Friday, May 8, 2015

የዘንድሮው የግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ቶሎ ተጠናቀቀ።

ለወትሮው ብዙ አጀንዳ ቀርጾ ረጅም ቀናት ይወስድ የነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በጥቂት ቀናት ውስጥ መጠናቀቁ ተሰምቷል።
በምክንያትነት ተወስዷል ተብሎ ከውስጥ አዋቂ ምንጮች የቀረበው መረጃ እንደሚያስረዳው የ2007ቱ ሀገር አቀፍ የምርጫ  ሁኔታ ሲሆን የጉባዔው ቀናት መርዘም ከምርጫው ጊዜ ጋር እንዳይደራረብና በጉባዔው ሊነሱ የሚችሉ ሰፊ ክርክሮች በመራጭነት በተመዘገቡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች ላይ ሊፈጥር የሚችለው ተጽእኖ ቀላል ባለመሆኑ በአስቸኳይ ጉዳዮች ላይ ብቻ በመነጋገር ሌሎች አጀንዳዎችን ለማሸጋገር መገደዱን ለማወቅ ተችሏል።
  ከዚሁ በተጨማሪ ለጉባዔው ሰፊ አጀንዳዎች ለቀጣይ ጉባዔ መሸጋገር  በምክንያትነት ተያይዞ የቀረበው ጉዳይ በጥቅምቱ ጉባዔ ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፉት ብዙ ውሳኔዎች በአፈጻጸም ድክመት ተወዝፈው ስለቆዩ ለአፈጻጸሙ ምክንያት የሆነው ጭብጥ እንደሚያስረዳው  ጉዳዩ ቢነሳ ለሰፊ ክርክርና ጭቅጭቅ ስለሚያበቃ ጊዜ ወስዶ ለማየት የጥቅምቱ ጉባዔ በፓትርያርኩ መመረጡን ተያይዞ የደረሱን መረጃዎች ያስረዳሉ።
  በአባ ማቴዎስና አባ ሉቃስ ተወዝፎ ምንም ያልተነካው የሲኖዶስ ውሳኔዎች አካል የሆነው ጉዳይ ማኅበረ ቅዱሳን የእስከዛሬ ገቢና ወጪውን በቤተክርስቲያኒቱ ባለሙያዎች የማስመርመር፣ በህጋዊ የቤተክርስቲያን ሞዴል መጠቀም፣ ማኅበሩ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር ሆኖ በየአመቱ በሚታደስ አዲስ ደንብ እንዲተዳደር ማድረግና ያለውን ሀብትና ንብረት ማስመዝገብን የተመለከቱ ውሳኔዎች በጭራሽ እስካሁን አለመነካታቸውንና በሁለቱ ጳጳሳት ከለላ ስር ውሳኔው ተዳፍኖ መቆየቱ ይነገራል። ቅዱስ ፓትርያርኩ አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ የነበረው የማኅበሩ ልቅ እንቅስቃሴ ተወስኖ በተሰጠው ምህዋር ላይ ብቻ እንዲንቀሳቀስ  የሚያደርገው አዲስ የመተዳደሪያ ደንብ እንዲቀረፅ ብዙ የተናገሩለት በጳጳዳቱ ዳተኝነት ጭራሽ የታሰበበት አይመስልም።
 ይልቁንም (የማኅበረ ቅዱሳን ሲኖዶስ) አባላት የሆኑት አባ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ: አባ ሉቃስ የሲኖዶሱ ፀሐፊ፣ አባ ቀሌምንጦስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ የያዙትን ቁልፍ ቦታ ለማኅበረ ቅዱሳን በሚጠቅም መልኩ ለማከናወን ቢጥሩም በፓትርያርኩ እምቢ ባይነት ባለመሳካቱ ወጣቶችን በማስተባበር በሽፋን ባቀረቡት አቤቱታ እንደተነገረው በቀጥታ ፓትርያርኩን በመወንጀል አቡነ ጳውሎስ ላይ የተደረገውን ዘመቻ ለማስቀጠል ተዘጋጅተው የነበረ ቢሆንም የዘመቻ ጽሁፍ ተቀባይነት ከማጣቱም በላይ አባ ቀሌምንጦስን ፓትርያርኩ እንደገሰጿቸው ታውቋል።  ይህን ዘመቻ በይደር ለጥቅምት በማቆየት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የተላለፉት ውሳኔዎች ሊታዩ የሚችሉት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ያቀረቧቸው ጠያቄዎች ምላሽ ሲሰጣቸው ብቻ መሆን እንዳለበት ዱለታው የተጠናከረ ሲሆን ከዚህ ዱለታ ጀርባ ሌሎች ጳጳሳትም እንዳሉበት ተያይዞ ይነገራል።
 የማኅበረ ቅዱሳን ቅምጥ ኃይል የሆነው የወጣቶቹ ኅብረት ለአደጋ ጊዜ እንደሽፋን የሚያገለግል ኃይል ሲሆን በቀጥታ የማኅበሩ አባል ጳጳሳትንና ማኅበሩን ከተጠያቂነት ለማዳን ለሽፋን ያገለግላል።
በወጣቶች ደም ለመነገድ መሞከር ወንጀል ነው።