Friday, July 13, 2012

«ክስን፤ ጥቆማንና ዳኝነትን ለይቶ ያልወሰነ ስብሰባ!»


የታመመ ሰው ሕክምና የሚሄደው ለሕመሙ ተገቢውን ህክምና ለማግኘት ነው። ሐኪሙ፤ ከታማሚው የሚያገኘውን የቃል መረጃና በምርመራ ያገኘውን ውጤት አንድ ላይ አዋሕዶ ካልሰራ በስተቀር ፈዋሽ መድኃኒት ማዘዝ አይችልም። ቢያዝ እንኳን ለማያውቀውና መርምሮ ላልደረሰበት በሽታ የሚሰጠው መድኃኒት ከፈዋሽነቱ ይልቅ ጎጂ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ይሆናል።
እንደዚሁ ሁሉ በጥቅምት ወር 2004 ዓ/ም ላይ የቤተክርስቲያን መሪዎች ሊቃነ ጳጳሳት ስብሰባ ተቀምጠው ነበር። ታማሚውን፤ የሕመሙን ዓይነትና ለሕመሙ የተስማማ መድኃኒት ለይቶ ለመስጠት በተሰየመ አጀንዳ ላይ ውይይት አድርጎ ማዘዙን የተመለከተ መረጃ «አባ ሰላማ» በድረ ገጹ አስነብቦናል። ይህንኑ ተመልከተን አንዳንድ ጥያቄዎችን አጫረብንና በዚያ ላይ የተድበሰበሰውን አካሄድ ለመግለጥና  «ሲያውቅ የተኛ ቢጠሩት አይሰማም» እንዲሉ  መደረግ የነበረበትን አካሄድ ሁሉ ለማኅበረ ቅዱሳን ደስታ ሲባል የተተወ መሆኑን ብናውቅም ለታሪክና ለትውልድ ትልልቁን ግድፈት ለማሳየት ወደድን።

1/ የቀረበው ክስ ነው ወይስ ጥቆማ?

ሀ/ ክስ ፤/accusation/
ክስ /accusation/ በእንግሊዝኛው ፍቺ፤ አንድ ሰው ወይም ቡድን በሌላ ሰው ወይም ቡድን ላይ ሕገ ወጥ ነገር ፈጽሟል ብሎ የሚያቀርበው የሕግ መብትን የማስከበር አቤቱታ ነው።
ይህንኑ ቃል አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ እንዲህ ሲሉ በመዝገበ ቃላቸው ላይ ፈትተውታል።
«ከሰሰ- በዳኛ ተማጠነ፤ እገሌን አቅርብልኝ፤ ዳኘን አለ። በደሉን፤ ግፉን ተናገረ፤ አመለከተ፤ ጠላቱን አሳጣ» በማለት ተርጉመውታል።
ክስ በሚለው ቃል ላይ እንደ አስረጂ በቀረቡት ትርጉሞች ላይ ከተግባባን  በማኅበረ ቅዱሳን ከሳሽነት እና በተከሳሽ 7 ድርጅቶችና 16 ግለሰቦች  መካከል  ለተቀደሰው ጉባዔ ቀርቦ የታየ ነገር ነበርን? ብለን ብንጠይቅ አዎ ለማለት የሚያስችል ጭብጥ የለንም። ምክንያቱም «ክስ» የሚለውን ዐውደ ቃል ሊያሟላ የሚችል ሂደት አልነበርምና ነው። ይሁን እንጂ የሊቃነ ጳጳሳቱ ስብሰባ የሰጠው ውሳኔ እንዲህ ሲል ይናገራል።

«………….7 ድርጅቶችና 16 ግለሰቦች የቀረበባቸው ክስ በተጨባጭ በመረጋገጡ» ይላል። ማን ከሳሽ? ማን ተከሳሽ? ማን መርማሪ? ምን ዓይነት መልስና ማስረጃ ቀረቦ ታየ? የሚታወቅ ነገር የለም። በክስ አግባብና  አካሄድ ያልሄደ ሆኖ ሳለ እንዴት ነው በተጨባጭ የሚረጋገጠው? እዚያው ፍጪው! እዚያው አቡኪው! ከመሆን የዘለለ አልነበረም። ስለዚህ በየትኛውም መመዘኛ «ክስ» የሚለውን ስያሜ ለመያዝ የሚያበቃው ስላልሆነ ይህንን ስም ሲያነሱት ሊያፍሩ ይገባቸዋል። በዚህ ዘመን በተደበላለቀ ጫወታ/game/፤ ትላልቆች የተቀመጡበትን ሥፍራ ለሌሎች ዓላማ መሳካት ማዋል ያስተዛዝባል። ያሳዝናልም።

ለ/ ጥቆማ /indication/  informant/

ጥቆማ የሚለውን ስማዊ ቃል /A sign or piece of information that indicates something/ በማለት ይፈታዋል። ስለአንድ ነገር የሚቀርብ ቅንጣት መረጃ ወይም ማሳያ/አመላካች / ነገር ጥቆማ ሊባል ይችላል።
ይህንኑ ጥቆማ የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድም በመዝገበ ቃላቸው ላይ እንዲህ ፈትተውታል።
«ተፈላጊ ነገር ያለበትን ሥፍራ፤ ነገር አመለከተ» ማለት ነው ይሉናል አለቃ።
ስለሆነም ጥቆማ መረጃን በመስጠት ወይም በማሳየትና በማመላከት ዙሪያ የታጠረ ስለሆነ መረጃ ሰጪውን አካል ከሳሽ ሆኖ የሚያቀርብበት ሁኔታ የለም። ይልቁንም ከሳሽ ሊሆን የሚችለው መረጃውን የተቀበለና በመረጃው ባለቤትነት ከሳሽ መሆን የሚችለው ሌላ ሁለተኛ አካል ነው።
የጥቆማ ትልቁ ጉድለት በዓላማው እውነታን የተመረኮዘ ላይሆን የሚችልበት ሁኔታ ስለሚኖር መረጃ ሰጪ አካል ስለሰጠው መረጃ ኃላፊነቱን መውሰድ አይፈልግም። ይልቁንም በጀርባ ሆኖ የመረጃውን ተፈጻሚነት በመከታተልና ግፊት በማድረግ ላይ መጠመድን ይፈልጋል። ጥቆማዎች ሌላውን ለመጉዳት በሀሰት ላይ የተመሰረቱ ወይም በትክክል ጠቃሚነት ያላቸው ሊሆኑ ስለሚችሉ የተሰጠው አካል ይህንን ለማጣራት ሥራውን ከባድና ውስብስብ ያደርግበታል። በእርግጥ ለሊቃውንት ጉባዔው የቀረበው ጥቆማ የተብራራና ምንም ተጨማሪ ማጣራት ሳያስፈልገው የማኅበረ ቅዱሳንን ዓላማ ማሳካት አስፈልጓል። ምክንያቱም ማጣራት ለሚባለው ውስብስብ ሥራ የበቃ ሊቃውንት ጉባዔ ስለሌለ የተሰጠውን እንዳለ ሳያላምጥ በመዋጥ መልሶ ሊመግብ ፈልጓል። ጥቆማን ማጣራት የተጻፈውን መገልበጥ አልነበረም። ይህ የሰነፍ ተማሪ ስራ ነው።
ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ የደኅንነቱ መሥሪያ ቤት በየእለቱ ልዩ ልዩ መረጃዎችና ጥቆማዎች ሲደርሱት በመረጃዎቹና በጥቆማዎቹ ላይ የራሱን ምርመራ፤ ማጣራትና የማበጠር ሥራ ሳይሰራ ወደእርምጃ ቢገባ ደኅንነትን ከማረጋገጥ ይልቅ ሁከትና ብጥብጥን የሚያስፋፋ መሥሪያ ቤት ይሆናል ማለት ነው።  
የታላቁ ጉባዔ መርማሪ ቡድን ሊቃውንት ጉባዔ በደረሰን ጥቆማ ላይ ማጣራት አድርገን፤ ምናምን…… የሚል ሀተታ ሲያቀርብ ተመልክተነዋል። ጥቆማው ምንድነው? በጥቆማው የተጠየቀው ማነው? ምን ምርመራ ተደረገ? ጥቆማው ሀሰት ላለመሆኑ ዋስትናው ምንድነው? ምንም አይታወቅም። በአንድ በኩል ክስ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጥቆማ የሚል ጉባዔ ምን አልባት ጨረቃ ላይ ካልሆነ እስከዛሬ በቤተክርስቲያን አልታየም።
ማኅበረ ቅዱሳን በጽሁፍ ያቀረበው ጥቆማ ሳይሆን ክስ ነው የሚለው ሚዛን ይደፋል።  በግልጽ በስምና በአድራሻ የቀረበ ነገር ጥቆማ አይባልም። ስለሚያውቀው ነገር ጽፏልና። የማኅበረ ቅዱሳን ድርሻ ሊሆን የሚችለው በክሱ ላይ ወይ ራሱ ከሳሽ ሆኖ ወይም ጉባኤው ከሳሽ ሲሆን  ምስክር መሆን ብቻ ነበር የሚችለው። ግን አልሆነም።
ይሁን እንጂ «ጥቆማ» ቀርቦልኛል የሚለው ጉባዔ በጥቆማ ብቻ ማንንም ወንጀለኛ ማድረግ አለመቻሉ እየታወቀ እርሱ ግን የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል። ሁሉም በየደረጃው የተሰጠውን ግዴታ ተቀብሎ ተግብሮታል ማለት ይቻላል። ጥቆማ ስለተባለው ነገር እውነተኛነት የተሟላ ማረጃ ማግኛ መንገድ እንጂ በራሱ የውሳኔ መስጫ ሊሆን አይችልም። ጥቆማ ለክስ የሚያደርስ የመረጃ ኃይል ከመሆን በዘለለ የክስ መድረክ ሆኖ የሚያስፈርደው በምን ስሌት ነው? የሚያስተዛዝበው ነገር በዚያኛው በትላልቁ የኃይል ሰልፍ በኩል የሚወሰድ እርምጃ ሁሉ በጅምላ ትክክል ነው ብሎ የሚቀበል ትውልድ እንደማይኖር አለማወቅ እነማን ምን እየሰሩ ነው? እንድንል አድርጎናል። ክስ የተባለውን የሕግ ዓውድም ይሁን በጥቆማ ተመስርቶ እውነታ ላይ ደርሶ ወደ ክስ የሚያንደረደርውን የሕግ አግባብ ያልተከተለው የሲኖዶስ ውሳኔ ጭብጥ የሚያሳየን ነገር ጩኸቱን ሲያሰማ የኖረው ማኅበረ ቅዱሳን ሳይደሰት አንበተንም ከሚል ያላለፈ እንጂ ስለቤተክርስቲያን ኅልውና ከመጨነቅ አይደለም። ምክንያቱም በውሳኔው የመጣው ለውጥና የሚጠበቀው ለውጥ ምንድነው? ምንም!!!
ስለዚህ ክስም፤ ጥቆማም ሳይኖር ማኅበረ ቅዱሳንን ፈርተው ውሳኔ ሰጥተዋል። ያንን ባያደርጉ በስለላ ማኅደር ከተከማቸው ፋይላቸው ለንባብ ይበቃልና!! 

2/  ሁለት ጊዜ ውግዘት አለ?

ሌላው ጫወታ/game/ የቤተክርስቲያኒቱ አባል ያልሆኑ፤ ከዚህ ቀደም የተባረሩ፤ የራሳቸውን መንገድ ተከትለው የሚኖሩ ሰዎችን አውግዘናል ያሉበት ነገር አስገርሟል። ክስም ይሁን ጥቆማ ቢኖርም፤ ባይኖርም የተሰናበቱና የቤተክርስቲያኒቱ አባል ያልሆኑ ሰዎችን አውግዘናል ማለት ምን ማለት ነው? ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ነው? ወይስ ካሉበት ቦታ እንዲሞቱ ነው? ወይስ የትኛውንም እምነት ተከትለው በሚጽፉት ነገር አፋቸው ይዘጋ በማለት ለመራገም ነው? ነገሩ ግራ የሚያጋባ ነው። ስለቅድስት ማርያም፤ ስለመላእክት፤ ስለቅዱሳን  ወዘተ የሚጽፉት ከቤተክርስቲያን አባልነታቸው ወጥተው ሆኖ ሳለ አሁን ዳግመኛ ማውገዝ ምን ለማትረፍ ነው? ስለድንግል ማርያም እንዳትጽፉ ማለት የሚችል ሲኖዶስ የትም ዓለም አይኖርም። ምክንያቱም ድንግል ማርያም በዘር እብራዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለችም። ድንግል ማርያምን የክርስቶስ እናቱ እንደሆነች የሚያውቁት የኛዎቹ ሲኖዶሶች ብቻ ሳይሆኑ ዓለሙ ሁሉ ነው። ስለዚህ በቅድስት ማርያም ማንነትም ይሁን በመላእክት ላይ የይገባኛል መብት በግል የተሰጠ አንዳች ሳይኖር ይህን አትጻፉ! ይህንንም አትበሉ!  ማለት የሚችለው ማነው?
ምናልባት መልከ ጼዴቅ ካህን ዕብራዊነቱ ቀርቶ ኢትዮጵያዊ ነው ብላችሁ እንደቀባጠራችሁት ማርያምም ኢትዮጵያዊ ስለሆነች ከዛሬ ጀምሮ ያለእኛ ትእዛዝ ልትሉ ካልሆነ በስተቀር አብሮአችሁ የሌለውን ማውገዝ ጅልነት ይሆናል። ማቴዎስም፤  ታዴዎስም፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ናቸው የሚል ወሬም አንብቤአለሁ። ወዴት ጠጋ ጠጋ!! እምነት እንጂዘር አያጸድቅም። ዕብራዊ ነን ማለቱን ትታችሁ ኢትዮጵያዊ ሁኑ።  ከዝንጀሮ የመጣን የተከበረ አጥንት/Lucy/ ሀገር  ሰዎች ነን ትሉ አይደለም እንዴ?
ስናጠቃልል የምናገኘው ጭብጥ፤
ሀ/ ክስ ነበረ ወይ? ብንል አልነበረም ይሆናል መልሱ። ክስ- ከሳሽ፤ ተከሳሽና ዳኛ ባለበት የሚደረግ ሂደት ነውና።
ለ/ ጥቆማ ነበረ ወይ? ብንል ጥቆማ የሚመስል ነገር ነበር ማለት እንችላለን። ይሁን እንጂ ጥቆማው፤ ጥቆማን መርማሪና ጥቆማ የቀረበበት ተመርማሪ ነበርን? ብልን አልበረም። የሆነው ነገር ማኅበረ ቅዱሳን ጠቋሚና መርማሪ፤ ሊቃውንት ጉባዔ አጽዳቂ፤ ሲኖዶስ ደግሞ ወሳኝ ሆነው በጋራ የድራማ ሥራ መጠናቀቁ ብቻ ነው የሚታየው።