Monday, September 12, 2016

ኦርቶዶክስ ሆይ ድምፅሽ ወዴት አለ?


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወቅቱን የሀገሪቱን ቀውስ ከጸሎት ባሻገር በመምከርና በመገሰጽ ወደሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ በመመለስ ረገድ ልትጫወተው የምትችለው ድርሻ ትልቅ እንደሆነ ይገመታል። ነገር ግን "መጽሐፉም ዝም፣ ቄሱም ዝም" እንዲሉ ሆነና እያየች እንዳላየች፣ እየሰማች እንዳልሰማች መሆንን የመረጠችው ለምን ይሆን?
ከሰማያዊው መንግሥት  ምድራዊውመንግሥት አስፈርቷት ነው? ወይስ ዝም እንድትል ከሰማያዊው መንግሥት መልእክት መጥቶላት ይሆን?
ቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ ሆና ቤተ መንግሥቱንም፣ ሕዝቡንም ልትገስጽ፣ ልትመክር ካልቻለች ወደምድራዊ ውግንና ወይም ሥጋዊ ፍርሃት ገብታለች ማለት ነው። የተሰጣትን እውነት የመናገር ብርሃናዊውን መቅረጽ የምትቀማው መናገር ሲገባት ዝምታን ከመረጠችና ዝምታ በሚገባት ሰዓት መናገር ከፈለገች ብቻ ነው። እናም ዝምታዋ ዞሮ ዞሮ የተሰጣትን መንፈሳዊ ሃብት እንድትቀማ ያደርጋታል። ለሌላው አሳልፎ እንዲሰጥ ይሆናል። ለልክ እንደጥንታዊዋ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ማለት ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ሳይፈጸም አይቀርም። ደግሞም እያየን ያለንበት ወቅት ላይ ነን።
መንግሥት ሆይ፣ ሕዝብህን በሕግና በፍርሃት ግዛ። ሕዝብ ሆይ፣ ለመንግሥትህ በሕግና በፍርሃት ተገዛ ማለት የእርቅ አንደበት እንጂ ለማንም መወገን አይደለም። ምን ጊዜም ብጥብጥና ሁከት ለሕግና ለተአዝዞት ፈቃደኛ ካለመሆን የሚመጣ ስለሆነ የትኛውም አካል ለሕግ ተገዢ ይሁን ብሎ መናገር የሚያስፈራ ጉዳይ አልነበረም። ገዳይም፣ ሟችም፣ ሕግ አፍራሽም፣ ሕግ ደንጋጊም ሁሉንም እንደ ልጆቿ አድርጋ በማየት ለሕግ ተገዙ ልትል ሲገባት የኦርቶዶክስን አንደበት ሌሎች እየተናገሩበት ይገኛል። ልጆቿን ልጆቻቸው አድርገው አንደበቷን ወስደው እየተናገሩበት ይገኛሉ። ይሄ መነሳት የነበረበት ከእርሷ ቢሆንም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጎዶሎ ወንጌል የሌላት ሆኖ ሳለ የወንጌል ሙሉ ነን የሚሉ ቀድመው የአስታራቂነት ሽምግልናውን ወስደዋል። ለመሆኑ የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ በሕይወት አለህ?