Saturday, July 14, 2012

ማኅበራት የክፍፍል መድረኮችና የሁከት ምንጮች ሆነው እያስቸገሩ ነው!



ከወደ ጠቅላይ ቤተክህነት አካባቢ ሰሞኑን «ጉባዔ አርድእት» የሚባል ጊዜያዊ ማኅበር ይቋቋማልን እንደማንኛውም ሰው ሰምተናል። እኛን ግራ የገባን ይህ «ጉባዔ አርድእት« የተባለው መቋቋሙ ሳይሆን ከተቋቋመ 20 ዓመቴን ሞልቻለሁ የሚለው ጎረምሳው ማኅበር ማቅ ግን ሽብር የገባበት ምክንያት አስገራሚ መሆኑ ነው። 

ሁለት ነገር እንድናነሳ ተገደድን። አንደኛ ማኅበሩ ከእኔ ወዲያ ሌላ ማኅበር አያስፈግም  የሚል የጽንፈኝነት ጥግን የታጠቀና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በእኔ በኩል ያላለፈ መንፈስ ቅዱስ እንዴት እዚያ ይደርሳል? ስለዚህ እፍ! ያላልኩበት  ማኅበር ሊኖር አይችልም የሚል ስግብግብነት የሞላው ጠባብ አስተሳሰቡ ነው።

በአንድ በኩል የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና የቅድስት ሥላሴ ኰሌጅ ደቀመዛሙርት ማኅበራት መኖራቸውን እደግፋለሁ ሲል እየተደመጠ በሌላ በኩል ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ስብስብ እንደሆነ የሚነገርለት «ጉባዔ አርድእት» መቋቋምን  ስመለከት ዓይኔ ደም ይለብሳል  ዓይነት ቅናት ከሰይጣን እንጂ ከመንፈስ ቅዱስ ሊሆን አይችልም።
ይህ ይቋቋማል የሚባለው የጉባዔ አርድእት ማኅበር አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ  በሥራ ላይ ያሉ የቤተክርስቲያኒቱ ሰዎች እስከሆኑ ድረስ ማኅበረ ቅዱሳንን ይህን ያህል ያስጨነቀው ለምንድነው?   ቤተክርስቲያኒቱን  ይጥቀምም፤ አይጥቀምም ራሱ ማቅ እንደ ማኅበር የተቋቋመበትን መንገድ ሌሎች የዚሁ መብት ተጠቃሚ የመሆን  መብት እንዳይኖራቸው መጮሁስ ምን ይባላል?

ማንም የሾመው ባይኖርም« ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው እንዲሉ» ራሱን በራሱ ሾሞ  ከጉባዔ አርድእት አባላት መካከል  አንዳንዶቹን በተሐድሶነት ይወነጅላል።  በተለመደ የድራማው ትወና  አፈኞቹን ጉዳይ ፈጻሚዎቹን በደንብ ጭኖና አስፈራርቶ እነዚያ የሚወነጅላቸውን ሰዎች በቀጣይ ጉባዔ እስኪያስወግዝ ድረስ የቤተክርስቲያኒቱ አባላት መሆናቸውን አምኖ መቀበል የግድ ይሆናል። ስለዚህ ጉዳይ ፈጻሚ  አባቶቹ የማኅበሩን ተልእኰ ተቀብለው ውግዘት  እስኪያወርዱ ድረስ በሥራ ላይ ያሉ ሰዎች የቤተክርስቲያኒቱ አባላት ናቸውና ማቅ ማኅበር ሆኖ እንደሚንቀሳቀሰው ሰዎቹንም ማኅበር እንዳያቋቁሙ የሚከለክላቸው ምንም አሳማኝ ነገር የለም።
ይልቁንም  ማኅበርሩን እንደዚህ ሽብር ውስጥ የከተተውን ነገር ከማኅበሩ ግልጽና  ስውር ዓላማ አንጻር ከታች የተመለከቱትን ነጥቦች ማንሳት እንችላለን።

1/ ጉባዔ አርድእት በቤተክርስቲያን ሙያ የበለጸጉ ምሁራንና በዘመናዊውም የበሰሉ ሰዎች ስብስብ እንጂ እንደ ማቅ አባላት የክብር ቅስና ያልተሸከሙና  የንግድ ግዛት /ኢምፓየር/ ያላቋቋሙ በመሆናቸው፤

2/ የጉባዔ አርድእት አባላት ናቸው ተብለው የሚነገርላቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ በቤተክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የአመራር እርከን ላይ የሚገኙና  በሰንበት /ቤት ሽፋን አንድ እግራቸውን እንደማቅ ውጪ ያላደረጉ ስለሆነ፤

3/ በዚሁ በአዲሱ ማኅበር ውስጥ ይካተታሉ የሚባሉት ሰዎች አብዛኛዎቹን ማቅ ሲወጋቸውና ሲያደማቸው የቆዩ በመሆናቸው ውሎ አድሮ የእጄ ይከፈለኛል የሚል ፍርሃት ማቅን ስለሚያስጨንቀው፤

4/ በማኅበረ ካህናቱ ዘንድ «ማቅ፤ ጢም የሌለው አልቃኢዳ» እየተባለ መጠራቱ የሚታወቅ ሲሆን ጉባዔ አርድእት ህልው ሆኖ ከተቋቋመ በአባልነት ይሁን በተሳታፊነት ማኅበረ ካህናቱን ሁሉ ስለሚጠቀልል  መንቀሳቀሻ ስፍራ ያሳጡኛል የሚል ስጋት፤

5/ በሕዝብና በመንግሥት ዘንድ አስቸጋሪነቴ ግልጽ ይወጣል ከሚል ፍርሃት፣

 6/ ተሐድሶ ወይም ጴንጤ እያልኩ የዓይኑ ቀለም ያላማረውንና ለእኔ ያልተንበረከከውን ሁሉ ለማድቀቅ ይቸግረኛል ከሚል እሳቤ የተነሳ፤
7/ የታዛዦቼን ሊቃነ ጳጳሳት ቅስም በመስበርና በማስፈራራት ለአቡነ ጳውሎስ እንዲገዙ በማድረግ የሲኖዶስ ላይ ስውር ድምጼ ይታፈናል፤ አባ ጳውሎስም  ጉባዔ አርድእትን እንደአንድ ኃይል ሊጠቀሙት ይችላሉ ብሎ በመስጋት፤

8/ አሁን ያለኝ እንቅስቃሴ ከጫፍ እጫፍ መድረሱ እክል ሊገጥመው ይችላል ብሎ ለእጀ ረጅምነቱ ከመጨነቅ አንጻር ሲሆን

ከብዙ በአጭሩ ሊነሳ የሚችል ውጥረቶቹ እንደሆኑ እነዚህን ልንገምት እንችላለን። እንዲያውም ከግምት በዘለለ የማኅበሩ አፈቀላጤ የሆነው «ደጀ ሰላም» ማቅ ይደርስብኛል ብሎ ከሚያስበው አንዱን ስጋት እንዲህ ሲል ተናግሯል።

«የአባ ጳውሎስን ዐምባገነንት ለማጠናከር፣ መንፈሳውያን ማኅበራትን ለማፈራረስ፣ የግል እና የቡድን ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ….» በማለት በግልጽ አስቀምጧል።


ስለዚህ ከዚህ ፍርሃት ለመገላገል ያለው የነፍስ ውጪ ትንቅንቅ ይህ አዲሱ ማኅበር በሁለት እግሩ ሳይቆም ባለና በሌለ ኃይል ህልውና እንዳያገኝ ማዳፈንና ደፍቆ ማስቀረት የማቅ የመጨረሻ ውሳኔ ሆኗል ማለት ነው።
በአንድ በኩል ስለማኅበራት መኖር የማኅበራትን ስም እየጠቀሰ የሚናገረው ይህ ሰለፊ ቡድን ማንነቱን ገምግሞ ሊመጣብኝ ይችላል ከሚለው ፍርሃት የተነሳ በተለየ ሁኔታጉባዔ  አርድእትን እንደአዲስ ከመቋቋሙ በፊት ለመድፈቅ የሚያደርገውን መቅበዝበዝ  ስንመለከት  ማቅ  ኃይሉ፤ ክንዱ፤ ብርታቱና ጥበቃው ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከምድራዊ ተንኮሉ፤ የገንዘብ ጡንቻና የሴራ መጎንጎን ብቃቱ አንጻር ብቻ ኅልውናውን ከማስጠበቅ ውጪ ሌላ የሚታመንበት ሰማያዊ ኃይል የሌለው የሲሲሊ ማፊያ መሰል ቡድን መሆኑን ያስመሰከረበት ሆኖ አግኝተነዋል።

ማቅን የሚጠሉ ሰዎች ለጥላቻቸው መነሻ የሆነውን  ምክንያት ሲሰጡ በተቃራኒው ደግሞ ማቅ ለቤተክርስቲያን የማደርገውን ትግል ካለመቀበል የመነጨ ነው የሚል ጩኸት እንደሚያሰማው ሁሉ ፤ ጉባዔ አርድእትም በበኩሉ ለመልካም ስራ መነሳቴ የዓሳ እሾክ ሆኖብህ ነው ቢል ተገቢ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ለራሱ መከላከያ የሚያቀርበውን መልስ ትክክል አድርጎ ከተቀበለ፤ እንደዚያው ሁሉ ሌሎችም ለራሳቸው መከላከያ አድርገው ቢያቀርቡ ሊያስገርመው አይገባም።  እኔና የኔ አጋሮች ብቻ ይኑሩ ማለቱ ስስታምና ራስ ወዳድ  ማኅበር መሆኑን ያረጋግጥበታል።
እኔ ስናገር ሁሉ ነገር ትክክል ነው፣ እንደእኔ ሌሎች ሲናገሩ መስማት  ያመኛል ማለት ከመንፈሳዊ አስተሳሰብ የሚመነጭ እሳቤ አይደለም።

ሌላው የዚህን ስድ ማኅበር የባለጌ ለቅሶ አስገራሚ የሚያደርገው ነገር፤ ቤተክርስቲያኒቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ / ጠንካራም ይሁን ደካማ/ በሥራ ላይ የአስተዳደር መዋቅር ያላት ሲሆን ማኅበራት በሚቋቋሙበትና ፈቃድ በሚያገኙበት ደንብ ሊስተናገድ የሚችለውን አዲስ ማኅበር አስቀድሞ ይዘጋ በማለት የሚያደርገው የሁሉን ዐቀፍነትና የሁሉን ገዢነት አባዜው ጉዳይ ነው። አዲሱን ማኅበር ከመቋቋም  ለመከልከልም ሆነ ለመፍቀድ የሚያስችለው ቤተክርስቲያኒቱ ያላት ደንብ እንጂ የማቅ እሪታ ሊሆን አይችልም።  ምናልባትም ደንቡ የተጣሰበት ወይም የተረገጠበት አግባብ ካለ ያንን አንስቶ ለሁላችን ገዢ የሆነው የማኅበራት መቋቋሚያ ደንብ ይከበር በማለት በመርህ ደረጃ ከመከራከር በዘለለ  ማቅ የቤተክርስቲያን ደንብ ሆኖ ማንንም ለመከልከልም ሆነ ለመፍቀድ መብት የለውም። 
 ካለን ተሞክሮ ተነስተን ስንመለከት ማቅ ደንብ ቢከበር ወይም ቢጣስ  ጉዳዩ አይደለም። ማኅበራት ዐሥር ጊዜ ደንቡን ጥሰው ማቅን እስከተስማሙት ድረስ እሱ ስለደንብ አይገደውም! ይልቅ የእሱ ፍርሃት ስድና ድንበር የለሽ መደዴ ተግባሩ እንቅፋት እንደሚገጥመው በመጠርጠር ሲሆን፤ በአፈጉባዔው በደጀ ሰላም በኩል ያንን ስጋት እንዲህ ይላል።

«የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ዋና ሥራ አስኪያጅና የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችን እንዳሻቸው ለመሾምና ለመሻር፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ከአንዱ ሀገረ ስብከት ወደ ሌላው እንዳሻቸው ለማንከራተት፣ ኤጲስ ቆጶሳትን እንዳሻቸው ለመሾም. . . ወዘተ በማስቻል ዐምባገነናዊ አስተዳደራቸውን ለማጠናከር፤ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን፣ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበርና ሌሎችም በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መስፋፋትና መጎልበት ዙሪያ የሚሠሩ ማኅበራትን በ”ባዕድ አደረጃጀትና ተቀጽላ” እንዲቆጠሩ በማድረግ ለማፈራረስ…….» ነው ጉባዔ አርድእት የሚቋቋመው ይለናል።

ስለዚህ  እኔ  ምድራዊው  አምላካችሁ ማቅ  ከማደርግላችሁ ጥበቃ ውጪ ህልውናችሁ ማብቃቱ ቁርጥ ነው።  ይህ አዲሱ ጉባዔ እንዳይቋቋም ካገኘሁት ምድራዊ መገለጥ የደረስኩበት ትንቢት፤ ያለእኔ እውቅና ሊቃነ ጳጳሳት ይሻራሉ፤ ይሾማሉ፤ ማኅበራት ይዋከባሉ፤ ስለዚህ ይህን ባእድ ኃይል አስቀድመን ድባቅ እንምታው ይለናል ይህ  እከይ  ማኅበር።
ስናጠቃልል ማኅበሩ እንኳን ትንቢት ከቅዠት ያለፈ ህልም እንኳን የማይታየው ሆኖ ሳለ ይህን ያህል በክፉ ሃሳብ ሜዳ ላይ እየተንደባለለ የሚላላጠው፤ ጥቅሙንና ስልታዊ መንገዱን ለመጥረግ እንጂ ሕግና ደንብ ስለተጣሰ ወይም ስለሚጣስና ያንን ከማስከበር አንጻር አይደለም። የራሱ ክፋትና ተንኰል እረፍት እየነሳውና የበደል እጁ እያክለፈለፈው እንጂ  የጉባዔ አርድእት መቋቋም ምናልባት ለማቅ ችግር ይሆን እንደሆን እንጂ የቤተክርስቲያን ችግር የሚሆነው ማቅ በሚያሰላው ስሌት አይደለም። 

ቀኝም ነፈሰ ግራ ማቅ በተመሰረተበት ደንብ ሌላ ማኅበር እንዳይመሰረት የሚከለክለው ደንቡ ራሱ እንጂ ደንብ የወለደው ማቅ አይደለም። ስለዚህ «ጉባዔ አርድእት» በህግና በህግ አግባብ ከመቋቋም ሊከለከል አይችልም። 
  ይሁን እንጂ ለማኅበራት ካለን ግምገማ ተነስተን እንደእኛ ምልከታ «ጉባዔ አርድእት» ይሁን «ማቅ»  ለቤተክርስቲያኒቱ ትልቁ ሸክምና ጠንቅ  ከመሆን አልፈው  የሚጠቅሙ አካላት ይሆናሉ ብለን አናስብም።

 እስካሁን በሚታየው ሁኔታ ማኅበር ተብለው በቤተክርስቲያን ውስጥ የተተከሉት ብጥብጥና ሁከትን ሲቀፈቅፉ እንጂ  አንድም የልማት አካል ሲሆኑ አልታዩም። ከማስመሰያ ያለፈ ግዘፈ አካል የላቸውም። የሚነግዱትና የሚያስነግዱት ለራሳቸው  ጡንቻ ማጠናከሪያነት ብቻ ነው። እንዲያውም በቤተክርስቲያኗ ኪስ ሊገባ የሚገባውን በሚሊዮኖች ብር በራሳቸው ካዝና የሚያግበሰብሱ የመስቀሉ ስር ቁማርተኞች ማኅበራት ሆነው ይታያሉ። ስለሆነም ማኅበረ ምእመናን ያሉባት  ቤተክርስቲያን አንዲት እንጂ በስምና በቡድን የተከፋፈለች ስላልሆነ አንዲቷ ቤተክርስቲያን ተጠናክራ፤ አጋድመው ከሚግጧት ማኅበራት ሁሉ ነጻ መውጣት አለባት እንላለን። ከጽዋ ማኅበርነት ያለፈ አስመጪና ላኪ ማኅበር ውሎ አድሮ ጠንቅ  ነውና ማኅበራት ሁሉ ይፍረሱ! 

ምክንያቱም ማኅበራት የክፍፍል መድረኮችና  የሁከት ምንጮች ሆነው እያስቸገሩ ነውና!