Sunday, July 29, 2012

እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ!


እግዚአብሔር ይወድሃል! በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ እያለህ መግቦቱን ያልከለከለህ ስለሚወድህ ብቻ ነው። ሰዎች በኃጢአት ውስጥ ስንኳ እያለን ዝም የሚለን በሕይወት እንድንኖር ጊዜ የመስጠት ፍቅሩ ነው። ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም።  ወይኑ የሚያፈራው መራራ መሆኑን እያወቀ እንኳን ወይኑን ቶሎ አይነቅለውም። ወይኑን ይንከባከባል። ጣፋጭ ፍሬ እንዲያፈራ ይጠብቀዋል። ነገር ግን ወይኑ በተደረገለትና በተሰጠው ነገር ሁሉ ፍሬያማ መሆን ካልቻለ «ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ?» ብሎ የወይኑ ባለቤት መራራውን ወይን ይነቅለዋል። የመራራው ወይን መጨረሻም እጣ ፈንታ መራራ ይሆናል።
   እናም ወንድሜ ሆይ! መግቦቱን፤ ፍቅሩንና ትእግስቱን እንድናውቅለት እግዚአብሔር ይፈልጋል። በፍቅርና በምሕረት እንጂ በኃይልና በማስገደድ የሚገዛን እንዳልሆነም እንድንረዳ ይሻል። «በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ ድርቆሽም ጣልሁላቸው» እንዳለው  የሚስበን በፍቅሩ እስራት፤ ከሸክምም ነጻ በማውጣት፤ መግቦቱን በፍቅር እንጂ በማስገደድ አይደለም። ሆሴዕ 11፤4
ወንድሜ ሆይ፤ በሰውነታችን የወይን ተክል፤ መንፈስ ቅዱስን ብናስመርረው ከበረሃ ላይ ወድቀው እንደቀሩት ዐመጸኞች፤ የዐመጻ ዋጋችንን መቀበላችን አይቀርም።  ዐመጽን እንድንጸየፍ፤ ጽድቅን እንድንወድቅ አማራጭ የለው ምርጫችን ነው። ዐመጽን ጠላሁ፤ ጽድቅንም ወደድሁ ብሎን የለ! ዐመጽን ልንጠላ፤ ጽድቅንም ልንወድ ይገባል።
ጥያቄው መቼ? የሚል ይሆናል። መልሱንም  በቃሉ ይናገራል።  «የመዳን ቀን አሁን ነው» ያለው ሐዋርያው ለመዳን ፈልገው፤ ጩኸታቸውን ለማሰማት ለተነሱ የመራራ ነፍስ ባለቤቶች ሁሉ ነው። «በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው» 2ኛ ቆሮ 2፤6
ከዐመጻ ለመውጣት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደው ሰዓት፤ ኃጢአትን ለመተው ውሳኔ ባሳለፍንበት ቅጽበት ነው። በዚያም በመዳን ቀን ረዳሁህ የሚል አስተማማኝ ኃይል ይሰጠናል። ሰዓቱም አሁንና አሁን ብቻ ነው።
ምናልባት ተዘጋጅተንበትና ጊዜ ሰጥተን ሁኔዎችን  ካመቻቸን በኋላ ቢሆንስ? የሚል አስተሳሰብ ሊኖር ይችላል። ይሁን እንጂ «ቀን የሚያመጣውን ምን እንደ ሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ» እንደተባለው ነገ የእኛ ቀን ስለመሆኑ ቀናቶቹን በእጃችን የያዝናቸው ስላይደለ በሌለን ነገር ላይ ተስፋ እናደርግ ዘንድ የተገባ አይደለም። የእኛ ቀንና የተሰጠን ተስፋ አሁን ያለንባት የሕይወት ጊዜ ብቻ ናት። እሷም ብትሆን «ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁና» ያዕ 4፤14  ተብሎ ስለተጻፈ እንኳን ለነገው ቀን ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሕይወታችን ላይ ለሚመጣው ነገር የምናውቀው ምንም የለም። እናም መራራው ወይናችን የሚነቀለው ቀን ከመድረሱ በፊት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሳለን ለመገበን አምላክ ጣፋጭ ለመሆን አሁኑኑ እንሠራ!!  «እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ»
ከኃጢአት በመውጣት መንፈሳዊ ቤት ለመሆን የምንሠራው በቁርጠኝነት እንጂ በጠባይ፤ በቀጠሮና በመለሳለስ አይደለም። ያልጀገነ ተዋጊ ጠላቱን ሊያሸንፍ እንደማይችል ሁሉ ጠላትም ድል ለማድረግና በኃጢአት ምርኰ ይዞ ለማቆየት አይለሳለስምና ኃጢአትን በመተውና በመዳን መካከል ድርድር የለም። ጠላታችን በጀግንነት ካልተዋጋነው በስተቀር ካለማመደን ኃጢአት ውስጥ በነጻና በፍላጎት አያሰናብተንም። ጠላት ምን ጊዜም ጠላት ነው። እናም ውጊያችን መራራና ጠንካራ መሆኑን አውቀን መግጠም ይገባናል። በእኛና በጠላታችን መካከል ያለው ልዩነት ጠላታችን ውሱን ማንነት ያለው፤ ከኃይል በቀር ሥልጣኑን  የተቀማ ሲሆን በእኛ ዘንድ ያለው ሰይፍ ግን ሁሉን በእጁ የያዘ የፈጣሪ ኃይል፤ የሁሉ ገዢና አስገኚ፤ የዘላለማዊ ሥልጣን ባለቤት በመሆኑ የውጊያው አሸናፊነታችን በምክንያትና በሁኔታ ላይ ያልተወሰነ፤ እርግጠኛና አስተማማኝ ነው። ግን ይህንን ኃይል እንዴት መታጠቅ እንደምንችል፤ መቼ መታጠቅ እንዲገባንና እንዴት መጠቀም እንዳለብን ብዙዎቻችን እውቀቱ የለንም። ይህ አስተማማኝ አሸናፊነት እያለው የሰው ልጅ ሁሉ በኃጢአት የሚሸነፈው ታዲያ ለምንድነው?
እንደ ጳውሎስ ቁርጠኛና አሁኑኑ ወደውጊያው ለመግባት የሚወስን ጀግና መሆን ባለመቻሉ የሰው ልጅ ለሚሸነፍለት ኃጢአት ተሸንፎ ይኖራል። ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ቀንቶ ክርስቲያኖችን ለማሳደድና ወኅኒ ለመወርወር እንኳን ቅንጣት አላመነታም።  ከኢየሩሳሌም ተነስቶ 217 ኪሎ ሜትር በእግሩ ወደ ደማስቆ ለመጓዝ ቅሌን ጨርቄን አላለም።  የጳውሎስ ጉዞ የክርስቶስን ቤት ለማፍረስ ቢሆንም እንደቁርጠኛ ውሳኔውን ግን ለእግዚአብሔር ከታሰረለት ፍቅር የተነሳ ነበር። ለእግዚአብሔር ፍቅር ጠላትን የሚዋጋ ጊዜ መፍጀት እንደሌለበት  ያመላከተ ሆኗል። ጳውሎስ በመንገዱ ላይ ያጋጠመው ብርቱ ኃይል ከእርሱ የሚበልጥ በመሆኑም  «አንተ ማነህ?» ማለቱም የጀግንነቱ ልክ መገለጫ ነበር። እግዚአብሔርም ራሳቸውን ለእርሱ የሰጡትን እንደዚህ ዓይነቶቹን ሰዎች ይወዳል። ጀግናን ማን ይጠላል?


«እኔም። ጌታ ሆይ፥ ማንነህ? አልሁ። እርሱም አለኝ። አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ።
ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና»  የሐዋ 26፤15-16
ጳውሎስ በጀግንነቱ እምነት ተጥሎበት ምድራዊ የውጊያ ደብዳቤ ከኢየሩሳሌም ተሰጥቶት ነበር። በደማስቆ መንገድ ላይ ጀግኖችን ሁሉ የሚያሸንፈው የይሁዳ አንበሳ ባገኘው ጊዜ ደግሞ አገልጋይና ምስክር ልትሆን ሾምሁህ ሲባል ራሱን ለመስጠት አላቅማማም።
«ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም» ይለናል።
 ወንድሜ ሆይ ለመንፈሳዊ ውጊያ ቆራጥነት ያስፈልጋል። ራስን መስጠት የግድ ይላል። የጳውሎስ ጀግንነት ለእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ለመሆን እንጂ ከኃጢአት በመሸሽ ላይ ያልተመሰረተ ከሆነ የእኔና የአንተማ ከኃጢአት የመሸሽ ጀግንነት  እንዴት የከበደና የበለጠ ቁርጠኝነት ይጠበቅብን ይሆን?
አ-ዎ! ከባድ ጀግንነት ይጠበቅብናል። ምክንያቱም  ውጊያችን ከባድ ነው። «መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ» ኤፌ6፤12
ኃጢአትን ለመተው ስንወስን፤ ኃጢአትን የሚያሸንፍ ኃይል ይሰጠናል። የሚያሸንፈው በእኛ ያለው የእግዚአብሔር ኃይል እንጂ የኛ ብርታት አይደለምና። እኛ በቁርጠኝነት ለመዋጋት የምንሸከመው የእግዚአብሔር መንፈስ እንድናሸንፍ ይሸከመናል። ሰው ኃጢአትን መጥላትና በመጀገን፤ ለውጊያ በመዘጋጀትና በመዋጋት፤ በኃይሉ ትጥቅና በማሸነፍ መካከል ያለውን ልዩነትና ትስስር እስካላወቀ ድረስ ከኃጢአት ሸክም ነጻ መሆን አይችልም። የልምድና የልምምድ ባሪያ እንደሆነ ይኖራል።
አንዳንዴ ደግሞ ይህንን ጠንካራ ውጊያ እንዳንዋጋ የሚያዘናጋ የደኅንነት ስሜት ይሰማን ይሆናል። የምንጾም፤ የምንጸልይ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን የምናነብ፤ ዐሥራት የምናወጣ፤ መንፈሳችን የሚቀበላቸውን መልካም ነገሮች ስለምናደርግ ደኅንነት የተሰማን ይመስለን ይሆናል። እነዚህ በራሳቸው ጥሩዎች ናቸው። ነገር ግን ነጻና መዳናችን የሚረጋገጥባቸው ነገሮች አይደሉም።
ኖኅ «እግዚአብሔር አናገረኝ፤ በ120 ዓመት ውስጥም መርከብ ስራ አለኝ» ብሎ ለወገኖቹ ሲናገር ስቀውበት ይሆናል። እግዚአብሔር ተገልጾ አናገረኝ ፤መርከብም ለመሥራት 120 ዓመት ተሰጥቶኛል የሚልን ሰው ንግግር መስማት በእርግጥም ከባድ ነው። እውነታው ግን የተነገረውን በፍጹም ልቡ፤ በፍጹም ነፍሱና በፍጹም ኃይሉ አምኖ በመቀበል የሚገኝ  በመሆኑ በኖኅና በወገኖቹ መካከል ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል የሰፋ ነው። ማር 12፤30   ሰው ራሱን ለእግዚአብሔር ፈቃድ በፍጹም ልቡ፤ በፍጹም ነፍሱ፤ በፍጹም ኃይሉ ማስገዛት ማለት ለረጅሙ የ120 ዓመት አገልግሎት መዘጋጀት፤ በምድረ በዳ ላይ ምድሪቱን ውሃ ይሞላል ብሎ አምኖ በመቀበል የተረጋገጠ ነበር። ሰው አምኖ አድራጊውን ካልተቀበለ፤ ድርጊቱን የመፈጸም ኃይሉን እንደማይቀበል ያሳየ ነበር። የኖኅ ወገኖች እግዚአብሔርን ያውቁታል። ግን ቃሉን አምነው አልተቀበሉም።
ማንም ሰው መርከብ ሰውነቱን ከኃጢአት ማየ አይኅ ለመጠበቅ፤ እና በዚህ ሰውነት ላይ የሚገለጹ የመንፈስ ፍሬ በውስጡ እንዲኖሩ አስቀድሞ በፍጹም ልቡ፤ በፍጹም ነፍሱና በፍጹም ኃይሉ አምኖ መኖር አለበት። በኃጢአት ውስጥ እያለን መዘመርም፤ ማመስገንም፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብም፤ መጾምም ይቻላል። ፍሬ ማፍራት ግን ፍጹም ለእግዚአብሔር ፈቃድ ከመሰጠት የሚገኝ ነው።
ለእግዚአብሔር ፈቃድ መሰጠት ማለት ደግሞ በፍጹም ልብ፤ በፍጹም ነፍስ እና በፍጹም ኃይላችን እግዚአብሔርን መውደድ ማለት ነው። ሰይጣን ራሳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ አሳልፈን ሳንሰጥ ትእዛዛቱን ብቻ በመጠበቅ ደኅንነት እንዲሰማን ይፈልጋል። የሚጾሙ ዘማዎች ሞልተዋል። ዘማነትን ግን ከስጋቸው ላይ አውልቀው በመጣል የእግዚአብሔር ቅዱስ ስጋ እንዲሆኑ አይፈልጉም። ሲዋሹ ወይም፤ ሲሰርቁ፤ ሲያታልሉና ሲመኙ እየኖሩ ዝማሬንና ጸሎትን እንደማካካሻ መሳሪያ ለመጠቀም ይሞክራሉ። የወጭቱን ውስጥ ሳያጠራ ውጪውን እንደሚያደምቅ ፈሪሳዊ ከመሆን የዘለለ አይደለም።
 እናም ወንድሜ ሆይ ስጦታህ የተወደደ እንዲሆን መባህን አስቀምጠህ አስቀድመህ ከወንድምህ ታረቅ። ከልጅነቱ ጀምሮ ህግጋቱንና ትእዛዛቱን ሲጠብቅ የኖረው ወጣት ፍጹም የሚያደርገውን ነገር ለመፈጸም እንደተቸገረው እኔና አንተም ወደኋላ ከሚጎትት በደል ርቀን፤ ፍጹም ስለሚያደርገው የሥጋችን ቅድስና ዝሙትን እንጥላ! ጸሎትና ምስጋናን በሚያመወጣው አንደበታችን እርግማን፣ ነቀፋና ሃሜትን እናርቅ! ነፍሳችንን ለእግዚአብሔር ፍቅር እንጂ ለዚህ ዓለም ሥጋዊ ውዴታ፤ አምሮትና ፍላጎት አሳልፈን አንስጥ!
ዘማዎች ይመጸውታሉ፤ሃሜተኞች ይጸልያሉ፤ ቂመኞች ይጾማሉ። ያቃታቸው ነገር ልባቸው ላይ ያለውን ያንን ስር መንቀል ነው። ስጋቸውን ለነፍሳቸው ማስገዛት ነው።
እናም ወንድሜ ሆይ! ጨርሰህ ከኃጢአት ባህር አልወጣህም ከሆነ አሁኑኑ ውጣ! ንስሐም ግባ ! መዳንህም ፈጥኖ ይደረግልሃል።
ስለጾምህና ጸሎትህ፤ ምጽዋትህና፤ ዝማሬህ ጥቂት የደኅንነት ተስፋ ተሰምቶህም ከሆነ ራስህን መርምር። ልብህ፤ ነፍስህና ኃይል ለእግዚአብሔር የተሰጡ ስለመሆናቸው አንተ ራስህን ታውቃለህና ተመልከት።  ሰው ልቡን የእግዚአብሔር የቅድስና አዳራሽ ሳያደርገው በጾም፤ በጸሎትና በምጽዋት እንዲሸነግል ሰይጣን ይፈልጋል።በዓለማችን ላይ ብዙ ቤተ እምነቶች ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፤ ምጽዋት ይሰጣሉ። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ለመሆን የተሰራ አካል የላቸውም።«…የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ»  ያለውን ቃል አያውቁትም። ቢያቁትም በሕይወታቸው ውስጥ የለም። ነቢብና ገቢር ሁለት  ነገሮች ናቸው።
ስለዚህ ወንድሜ ሆይ! እኔና አንተም ኃጢአትን የመጥላት፤ ጽድቅንም የመውደድ የውዴታ ግዴታ አለብን። የቀደመው ኃጢአታችን በመስቀል ላይ ተደምስሷል። የግላችንን በደልና ዐመጻንም ይቅር ሊለን አንድያ ልጁ ዛሬም በታመነ ቃሉ ይጠራናል።
«ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን» 2ኛ ጢሞ 1፤9
ስለዚህ ወደጠራን ታማኝ አምላክ እንሂድ!  «በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው» 1ኛ ዮሐ 1፤9 ሞት ያላሸነፈው፤ ኃጢአት ያላወቀው፤ ሊቀካህናት  ኢየሱስ ክርስቶስ እንቅረብ!
የልባችንን በር እንክፈት! ንስሐም እንግባ! ኃጢአትን እንጸየፍ!
«እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል» ራእይ 3፤20