Monday, July 9, 2012

ክርስቶስ ሰምራ ዘብሔረ ቡልጋ በቀን ሦስት ሺህ ነፍሳት ከሲኦል ታወጣለች!

 መጽሐፍ ቅዱስ «መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ» ይላል። ምክንያቱም በዓለም ላይ ከእግዚአብሔር  ቃል ጋር የማይስማሙ ነገር ግን እውነትን የሚመስሉ ሀሰተኛ ትምህርትና ትንቢት በዓለሙ ገብተዋልና በማለት ጥንቃቄ እንድናደርግ ያስተምረናል። ነገር ግን እውነቱን ጋርደው እውነት የሚመስሉ አስተምህሮዎች ምን ጊዜም ከእግዚአብሔር መንፈስ የሚመጣ ሳይሆን ከሀሰት አባት መንፈስ የሚቀዳ ስለመሆኑ ቅዱስ ቃሉ «የሀሰት አባት ከራሱ አንቅቶ ሀሰትን ይናገራል» በማለት (ዮሐ 8፤44) እንዳስቀመጠው ዛሬም በስህተት ትምህርቶች ፍጥረቱ ተበክሏል።   ከስህተት ትምህርቶች አንዱ የሆነውን ገድል «ተስፋ» የተባለው ጸሐፊ በወንጌል ቃል ሽፍንፍኑን እየገለጠ ያሳየናል። ሰው ሃይማኖት ኖረው፤ አልኖረው ፤ እግዚአብሔርን ካደ፤ አልካደ ምንም ጥቅም የሌለው እንደሆነ የሚያደፋፍርና ከአምልኰ የለሽነትም ጭምር የሚታደግ  አስተማማኝ መጽሐፍ መገኘቱን በማብራራት እስኪገርመን ድረስ ገላልጦ ያሳየናል። ልብ ያለው ልብ ይበል! እንላለን።

የጽሁፋችን ምንጭ «አባ ሰላማ ድረ ገጽ» ነው።

«ወወሐባ ኪዳነ ከመ ታውጽእ ነፍሳተ እምሲኦል ሠለስተ እልፈ ነፍሳተ በበዕለቱ» ትርጉም "ጌታም በየቀኑ ከሲኦል ሦስት ሺህ ነፍሳትን እንድታወጣ ሥልጣን ሰጣት ወይም ቃል ኪዳን ሰጣት» ገድለ ክርስቶስ ሠምራ ዘጥቅምት ቁ 61
ገድሉን ለማንበብ ( እዚህ ይጫኑ )

ክርስቶስ ሠምራ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የታወቀች ቅድስት ሴት ናት። በየዓመቱ ግንቦት 12 መታሰቢያዋ ይከበራል። በዚህ ቀን በርካታ ምዕመናን እርሷን ከሲኦል እንድታወጣው ለመማጸን ወደ ቤተ መቅደሷ በመሄድ ሲሰግድ ይውላል። ንፍሮ በመቀቀል፣ ዳቦ በመጋገር፣ ጠላ በመጥመቅና ገድሏን በማንበብ ልመናና ጸሎት ያቀርብላታል። እርሷ የኖረችበት ነው በተባለው በጣና አካባቢ በሚገኘው ገዳሟ የሚሰበሰበው ሕዝብ ብዙ ነው። በዚያ ሰንጣቃ አለት የሚገኝ ሲሆን አንድ ሰው መጽደቅ እና አለመጽደቁን ለማወቅ በሰንጣቃው አለት በማለፍ እራሱን ይፈትናል። በዓለቱ ሾልኮ ካለፈ ጸድቋል ይባላል ካላለፈ ግን ተኮንኗል ይባላል። በብልሃት እንደምንም ያለፈ ሰው ጸድቄያለሁ ብሎ እራሱን አዘናግቶ ይኖራል።


      ይህን ሁሉ በማደረግ የሚደክመው ሕዝብ ግን እውነተኛውን የነፍስ እረፍት ባለማግኘቱ በሌሎች ገዳማትም እየተንከራተተ አድርግ የተባለውን ሁሉ ያደርጋል። በግሸን ተራራውን ወዙ ጠብ ጠብ እያለ የወጣ ሰው ኃጢአቱ ተሠርዮለታል ይባላል። በዚህ የሰይጣን ትምህርት ምክንያት በባዶ እግሩ የሚኳትነው ሰው ብዙ እንደሆነ በሥፍራው ተገኝቼ ታዝቤያለሁ። ወደ ላሊበላ በባዶ እግር የሄደ ይጸድቃል ስለሚባል ያለጫማ እየደሙ ሄደው የተመለሱ ስዎች አሉ። ብቻ በኢትዮጵያ የጽድቅ መንገዶች ስፍር ቁጥር የላቸውም። የእግዚአብሔር ቃል «ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል በክርስቶስ ኢየሱስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ» የሚለውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን በመሸፈን፤ በሰንጣቃ አለት፤ ተራራ በባዶ እግርህ በመውጣት፤ ንፍሮ በመቀቀልና ዳቦ በመጋገር ትጸድቃለህ ተብሎ ሲሰበክ የኖረው ወገናችን እንዲህ ሲንከራተት ስመለከት እጅግ ያሳዝነኛል። የክርስቶስን የመስቀል ሥራ በሰው ጥረት ለመተካት፤ የክርስቶስን ጽድቅ በሰው ጽድቅ ለመሸፈን የተጠነሰሰ የዲያብሎስ ወጥመድ ነው እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? የእርሱ ወዝ መንጠፍጠፍ መድማት መከራ መቀበል፤ እኛን ከእንዲህ ዓይነቱ ሥቃይ ለማዳን ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ንሥሐ የገባ ሁሉ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንደሚቆጠርለት መጽሐፍ ቅዱስ እየተናገረ (ሮሜ 4፥23) ወገኖቻችን ይህ የሥላሴ እውነት ባንድም በሌላም ነገር ተጋርዶባቸው በየተራራው ሲንከራተቱ እናያለን።

  አንዳንዶች ይህን ለምን እንደሚያደርጉ ስንጠይቃቸው «በብዙ መከራ ወደ መንግሥተ ስማያት ልንገባ ይገባናል» የሚለውን የሐዋርያውን ቃል ይጠቅሳሉ። ይህ ቃል ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መከራ ስለመቀበል ከዓለም በሚደርስብን ጥላቻ ሳንሰቀቅ ጸንተን ተስፋችንን እንድንወርስ የሚያስረዳ እንጂ በባዶ እግር ተራራ ስለመውጣት፤ በሰንጣቃ አለት ስለማለፍ ወይም ደረትን በድንጋይ ስለመድቃት፤ እራስን ከሰው አግሎ ታፍኖ ስለመኖር የሚያስተምር አይደለም። ጌታ ወደ ዓለም ሂዱና ተናገሩ ነበር ያለው። ከዓለም ተደብቆ ዘግቶ ስለመኖር ያስተማረ ሐዋርያም ሆነ ነቢይ አናገኝም። በገዳም ተወስኖ መጸለይን የምንወደው ቢሆንም እንኳ ከሰው ተገልሎ በአፉ ድንጋይ ከቶ ሳይናገር ከሰው ሳይገናኝ ኖረ የሚለው ግን ከሃይማኖት የወጣ ነው፤ በገዳም የሚጸልዩትም እየወጡ እንዲያስተምሩ ሕዝብን እንዲመክሩ ያስፈልጋል።
 
  ወደ ክርስቶስ ሠምራ ቃል ኪዳን ልመልሳችሁና ክርስቶስ ሰምራ ማናት? የሚለውን ላስቀድም። ክርስቶስ ሠምራ በሽዋ ክፍለ ሀገር በቡልጋ አውራጃ ጌየ በተባለች አገር ተወለደች። አባቷ በጊዜው ሀብታምና የተከበሩ ሰው ነበሩ፤ በአጼ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት በውበቷ የተደነቀች ሴት ስለነበረች 174 ባሪያዎችን ከነጉሡ ተሸልማለች። በዚያን ጊዜ ሽልማቱ ባሪያ ነበር። ገድለ ክርስቶስ ሰምራ ዘመስከረም ቁ 17። ክርስቶስ ሰምራ ባለትዳርና የ 11 ልጆች እናት ነበረች፤ ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ባሪያዋ አበሳጨቻትና በእሳት ትንታግ ጉሮሮዋን ጠብሳ ገደለቻት። በዚህ ኃጢአቷ ተጸጽታ በጌታ ፊት ጸልያ ባሪያዋን ከሞት አስነስታታለች። ከዚያ በኋላ ግን ትዳሯን እና ልጆቿን ትታ ደብረ ሊባኖስ ገብታ መነኮሰች። ምንኩስናን በደረ ሊባኖስ ከተቀበለች በኋላ ወደ ጣና ሄዳ በጣና ባሕር ውስጥ ለ12 ዓመት ያህል ሳትነቃነቅ ጸልያለች። በዚህ ጊዜ ሰውነቷ አልቆ አጥንት ብቻ ቀርቷት ነበር። አሳዎችም ባጥንቶቿ ውስጥ መመላሻ መንግድ ጎጆና መዝናኛ ሠርተው ነበር።
ክርስቶስ ሰምራ በዲያብሎስና በክርስቶስ መካከል ያለውን ጠላትነት ዘንግታ ዲያብሎስን ለማስታረቅ ወደ ሲኦል ወርዳ ከዲያብሎስ ጋር ተነጋግራለች የተባለላት ሴት ናት። ዲያሎስ ግን በዚያው በሲኦል ሊያስቀራት ሲሞክር በሚካኤል ኃይል ከብዙ ነፍሳት ጋር ለጥቂት ያመለጠችም ናት ተብሏል።

«ወ እምዝ ቦአት ውስተ ባሕረ ፃና ወቆመት ከመ አምድ ትኩል አሠርተ ወክልዔተ ዓመተ እንዘ ኢትወጽእ እስከ ያንሶሱ ማዕከል ሥጋሃ አሣ ባሕር» ትርጉም «ከዚያም ሰውነቷ ተበሳስቶ የባሕር አሣ መመላለሻ እስከሚሆን ድረስ እንደተተከለ ዓምድ ሆና ሳትወጣ ባባሕሩ ውስጥ አሥራ ሁለት ዓመት ስትጸልይ ኖረች» ገ/ክ/ ሰምራ ዘጥቅምት ቁ 4።

በዚህ ምክንያት ጌታ ተገልጦ በቀን በቀን ሦስት ሺህ ነፍሳትን ከሲኦል እንድታወጣ ሥልጣን ሰጥቷታል። ይህ ማለት ከተነሳች እስከ አሁን (በ ስድስት መቶ ዓመት ውስጥ) ወደ ቢሊዮን የሚጠጉ ነፍሳትን ከሲኦል አውጥታለች ማለት ነው።  በቀን ሦስት ሺህ ነፍሳት ከማውጣቷ በተጨማሪ የአራት ወር ያህል በየቀኑ በዓለም ላይ የዘነበውን የዝናብ ጠብታ ያህል ነፍሳትን እንድታወጣ ቃል ኪዳን ተሰጥቷታል። ስለዚህ ሲኦል በክርስቶስ ሰምራ አማካኝነት ባዶ ሆናለች ማለት ይቻላል።

«ወሶቤሃ አውስአ  ወይቤላ ንስኢ ወሐብኩኪ ዓሥራተ ብዙኃ ነፍሳተ መጠነ ነጠብጣብ ዝናም ዘ፬ቱ አውራኅ ለእለ አሐዱ ዕለት» ትርጉም «ጌታም ተናገራት እንዲህ አላት በአራት ወር ውስጥ በየቀኑ የሚወርደውን የዝናም ነጠብጣብ ያህል ነፍሳትን አሥራት ሰጥቸሻለሁ» ማለት ነው። 
የአራት ወር ያህል ዝናብ የሚያህሉ ነፍሳት ገና የተፈጠሩ አይመስለኝም። እነዚህ ሁሉ ከሲኦል ከወጡ የተኮነኑ ነፍሳት የሉም ለማለት ያስደፍራል።
 ታሪኩ በጌታ እና በሐዋርያቱ ቃል ሲመዘን፦
ለውሸታቸው ልክና መጠን የሌለው ያገሬ ደብተራዎች ይህን ያህል ለምን እንደሚጨነቁ ግልጥ አይደለም። ያነበብኋቸው ገድል ተብየዎች በሙሉ በሚያስቅ ተረት የተሞሉ ናቸው። በጣም የሚቆጨኝ ግን የዋሃን ምዕመናን ተረቶችንና ልብ ወለዶችን ሃይማኖት አድርገው መያዛቸው ነው። ከዚያም አልፈው በተረት የተሞላችውን ቤተ ክርስቲያን እንከን የለሽ አድርገው ስንዱ እመቤት እያሉ ሲመኩ እሰማለሁ። «የሚሉሽን ባልሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ» እንደተባለው አሁን የሚኮራበትን ሃይማኖት በጌታ ቃል ብንፈትሸው እሳት ፊት የወደቀ ገለባ ሆኖ ይገኛል።

  የእግዚአብሔር ቃል «ኃጥአን ወደ ዘለዓለም ቅጣት ጻድቃን ግን ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይሄዳሉ» ይላል ማቴ 25፥46። ይህ ቃል ክብር ምስጋና ይግባውና ከሰማይ ወርዶ እውነቱን የገለጠልን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ነው። ጌታ «እኔ መጥቼ ባልነገርኋችሁስ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር» ብሏል ዮሐ 15፥22። በእውነቱ በማያልፈው ቃሉ እውነቱን ነግሮናል፤ «የማይጠቅመውን ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል» ብሏል ማቴ 25፥30። ሰዎች ሲኦል ከገቡ በኋላ ተመልሰው በክርስቶስ ሰምራ አማካኝነት እንደሚወጡ ጌታም ሆነ ሐዋርያቱ አላስተማሩም፤ ሰው ሁሉ ንስሐ እንዲገባና በክርስቶስ በሆነው ቤዛነት በኩል ከሚመጣው ዘለዓለማዊ ፍርድ እንዲድን ነው ያስጠነቀቁት።

 ነቢያት «አልቦ ዘያድኅን ወዘይባልህ፤ የሚያድንም ሆነ የሚታደግ የለም» ብለዋል። ሰው ሁሉ ከሚመጣው የእግዚአብሔር ቁጣ ይድን ዘንድ አንድያ ልጁን ሰጥቷል። በእርሱ በኩል ንስሐ ገብተው የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። «በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም በ እርሱ በማያምን ግን  በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል» ይላል ዮሐ 3፥18። እውነቱ ይኸው በወንጌል የምናነበው ነው፤ የሐዋርያት እምነት የሚባለውም ይኸው ነው። በዚህ ትምህርት ጸንታ የምትኖር ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ትባላለች።
የቤተ ክርስቲያናችን ደብተራዎች ግን ሕዝባችንን የስሕተት ትምህርት አስተምረው ለእግዚአብሔር ቁጣ አዘጋጅተውታል። እግዚአብሔር በዘለዓለም መስዋእት ያቆመውን የጽድቅ መንገድ በማሳት ተራራውን ብትሳለም እንደ አርባ ቀን ሕጻን ኃጢአት ይሰረይልሃል፤ ክርስቶስ ሰምራን ስሟን ብትጠራ ከሲኦል ታወጣሃለች፤ ደብረ ሊባኖስ ብትቀበር እስከ ሰባት ትውልድ ትድናለህ ብለው እየሰበኩ ከእውነት አወጡት። ዛሬም የጥንት ደብተራዎችን ውሸት የአባቶቻችን እምነት እያሉ የሚመጻደቁ ሰዎች በማህበር ተደራጅተው የመዳን መንገድ እንዳይገለጥ እየተዋጉ ነው። እያወገዙ እያስወገዙም አሉ። እግዚአብሔር እንደ ሥራቸው የሚከፍላቸው መሆኑን ብናውቅም ሕዝባችን ከስኅተት መንገድ የሚመለስበትን ሁኔታ ከመፍጠር ሊያስቆሙን አይችሉም።
ሕዝቤ ሆይ ወደ እውነቱ ተመለስ
ተስፋ ነኝ
**************************
ለተጨማሪ መረጃ በስተግራ ካለው የመረጃ ዝርዝር ውስጥ /ሲኦል የወረደ ይወጣልን?/ የሚለውን ጽሁፍ ያንብቡ!!