለ እግዚአብሔር መመገብ የሚፈልግ በመሆኑ የስህተት አስተምህሮ አለ፤ በእግዚአብሔር ቃል ሲመረመር አደጋው የከፋ ነው፤ የክፉ መንፈስ አሰራር ወደማወቅ እንዳንደርስ ቃሉን በክሏል በማለት ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተሳስቶ ከሆነም በየዋህነት መንፈስ በማቅናት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ "2000 ሺህ ዘመን የኖረችን ቤተክርስቲያን ዛሬ የተነሱ አፍቃሬ ተሐድሶ መናፍቃን ሊያርሟትና ሊበርዟት ይፈልጋሉ" በማለት መጥፎ ስም በመለጠፍና ምላሽ መስጠት ሲከብዳቸው ሽልማት የሚያሰጥ ቢሆን ኖሮ የስም አጥፊዎችን ዋንጫ ያለተቀናቃኝ የሚቀበሉበትን የተመረጡና ለመስማት የሚዘገንኑ ስድቦች፣ ዛቻዎችና ውግዘቶችን በማዥጎድጎድ የሚጠይቅ እንዲሸማቀቅ፣ አዋቂ ጠያቂ እንዳይኖር  አንገት  ማስደፋትንና ማስወገዝን እንደበቂ መልስ ሲቆጥሩ ኖረዋል። ዛሬም በዚሁ ግብራቸው አሉ።
በእርግጥ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ፍጽምትና ንጽሕት የመሆኗ ምስጢር የመሠረታት በዓለቱ ላይ በፈሰሰው ደሙ ነውና የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ህፀፅ አልባ ናት። ነገር  ግን የአክሌሲያ ጉባዔ አባላት  የአዳም ልጆች መሆናቸውን በመዘንጋት የቤተክርስቲያኗን መንፈስና ባህርይ እንዳለ ወደሰዋዊ ማንነት በመውሰድ እኛ ፍጹማንና ንጹሐን ነን በማለት ከስህተት አልባ ማንነት ጋር ራስን መቁጠር ትልቁ የስህተት መጀመሪያ ነው።  ምክንያቱም ዓለም ላይ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት የተከፋፈሉት  የአስተምህሮ ስህተቶች ወደክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሰተት ብሎ በመግባቱ የተነሳ ነው። የሚገርመው ደግሞ ሁሉም አብያተ ክርስቲያን ለራሱ ትክክል ሲሆን ሌላውን እንደስህተተኛ የመቁጠሩ ችግር ስህተቱን እንዳያውቅ አድርጎታል። ሌላውን ስህተተኛ ማለት እኔ ብቻ ትክክል ነኝ ከሚል ነጥብ ይጀምራልና ስህተቱን መቀበል አይችልም።
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በቀደመው ዘመን በገላትያ ቤተክርስቲያን የገባውን የስህተት መንፈስ በሐዋርያው ጳውሎስ ሲጠቀስ እናነባለን። የገላትያ ሰዎች በክርስቶስ አዳኝነት አምነው ወደ ሕይወት መንገድ የተመለሱ ሕዝቦች ነበሩ። ፍጽምትና ንጽሕት ወደሆነችው የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ተጨምረው የቆዩ ሆነው ሳለ ሰብአዊ ማንነታቸው አሸንፎአቸው ወደስህተት መንገድ በመግባታቸው በሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ የተወቀሱ ሕዝቦች ሆነዋል።

«የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?» ገላ 3፤1

ክርስቶስ ኢየሱስ በፊታቸው የተሰቀለ ሆኖ በእምነት ይታያቸው የነበሩት ሕዝቦች የያዙትን  የሕይወት ማንነትና እውነትን በመተው፤ የጠላት አዚም ሸፍኖአቸው ለእውነት እንዳይታዘዙ እስከመሆን መድረሳቸውን  እናያለን። ሥራቸውን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የጀመሩ ሆነው ሳለ ቁልቁል ተመልሰው የሥጋን ሃሳብና የስህተትን አስተምህሮ ወደማመን መመለሳቸው በእርግጥም አሳዛኝ የሰው ልጆች ማንነት ማሳያዎች እንደሆኑ የሚያስገነዝበን ነገር ነው።

«እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን?» ገላ 3፤3

እንግዲህ ክርስቲያኖች ፍጽምትና ንጽሕት በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እምነታቸውን ሊጀምሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህንን ፍጽምና ወደአለማወቅ በመመለስም ስህተት ሊታይባቸው እንደሚችል አስረጂ ነው። ምን ጊዜም ቢሆን የስህተት መንፈስ አገልግሎት የሚገባው፤ የእውነቱን መንፈስ ከሰው ልቡና ላይ በመውሰድ ወደስህተት መንገድ በማምራት ስለሆነ በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሉ ሰዎች ውስጥ የስህተት አስተምህሮ ሊገባ እንደሚችል እናረጋግጣለን።
ብዙዎች የአብያተ ክርስቲያናት አባላት በክርስቶስ ፍቅር ላይ ጸንተው ከመቆም ይልቅ ወደ ምድራውያንና ሰማያውያን ፍጥረቶች ፍቅራቸውን ስለለወጡ የሕይወት መንገድን ስተው መገኘታቸው እውነት ነው።
በሌላ ቦታም እንዲህ የሚል አስረጂ እናገኛለን። ሐዋርያው ጳውሎስ መንፈሳዊ ልጁ የሆነው ጢሞቴዎስን በተሰሎንቄ ለነበረችው ቤተክርስቲያን የላከበት ዋናው ምክንያት ተሰሎንቄዎች ከእምነት ጽናታቸው ወደኋላ እንዳይመለሱ በመንፈስ ያበረታታቸው ዘንድ ነበር። ምክንያቱም ፈታኝ የምንጊዜም አዚሙን የሚያፈሰው የአማኞችን ልቡና በማደንዘዝ ወደ አልሆነ አቅጣጫ በመመለስ ስለሆነ ከዚህ ፈታኝ ይጠበቁ ዘንድ ነበር።

«ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ። ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ» 1ኛ ተሰ 3፤5

የስህተት መንፈስና አስተምህሮ በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን አጋጥሞ እንደነበር ስንረዳ 2000 ዓመታትን በመጥፋትና በመነሳት፣ በመለያየትና በመታወክ በጦርነትና በመከራ ባሳለፈች ቤተ ክርስቲያን ውስጥማ እንዴት ብዙ አይገኝ?  የስህተት አስተምህሮ ማስተካከያ ሚዛኑ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው።
ከከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል ተብለው የሚጠሩ መነኮሳት በዋሻና በፍርክታ ገዳም መስርተው ሰው ሁሉ ወደዚያው እንዲከትም ከማድረግ ውጪ ሀገር ላገር ዞረው፤ እንደሐዋርያቱ ወንጌል ላልበራለት ሕዝብ ወንጌልን ስለማስተማራቸው ከአፋዊ ትውፊት በዘለለ መሬት ላይ ያለው እውነታ ያንን አያሳይም። ወንጌል ለሕዝቡ የበራ ቢሆንማ ኖሮ እስከዛሬ በዛፍ ስር ቡና የሚደፉ፤ ደም የሚያፈሱ፤ቅቤ የሚቀቡ፤በጨሌ፤ ቆሌና የቤት ጣጣ አምልኮ ሰርጾባቸው የሚኖሩ ባልኖሩ ነበር። እምነት አለን፤ አውቀናል የሚሉት እንኳን እስከፕሮቴስታንት መምጣት ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን አያውቁትም። በመላዋ ኢትዮጵያ ይቅርና ክርስትና አስቀድሞ ገብቷል በተባለባት በትግራይ  እንኳን ከአደይ ማርያምና ከአቡነ አረጋዊ በዘለለ የኢየሱስን ወንጌል በደንብ የሚያውቁ ምእመናን ቀርቶ ካህናቱ ቁጥር ስንት ይሆን?
ደረትን ነፍቶ ኦርቶዶክሳዊ ስለመሆን አረጋጋጭ ከሆኑት ከድርሳናት ውጪ መጽሐፍ ቅዱስን ይዞ መገኘት በራሱ ኮትልኳል ወይም ጰንጥጧል የሚያሰኝ በመሆኑ ይዞ መገኘት ቀደም ሲል ያሳፍር ነበር። ይህ በእድሜአችን ያየነው እውነት ነው። አንዳንዶች «ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው» የሚለውን ቃል ጠምዝዘው ለራሳቸው መሸንገያነት በመጠቀም አንድም ሐዋርያ ሳይመጣ ያመንን ስለሆንን ቃሉ እኛን ኢትዮጵያውያንን ያመለከታል ለማለት ቢፈልግም የሐዋርያ ወይም የሰባኬ ወንጌል አለመምጣት እንደ ጉዳት እንጂ እንደጠቃሚ ነገር መቁጠር ስንፍናን መደገፍ ነው። መጽሐፍ የሚለን እውነት ይህንን ነው።

«እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?» ሮሜ 10፤14

እንደዚሁ ሁሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እውነተኛ ወንጌል በማስተማርና ሕዝቡን ከክርስቶስ ወንጌል ጋር በማስማማት እንዲኖር ለማድረግ እስከሞት ድረስ ከታገለው ከአባ እስጢፋኖስ ዘጉንዳጉንዶ በስተቀር ግብጻውያን ጳጳሳት ይሁኑ ተከታዮቻቸው ከልምድ አምልኮ በዘለለ የሰሩት የወንጌል አገልግሎት አልነበረም ማለት ይቻላል። ወንጌል በመጽሐፈ ግጻዌ በጥቅስ ደረጃ በየሥርዓተ ቅዳሴው ላይ ተመርጦ ከሚነበብ ውጪ ከተአምረ ማርያምና ከድርሳናት እኩል በመድረክ ተሰብኮ አያውቅም። አቡነ ቴዎፍሎስ የወንጌልን አስፈላጊነት በማመን አዳሪ ት/ቤቶችን በማጠናከር፤ ሰንበት ት/ቤቶች በማቋቋምና በቃለ ዓዋዲ እንዲደነገግ እስኪያደርጉ ድረስ አብያተ ክርስቲያናት በግእዝ ቀድሰው፤ በግእዝ አንብበው፤ ለዓለመ ዓለም ካሉ በኋላ እግዚኦ መኀረነ ክርስቶስ እንበል 12 ጊዜ ብለው ጣት ከማስቆጠር ባለፈ ህዝቡ ወንጌልን እንዲያውቅ መርሐ ግብር ተቀርጾለት የስብከት መድረክ እንዳልነበረው ጠንቅቀን እናውቃለን።
እንዲያውም ወንጌል እቃ ግምጃ ቤት ገብቶ የሸረሪት፤ የአቧራና የአይጥ ቀለብ ሲሆን በአንጻሩ ልፋፈ ጽድቅ በየአንገት ላይ የሚንጠለጠል ክቡር መጽሐፍ ሆኖ ለዘመናት ኖሯል። ዛሬም እስከመቃብር ድረስ አብሮ የሚወርድ፤ ክቡር አዳኝ መጽሐፍ ሆኖ መቆጠሩን አላቋረጠም። የዲቁናም ይሁን የቅስና ማእርግ የሚሰጠው ሥርዓተ ቅዳሴውንና ኩሳኩሱን ከመልክዓ መልክዑ ጋር መሸምደዱ እንጂ ወንጌልን ተንትኖ ሕይወት የሚገኝበትን ቃል ማስተማር ስለሚችል የሚሰጥ ማእርግ አይደለም።
በዚህም የተነሳ ቀደምት የሆነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዘርዓ ያዕቆብና ተከታዮቹ ፀረ ወንጌል አድናቂዎቹ ባስገቡት የሕጸጽ አስተምህሮ ከዘመን ዘመን ድምፅና ተሰሚነቷ እየቀነሰ ቁጥሯ እየተመናመነ ከመገኘቷ ባሻገር ዛሬም ህፁፀ አእምሮ በተሸከሙ ዘርዓ ያዕቆባውያን የተነሳ ወንጌል ተገቢውን ስፍራ መያዝ አልቻለም። ከዚህ በታች የምናቀርባቸው መጽሐፍ ቅዱሳችን በምንለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ ስህተቶች፤ ነገር ግን እውነት እንደሆኑ ቆጥረን የምንከራከርላቸው ሲሆኑ ችግሩን እንደችግር ያለመቁጠራችን ዋና ምክንያት ከላይ በሐተታ እንደዘረዘርነው  አንድም እኛ ፍጽምትና ንጽሕት በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለን ስህተት አልባዎች ነን ከማለት የመነጨ ሰውኛ ማንነትን ካለመቀበል ችግር፤ አለያም- ክርስቶስ ከፊታቸው ተስሎ የነበሩት ገላትያውያን እንደሆኑት የሆነ አዚም አደንዝዞን እውነትን ለመቀበል ባለመፈለግ፤ አለያም ሳያዩ የሚያምኑ……በሚለው የሽንገላ ቃላት ተታለን እውነተኛውን የክርስቶስ ወንጌል የሚሰብክ እንዲኖረን ባለመፈለግ ራሳችንን ስናሞኝ በመኖራችን የተነሳ ነው።
የስህተት ትምህርት አስረጂዎች፤
ብዙውን ጊዜ «ከእውነተኛ የወንጌል አስተማሪዎች እጦት የተነሳ» /ከአስተማሪዎች እጦት የተነሳ አላልኩም/ ሕዝቡ እስካሁን ለወንጌል ቃል አዲስ በመሆኑ አሳማኝ መልስ መስጠት ስለማይችል እንደችግር መፍቻ መፍትሄ የሚጠቀምበት መንገድ በመሳደብ፤በማሳደድ፤በማሽሟጧጥ፤ በመደባደብ ብሎም በመግደል ልዩ ለሆነ ሃሳብ ሁሉ ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል። አሁንም ይህ አድራጎት አላቋረጠም። ከዚህ በታች ለሚቀርቡ አስረጂዎች ምላሽ መስጠት የሚችል አንድም ሰው እንደሌለ እርግጠኞች ስንሆን የሚሳደብ ወይም የሚያንቋሽሽ ክርስቲያን ነን ባይ ፍልፍሎችን ግን በሺህዎች እንጠብቃለን።

ጥያቄ 1፣
ስለታቦተ ጽዮን ትረካ፤
****************
1.1 ስለታቦተ ጽዮን አመጣጥ ታሪክ "በታቦተ ጽዮን ፍለጋ" መጽሐፍ፣

የታቦተ ጽዮን ፍለጋ መጽሐፍ አስተርጓሚ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን የሚናገረው ትረካ «ክብረ ነገሥት» የተባለውን መጽሐፍ ውሸታም ነው ብሎ ከቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ሲወረውረው እናያለን። ከክብረ ነገሥት በተለየ መልኩ አዲስ ግኝት አለ ብሎ መናገር ወይም ማስተዋወቅ ማለት ክብረ ነገሥት ተአማኒ አይደለም ወይም ላይሆን ይችላል ብሎ መመስከር ነው።
ማኅበረ ቅዱሳን ትውፊትንና ባህልን፤ ልምድንና አምልኰትን ለይቶ የማያውቅ የጅምላ እምነት አራማጅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ራሱ እገዛበታለሁ የሚለውን የቤተክርስቲያኒቱን የትውፊት መጽሐፍ ሲሽር  ሃይ ባይ ከልካይ የለውም። እንደሚታወቀው ግራሃም ሐንኰክ የተባለ እንግሊዛዊ ምሁር /The sign of the seal/ በሚል ርእስ እ/ኤ/አ በ1992 ዓ/ም ያሳተመውን
መጽሐፍ ይህ የትውፊት ጠበቃ ነኝ የሚለው የጅምላ እምነት አራማጅ ማኅበር፤ /ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ/ በሚል ርእስ በጌታቸው ተስፋዬ አስተርጉሞ ያሳተመው መጽሐፍ እንደሚተርከው ታቦተ ጽዮን ወደኢትዮጵያ የመጣችው በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን በልጁ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ቀዳማዊ ምኒልክ እጅ ሳይሆን  በግብጽ በኩል ኤሌፋንታይን አቋርጣ ከዓመታት ቆይታ በኋላ የዓባይን ሸለቆ ተከትላ ቀስ በቀስ በጣና አድርጋ ነው በማለት የመጽሐፉን ትርክት በትርጉም ሥራው አጽድቆ ገበያ ላይ ካዋለው አመታት ተቆጥረዋል። በዚህ መጽሐፍ ጥናት መሠረት ክብረ ነገሥት ውሃ በልቶታል። «ክብረ ነገሥት» ስለታቦተ ጽዮን አመጣጥ የሚተርከው የእነ ቀዳማዊ ምኒልክ ታሪክ በውሸታምነቱ ተመዝግቧል ማለት ነው። ማኅበረ ቅዱሳን የታቦተ ጽዮንን አመጣጥ በግራሃም ሃንኰክ አተራረክ መሠረት የሚያምን ከሆነ የክብረ ነገሥትን ትረካ ዋጋ ቢስ በማድረጉ ለምን? ተብሎ ሊጠይቀው በተገባ  ነበር። የሚገርመው አንድም የሊቃውንት ጉባዔ ይሁን የጳጳሳቱ ዓለም የክብረ ነገሥትን ትረካ የሚቃወመውን የማኅበረ ቅዱሳን እትም መጽሐፍ ሲያወግዝ ወይም ታሪካችንን አፋልሷል ሲል አልተሰማም። ሁሉም ስለታቦተ ጽዮን አመጣጥ አንድ የሆነ እምነት የላቸውም ማለት ነው።  ከዚህ አንጻር ስለታቦተ ጽዮን አመጣጥ የሚናገር የተለያየ ሃሳብ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ስላለ እውነተኛው የትኛው እንደሆነ ስለማይታወቅ ሁለቱንም ሃሳብ ላትስማሙ ተስማሙ ብለን ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምትቀበለው  ወደሌላ ሦስተኛ ተቃራኒ ትረካ አልፈናል።

1.2/ የኢት/ ኦር/ ቤተ ክርስቲያን ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ አልመጣችም የሚልና የምታምነው መጽሐፍም አላት!

ከላይ እንዳስቀመጥነው ማኅበረ ቅዱሳን ክብረ ነገሥትን ውሸታም በማለት በግብጽ በረሃ አድርጋ ነው ታቦተ ጽዮን የመጣችው የሚለውን የግራሃም ሃንኰክን መጽሐፍ ለተከታዮቹ ሲያከፋፍል የምንረዳው ሁለት የተለያየ የአመጣጥ ትረካ መኖሩን ነበር። ይሁን እንጂ ሰማንያ አሀዱ በተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጽሐፈ እዝራ ካልዕ ምዕራፍ 1 ቁጥር 54 ላይ እንዲህ በማለት ከላይ የቀረቡትን ሃሳቦች ሁሉ ውድቅ በማድረግ ታቦተ ጽዮን ወደኢትዮጵያ እንደመጣች ሳይሆን ወደባቢሎን መሄዷን በግልጽ ይናገራል።

«እግዚአብሔርን የሚያገለግሉበትን ንዋየ ቅድሳቱንና ጥቃቅኑንና ታላላቁን ዕቃ ሁሉ የእግዚአብሔር ማደሪያ ታቦትንም፤ ከቤተመንግሥት ዕቃ ቤት ያለውን ሣጥኑንም ሁሉ ማርከው ወደ ባቢሎን ወሰዱ» እዝራ ካልዕ 1፤54

ናቡከደነጾር ከ634-562 ዓ/ዓ የነበረ የባቢሎን ንጉሥ ኢየሩሳሌምን ጥሶ፣ ቤተ መቅደሱን አፍርሶ፣ እስራኤላውያንን በባርነት አግዞ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። እንደመጽሐፈ እዝራ አተራረክ ከቤተ መቅደሱ ንዋያተ ቅድሳት መካከል ታቦቱን ጨምሮ ወደባቢሎን ያልተወሰደ እንደሌለ እናነባለን። ይህ መጽሐፍ ታቦተ ጽዮን በግብጽም ሆነ በቀዳማዊ ምኒልክ በኩል ወደኢትዮጵያ መጥታለች የሚለውን ታሪክ ውድቅ ያደረገ ትርክት ነው። እርስ በእርሳቸው ያልተስማሙት የክብረ ነገሥትና የታቦተ ጽዮንን ፍለጋ መጻሕፍት ትረካ ውድቅ በማድረግ ወደ ባቢሎን ማርኰ ስለመውሰዱ ሰማንያ ወአሀዱ የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ አፖክሪፋ መናገሩ ነገሩን ሁሉ መያዣ መጨበጪያ የሌለው አድርጎታል። አሁን እንግዲህ ሊነሳ የተገባው ጥያቄ፤
ሀ/ ክብረ ነገሥት የተባለው መጽሐፍ ታሪክ ትክክል ነው?
ለ/ ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ የተባለው መጽሐፍ ትረካስ ትክክል ነው? ወይስ
ሐ/ ታቦቱ ወደባቢሎን በምርኰ ተወስዷል የሚለው የመጽሐፈ እዝራ ካልዕ ቃል ትክክል ነው ወይ? ብለን እንጠይቃለን። መላሽ የለም እንጂ ጥያቄስ ሞልቷል።

1.3 ታቦቱ ከሰሎሞን ሞት በኋላ እስከ 300 ዓመት ድረስ በኢየሩሳሌም እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።

 አፖክሪፋ ወይም ቀኖና መሰል መጻሕፍት ወይም ታሪክ ቀመስ መጽሐፍ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፉ ስላልሆኑ ሊሳሳቱ ይችላሉ። የኢት/ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመኗ ሁሉ ከሰራችው ስህተት ከሁሉ የከፋው እንደቀኖና መጻሕፍት እንጂ እንደምሉዕ የቤተ ክርስቲያን ዶግማዊ መጻሕፍት ቆጥራቸው የማታውቃቸውን መጻሕፍት በ2000 ዓ/ም ባሳተመችው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስርዋጽ በማስገባት ዶግማዊ መጻሕፍት አድርጋ መቁጠሯ የቁልቀሊት መሄዷን ማፋጠንዋ እንጂ የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነት አይለውጠውም። ቅዱስ አትናቴዎስን አደንቃለሁ፣ እወዳለሁ እያለች በአደባባይ የምትለፍፍ ቤተ ክርስቲያን እነቅዱስ አትናቴዎስ በቅርጣግና ጉባዔ ላይ ካጸደቋቸውና በእስትንፋሰ እግዚአብሔር ተጽፈዋል ከተባሉት 39 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውጪ ለመያዝ ድፍረቱን ከየት አገኘች? ለመሆኑ አትናቴዎስን ከስም ውጪ ተግባሩን ተረክባለች ወይ ብለን እንድንጠይቅ የምንገደደው በእነቅዱስ አትናቴዎስ ቅቡል የተደረጉት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ቁጥር ለመቀበል ለምን አመጸኛ ሆንሽ? እያልን ነው።
ወደጀመርነው ሃሳብ ስንመለስ መጽሐፈ ነገሥት እስከ ባቢሎን ምርኰ ድረስ ታቦቲቱ ኢየሩሳሌም እንደነበረች ይናገራል።
 ታቦተ ጽዮን በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ወደኢትዮጵያ መጣች የሚለውን አባባል ውድቅ የሚያደርገው ሌላው አስረጂ ከ300 ዓመት ቆይታ በኋላም በኢዮስያስ ዘመን/ ከ649-609 ዓ/ም/ ኢየሩሳሌም እንደነበረች መጽሐፍ ቅዱስ መናገሩ ነው። ኢዮስያስ ንጉሥ ሰሎሞን ከሞተ ከ300 ዓመት በኋላ በኢየሩሳሌም የነገሠ ንጉሥ ነበር።  የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የሚነግሩን የሕጉ መጽሐፍ መነበቡን/ 2ኛ ነገ 22፤8/ ንጉሡ የሕጉን መጽሐፍ ሲሰማ ልብሱን መቅደዱን /2ኛ ነገ 22፤11/ የእግዚአብሔር ቤት ይጠገን ዘንድ ማዘዙን /2ኛ ዜና 34፤10/ ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት በመቅደሱ እንዲያኖሩት ማድረጉን መጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን።
«እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለእግዚአብሔርም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ፦ ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ» 2ኛ ዜና 35፤3
እንደእኛ እምነት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ስለማይሳሳት መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃወሙ መጻሕፍት ሁሉ ስሁታን ናቸው እንላለን። በዚሁ መሠረት ታቦቲቱ ወደኢትዮጵያ መጥታለች የሚለውን ትረካ ከ300 ዓመት በኋላ እዚያው ኢየሩሳሌም መኖሯን መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚነግረን የሰውን ትርክት ትተን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንቀበላለን። ለሰው ሊነገር የሚገባው የማኅበረ ቅዱሳንን? ወይስ የክብረ ነገሥት? ወይስ የእዝራ ካልዕን? ወይስ የመጽሐፈ ነገሥትን እውነት? ሁሉም ታሪኮች ስለአንዱ ታቦት የተለያየ ነገር ያወራሉና ቤተ ክርስቲያን ሆይ የትኛውን ቃል ለሚጠይቁሽ ትናገሪያለሽ?  ሌላው ማፈሪያ ትምህርትሽ ደግሞ የሙሴ ሁለት ጽላት ( የማርያምና የሚካኤል) ነው የሚለው ተረትሽ ነው። ዐሥርቱ ትእዛዛት  በሁለቱ ሰሌዳ ላይ በቀኝና በግራ ከመጻፉ በስተቀር የሚካኤልና የማርያም የሚባል ጽላት አልነበረም።

"ታደርጉትም ዘንድ ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን አሥሩን ቃላት ነገራችሁ፤ በሁለቱም በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው። " (ዘዳ 4: 13)

 ድንግል ማርያም ከመፈጠሯ ከ2000 ዓመት በፊት ለድንግል ማርያም  ጽላት ተቀረላት የሚለው ተረት ገደብ ይበጅለት።  ሲጀመር ጽላት የትእዛዛቱ ቃል ማክበሪያ እንጂ የሰው ምስልና የሆነ ያልታወቀ ኅቡዕ ጠልሰም መቅረጫ አልነበረም። ቤተ ክርስቲያኒቷ መጻሕፍትን መርምረው ከሚጠይቋት የምትሰጠው  መልስ እውነቱን በመግለፅ ነው ወይስ ተሐድሶ መናፍቅ በሚል የውግዘት ማስፈራሪያ?

2/ ቤተ ክርስቲያን ዲያብሎስን ክብሩ የወደቀው በምንድነው ብላ ታስተምራለች? ዲያብሎስ የወደቀ በትዕቢቱ አምላክ ለመሆን ስለፈለገ ነው ወይስ ለአዳም ስገድ ተብሎ እምቢ በማለቱ ነው?
እንደቤተክርስቲያን አስተምህሮ ሰይጣን እስከነሠራዊቱ የወደቀው በመታበዩ ምክንያት እንደሆነ ነው የሚታመነው።

ትንቢተ ኢሳይያስ 14፥12
«አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ!»
ይለዋል።
ራሱን የሁሉ ገዢ ለማድረግ ክሳደ ልቡናው ስለተነሳሳ በስሁት መንፈሱ ለውድቀት ተዳርጓል የምትል ቤተክርስቲያን፤ «የለም! ሰይጣን የወደቀው በትእቢቱ መላእክትን እኔ ፈጠርኳችሁ ስላለ ሳይሆን ለአዳም አልሰግድም ስላለ ነው» የሚል አስተምህሮ ይዛ መገኘቷ ነገሩን ሁሉ አስገራሚ ያደርገዋል።
 መጽሐፈ መቃብያን ለአዳም ስላልሰገደ ዲያብሎስ ወደቀ ይለናል።
እንደዚህ የሚል ትምህርት በቤተክርስቲያናችን የለም የሚል ሰው ቢኖር ቁጥሩ ከአፖክሪፋ የሆነውንና እንደመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክፍል እንዲቆጠር በግድ የተበየነበትን መጽሐፈ መቃብያንን አያነብም ወይም ስለተሸከመው ብቻ የገባው ይመስለዋል ከማለት ውጪ ምን ልንል እንችላለን?

«የሚጠፉ በኔም የሚስቱ ሰዎች ፈጽመው ይበዙ ዘንድ፤ የአዳምም ልጆች ይጠፉ ዘንድ፤ ይህንን በተናገሩ ጊዜ እኔ ደስ ይለኛል፤ ለሚዋረድልኝ ለአዳም አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለአባታቸው ስለአዳም ከማዕረጌ አዋርዶኛልና፣ 3ኛ መቃ 1፤15

እንዲሁም በ2ኛ መቃብያን ላይ በተጨማሪ እንዲህ የሚል እናገኛለን።

«ክሳደ ልቡናውን በማጽናትና ራሱን በማኩራት ፈጣሪው ለፈጠረው ለአዳም መስገድን እንቢ እንዳለ»2ኛመቃ 9፤1-3

የጥንቱ ተጨማሪ ቀኖና የአሁኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን የዶግማ መጽሐፍ ክብርን የተጎናጸፈው መቃብያን፣ ዲያብሎስ የወደቀው ለአዳም አልሰግድም ብሎ እምቢ በማለቱ ነው ይለናል። ይህ የመቃብያን መጽሐፍ ዲያብሎስ የወደቀው ለአዳም አልሰግድም ብሎ እንጂ ራሱን ከፈጣሪ ጋር አስተያይቶ በትእቢት አይደለም ከሚለው ከቁርአን ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ አለው። ሱረቱል አልበቀራህ ወይም የላም ምዕራፍ 2፤ 34
وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ أَبَى وَاسْتَكْبَرَ وَكَانَ مِنَ الْكَافِرِينَ ንባቡም ።
Waith qulna lilmalaikati osjudoo liadama fasajadoo illa ibleesa aba waistakbara wakana mina alkafireena
ወደአማርኛ ሲመለስ፤
«ለመላእክትም ለአዳም ስገዱ ባልን ጊዜ (አስታውስ) ሁሉም ወዲያው ሰገዱ። ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ኮራም ከከሀዲዎቹ ሆነ»  የቁርአንና የመቃብያን መመገጣጠም የአጋጣሚ ነው ወይስ የክርስትና ቁርጥራጭ ሃሳቦችን ለመሀመድ ያስተማረ የመቃብያን አቀናባሪ ግብፃዊ መነኩሴ ይኖር ይሆን?
(የጥቅሱ መጨረሻ)
 ይህንን የመቃብያን መጽሐፍ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር በእኩል ደረጃ አትቀበለውም።  እነሱ ያልተቀበሉትንና ያልፈለጉትን መጽሐፍ ጭነውብን ነው ወይስ ለእኛ ለኢትዮጵያኖች ለብቻችን መቃብያን መጽሐፍ ከሰማይ የወረደልን ሆኖ ይሆን?
ዲያብሎስ ክብሩ የተዋረደው ለአዳም አልሰግድም ብሎ እንቢ ስላለ ነው? ለአዳም እንዲሰግድ የታዘዘውስ መቼ ነው? ይህስ ከየት የተገኘስ አስተምህሮ ነው? ብሎ ለሚጠይቃት አንድ ምስኪን ልጇ ቤተ ክርስቲያን ምን ብላ ትመልስለታለች?  መቃብያንን የምትመድበው እስትንፋስ እግዚአብሔር ካለበት መጽሐፍ ወይስ ከህፁፅ አፖክሪፋ?

3/እንጠይቃለን መላሽ ከተገኘ፣ ለሰዎች በቀይና በጥቁር መጻፍን ያስተማረው ማነው?

ለሰዎች በጥቁርና በቀይ ቀለም መጻፍ ያስተማረው አጋንንት ነው ትይናለሽ። ይህንን እንዴት እንመን።
ለዚህ ጥያቄ አዎን አጋንንት ነው ያስተማሩት የሚል ምላሽ ቢሰጥበት ሰዎች መቃወማቸው እርግጥ ነው። ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ በጥቁር ወይም በጥቁርና ቀይ መጻሕፍት እያዛነቁ መጻፍ የተለመደ ስለሆነ የጥቁርና ቀይ ቀለማትን ምንጭ ከአጋንንት ጋር ማያያዝን ማንም አሜን ብሎ አይቀበልም። ምክንያቱም የአጋንንት ተማሪና መንገዱንም ተቀባይ ፈቃደኛ ሰው መቼም የእግዚአብሔር መሆን አይችልም። ይሁን እንጂ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የማትቆጥረው መጽሐፈ ሄኖክ የተባለው አፖክሪፋ / */በቀይና በጥቁር ቀለም መጻፍ ለሰው ልጆች ያስተማረው አጋንንት ነው ይለናል። መጽሐፈ ሄኖክ 19፤22-24 ይመልከቱ። እንግዲህ ለመልካም ይሁን ለጥፋት በዚህ ዘመን የሰው ልጅ የሚጠቀምበት የመጻፊያ ጥቁርና ቀይ ቀለም ተጠቃሚዎች ሁሉ የአጋንንት ተማሪዎች ናቸው ማለት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ተስፋ ገ/ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋና ትንሣዔ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤቶች ይበልጥ የአጋንንትን ትምህርት ፈፃሚዎች ናቸው ማለት ነው።
ይሁን እንጂ የጽሕፈት፤ የፊደላትና የእውቀት ባለቤት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንጂ አጋንንቶች ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። አጋንንት የበጎ ነገር ጠላቶች እንጂ ለሰው ልጅ የእውቀት ምንጮች የመሆን ተፈጥሮ የላቸውምና። ሰዎች የተሰጣቸውን እውቀት ላልተፈለገ ዓላማ ሊገለገሉበት ይችላሉ እንጂ አጋንንት የአዳምን ልጆች የጽሕፈት እውቀት አስተማሩ ማለት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ሰውን የአጋንንቶች ወዳጅ አድርጎ የሚያቀርብ የክህደት አስተምህሮ ነው። ጥቅመ ሰናኦር ቋንቋን የሰጠ እግዚአብሔር፤ የቋንቋ መጻፊያ ቀለማትን ደግሞ ሰይጣን በመፍጠር በምንም መልኩ የፈጣሪ አጋዥ ሊሆን አይችልም። ቤልሆር ከክርስቶስ ጋር ምንም ኅብረት የለውምና።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር ለነቢያቱ ይህን ጻፉ፤ እንዲህም ጻፉበት እያለ የጽሕፈት ባለቤትነቱን ይመሰክርለታል። «ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ ማለዳም ተነሣ» ዘጸ 24፤4
«ሙሴም በዚያ ቀን ይህችን መዝሙር ጻፈ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተማራት» ዘዳ 31፤22
«አንድ የመጽሐፍ ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት» ኤር 36፤2
«ዳግመኛም ሌላ ክርታስ ውሰድ፥ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው ክርታስ ላይ የነበረውን የቀድሞውን ቃል ሁሉ ጻፍበት» ኤር 36፤28
እጅግ ብዙ አስረጂዎችን ማቅረብ ይቻላል። እውነትን ለመግለጥ በቂ ነውና በሄኖክ ስም ራሱን በእግዚአብሔር ቦታ አስቀምጦ እኔ ለሰው ልጆች እውቀትን የሰጠሁ ነኝ የሚለው ክፉ መንፈስ ግን በእግዚአብሔር ቃል የተሳሳተ አስተምህሮ ነው። አጋንንት ጽሕፈትን እንዴትና መቼ እንዳስተማረ ማስረጃ ከሚያቀርቡ የቅርብ ወዳጆቹ ለመስማት ዝግጁ ነን። ይሁን እንጂ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እጅግ የምታደንቀው የሃይማኖት አባት አትናቴዎስ የማያውቀውንና የኮፕት ቤተክርስቲያንም እንደቅዱሳት መጻሕፍት የማትቀበለውን መጽሐፈ ሄኖክ የመምህርነቱን ስፍራ ለአጋንንት ሰጥቶት ይገኛል። የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንስ ያልተቀበለችው ለምን ይሆን? አጋንንት እስከተጠበቀላቸው የፍርድ ቀን ድረስ የሰው ልጆች ተቃዋሚዎች እንጂ በጎ አድራጊዎች ሊሆኑ አይችሉም።  በእርግጥ በቀይና በጥቁር ቀለም ለሚፅፉ፣ ቃል ኪዳን ለገቡ ደብተራና ኅቡእ ስም ደጋሚ ባለተዋርሶ የቤተክርስቲያን ሰዎች በትርፍ ጊዜአቸው ለመስተሐምም፣ ለመቅትል፣ ለመስተአብድ፣ ለመስተባርር፣ ለአምጽኦ ብእሲት፣ ለመስተፋቅር፣ ለመስተጻልእ፣ ለመንድግ ወዘተ ሰይጣናዊ ሥራ ያገለግሉ ይሆናል።

4/ የቤተክርስቲያኒቱ ዲያቆናት ሲኦል ውስጥ ለሚቃጠሉ ሰዎች ምሳሌ ናቸው!

ቤተ ክርስቲያኒቱ ካልጠፋ ምሳሌ ዲያቆናቱን ወደእሳት ከሚወረወሩት መካከል አድርጋቸዋለች። አስፀያፊ ምግባር ያለው በፍርድ ቀን እግዚአብሔር ፊት ሲቆም ጳጳስም ቢሆን ከቅጣት ሊድን አይችልም። ፍርድ በክርስቲያናዊ ማንነት የሚሰጥ ዋጋ እንጂ በማእረግ ሚዛን የሚደረግ ማበላለጥ አይደለም። ለእያንዳንዱ እንደስራው የሚከፍል እግዚአብሔር ዲያቆናትን  ብቻ ለይቶ ወደእሳት አይጥልም።
ዲያቆናት ጥርስ ማፋጨትና እሳቱ ወደማይጠፋ ቅጣት ይወርዳሉ የሚል የዉሸት ምሳሌ የመጣው ከየት ነው?
በማቴዎስ ወንጌል ላይ የተሰጣቸውን መክሊት ከሦስተኛው በስተቀር ሌሎቹ አራብተው ለባለቤቱ ዋናውን የመለሱ ሠራተኞችን ማንነት የሚገልጽ ቃል አለ።
(የማቴዎስ ወንጌል 25፤14-30 ያለውን ይመለከቷል)
በቁጥር 15 ላይ «ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ» ይላል። እነዚህ ሰዎች በተሰጣቸው መክሊት አትርፈው ዋናውን ለባለዋናው መመለስ በሚገባቸው ወቅት የተገኘባቸው ትጋት እንዲህ ተቀምጧል።
« አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ»
በዚህ ውስጥ ያተረፉት ሲሾሙና ሲሸለሙ፤ ያላተረፈውን ባለአንድ መክሊት ባሪያ ግን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት እሳት መጣሉን ቃሉ ይናገራል። ይህንን ቃል አንድምታ በተባለው ትርጉም ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል ተቀምጧል።
ባለአምስት መክሊቱ ሊቀጳጳስ ነው፤ ባለሁለቱ መክሊት በቄስ ይመሰላል። ባለአንድ መክሊቱ ደግሞ በዲያቆን ይመሰላል በማለት እጣ ፋንታውን በቤተክህነቱ የስልጣን እርከን መሠረት ይደለድልና ዲያቆናትን « ወለገብርሰ ዘእኩይ» ተብለው እድል ፈንታቸውም የዘላለም እሳት እንደሆነ በምሳሌ የተቀመጡበት የሥልጣን እርከን ትርጉም በፍጹም ትክክል አይደለም እንላለን። (ወንጌል ቅዱስ ንባቡና ትርጓሜው 1916 ዓ/ም)
በዚህ ዘመን ያለውን ግብር ተመልከተን ብንመዝን በያዙት ሥልጣንና ኃላፊነት ደረጃ ተጠያቂ በመሆን የሚወዳደራቸው የማይኖረው ለራሳቸው የባለአንድ መክሊቱን ሥፍራ ቆርሰው የያዙት ጳጳሳቱ በሆኑ ነበር። ለተልእኰ በመፋጠንና ከሙጋድ ጢስ ጋር ሲታገል የሚኖረውን ዲያቆን የገብር ዘሀካይን ደረጃ በማጎናጸፍ  መክሊቱን የቀበረ፣ በተሾመበት ያልታመነ፣ ክፉና ተንኮለኛ አድርጎ መተርጎም የጤነኛ ቤተ ክርስቲያን አስተምሀሮ አይደለም። ስልጣኑም፣ ሚስቱም፣ ቤቱም፣ መኪናውም ብሩም ሁሉን ሰብስቦ ነፍሴ ሆይ እረፊ፣ ደስ ይበልሽ  የሚል ጳጳስና አለቃ ባለባት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌሊት ለሰዓታት፣ ቀን ለቅዳሴ የሚባትለውን ዲያቆን ገብርሰ ዘለእኩይ ማለት ተሳልቆ ነው።  እንደዚህ ጽሁፍ አቅራቢ "ገብርሰ ዘለእኩይ" የሚባለው በብዙ የተሾመ፣ በብዙ የሚጠበቅበትና በብዙ ሊሰራ ሲገባው ስጋውን በምቾት  ያሰረ ሹም ነው።
ስናጠቃልል እስካሁን ለዘረዘርናቸው መጠይቅ መላሾች እውነቱ የቱ ነው? በማለት እንጠይቃለን። ስህተት ካለብን  ስለሃይማኖት ከማሽሟጠጥ ይልቅ እውነቱ ሊነገረን ይገባል።  ያ መሆን ካልቻለ እውነቱን ለመቀበል ባንፈልገውም እውነት ምን ጊዜም እውነት እንደሆነ ሲኖር ውሸትም ለእውነት ጊዜውን ጠብቆ ሥፍራውን መልቀቁ አይቀርም።
«ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና» 2ኛ ቆሮ 13፤8