Sunday, July 1, 2012

አፄ ዓምደ ጽዮንና የኢትዮጵያ አንድነት

ፀሐፊ፤ ሔኖክ ጌትነት

አፄ ዓምደ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ

ግዛት      ከ1314-1344 ፤  ቀዳሚ ንጉሥ  አፄ ውድም አርእድ(አባት)
ተከታይ ንጉሥ፤  አፄ ነዋየ ክርስቶስ/ ሰይፈ አርእድ ልጅ/
ባለቤት ብሌን  ሳባ/ የባሕረ ነጋሲ ንግሥት/
ሙሉ ስም፤  ገብረ መስቀል
ሥርወ-መንግሥት፤   ሰሎሞናዊ
አባት ፤     ውድም አርእድ
ሀይማኖት  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና
ቀዳማዊ አጼ ዐምደ፡ጽዮን (የዙፋን ስም ገብረ መስቀል) ከ1314 እስከ 1344 ዓ.ም. የነገሡ ሲሆን በጥንቱ ዘመን ከተነሱ ነገሥታት ውስጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ሰፋ ያለ አሻራ ትተው ካለፉት (ለምሳሌ፦ ዘርአ ያዕቆብ ) ጎን ወይም በላይ ስማቸው ይጠቀሳል። አጼ ዐምደ ጽዮን የአጼ ይኩኖ አምላክ የልጅ ልጅና የአጼ ውድም አርእድ ልጅ እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ይኩኖ አምላክ አዲሱን የሰሎሞን ስርወ መንግስት ቢመሰርቱም፣ በልጅ ልጆቻቸው የነበረው ፉክክርና አዲስ ከሚስፋፋው የእስልምና ሃይማኖት የሚሰነዘረው ጥቃት ስርዓቱን ስጋት ላይ የጣለ ነበር። አጼ አምደ ጽዮን ይህን ፉክክር በማስቆምና በዘመናት በማይደበዝዘው ጀግንነታቸው የኢትዮጵያን ድንበር ከሞላ ጎደል አሁን በሚታወቀው መልኩ በማስቀመጥ፣ የአዲሱን ስርወ መንግስት መሰረት በማጽናት እንዲሁም በማረጋጋት ዝናቸው በጥንቱ አለም ክአፍሪቃ ቀንድ እስከ አውሮጳ የተንሰራፋ ነበር።
1/ የአጼ ዐምደ ጽዮን ዘመንና ዘመቻዎች
ዘመቻ ወደ ደቡብ ምዕራብና ሰሜን ኢትዮጵያ
ዓምደ ጽዮን በእንዴት መንገድ ወደ ስልጣን እንደመጡ መረጃ የለም፣ ስለሆነም ታሪክ አጥኝው ታደሰ ታምራት ንጉሱ ከአባታቸው ጋር ትግል ገጥመው ዘውድ ላይ እንደወጡ መላ ምት ያቀርባል ። ንጉሱ በመንግስታቸው መጀመሪያ (፲፫፻፲፮ ዓ.ም. ) የተሳካላቸው ዘመቻዎች በጎጃም፣ ዳሞትና ሐድያ በማድረግ እኒህ አካባቢወች እንዲገብሩ ሆነ[5]። ሆኖም በኒህ ዘመቻወች ትኩረታቸው ስለተሳበ በተገኘው ክፍተት የእንደርታ ገዢ የነበረው ይብቃ እግዚ የአምባ ሰናይት፣ ብልሃትንና ተምቤን ሰራዊትን በማደራጀት በንጉሱ ላይ ተነሳ ። በ1320ዓ.ም ንጉሱ የይብቃ እግዚን አመጽ ከደመሰሱ በኋላ በአምባ ሰናይት የጦር ዕዝ አቋቋመው ወደ ስሜን በመዝመት እስከ ቀይ ባህር ድረስ ያለውን ክፍል ለመቆጣጠር ቻሉ። በዚህ ወቅት እንደርታን እንድታስተዳድር የተሰየመችው የትግሬ ተወላጅ የነበረችው የንጉሱ ሚስት ንግስት ብሌን ሳባ ነበረች። ስልጣኗም ባልታ ብሃት በመባል ይታወቅ ነበር። ቆይቶ እንደርታን እንዲያስተዳድር የተደረገው የንጉሱ ሦሥተኛ ልጅ ባህር አሰገድ በማዕከለ ባህር ማእረግ ነበር፣ ግዛቱም እስከ ቀይ ባህር ወደብ ድረስ የተንሰራፋ ነበር ።

 
ዘመቻ ወደ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ
የንጉሱ ትኩረት ወደ ሰሜን መሆኑን የተረዱት የደቡብ እስላማዊ ክፍሎች፣ በቀይ ባህር ንግድ ላይ ያላቸውን ቁጥጥር እና ሃይል ተመርኩዘው የአርብቶ አደሩን ክፍል በማስተባበር የሃይል ማደግ አሳዩ። በተለይ በወላስማ ሱልጣኖች የሚመራውና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ የሚገኘው የይፋት ግዛት በሃይል ተጠናከረ። ይህ ክፍል፣ ከአጼ ዐምደ ጽዮን ዘመን በፊት ጀምሮ ለመካከለኛው የኢትዮጵያ መንግስት ግብር ከፋይ ነበር። ሆኖም ክፍሉ በዚህ ዘመን እራሱን ችሎ ለመገንጠል ፈለገ። በዚህ ሁኔታ የክርስቲያንና የእስልምና ግዛት በሰሜንና በደቡብ እየተጠናከሩ ሁለት የሃይል ማዕከሎች በመፍጠር ፉክክር ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ጦርነት መነሳቱ ግድ ሆነ።
ወደ ግብጽ ተልኮ የነበረው ጥንታይ የተሰኘው የንጉሡ መልዕክተኛ ሃቀዲን በተባለ የይፋት ገዢ መታሰር በመጨረሻ ጦርነቱ ገንፍሎ እንዲወጣ አደረገ። ዐምደ ጽዮን ይፋትን ከደመሰሰ በኋል በጀበልና ወርጂ አርብቶ አደሮች ተቃጥቶበት የነበረውን ጥቃት ድል በማድረግ እንዲሁም የክርስቲያን ክፍሎች፣ ተጉለት፣ ዜጋና መንዝ አመጾችን በማጥፋት ሃቃዲንን በማሰር ከስልጣን አስወገደው ። በርሱ ቦታ ወንድሙን ሳባራዲንን ከላይ የተገለጹት ክፍሎችን አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመው።
ስምንቱ የደቡብ መንግስታትም፣ የሱማሌንና የሃድያን ጨምሮ ለሱ ግብር ይከፍሉ እንደነበር ሳልት የተሰኘው የእንግሊዝ ጸሐፊ ዘግቦት ይገኛል።
 የኢትዮጵያም ደብር በኢየሩሳሌም የተከፈተው በኒሁ ንጉስ መልካም ፈቃድ ነበር። ከዚህ በተረፈ «የወታደሩ እንጉርጉሮ» የተሰኙት አራቱ የአማርኛ መዛግብት በዚህ ዘመን እንደተጻፉ ታሪክ ዘጋቢዎች ይናገራሉ።

የአፄ ዓምደ ጽዮን ዘመቻዎች፤ 
 
የጽሁፉ ማጣቀሻ

  ##ኤድዋርድ ኧለንደርፍ Vol. 29, No. 3 (1966), pp. 600-611  ለተጨማሪ እዚህይጫኑ
 ##   ዶናልድ ክሩሚ ለተጨማሪ እዚህ ይጫኑ
   ## ታደሰ ታምራት፣ pices 4, ቅጽ 1, ገጽ 505
   ##  Marrasini, Lo Scettro e lacroce, La Camagna Di 'Amda Seyon I contro l'Ifat (1332)
   2/  ሥነ ግጥም ለአፄ ዓምደ ጽዮን፤
የዚህ ግጥም ምንጭ ከታች ከተጠቀሰው የኢጣሊያ መጽሐፍ  ነው።