Wednesday, July 11, 2012

«ቤተክርስቲያንህን እወቅ» የሚለው መጽሐፍ፤ የማኅበረ ቅዱሳን የመጽሐፍ ምንተፋ (plagiarism) ውጤት ነው


ስለማኅበረ ቅዱሳን ማንነት ገና ብዙ እንጽፋለን። የተገኙ መረጃዎችን ሁሉ እናስነብባለን። ምክንያቱም ማኅበረ ቅዱሳን ያልሆነውን ሆኖ በመታየት የዋሃንን የሚያሳስት፤ የተሳሳቱትን ወደእውነት ማወቅ እንዳይደርሱ በሩን የሚዘጋ የእውነት ሁሉ እንቅፋት ስለሆነ ነው። ከዚህ ቀደም እንደምንለው ሁሉ በቅንነትና ለቤተክርስቲያን በመቆርቆር እየተከተሉ ያሉትን የዋሃንን ሳንጨምር ነው።
ብልጣብልጦቹና መሰሪዎቹ ሲነግዱም ሆነ የሰው እውቀት ሲዘርፉ ራሳቸውን የሚደብቁት፤ ለቤተክርስቲያን የሚቆረቆሩ አፍላ የወጣቶች ማኅበር ተደርገው እንዲታሰቡ ማታለያን በመጠቀም ሲሆን በግብር ግን ከዚህ በታች እንደቀረበው ጽሁፍ የሌላውን እውቀትና ሀብት ያለምስክር በመዝረፍ እንደራሳቸው ፈጠራ ገበያ ላይ አውጥቶ በመቸብቸብ ነው።
 የሙት ወቃሽና ከሳሽ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን እነ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ፤ እነ ነጋድራስ ባይከዳኝ፤ እነ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ አጽማቸው እንዳያርፍ ስማቸውን በማኩሰስ ከሙት ዓለም እየጠራ መወንጀሉ ሳያንስ፤ እነዚህ ሊቃውንት አባቶች ካካፈሉን የእውቀት ማእድ እየሰረቀና በስሙ መጽሐፍ እያሳተመ ሲሸጥ ሃፍረት ያልፈጠረበት ኅሊና ቢስ ማኅበር መሆኑ ከምንም በላይ አረጋጋጭ ነው።
 ማኅበሩ ከእነዚህ መናፍቃንና ተሐድሶ በማለት ከሚከሳቸው ምሁራን መጻሕፍት ውስጥ ለምን መስረቅ ፈለገ? ቃል በቃል ከሰረቀስ በኋላ ለምን ያገኘበትን ምንጭ ያልጠቀሰ? ብለን ብንጠይቅ፤ ድሮውን ሲፈጠር ጀምሮ ማኅበሩ እውቀት በዞረበት ያልዞረ፤ በብልጣብልጥ ዘመንኛ ጥበብ የሚሸቅጥ፤ ግብረ እኩይ ማንነቱን በሚያጣፋው ነጠላ የሚሰውር፤ ከዚህም ቡጭቅ፤ ከዚያም ቡጭቅ አድርጎ የሚኖር  የዋህ መሳይ አውደልዳዮች የተሰባሰቡበት ማኅበር ስለሆነ ብቻ ነው። በአንድ ወቅት ከፕሮቴስታንቱ ከዶ/ር መለሰ ወጉ መጽሐፍ ላይ ገልብጦ አቶ ማኅበረ ቅዱሳን ስለጻፈው ጽሁፍ «አባ ሰላማ ብሎግ» በመረጃ አጣቅሶ አስነብቦን ነበር። አሁን ደግሞ  ሙት ከሳሹ አቶ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ተሐድሶ ናቸው ይወገዙልኝ ካላቸው ከብላቴን ጌታ ኅሩይ መጽሐፍ ውስጥ እውቀት በመስረቅ ምንጩን ሳይጠቅስ ቃል በቃል በመገልበጥና ፊደላትን በማስተካከል ብቻ አሳትሞ የነገደበትን መጽሐፍ በመንቀስ «ዓውደ ምሕረት» ብሎግ እነሆ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ይህ ነው ተዋወቁት ይለናል። በግብሩ የምትደግፉትም እፈሩ! ያፈራችሁበትም ተሸማቀቁ! ግብሩን አይታችሁ የተለያችሁትም ጥሩ ውሳኔ አድርጋችኋል። ንስሐ ማለት ከክፉ መሸሽ ነውና።
መልካም ንባብ!!

 ማኅበረ ቅዱሳን ከሚታወቅበት የክፋት ሥራዎቹ መካከል አንዱ የሰውን ጽሑፍ በመስረቅ እና የራሱ ሀሳብና እቅድ አድርጐ በሚያሳትማቸው መጽሔቶቹ፣ ጋዜጦቹ መጽሐፍቶቹ ላይ በማውጣት ነው፡፡ አንባቢ ከኔ ወዲህ ላሳር ብሎ የሚያምነው ይህ ማኅበር አይታወቅብኝም ብሎ የሰው ሥራ እየመነተፈ ከሳተማቸው መጽሐፍት መሀል ለዛሬ አንዱን እናያለን።
ይህ ሊቅ የማያስወድድ ባህሪው እያንደረደረ እና እያንቀዠቀዠ ወስዶ ይወገዙልኝ ካላቸው በርካታ ግለሠቦች መካከል የሀገራችንን የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እድገት እዚህ ደረጃ ያደረሡ፣ 42 የሚደርሡ መጽሐፍቶችን የዳሰሱ ይልቁንም እንደነ ጎህ-ጽባሕ እና አዲስ ዓለም የተሠኙ መጻሕፍቶችን የደረሱ እና ባለ ትልቅ ራዕዩና ከዘመናቸው ቀድመው የተፈጠሩት ታላቅ ሰው ይጠቀሳሉ። እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊና ኦርቶዶክሳዊ (በማ.. አጠራር ፕሮቴስታንታዊ ተሀድሶ ተብለው የተፈረጁ) ክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ይባላሉ፡፡ እኚህ ታላቅ አባት ከነ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ከነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እና ከነ ፕሮፌስር ጌታቸው ኃይሌ ጋር ፕሮቴስታንታዊ ተሀድሶ ተብለው የተፈረጁ ሲሆን ማኅበሩ ይህን  ስም የሰጣቸው ስራዎቻቸውን ሁሉ ካስወገዘ በኋላ በስሙ ለማሳተም ፈልጎ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።


ማኅበሩ 1988 . ከእርሳቸው ገልብጦ ባሣተመውቤተ ክርስቲያንህን እወቅየሚለው መጽሐፍ በተለይ የቅ/ጳውሎስንና የቅ/ጴጥሮስን ታሪክ ከእነሙሉ ሥራቸው ብላቴን ጌታ ኅሩይነቅዕ ንጹህ- ዜና ሐዋርያትብለው 1923 . ካሣተሙት ወስዶ ተጠቀሞበታል። ለማሳያ ያህል የሚከተሉትን ታሪኮች እናቀርብላችኋለን፡-
1.     ዜና ሐዋርያት ገፅ 324 (1923)
Ø ቅዱስ ጴጥሮስ ፊቱ ሰፊ ሆኖ ሪዛም ነበር፣ ቁመቱም ካጭር የረዘመ ከረዥም ያጠረ መካከለኛ ነበር፡፡
v ቤተ ክርስቲያንህን እወቅ ገፅ 65 (1988)
Ø ቅዱስ ጴጥሮስ ፊቱ ሰፉ ያለ ሲሆን ረዥምና መካከለኛ ቁመት የነበረው ራሰ በራ ሰው ነው፡፡
2.    ጥሩ ምንጭ ገፅ 330
Ø ቅዱስ ጳውሎስ መልኩና ሠውነቱ የምሥራቅ ሊቃውንት ቃል ለቃል ተያይዞ እንደመጣላቸው ከጻፉት መጻሕፍት ያገኘነውን ከዚህ ቀጥለን እንጽፋለን፡- ጭንቅላቱ ትልቅ ሆኖ ራሡ በራ ነበር፡፡ የሁለቱም ሽፋሉ ጠጉር የተጋጠመ ያውም የረዛዘመ ነበር፡፡ ዓይኖዋ ሰማያዊ ቀለም የመሠሉ ብሩሀን ነበሩ፡፡ አፍንጫውም ትልቅና ቀጥ ብሎ የወረደ ጉንጭና ጉንጩ የሮማን ፍሬ የመሠሉ ነበር፡፡ ጽሕሙና ሪዙም ረጃጅም ነበር፡፡ ጽሕም ማለት ከአገጭ ላይ በቅሎ ወደ ታች የሚወርደው ነው፡፡ ሪዝ ማለት ግን ከላይ ከራስ ጠጉር ተያይዞ የበቀለና ወደ ታች በጉንጭ ላይ ወርዶ ከጽሕም ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ አንገቱ አጠር ያለው ሆኖ ትከሻው ክብና ጎባጣ ነበር፡፡ እግሮቹ ከጉልበቱ ላይ የተቃረቡ ሆነው ከቅልጥሙ በታች የተራራቁ ነበሩ (ወርኃ ነበር ማለት ነው)፡፡ ቁመቱ ግን ከረዥም አጠር ያለ ከድንክ ረዘም ያለ ለአኃውን አሳቻ ነበር፡፡

v ቤተ ክርስቲያንህን እወቅ ገፅ 125
Ø የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲተላለፍ የኖረውን ትውፊት በማሠባሠብ ስለ ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተክለ ሰውነት እንዲህ ይላሉ፡-
ጭንቅላቱ ትልቅ ሲሆን ራሰ በራ ነበር፡፡ የሁለቱም ቅንድቦች ጠጉር የተጋጠመ አይኖቹ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ሲሆኑ ዘወትር ብሩሃን ነበሩ፡፡ አፍንጫው ትልቅና ቀጥ ብሎ የወረደ ጽሕሙና ሪዙም ረጃጅም ናቸው፡፡ አንገቱ አጠር ያለ ሆኖ ትከሻው ክብና ግብብ እግሮቹ ደግሞ ከጉልበቱ ላይ የተቃረቡ ናቸው፡፡ ቁመቱ አጠር ያለ እና ደንዳና ሰው (ከድንክ የረዘመ) እንደነበረ ይነገርለታል፡፡
3.    ጥሩ ምንጭ ገፅ 117
Ø ተሰለንቄ በቀድሞ ዘመን የመቆዶንያ ዋና የወደብ ከተማ ነበረች። ዛሬ ግን የግሪክ መንግስት ሆናለች። ስሟም ቴርማ ይባል ነበር። ቴርማ ማለት ፍልውሃ ማለት ነውና አጠገብዋ ፍልውሃ ስለመኖሩ ነበር።በኃላም ካሳንድር የተባለ ጌታ የትልቁን እስክንድር እህት ሳሎኒቃ የምትባለውን አግብቶ የቴርማ ገዢ ሆኖ ነበርና ሚስቱን ሳሎኒቃን ደስ ለማሰኘት ሲል ቴርማ መባሏን አስቀርቶ ተሰሎንቄ ብሎ ስለሰየማት ከዚያ ዘመን ጀምሮ አስካሁን ተሰሎንቄ እየተባለች ትጠራለች።
ተሰሎንቄ ከአውሮፓ ወደ እስያ ለሚተላለፍ ንግድና ሰው ሁሉ ዋና የባሕት በር ስለሆነች ከአድርያቲክ ባህር ጀምሮ እስከ ተሰሎንቄ የሰረገላ መንገድ ተሰርቶ ንግዱም ሰውም ያለችግር ይመላለስ ነበር።
v ቤተ ክርስቲያንህን እወቅ ገፅ 118
ቀድሞ የመቆዶንያ ዋና ወደብ ነበረች። ዛሬ ግን በግሪክ ሥር ናት። ስሟ ቀድሞ ቴርማ ይባል ነበር። ትርጉሙም ፍል ውሃ ማለት ነው።ይህ ስም ከአጠገብዋ ከነበረው የፍል ውሃ የተወሰደ ነበር። በኃላ ግን ካሳንደር የተባለ ገዢ የታላቁን እስክንድር እህት ሰሎኒቃን ስላገባ ከተማዋን በሚስቱ ሰየማት። ከአውሮፓ ወደ እስያ በሚያልፈው ዋና መስመር ላይ ስለምትገኝ ከተማዋ ዋና የንግድ ማዕከል ነበረች።

የሀሳብ አወራረዱን ተመለከቱ፤ የታሪኩን አወቃቀር ተመልከቱ፤ ሁለቱ መጽሐፍት በአጋጣሚ ታሪኮቻቸው ሁሉ በሀሳብ አወራረድና በታሪክ አወቃቀር አንድ አይነት ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊኖር አይችልም። አንዱ የአንዱ ቅጂ ካልሆነ በቀር። ምንተፋ(plagiarism) የሚባለው ይኸው ነው።
በአጠቃላይ ሁለቱን መጽሀፍት ጎን ለጎን አስቀምጦ ያየ አስተዋይ አንባቢ ቤተክርሰቲያንህን እወቅ የጥሩ ምንጭ ግልባጭ መሆኑን በቀላሉ ይገነዘባል። መጽሀፉን አይተነዋል ለማለት ቤተክርስቲያንህን እወቅ ላይ በአንዳንድ ቦታ በምንጭነት የተጠቀሰ ቢሆንም ባነሳናቸው ነጥቦችና ላይ በሌሎችም የመጽሐፉ ክፍሎች ጥሩ ምንጭ በምንጭነት አልተጠቀሰም። ጥሩ ምንጭ የተጻፈበትን የቀድሞ አማርኛ በዘመናዊው አማርኛ አቃንቶ መጻፍ የመጽሀፉ ባለቤት አያሰኝምም አያስደርግምም። ማኅበረ ቅዱሳን ሕሊና ቢኖረው ኖሮ ቤተክርስቲያንህን አወቅ የብላቴን ጌታ ኅሩይ መጽሀፍን በዘመኑ አማርኛ አስተካክዬ ሀሳቡን ለማብራራት የታከሉ ምሳሌዎችን ቀንሼ አና የሌሎች ሐዋርያትን ታሪክ አክዬበት ያሳተምኩት መጽሐፍ ነው ማለት ነበረበት።
እነ መጋቢ ሐዲስ በጋሻውንየጻፋከው መጽሐፍ ርዕስ ከአንድ የጴንጤ ሰባኪ ስብከት ርዕስ ጋር ተመሳሳይ ነው ስለዚህ መናፍቅ ነህእያለ እያዋከባቸው ያለው ማኅበር ለራሱ ጊዜ ከሞቱ 80 ዓመት በኋላ መናፍቅ ናቸው ይወገዙልኝ ሲል የጅምላ ይወገዙልኝ ጩኸት ካሰማባቸው ኢትዮያዊያን ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑት ስመ ጥሩው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴን መጽሐፍ መንትፎ በስሙ ማሳተሙ የሚያስገርምም የሚያሳዝንም ነው።
እንግዲህቤተ ክርስቲያንህን እወቅብሎ ማኅበሩ ያዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ የሁለቱን ሐዋርያት ታሪክ፣ ሥራ፣ እራሱ የደከመበት የተመራመረበት አሥመስሎ አሳትሞታል፡፡ ይህ ማኅበር ሊቃውንት እንዳይታወቁ ብሎም ከእነ ሥራቸው እንዲረሡ፣ እንዲጠፉ እየጣረ የሚገኘው ዛሬ ሳይሆን ከመነሻው ጀምሮ ነው፡፡ የእኝህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጽሑፍ መሥረቅ ሳያንሳቸው አሁን ደግሞ ይወገዙልኝ ከሚላቸው ውስጥ ደምሮአቸዋል፡፡
በአንድ ወቅት / ሃይለማርያም ላቀው የተባለ በስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ ላይቤተ አብርሃምአምድ አዘጋጅ የብላቴን ጌታ ኅሩይን ታሪክ በጋዜጣው ላይ ጽፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ ይኸው ግለሰብ የእሳቸውን የሕይወት ታሪክና ሥራ በመጽሐፍ መልክ እያዘጋጀ እንደሆነ ታማኝ ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ለመሆኑጎህ ጽባሕእናአዲስ አለምየተሠኙ መጻሕፍቶቻቸውን ምን ይላቸው ይሆን? በጉጉት እንጠብቃለን፡፡
ማህበሩ በነካ እጁ የሌሎችን ሥማቸውን ያጠፋቸው ሊቃውንት አስወግዞና አስረግጦ መጽሐፎቻቸውን በስሙ ያሳትም ይሆናል ብለንም እንጠብቃለን። ሃሳብን አሳጥሮ እና ከርክሞ ማቅረብ ደራሲ እንደማያደርግ ከሁሉ በላይ ምናልባት በውስጣችሁ  ካለ ህሊናችሁ ይነግራችሁ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በስነ ጽሁፍ ህግ ምንተፋ በእንግሊዘኛ ስሙ/ plagiarism / የሚባለው እንዲህ አይነቱ ወንጀል ነው። ይህ ወንጀል በጽሁፍ ስራ ከሚፈጸሙ  ወንጀሎች ሁሉ ትልቁ እና ዋነኛው ነው።
ይሄ ሁሉን አንክስ ሲል ጊዜ የጣለው ማኅበር አባላቱ  በተለይ በጽሑፍ ሥራ ላይ የተሠማሩት ከፕሮቴስታንት መጽሐፍቶች ላይ ሳይቀር እንደወረደ በመገልበጥ ለአደባባይ ያበቁ እና ደራሲ የተሰኙ የስምአ ጽድቅ አምደኞችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህን በተመለከተ ወደፊት በበቂ ሁኔታ የተዘጋጀ ሥራ ስላለ ማን ከማን ወሠደ የሚለውን አሳፋሪ ሥራ እንገልጣለን፡፡ የጽሁፍ ሥራ ጸጋ ሲሆን ከላይ ይሰጣል። ምንጩም የማይቋረጥ ይሆናል። የጽሁፍ ስራ እልህ ሲሆን እንዲህ ሰው አያውቅም እያሰኘ የሰው ሥራ ያስገለብጣል። መጽሐፍ ካላሳተምኩ የሚል እልህ የትም አያደርስም እና የሰው ሥራ ከመመንተፍ ልባችሁንም፣ ህሊናችሁንም፣ እጃችሁንም  እግዚአብሔር ይፈውስላችሁ።