Sunday, July 8, 2012

የጉጂ ቦረና ሐገረ ስብከት ችግር መንስዔው እና አሁን ያለበት ሁኔታ!

አንዳንዶች ስለማኅበረ ቅዱሳን ሽፍታነት ስንናገር ከሜዳ አንሰተን የጥላቻ ስም የምንለጥፍበት አድርገው ይቆጥሩናል። ነገር ግን አጣፍቶ ከሚለብሰው ነጠላ ጀርባ የሽፍታነት መገለጫ ያለበት የመሠሪ አባላት ስብስብ መሆኑን የሚያሳያቸው ግብራት ከምንም በላይ ማረጋገጫዎች ናቸው። /ይህንን ስንል ግን በቅንነትና በየውሃት መንፈስ ያሉትን አባላቱን ሳንጨምር ነው/ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ እስካሁን ያልበረደው የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ሀገረ ስብከቶች እየታመሱ ከቆዩ ሁለት ዓመት ያለፋቸው መሆኑ ነው። የማኅበረ ቅዱሳን ተላላኪ አገልጋይ የሆነው ሲያምር ተ/ማርያም በመንበረ ፓትርያርክ ውሳኔና በሥራ አስኪያጁ ደብዳቤ ወደ ትንሣዔ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤት መዛወሩን ከአንዴም ሦስቴ ደብዳቤ ተጽፎለት ሳለ እሱ ጫንቃውን ያሳበጠውን ማኅበር ተተግኖ ሽፍትነቱን በማጠናከር በእምቢታው ከጸና ሁለት ዓመት አልፎታል። ቤተክርስቲያን ስታዘው ያልተቀበለ ሽፍታ፤ ሃዋሳ ሆኖ የማንን ቤተክርስቲያን ሊመራ ይፈልጋል? ብለን ብንጠይቅ ያልጨረሰው የማኅበረ ቅዱሳን ስራ ስላለ ያንን ሳይፈጽም እንዳይመለስ ኅሊናውን ስላሳመነ እንደሆነ ግልጽ ይሆንልናል። የሀገረ ስብከቱን መኪና ይዞ ጠፋ፤ ማኅተምና የጽ/ቤት ንብረቶችን አላስረክብም አለ፣ በህግ ተጠየቀ፤ ከዚህ ሁሉ ሽፍትነቱ ይባስ ብሎ ከደጅ ሆኖ በማኅተሙ እየጻፈ ሰው ያግድ ጀመር። እንግዲህ እነዚህ የሽፍቶች አባላት ስብስብ ናቸው ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉት! አሸባሪ ማለት ከዚህ ውጪ ምን ሊመጣ ነው? እንኳን በበላይ አካል ተዛውረሃል የተባለ ግለሰብ ይቅርና ጠንካራ ሠራተኛ የሆነ ሰው እንኳን አታስፈልግም ከተባለ ጥያቄውን በሕግና በሕግ ብቻ ለማስፈጸም ይፈልጋል እንጂ ቀሚስ ለብሶ ይሸፍታል እንዴ? ሽፍትነት የተፈጥሮው የሆነው ማቅ አንድ አባሉን «ግብረ ጥፉን በስም ይደግፉ» እንድንል ሆኖ ለክፋት የጥበብ መግቦቱ፤ «መጋቤ ጥበብ»፤  ለክፋት ስማዊ ግብሩ «ሲያምር» የተሰኘው «መጋቤ ጥበብ ሲያምር ተ/ ማርያም» ያደረሰው ግፍና ዐመጻ እንድታነቡ ከታች አቅርበነዋል። የጽሁፋችን ምንጭ «ዓውደ ምሕረት» ብሎግ ነው።

 
  •     ሲያምር የተባለው የማቅ አባል የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ ነው።
  •     አቡነ ሳዊሮስ ስማቸው አላግባብ ጠፍቷል።
  •     አጣሪ ኮሚቴው እንዳይሄድ ተወስኗል።
የጉጂ ቦረና ሊባን ዞኖች ሀገረ ስብከት በማኅበረ ቅዱሳን አማካኝነት የተቀሰቀሰው ችግር እስካሁን አልተፈታም። ችግሩ አሁንም የማኅበሩ አባልና የቁርጥ ቀን ልጅ በሆነው ሲያምር ተ/ማርያም በተባለ ግለሰብ መሪነት በማኅበሩ ጭፍሮች አቀናባሪነት እየሄደ ያለበት መንገድ የህዝቡን ትዕግስት ያስጨረሰ ሲሆን ከብዙ የገንዘብ ጉድለቶች ጋር ተያይዞ ስሙ የሚነሳው ይህ ግለሰብ አሁንም በቦታው ተመልሼ ካልተመደብኩ በማለት ችግር እየፈጠረ ይገኛል።
ችግሩ ሲቀሰቀስ መነሻ የሆነው ዋነኛ ጉዳይ ሁሉን ልምራ ሁሉን ልቆጣጠር የሚለው ማኅበረ ቅዱሳንን የወቅቱ የጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖች ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳዊሮስ በኔ ሀገረ ስብከት ይህን ማድረግ አትችልም! አቅምህን አውቀህ ኑር! ብለው በማዘዛቸው ነው። በወቅቱ ይህንን ለማስፈጸም የሚያስችል አቅም ስላልነበረው ውስጥ ውስጡን አድፍጦ ከቆየ በኋላ አቡነ ሳዊሮስ አካባቢውን ለቀው ወደ ወሊሶ ከመጡ በኋላ ማኅበሩ የአመጽ ስራውን በግላጭ ጀመረ።
ችግሩ የተጠነሰሰው የአካባቢው ባለ ሀብቶች ለሻኪሾ ማርያም ቤተክርስቲያንን መንበር እኛ እናሰራ በማለት ጥያቄ ባቀረቡ ጊዜ ማን ይስራው? የሚል ጥያቄ በተነሳበት ወቅት ነው። የአካባቢው ባለሀብቶችና የቤተክርስቲያንዋ ሰበካ ጉባኤዎች ጨረታ ወጥቶ ይሰራ ሲሉ እነ ሲያምር ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን ይስራው በሚል ይሞግታሉ። ይህ ነገር እየከረረ ሄዶ መጨረሻ ላይ በጨረታ ይሰራ የሚል ውሳኔ ላይ ሲደረስ እነ ሲያምርም ነገሩን የተቀበሉ በመምሰል ጨረታው እንዲወጣ ታዞ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው መጋቤ ጥበባት ጸጋ ዘአብ አሸነፉ። መጋቤ ጥበባት ጸጋ ዘአብ በመንበር ሥራ ታዋቂ ግለሰብ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡  የገንዘብ ነገር የማይሆንለት ማቅም በዚህ ነገር ጥርሱን ነክሶ አቡነ ሳዊሮስን ለመዋጋት ተነሳ። ህዝብ ሁሉ ሰለሚደግፋቸው ግን አቡነ ሳዊሮስ በቦታው ላይ እያሉ ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ ሲያምርም በሁሉ ነገር ታዛዥ መስሎ በውስጡ ግን ነገር እየበላ ከማኅበሩ ጋር እየሰራ ቆየ፡፡ አቡነ ሳዊሮስም ከፍተኛ የሳይነስ ህመም ስላለባቸው በግንቦት 2002 ሲኖዶስ ዝውውር እንዲደረግላቸው ጠየቁ፡፡

ይህን ነገር አስመልክቶ እውነት በዞረበት አልፎ የማያዋውቀው የማህበረ ቅዱሳኑ ብሎግ አንድ አድርገን በወተርታራ ብዕሩ የዘገበው ዘገባ ፍጹም ሐሰት እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ እነ መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ነገሌ ቦረና በቀንደኛው የማቅ አቀንቃኝ በሆነው ዓለም ቀር አማካኝነት  መጋቢ ሃይማኖት ተስፋዬ መቆያ የሰባኪያንና የዘማሪያንን ወጪ በመቻል እነ ዓለምቀር ደግሞ ምግብና መጠለያ በማዘጋጀት ለሀገረ ስብከቱ ቢሮ ማሟያ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ከማገልገልና ከመታዘዝ በቀር የፈጸሙት አንዳች ጉድለት ሳይኖር ጭፍኑ የማቅ ብሎግ አንድ አድርገን ስማቸውን ሊያጠፋ የፈለገበት መንገድ ሀሰት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አቡነ ሳዊሮስም ቢሆኑ አካባቢውን የለቀቁት ችግር ተፈጥሮ ሳይሆን  በጤና ችግር መሆኑ እሙን ነው፡፡
 አቡነ ሳዊሮስ የጠየቁት ዝወውር ተፈቅዶላቸው ወደ ወሊሶ ከሄዱ በኋላ ሲያምር በማኅበሩ ቀጭን ትዕዛዝ የስም ማጥፋት ዘመቻውን ጀመረ፡፡ በመጀመሪያ የስም ማጥፋት ዘመቻውን የጀመረው 30,000 ብር ከሻኪሾ ማርያም ቤተክርስያን አቡነ ሳዊሮስ ወሰዱ በማለት ነበር፡፡ ይህ 30,000 ብር ግን የወጣው ለመንበር ማሰሪ እንደሆነና ራሱ ሲያምርን ጨምሮ በወቅቱ በነበሩ እማኝ አቡነ ሉቃስ ፊርማ  ለመንበር ማሰሪያው ቀብድ የተሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ህዝቡም እውነታውን ስለሚያውቅ በነገሩ ማዘን ጀመረ። ብጹዕነታቸውም እንዲህ ያለውን ክስ ለእሳቸው እንግዳ ነበርና በፈጠራ የተጀመረው ክስ በመስማታቸው በነገሩ ከማዘን ያለፈ ያደረጉት ነገር አልነበረም። በዚህ ጊዜ የብጹዕነታቸውን  ቅድስና የሚያውቁና በነገሩ ያዘኑ የህዝብ ወገኖች ይህን የስም ማጥፋት ወንጀል በዝምታ አናይም በማለት ማኅበሩን ፊት ለፊት ተጋፈጡ።



ለዓመታት የካበተ የክስ እና የወንጀል ልምድ ያለው ማኅበር ነገሩን በምን መንገድ ማስኬድ እንዳለበት ስለሚያውቅ አባላቱ ጥቂትም ቢሆኑ ለሁከቱ ግን አላነሱም ነበር። ፊት ለፊት በሚታይ የትኛውም መድረክ ማቅ 50 ሰው ቢያቆም ከሱ በተቃራኒ ደግሞ 1000 እና 2000 ሰው መቆም ቢችልም ጨዋታውን በደብዳቤ በማድረግ ሀገረ ስብከቱን ማመስ ቀጠለ፡፡
ችግሩ የመልካሙ አባት የብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ ስም ያላግባብ የጠፋበት ስለነበር ህዝቡን ይበልጥ እልህ ውስጥ ከቶት ተወካዮች እየመደበ የቤተክህነትን ቢሮክራሲና የማኅበረ ቅዱሳንን ተንኮል በመቋቋም ነገሩን በመከታተል እና ቀጣዩን አባት  በትዕግስት  በመጠባበቅ ቆየ። በቦታው ላይ አቡነ ገብርኤል ከአዋሳ ጋራ በሞግዚትነት ደርበው እንዲይዙ ተሾሙ፡፡ እሳቸውም አዋሳ ላይ የፈጠሩት ችግር አልበቃ ብሏቸው ችግሩን ወደ ጉጂ ቦረናም ለማስፋፋት ከጠቅላይ ቤተክህነት ስልጠና ይሰጣችኋል ብለው የየደብር አስተዳዳሪዎችን የወረዳ ሊቃነ ካህናትን አበልና የትራንስፖርት ወጪያቸውን ከደብራቸው ችለው ወደ አዋሳ እንዲመጡ አዘዙ። በተነገራቸው መሰረት በጠቅላይ ቤተክህነት ሰራተኞች አማካኝነት ስልጠናው በገብርኤል ቤተክርስቲያን ይካሄዳል ብለው ሲጠብቁ ሰዎችን በመላክ ስብሰባው ሴንተራል ሆቴል ነው ተባሉ። ሴንተራል ሆቴልም ተሰብሳቢዎቹ ከጠቅላይ ቤተክህነት ይመጣሉ የተባሉ ልኡካኖችን ሲጠብቁ አቡነ ገብርኤል እና ከአዲስ አበባ የመጡ የማኅበረ ቅዱሳንን የበላይ አመራሮች ስለ ማኅበሩ የወደፊት ራዕይና ለተሰበሰበው ምዕመን ማስተማርና መግለጽ ጀመሩ፡፡
ተሰብሳቢዎቹም እኛ የመጣነው ከጠቅላይ ቤተክህነት በመጡ ልዑካን ሴሚናር ይሰጣችኋልተብለን ነው እንጂ ስለማኅበረ ቅዱሳን ዓላማና እቅድ ወይም ደግሞ አደረጃጀት ሴሚናር ሊሰጠን አይደለም በማለት የተቃውሞ ድምጽ ለአቡነ ገብርኤል አሰሙ። አቡነ ገብርኤልም ማንኛውም ቤተክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳንን የመቀበል ግዴታ አለበት፡፡ በማለት በቁጣ ተናገሯቸው። ከዚህ ጊዜም ጀምሮ በተለያየ አካባቢ የተቃውሞ ድምጽ ከምእመኑ እየተሰማ በመምጣቱ ምዕመኑም በተደጋጋሚ ለቅዱስነታቸው አቤቱታ በማቅረብ በርካታ ምዕመናን ከተለያየ አካባቢ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በመምጣት አቤቱታቸውን ስላሰሙ አቡነ ገብርኤል ደርበው ከያዙት የጉጂ ቦረና ሃገረ ስብከት እንዲነሱ ተወሰነ። ከዚህም ጋር ተያይዞ አለአግባብ ሥልጣንን ተጠቅመው በፈጸሙት ወንጀል እነ ሲያምር ሊቀ ስዩማን ልሳነ ወርቅ ሁንዴ እነ መሪጌታ ሰለሞን ጨምሮ ሰባት ግለሰቦች እገዳ ተጣለባቸው፡፡


ሲያምር ተ/ማርያም ከቦታው እንዲዛወር የተጻፈበትን ደብዳቤ  ለማንበብ ( እዚህ ይጫኑ )


ከዚህም በኋላ በሥራ አስኪያጅነት ሌላ አባት በጊዜያዊነት ተሹመው ከአጣሪ ኮሚቴ ጋር መጥተው የነበረ ሲሆን በሲያምር ቦታ ተመድበው እንዲሰሩ መሾማው ሲሰማ  ሲያምርና ማኅበረ ቅዱሳን በአንድ ሌሊት ዱርዬ ገዝተው በጩቤ በማስፈራራት አባረዋቸዋል፡፡ አስከ ግንቦት ሃያ አምስት 2003 ሃገረ ስብከቱ ያለ ሥራ አስኪያጅ የቀጠለ ሲሆን ግንቦት 25 2003 ዓም አ.ም. ሲያምር እገዳው ተነስቶለት ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚቤት ተመድቦ እንዲሰራ ሲታዘዝ ሊቀ ትጉሀን ተሾመ ኃ/ማርያም በቦታው ተሾሙ፡፡
ሀገረ ስብከቱ ያለ ሊቀ ጳጳስ መቆየቱ አግባብ ስላልሆነ በግንቦት 2003 ዓ.ም.ሀ/ስብከቱን ደርበው እንዲይዙ አቡነ ዮሴፍ ተሾሙ፡፡ የአቡነ ዮሴፍን ሹመት የሰሙት የማቅ ሰዎችም ባሌ ድረስ በመሄድ በትክክለኛው መንገድ በሻሸመኔ መሄድ ሲገባቸው እነርሱ ግን ህዝብ እንዳያገኛቸው ሲሉ በበረሐው ነገሌ እንዲገቡ አደረጉዋቸው፡፡ ነገሌ ከገቡ በኋላ በሀገረ ስብከቱ ቢሮ በመሰብሰብ ሊቀ ጳጳሱን የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ብቻ እንዲቀበሉዋቸው አድርገዋል፡፡ ከዚህ በፊት ይደረግ የነበረው ግን የወረዳ ሊቀ ካህናትና የደብር አስተዳዳሪዎች ከሰበካ ጉባኤ የተወጣጡ ምእመናን ያሉበት አቀባበል ይደረግ ነበር፡፡  በአቀባበሉ ላይም ሆነ ከዛ በኋላ የማቅ ሰዎች  አዋክበው ህዝቡ ከኛ ጋር ስለሆነ እኛን ይስሙ በማለት ያሳምኗቸዋል። አቡነ ዮሴፍም የማኅበረ ቅዱሳንን አባላት በመያዝ የወረዳ ሊቀ ካህናትን ሲያግዱ፤ የደብር አስተዳዳሪዎችን ከስልጣናቸው ሲያነሱ፤ ሰባኬ ወንጌሎችን ሲያግዱ ከቆየ በኋላ በማያውቁት ጉዳይ ከማኅበረ ቅዱሳን በታዘዙት መሰረት በሲያምር የፍርድ ቀን ፍርድ ቤት በመግባት ይግባኝ በማለት ለሲያምር ተከራክረዋል። ፍርድ ቤቱም ችሎት ደፍረዋል  በማለት  ለጊዜው በማረሚያ ቤት ሊያቆያቸው ሲል በወቅቱ የነበሩት ስነ ስርዓት አስከባሪ ፖሊሶችና ከዳኛው ጋር የነበሩ ሌሎች ዳኞች በመለመናቸው ሳይታሰሩ ወጥተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አቡነ ዮሴፍ ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት በሚል ማኅበረ ቅዱሳን ባጠናላቸው መሰረት ቅዳሜ የገበያ ቀን በመሆኑ ምዕመኑ በማይገኝበት ቀንና ሰዓት ወደ ክብረ መንግስት እንዲመጡ ተደረገ፡፡ ምዕመኑም ቀድሞ ስላወቀ ተወካይ ልኮ መድኃኔዓለም ቤተክርሰቲያን መጥታችሁ አነጋግሩን በማለት ከሦስት አጥቢያ የተወጣጣ ሕዝብ ደብደቤ ይዞ በሚሄድበት ሰዓት በክብረ መንግስት የማቅ ተጠሪ የሆነውና የመድኃኔዓለም ደብር አስተዳዳሪ፣ የወረዳው ቤተክህነት ጸሐፊ፣ የወረዳው ስብከተ ወንጌል ሃላፊ፣ የዘንባባ ማርያም አስተዳዳሪ፣ የጨንቢ ሚካኤል አስተዳዳሪ፣ የመሊካ ገብርኤል አስተዳዳሪ፣ የገጠር ቤተክርስቲያኖች ተጠሪ የሆነው ባለስምንት ስልጣኑ ቀሲስ መኮንን ጉተማ የህዝብ ተወካዮች አቡነ ዮሴፍን እንዳያገኙ በህግ አምላክ እያለ ማይክራፎን ይዞ ቢጮህም በአካባቢው የነበሩ የመንግስት ባለስልጣኖች ወረቀቱን አቡነ ዮሴፍ እንዲቀበሉና በማግስቱም ህዝቡን እንዲያነጋግሩ ይጠይቁዋቸዋል፡፡ አቡነ ዮሴፍ የማቅ ሰዎችን ወሬ አምነው ስለነበር ህዝቡ ቢሮ ከሰማሁት ውጭ አያወራም በማለት በማግስቱ ህዝቡን ለማነጋገር በሚካኤል ቤተክርስቲያን ቀጠሮ ይይዛሉ።በዚህም መሰረት በማግስቱ በ28 01 2004 ዓ.ም. ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ላይ የአምስቱም ደብር ህዝብ በተገኘበት የተመለከቱት ነገር እነርሱ ሲዋሿቸው የነበረውን ግልባጭ ነው፡፡
በሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ የጠበቃቸው ነገር ከጠበቁት እና ካሰቡት ነገር እጅግ የተለየ ስለነበር ከፍተኛ የሆነ ድንጋጤ ወርሷቸው የሚናገሩት ሁሉ ጠፍቷቸው እንዲያውም በቦታው የነበሩትን የወረዳውን መስተዳዳር ሃላፊዎች  ልታስገድሉኝ አመጣችሁኝ? እያሉ ጭንቅ፤ ጥብብ እያላቸው የህዝቡን ምሬትና ሮሮ የማቅንም ክፉ መንገድ ሰምተው ሲያበቁ  መፍትሔ ማፈላለጉ የግድ መሆኑ ሲገባቸው ከአምስቱም ደብሮች ሁለት ሁለት ሽማግሌዎች ተመርጠው በወረዳ ቤተክህነት ላይ ያለውን ችግር አጣርተው ለጠቅላይ ቤተክነትና ለመንግስት ለሀገረ ስብከቱ እንዲያቀርቡ አዝዘው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አካባቢውን ለቅቀው መጡ፡፡
እሳቸው አካባቢውን ቢለቁም የሚሆነው አይታወቅም እና ከሻኪሶ፣ ከክብረ መንግስት፣ ከነገሌ ቦረና፣ ከቀርጫ፣ ከገርባ፣ ከሀገረ ማርያም፣ የተወጣጡ ምዕመናን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ተከትለዋቸው መጥተው አቤቱታ በማቅረባቸው አቡነ ዮሴፍ ወደ ሀ/ስብከቱ ተመልሰው ላይመጡ በወጡበት ቀርተዋል፡፡
በስተመጨረሻም የነገሩ አካሄድ ግራ እያጋባ ስለሄደ እና ነገሩ ከቤተክህነት አቅም በላይ መሆኑ ስለተደረሰበት ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መግትሔ እንዲፈልግለት የሚጠይቅ ደብዳቤ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፊርማ ተጽፏል። ( እዚህ ይጫኑ ) ደብዳቤው በደንብ እንዲነበብ ቃሉን አቅርበነዋል።

ለክቡር አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት
አዲስ አበባ
       ጉዳዩ፡   በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጉጂ ቦረና ሊበን ዞን ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ላይ የደረሰው ወቅታዊ ችግር መፍትሔ እንዲሰጠው የቀረበ ጥያቄ ነው
የዚሁ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ችግር ያሳሰበው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ለመ/ቤትዎ ያመለከተ መሆኑን ጠቅሶ ትኩረት እንዲሰጠው በቁጥር 2ዐ85/14430/04 በቀን 24/04/2004 ዓ.ም ከተጻፈው 3 ገጽ አባሪ ጋር ያቀረበልንን ስንመለከተው በሕግ የበላይነት ተረጋግጦ ውሳኔ ባገኘውና የሥራ ውላቸውን ካቋረጡ መጋቤ ጥበባት ሳያምር ተ/ማርያም ከሚባሉት ግለሰብ ጎን በመሠለፍ በቁጥር ከ12 የማይበልጡ እነ አቶ ፍቃዱ ታምሩ የሚባሉት ግለሰቦች ጠልቃ በመግባት የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት የበላይነት ሥራ አስኪያጁን ወደ ሀገረ ስብከት እርሱን አናስገባም በማለታቸው መንፈሳዊውና ማኅበራዊ አገልግሎት መቋረጡን በማስመልከት ይህ ከቤተ ክርስቲያኒቷ ማዕከላዊ አስተዳደር አቅም በላይ የሆነው ችግር በክልሉ መስተዳድር በኩል እንዲፈታ የሚያስችል ማሳሰቢያ እንድንጽፍለት የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በተደጋጋሚ አመልክቷል፡፡
ስለዚህ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ መልካም አስተዳደር ላይ ሆን ብለው ሕዝብን ለሕገ ወይ ብጥብጥ የሚያነሣሡ ግለሰቦች እንዳሉ በሀገረ ስብከቱ ሪፖርት የተገለፀ ስለሆነ፣ ይህ ሕገ ወጥ ድርጊት ሀገሪቱ ለምትከተለው የዕድገት ጎዳና ጠንቅ ሊሆን እንደሚችል ከክቡርነትዎ ግንዛቤ ስለማይሰወር ጉዳዩ ትኩረት አግኝቶ ከአካባቢው መልክዐ ምድር አቀማመጥ ጠራፋማነት አንጻር ታይቶ የማያዳግም አስተዳደራዊ መፍትሔ እንዲሰጠው እያሳሰብን ለአፈጻጸም ይረዳ ዘንድ የቀረበውን ማሳሰቢያ 3 ገጽ ፎቶ ኮፒ ጽሑፍ ከዚህ ጋር አቅርበናል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን


የችግሩን መቋጫ እየጠበቀ ያለው የአካባቢው ህብረተሰብ አሁንም ተስፋ ሳይቆርጥ እየታገለ ይገኛል።

የአቡነ ሳዊሮስ ጉዳይ፤


ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ በግልጽ የሚታወቀው ሰብዕናቸው ቅን መልካም ተግባቢ የሆኑና የእግዚአብሔር ቃልና ሀሳቡ የሚስፋፋበትን መንገድ በማመቻቸት የሚተጉ ሰው በመሆናቸው ነው። ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው ማኅበር ሥራ የሚለው በሀገረ ስብከቱ የማህበሩ መንገስ እንጂ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ስላልሆነ እሱ የሌለበት የማንኛውም መልካም እንቅስቃሴ ሁሉ ጠላት ነው። ማህበሩ ሳይኖር 10000 ሺህ ሰው ክርስትና ከሚነሳ ማኅበሩ ባለበት 1000 ሺህ ሰው ቢሰልም ደስ ይለዋል። የሚያቀርበውም ሪፖርት እኛ በአካባቢው በመኖራችን 1000ሺህ ሰው ብቻ ሰልሟል ባንኖር ኖሮ ግን ቁጥሩ ከዛ ያልፍ ነበር የሚል ነው። በብዙ ቦታዎች ላይ ማኅበሩ ስለመኖሩ የሚያቀርበው ሪፖርት ኖረን ይሄን ለውጥ አመጣን ሳይሆን ባንኖር ኖሮ እንዲህ ይሆን ነበር የሚል ሽብር አዘል ነው።
በዚህ እይታም እነርሱ ሳይሳተፉበት ወንጌል ሀይል ማግኘትዋ የህዝቡ ወደ ቤተክርስቲያን መመለስ የማያምኑት ወደ እምነት መምጣት እንቅልፍ ነስቷቸው የወንጌሉን እንቅስቃሴ ለማዳፈንና ቦታውን ለመቆጣጠር ውስጥ ውስጡን እንቅስቃሴ ጀመሩ። በዚህ እንቅስቃሴያቸው በብዙ ነውርና ገንዘብ ዘረፋ የሚታወቁትን አነ ቀሲስ መኮንንን እነ ሲያምርንና ሊቀ ስየማን ልሳነወርቅን እና መሪጌታ ሰለሞንን ከጎናቸው ለማሰለፍ ቻሉ።

ሲያምር ተ/ማርያም ወደተዛወረበት ትንሣዔ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤት መዛወሩንና ሥራ እየተበደለ መሆኑን በተደጋጋሚ ከተጻፈለት በኋላ በሽፍትነቱ ስለጸና ከሥራ መሰናበቱን የሚገልጸውን ደብዳቤ ለማንበብ ( እዚህ ይጫኑ )


 ከሚያገኙት ደሞዝ ጎን ለጎንም የማኅበሩ ተከፋይ የሆኑት እነዚህ ሰዎች በሙሉ ልባቸው በማኅበሩ በመስራት ህጋዊ መዋቅሮችን በማፍረስ ነገሮችን ሁሉን ነገር በማኅበሩ ቁጥጥር ስር ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። አዲስ አበባ ቤተክህነት አካባቢ በማኅበሩ ሰዎች የሚደረግላቸውን ከለላ በመጠቀምም አቡነ ሳዊሮስን ውስጥ ውስጡን መቃወም ጀመሩ። ይህንን አካሄዳቸውን የሚቃወሙትን የአካባቢው ተወላጆች ዲያቆናትና ሰባኬ ወንጌሎችን እያሳደዱ መምታች ጀመሩ፡፡ ለእውነት በመቆማቸው እና ቤተክርስቲንን እንጂ ማህበረ ቅዱሳንን አናገለግልም በማለታቸው ታግደው ከነበሩት ሰዎች መካከል መጋቢ ሓይማኖት ተስፋዬ መቆያ፤ ዲያቆን ስንታዩ፤ ዲያቆን ሀይማኖት፤ ዲ/ን ብሩክ፤ ዲ/ን አብርሃም፤ ዲ/ን ግርማ፤ ዲ/ን ብሩክ፤ ዲ/ን ብንያም ….እና ሌሎችንም ዲቆናትና ካህናት ከስራ አግደው ነበር፡፡
ይህንንም አድርገውም ቢሆን የተቃውሞው አካሄድ ስር አልሰድ ብሎ ሲያስቸግራቸውም ሌላ የጀርባ ቁስል ቢፈልጉ ሰላጡባቸው እና አቡነ ሳዊሮስን በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ የሚችሉበት መንገድ ሲጠፋባቸው ገንዘብ በልተዋል ለማለት የሚመስል ምክንያት ማፈላለግ ጀመሩ።
በሉ ብለው የሚያስወሩባቸው እና እነ አንድአድርገን እና አጫፋሪዋ ሎሚ የጻፉት ገንዘብ 30,000 ብሩ የመንበር ማሰሪያ ሲሆን 15,000 ብር ደግሞ ከሀገረ ማርያም ቅድስት ማርም ቤተክርስቲያን ሲያምር ተክለ ማርም እና አሁን አጣሪ ሆኖ ተሹሞ የነበረው አለም እሸት መውሰዳቸው የሰነድ ማስረጃ የተገኘባቸው ናቸው፡፡ ሌባ ሌብነቱ ሲታወቅ ሌባ ሌባ እያለ እንደሚሮጥ እነ ሲያምርም ሌብነታቸው ተደርሶበት ከህዝብ ዘንድ ጥያቄ ሲነሳ አቡነ ሳዊሮስ አካባቢውን ከለቀቁ በኋላ በእሳቸው ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ጀመሩ።
ብጹዕነታቸውን አሁንም ቢሆን የአካባቢው ህዝብ በመልካም ስራቸው የሚወዳቸው ሲሆን ከነዚህም መልካም ሥራዎቻቸው ጥቂቶቹ በደርግ ተወስዶ የነበረው የሀገረ ስብከቱ መሬቶችን ለቤተክርስቲን ጥቅም ማስመለሳቸው በቦሬ ወረዳ ላይ የጥምቀተ ባህር ቦታን ፕሮቴስታንቶች በጉልበት ለመውሰድ ሲሞክሩ ጨፌ ኦሮሚያ ድረስ በመሄድ ማስመላሳቸው በየገጠሩ ቤተክርስቲያን በማሰራት የምዕመን ቁጥር እንዲያድግ በማድረግ ጉባኤዎች እንዲዘጋጁና ህዝቡ በወንጌል ቃል እንዲጽናና በማድረግ ህዝቡን አስተባብሮ በመምራት የተመሰከረላቸው አባት ናቸው።


የሲያምር ነገር፤


ሲያምር የአዳሜ ቱሉ ልጅ ሲሆን በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ሰው ነው። በቅልስልስነቱ የሚታወቀው ሲያምር የገጠመውን ሰው ሁሉ የማኅበረ ቅዱሳን አባል እንዳልሆነ እና ለእውነት እንደሚሰራ ይናገራል። ቀርቦ ላደመጠው ሰው ከቅልስልስነቱ ጀምሮ የአነጋገር መንገዱ ሰዎችን ልብ የሚያስገዛ ሲሆን አብረውት የሚሰሩ አንዳንድ የማኅበሩ አባል ያልሆኑ ሰዎች እንኳ ስለእሱ ማኅበረ ቅዱሳን አለመሆን ደፍረው የሚናገሩ ናቸው። ሲያምር ግን አዲስ አበባ ሲመጣ በማኅበሩ ዋና ማዕከል መመሪያ እየተቀበለና የአሰራር ሂደቱን በተመለከተ ሪፖርት የሚያቀርብ ሲሆን። ወደ ነገሌ ቦረና ሲመለስ ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለበት ከማንያዘዋል መመሪያ የሚቀበልና የሰራቸውን ማኅበሩን የሚመለከት ስራዎች ለማንያዘዋል ሪፖርት የሚያቀርብ ሰው ነው።
የሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅነቱ በሰጠው ክፍተት ከፍተኛ ገንዘብ በመዝረፍ ወንጀል የሚጠረጠር ሰው ሲሆን በአንዳንድ የዝርፊያ ወንጀሎችም የኦዲት ሪፖርት ጭምር የቀረረበት ሰው ነው። የማኅበሩ አባል በመሆኑ ግን ማኅበሩ ከለላ እየሰጠው እስካሁን በዝርፊያ ወንጀል  ሳይከሰስ ቀርቷል። 


የማኅበረ ቅዱሳኑ ሽፍታው አባል በሕግ እንዲገደድ የሕግ  ትብብር የተጠየቀበትን ደብዳቤ ለማንበብ ( እዚህ ይጫኑ )

በጉጂ ቦረና ሊባን ዞኖች ሀገረ ስብከት ለተፈጠረው ችግር ዋነኛው ተጠያቂ እሱ ሲሆን በክብረ መንግስት ከተማ ህዝብ አይንህ ላፈር የተባለ ሰው ነው። ሰውየው በህዝብ ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠላ ቢሆንም የማኅበሩ ተከፋይ መጽሔቶች መካከል አንድዋ የሆነችው ሎሚ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው በማለት የጎደፈ ስሙን በሀሰት ቅባት ለማስዋብ ሞክራለች። በዚህ አጋጣሚ እውነቱ ወዴት ነው ብለው ሳይመረምሩ ለማኅበሩ የሚሰሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች በታሪክና በህሊና ፊት ተጠያቂ ከመሆን ስለማያመልጡ ስራቸውን ለእውነት ለማስገዛት እንዲሞክሩ እናሳስባለን።
እንግዲህ ይህ ህግ አያዘኝም ብሎ ህግ እየጣሰ በሚያስቸግረው በማኅበረ ቅዱሳን ጉያ ተከልሎ የሚፋንነው ግለሰብ ህገ ወጥነቱ ታውቆ ከስራ የተሰናበተና ሲሆን በጠቅላይ ቤተክህነቱ እውቀት ምንም አይነት ስራ በቤተክህነት አካባቢ የሌለው ሰው ነው።
የሲያምር ህገ ወጥነት ልክ አጥቶ ችግሩ ሳይፈታ የሀገረ ስብከቱ ንብረትም ሳይመለስ እንዲሁ በእንጥልጥል ሳለ የከተራ እለትእዚህ አዲስ አበባ ከተማ ታቦት ሲሸኝ ያየው የአካባቢው ተወላጅ የሆነ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ለፖሊስ ጠቁሞ አስያዘው። በጥር ወር 2004 ዓ.ም. ተከሶ በነገሌ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ጥፋተኛ መሆኑ ተወስኖበት በእጁ ላይ ያለውን ንብረት እንዲያስረክብ ቢታዘዝም እስካዛሬ ድረስ ማህተሙንና ጽ/ቤቱን አላስረከበም። እንዲያውም እጁ ላይ ባለው ማኅተም ወንጀል እየፈጸመበት ይገኛል። 

ሲያምር ተ/ማርያም ወደተዛወረበት ቦታ ሄዶ መስራት ሲገባው የሀ/ስብከቱን ንብረት ሳያስረክብ በመጥፋቱ የተጻፈበትን ደብዳቤ ለማንበብ ( እዚህ ይጫኑ )
እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ተደርጎ የማያውቀውን እንዲህ ያለውን ወንጀል የፈጸመን ግለሰብ ሎሚ መጽሄት እያንቆለጳጰሰ መጻፏ ያስገርማል። ፕሬሱ ኃላፊነት የማይሰማቸው ለእውነት ሳይሆን ለገንዘብ እና ለማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ አስፈጻሚነት ራሳቸውን የሾሙ ሰዎች ስብስብ እየሆነ መምጣቱ ያሳዝናል። ከብዕራቸው በቀር በልባቸው ያልተገዙለትን ፍትህ ጉደለ ብለው መጮሀቸው ትርጉም አልባ ያደርግባቸዋል። እነርሱ ባለቻቸው ትንሽ እድል ፍትህን እየረገጡና እውነትን እየካዱ ህዝብ የምንለውን ሰለሚሰማ ችግር የለም በሚል መንፈስ እውነትን ለመጨፍለቅ መወሰናቸውን ስናይ ስልጣን ቢኖራቸውምማ የሚያደርሱት በደል ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግተንም። የሁሉንም ወገን ሀሳብ ግራ ቀኝ አቅርቦ ህዝብ እንደፈርድ ከማድረግ ይልቅ የምንሰራው ለማኅበረ ቅዱሳን ነው በሚል መንፋስ እይናቸውን በጨው አጥበው ከማኅበረ ቅዱሳን ብሎግ ደጀ ሰላም ላይ እየወሰዱ የውንጀላ እና የክስ ጽሁፎችን ማውጣታቸውን ስናይ በሀገራችን ፕሬስ ወገናዊነትና በጋዜጠኞቹ የሙያ ስነ ምግባር ማጣት እጅግ እናዝናለን።
 የሎሚ መጽሔት ቅባት የልብ ልብ የሰጠው ሲያምር ሰሞኑን ወደ ሀገረ ስብከቱ ለመመለስ በቤተክነቱ አካባቢ ባሉ የማኅበሩ ሰዎች አማካኝነት ደፋ ቀና እያለ ይገኛል። ቤተ ክህነት አካባቢ ወደ ስራ ለመመለስ እየተቅለሰለሰ ወደ ጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት በመመላለስ ህግ በህገ ወጥነቱ የሚያውቀው ሲያምር እጁ ላይ ያለውን ህገ ወጥ ማኅተም ተጠቅሞ በማን አለብኝነት መንፈስ ያለስልጣኑ ለራሱ ስልጣን ሰጥቶ የበተክርስቲያን አስተዳዳሪዎችን ከስራ በማባረር የሰበካ ጉባኤ በማፍረስና አዲስ በማስመረጥ ስራ ተጠምዶ ይገኛል። የቤተክህነት መቅለስለሱ ምክንያትም ህገ ወጥ ስራውን ሕጋዊ ልባስ ለማልበስ ነው።
አስካሁን ደረስ ባለው ሂደት የሚሰሩትን የማያውቁትን ለጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት ሹመታቸው ያልጸደቀላቸው አቡነ ገብርኤል ሲያምርን መልሰው በቦታው ለመሾም ደብዳቤ ቢጽፉም በጠቅላይ ቤተክህነቱ በምን ስልጣን ተብለው ውድቅ ተደርጎባቸዋል። ይህም ቢሆን ግን የሰውየውን ህገ ወጥ አካሄድ ሊያግደው አልቻለም። በገጠሪቱ የሃገሪቱ ክልል ያሉ ካህናት ያላቸውን የህግ እውቀት ክፍተትና የማቅን ከለላ በመጠቀም ሀገረ ስብከቱን በህገ ወጡ ማኅተም ማመሱን አልተወም።
ይህ ግለሰብ በስልጣን ላይ ሳለ ተደጋጋሚ ወንጀሎችን የፈጸመ ሲሆን ከነዚህም ጥቂቶቹ፤


1.     በ2000 ዓ.ም. የታተመው የሚሊኒየሙ መጽሐፍ መሸጫ ዋጋው 100 ብር ሆኖ ሳለ በ600 ብር በመሸጥ ከመጽሀፉ የዋጋ ልዩነት 30,000 ብር ለግል ጥቅሙ አውሏል። ይህም በበቂ የሰው ማስረጃ የተረጋገጠ ነው።
2.    የመጽሐፉን ዋና ገንዘብም አስካሁን ለጠቅላይ ቤተክህነት አላስረከበም።
3.    ከሃገረ ማርያም ት/ቤት ተቀብሎ የነበረው ገንዘብ 360,000 ብር ጉድለት እንዳሳየ በኦዲተር ተረጋግጧል። ይህ 360,000 ብርም የት እንዳደረሰው አይታወቅም።
4.    ከአለምእሸት ጋር በመሆን 15,000 ሺህ ብር ከሀገረ ማርያም ወስዷል።


በነዚህ በተገለጹ እና በሌሎችም እሱ እንዳጎደላቸው በሚታወቁ ነገር ግን ማስረጃ ባልተገኘባቸው ወንጀሎች የሚጠረጠረው ሲያምር በሕግ መጠየቅ ሲገባው በቦታው እንዲመለስ ለማድረግ መሞከር ሊያስከትለው የሚችለው ችግር ግልጽ ነው። እንዲያውም ለጠቅላይ ቤተክህነት አልታዘዝ በማለት ከሰራ መሰናበቱ መሸፋፈን የማይቻል እውነት ስለሆነ የሱ ጉዳይ እዛው ጠቅላይ ቤተክህነት ሊታይ የሚገባው መሆኑ ግልጽ ነው።
እንደ እነ ሲያምር እና አለምሸት ያሉትን ወንጀለኞች አቅፎ የሚንቀሳቀሰው አፋኙ ማኅበረ ቅዱሳን ለእውነት ባይገዛ እንኳ አንዳንዴ ለራሱ ሲል እንዲህ ያሉ ወንጀለኞችን ከፊቱ ቢያርቅ ሊጠቅመው ይችላል እንላለን። ለነገሩ ማኅበሩ የወንጀለኞች ማጠራቀሚያ ስለሆነ ነፍሰ ገዳዮችን ለማቀፍ ያላመነታ ድርጅት ገንዘብ የሰረቁ ሰዎችን ማስጠለሉ ብዙም ላይደንቅ ይችላል።
ባለፈው ሳምንት ገልጸንላችሁ እንደነበረው አጣሪ ኮሚቴ ወደ ቦታው እንዲሄድ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም አሁን እንደሰማነው ደግሞ ውሳኔው ተሽሯል። ውሳኔው እንዲሻር ምክንያት የሆነው ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተሉ ያሉት ቅዱስነታቸው ሳያውቁት በጎን የተወሰነ ውሳኔ በመሆኑና በአጣሪ ኮሚቴው ውስጥ አንደ አለምሸት ያለ ቀንደኛ የማኅበረ ቅዱሳን አባል እና ተላላኪ በመገኘቱ ማጣራቱ ፍትሀዊነት ሊጎለው ይችላል ተብሎ በመገመቱ ነው።
የጉጂ ቦረና ሊበን ዞን ሀገረ ስብከት እና ቡሊ ሆራ ነዋሪ ህዝብ አሁንም እየተሰቃየ ይገኛል። ቤተክርስቲያን የፍትህ ምሳሌ መሆን ሲገባት ፍትህ ነጣቂዎች እንዲህ የሚፏንኑባት መድረክ ሆናለች። ለግል ጥቅም እንጂ ለእውነት የማያደሉ ሰዎች ስብስብ የሆኑ ማኅበራትን በጉያዋ ይዛም ተገቢውን ፍትህ የማስፈን እድልዋን መጠቀም አትችልም። ስለዚህ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ማኅበራትን ስርዓት ማስያዝ ግዴታዋ ነው። የህዝብ እንባ ወደ ላይ ወደ ቅዱሱ ጌታ ደርሷል። በፍቅር ያልታዘዙ ሁሉ በልምጭ የሚታዘዙት ቀን ከዕለት ወደ ዕለት እየቀረበ ይገኛል። ቤተክርስቲያን የልጆችዋን ጩኸት ትስማ። የሰማይ አምላክን አክብራና ፈርታም ለልጆችዋ ችግር በቶሎ ትድረስ።