Wednesday, July 11, 2012

የግንቦቱ ሲኖዶስ ካወገዛቸው ግለሰቦች መካከል ሦስቱ ውግዘቱን በመቃወም ጠቅላይ ቤተክህነቱን ይግባኝ ጠየቁ


(ደብዳቤ የጻፉት / አሸናፊ መኮንን፣ / አግዛቸው ተፈራ እና መምህር ጽጌ ስጦታው መሆናቸው ታውቋል)
የጽሑፍ ምንጭ፤ አባ ሰላማ ድረ ገጽ
(ደብዳቤ የጻፉት / አሸናፊ መኮንን፣ / አግዛቸው ተፈራ እና መምህር ጽጌ ስጦታው መሆናቸው ታውቋል)
የግንቦቱ ሲኖዶስ ስብሰባ ቤተክርስቲያንን የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ በማድረግ ያዋረደበትን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ ይህን የራሱን ክብር የቀነስበትን፣ በታሪክ ተወቃሽ የሚያደርገውንና ብዙዎችን ያሳዘነውን፣ የቤተክርስቲያንን ሕግና ስርአት ባልተከተለና፣ በየትኛውም መስፈርት ሲመዘን ሕገ ወጥ ሆኖ የተገኘውን ውግዘት፣ «ተወጋዦቹ» እየተቃወሙት ነው፡፡ አንዳንዶቹም ይግባኝ እየጠየቁበት መሆኑ ተሰምቷል፡፡ እስካሁን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ለጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤትና ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት በጻፏቸው ደብዳቤዎች ተቃውሟቸውን ያሰሙትና የተላለፈባቸው ሕገወጥ ውግዘት እንዲነሳና ጉዳያቸው እንደገና እንዲታይ የጠየቁት / አሸናፊ መኮንን፣ / አግዛቸው ተፈራ እና መምህር ጽጌ ስጦታው መሆናቸው የታወቀ ሲሆን ለዛሬው የዲ/ አሸናፊ መኮንንን ደብዳቤ እናቀርባለን (ሙሉውን ደብዳቤ ከዚህ ጽሑፍ በታች ያገኙታል)፡፡
እንደሚታወቀው / አሸናፊ መኮንን  እስካሁን 16 መንፈሳዊ መጻሕፍትን በመጻፍ ለበርካታ ምእመናን መጽናናትን ያመጣና እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ያስነሳው እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጅ ነው፡፡ መጻሕፍቱ በአብዛኛው መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ያተኮሩ፣ እየጣፈጡ የሚነበቡ፣ ሕይወትን የሚፈትሹና ለብዙዎች የመንፈስ እርካታን ያመጡ በመሆናቸው በየቤተክርስቲያኑ ደጅና የኦርቶዶክስ መጻሕፍት በሚሸጡባቸው የመጻሕፍት መደብሮች ውስጥ እየተሸጡ ለምእመናን በቅርበት የሚደርሱ፣ ቤተክርስቲያን ውስጥም በስፋት የሚነበቡና የማኅበረ ቅዱሳንን የተረት መጻሕፍት ከገበያ እያስወጡ ያሉ መጻሕፍት መሆናቸውን ብዙዎች የሚመሰክሩት ሐቅ ነው፡፡
/ አሸናፊ በጻፈው ደብዳቤ በሲኖዶሱ ውሳኔ ከልብ ማዘኑን የገለጸ ሲሆን፣ የተላለፈው ውግዘት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ያልተከተለ፣ የቤተ ክርስቲያኗን ህግና ስርአት ያፈረሰ፣ ታሪክን ያላገናዘበ መሆኑን አትቷል፡፡ ደብዳቤው በምድራውያን ፍርድ ቤቶች እንኳ የከሳሽ ክስ ብቻ ተሰምቶ ብይን እንደማይሰጥና ለተከሳሽም ቃሉን የሚሰጥበት እድል እንደሚሰጥ ጠቅሶ፣ «ውግዘት የተካሄደው የቤተክርስቲያን እምነትና ቀኖና ተነክቷል ተብሎ ከሆነ ይህ አካሄድም የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና ያፈረሰ ነው» ሲል ይሞግታል፡፡ እርሱ አንቀጸ ብርሃን የሚባል መንፈሳዊ ማኅበር የሌለውና ዳንኤል ተሾመ የሚባልና በተሐድሶ ዙሪያ መጽሐፍ የጻፈ ሰው እንደማያውቅ የገለጸ ሲሆን፣ ማኅበረ ቅዱሳን ግን እርሱን በኑፋቄ የሚከስበት ነጥብ ሲያጣ እንዲህ አይነቶቹን የሐሰት መረጃዎች በማቀበል ሆነ ብሎ ሲኖዶሱን አሳስቷል፡፡ ማንንም ለማነጋገር የፈራ የሚመስለው ሲኖዶስም ሁሉንም ሳይጠራና ሳያነጋግር፣ ተከሳሾቹም ስለቀረበባቸው መረጃ ምላሽ እንዲሰጡ ሳያደርግ በጭፍንና በጅምላ ማውገዙ እንደዚህ ያሉ ታሪካዊ ስሕተቶችን እንዲፈጽምና ራሱ እንዲገመትበት አድርጓል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን / አሸናፊን ለመክሰስና ለማስወገዝ የተንቀሳቀሰው በዋናነት የእርሱ መጻሕፍቱ በቤተክርስቲያን ውስጥ በስፋት በመነበባቸውና ለብዙዎች የመንፈስ እረፍትንና እርካታን በማምጣታቸው ቀንቶና ተመቅኝቶ እንደሆነ ለማኅበሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እየተናገሩ ነው፡፡ / አሸናፊ እስካሁን የጻፋቸውን 16 መጻሕፍት በግንቦት 2003 . በብፁዕ አቡነ ገሪማ ፊርማ ለሊቃውንት ጉባኤ በተጻፈ ደብዳቤ የሊቃውንት ጉባኤው ለሥራ እንዲጠቀምባቸው መመሪያ ተላልፎ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም ማኅበረ ቅዱሳን ነገር እየሰራ / አሸናፊን ለማስወገዝ፣ ከፓትርያርኩ ጋር ግጭት ውስጥ የነበሩትን ጳጳሳት በማሳደም ውስጥ ለውስጥ ብዙ ሴራ ሲጎነጉን መቆየቱ ታውቋል፡፡ ከሰሞኑ አንዳንድ የማቅ ቀንደኛ ጳጳሳት ለምሳሌ አባ ጢሞቴዎስና አባ ዮሴፍ በሰዎች ፊት፣ አሸናፊን ያወገዙት እንደተባለው ኑፋቄ ስለተገኘበት ሳይሆን እርሱን ከፓትርያርኩ ለመነጠል በማሰብ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በተለይ አባ ጢሞቴዎስ እንዳሉት «ዲያቆን አሸናፊን ያወገዝነው ምንም ለማይጽፈው ለገብረ መድኅን (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ነው) ጽሑፍ እየጻፈለት ስለሆነ ይህን ለማስቆም ነው፡፡ በተጨማሪም / እጅጋየሁ የጻፉትንና ያሳተሙትን መጽሐፋቸውን «የጻፈው አሸናፊ ስለሆነ ነው» በማለት ማቅ የሰጣቸውን የተሳሳተ መረጃ እንደወረደ በማስተጋበት ይህም ለማውገዝ ሌላው ምክንያት እንደሆናቸው ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ በዚህም ቤተክርስቲያኗን እንመራለን የሚሉ አንዳንድ ጳጳሳት በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ መገመት ይቻላል፡፡
ከዚህ ቀደም እውነትን በመመስከራቸውና ተከሰው ቀርበውና ተከራክረው በመርታታቸው «ጥፋተኛ» ተብለውና ቀኖና ተቀብለው ያለበደላቸው ደብረ ሊባኖስ ተልከው የነበሩትን መምህር ጽጌ ስጦታውንና መምህር ግርማ በቀለን፣ እንደ እስጢፋኖስ በድንጋይ ከወገሯቸው መካከል አንዱ የነበሩትና ዛሬ በሰዎች ፊት ያን አሳፋሪ ስራቸውን እንደጽድቅ እያወሩ የሚገኙት፣ አሁንም ከተወገዙት መካከል አንዱን ቢያገኙትም በድንጋይ እንደሚወግሩት እየዛቱ ያሉት የያኔው መነኩሴ የአሁኑ ጳጳስ አባ ዮሴፍም «/ አሸናፊ የተወገዘው እርሱን ከፓትርያርኩ ለመነጠል ተፈልጎ ነው» በማለት በሰዎች ፊት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ድራማ በስተጀርባ ማህበረ ቅዱሳን የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሯሯጥ፣ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎቹም አንዳንድ ጳጳሳት በአንድ በኩል ነውራቸውን ማቅ እንዳያወጣባቸው እርሱን ለማስደሰት፣ በሌላ በኩል አቡነ ጳውሎስን ያለ ሰው በማስቀረት በእርሳቸው ላይ ያሻቸውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን እንደሚያሳይ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች ይናገራሉ፡፡
በሕገ ወጥ መንገድ ውግዘት ያስተላለፈው ሲኖዶስ ከሕገ ቤተክርስቲያን ውጪ ማውገዙና ሕግ ማፍረሱ ሳያንስ፣ በመግለጫው መጨረሻ ላይ የተወገዙት ይቅርታ ከጠየቁ ቤተክርስቲያን በሯ ክፍት ነው ማለቱ የተወገዙትን ወገኖች በእጅጉ እንዳሳዘነ እየተነገረ ነው፡፡ ለሕገ ወጥ አሰራሩ ይቅርታ መጠየቅና ውግዘቱን ማንሳት ያለበትም ራሱ ሲኖዶሱ ሊሆን ይገባል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ የሌሎቹን ወንድሞች ደብዳቤዎች ይዘትና ደብዳቤዎቹን በቀጣይ እናቀርባለን፡፡
የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ማመልከቻ ለማንበብ ( እዚህ ይጫኑ )
  የሌሎቹን ወንድሞች ደብዳቤዎች ይዘትና ደብዳቤዎቹን በቀጣይ እናቀርባለን፡፡