Sunday, July 22, 2012

ለማኅበረ ቅዱሳን ፍርሀት የሆነው ጉባኤ አርድዕት በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ታወቀ።


ብዙ ጊዜ ስለማኅበረ ቅዱሳን በሚቀርቡ ጽሁፎች ላይ አስተያየት የሚሰጡ የማኅበሩ አቀንቃኞች የሚያዩን  ስለማኅበሩ ጭፍን አመለካከት እንዳለንና ሥራውን ሁሉ እንደምናቃወም አድርገውን ነው። ይሁን እንጂ ማኅበሩ እንደማኅበር የሰዎች እንጂ የቅዱሳን መላእክት ስብስብ ባለመሆኑ በጉዞው ውስጥ መልካምም ይሁን መጥፎ ሰውኛ ድክመቶች የሚገለጽበት መሆኑን ሁሉም አምኖ እንዲቀበልና ጥንካሬው ለቤተክርስቲያን ጠቃሚ እንደሚሆን ሁሉ ድክመቱም አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያመጣ በመገንዘብ ራሱን እንዲያይ፤ እኛም ማን መሆኑን በማወቅ የተሻለ ግንዛቤ ይዘን እንደባህሪው  የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ ነው። ለስህተት ትምህርቶችን የአዞ እንባ አፍሳሽነት፤ የሁሉን አውቃለሁና ጠበቃ ነኝ ባይነት መጥፎ ዐመል፤ የእኔ ላቡካው፤ እኔው ልጋግረው ግብዝነት፤ ከቤተክርስቲያኗ ኪስ ወደራስ ጓዳ የመሰብሰብ አባዜ፤ የሰላይ፤ የመቺ፤ የአሳዳጅና የፈራጅ ቡድን የማዋቀር ሲሲሊያዊ አካሄዱን ነቅሰን በማውጣት ይህን፤ ይህን ስትሰራ ቆይተሃል፤ ይህን ይህንንም እየሰራህ ትገኛለህ፤ መረጃዎቻችንም እነዚህ ናቸውና ከተነቃብህ እራስህን አርም፤ አስተካክል ወይም ቢያንስ ራስህን እስኪ  ጠይቅና ከሚወራው ውስጥ የትኛው እውነትና የትኛውስ ስም ማጥፋት ነው ብለህ ፈትሽ በማለት ለማሳሰብ ነው።  እኔ ቅዱስ እንጂ ስህተት የማይጎበኘኝ ነኝ ማለት ሲያበዛ ደግሞ አንተ ፈሪሳዊ ሆነህ ሳለ መጸብሐዊው አይጸድቅም የምትል ግብዝ ነህና መንገዳችንን አትዝጋ፤ የናቡከደነጾር የህልም ሀውልት ስለሆንክ ከተራራው የሚወርደው ዐለት ይፈጭሃልና ግዙፍነትህን አይተህ አትመካ እንለዋለን። ሌላውም  እንዲያይ የእስከዛሬ ማንነቱን ገልጠን ለሌሎች እናሳያለን። በዚህም ሥራችን ብዙዎች ራሳቸውን እንዲጠይቁ፤ የሚባለውን እውነትነት እንዲመረምሩ አድርገናል። በዚህም የመረጃ ስርጭትና ማንነቱን የመግለጽ ሥራችን ግምገማቸውን ወስደው ራሳቸውን ከማኅበሩ ክፉ ስራ ያገለሉ ብዙዎች ናቸው። ተሸፍኖ የነበረባቸውን የማኅበሩን ማደንዘዢያ መርፌ ነቅለው ከድንዛዜ ወጥተው፤ እስከዛሬ የት ነበርኩ? ያሉና ራሳቸውን የጠየቁ ብዙዎች ናቸው። ከዚህ በታች ያለውም የማኅበረ ቅዱሳን አቀንቃኝ ብሎጎች ማጭበርበርና የነፍስ ውጪ፤ ነፍስ ግቢ ውሸት ማሳያ ቀርቧልና  ሄዳችሁ ብሎጎቹን አንብባችሁ ከታች በቀረበው መረጃዎች ላይ ተመርኩዛችሁ ማቅ ማን መሆኑን ተመልከቱ! ሁሌም ውሸት! ውሸት! ውሸት! አቤት ማቅ?
ምንጫችን፤ ዓውደ ምሕረት ብሎግ፤

  •     ሊቀ ሥዩማን ኃይለ ጊዮርጊስ መኪና አልተቀማም
  •     ጉባኤ አርድእት ስብሰባ እንዳይሰበሰብ አልታገደም
  •     መንግስት ለማኅበረ ቅዱሳን የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ማንም አልሰማም በማለት ወደ ጉባኤ አርድዕት ለማዞር ሞክረዋል
የማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች በተለመደው ዋሾ ባህሪያቸው ያልሆነውን ሆነ እያሉ መዘገብን ቀጥለውበታል፡፡ ስለጉባኤ አርድዕት በመፈራረቅ በሰሩት ዜናም ገና በመደራጀት ላይ ያለውን ጉባኤ ተፈረካከሰ ተልፈሰፈሰ ሄደ ተመለሰ እያሉ የጅል ምኞታቸውን ይነግሩን ይዘዋል፡፡ ሊቀ ሥዩማን ኃይለጊዮርጊስም በጠቅላይ ቤተክህነቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ፊርማ መኪናው ስለተበላሸ ቅያሪ መኪና እንዲሰጠው የትብብር ደብዳቤ እንደተፃፈለት እያወቁ  ደብዳቤውን ከኛ በቀር ማንም አያገኘውም በማለት ተበላሽቶ ወደ ጋራዥ የገባውን መኪና ተቀማ በማለት ዘግበዋል፡፡
እነዚህ የማኅበሩ የውሸት ቃል አቀባይ የሆኑ ደጀ ሰላምና አንድ አድርገን የተባሉት ብሎጎች በጉዳዩ ላይ እርስ በእርሳቸው እንኳ መስማማት አቅቷቸዋል። ዋሽቶ ስምምነት የት አለና? ደጀ ሰላም ኃይለጊዮርጊስ መኪና የተቀማው በአቡነ ጳውሎስ ትዕዛዝ ነው ብላ ጀምራ ወደ ታች ወደ ወረድ ሲባል ደግሞ በምክትል ስራ አስኪያጁ በተስፋዬ ነው በማለት ራስዋን ተጣልታ ዘግባለች። አንድ አድርገን ደግሞ በምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ነው ትላለች።
እውነታው ግን ሌላ ነው በምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ፊርማ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው የኃይለጊዮርጊስ መኪና በብልሽት መቆምዋን እና እንዲያውም ተለዋጭ መኪና እንዲፈለግለት ልማትና ክርስቲያናዊ መምሪያን የሚጠይቅ ነው።
 ደብዳቤውን ለማንበብ ( እዚህ ይጫኑ )



ደብዳቤውን በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መኪናው በብለሽት ምክንያት መቆምዋን እየገለጸና እና ተለዋጭ መኪና ይፈልግ ተብሎ ሳለ እነ ውሸት ስንቁ ግን ተቀማ ብለው መጻፋቸው ሊያገኙት የፈለጉትን ተራ ውዥንብር የመፍጠር ትርፍ አላማው ምን እንደሆነ ያሳውቅባቸዋል።
እንደዚሁም ደጀ ሰላም
“..ባለፈው ሳምንት፣ ሰኔ 26 ቀን 2004 .ም፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጠቅላላ አገልግሎት ሓላፊ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገብረ ጻድቅ ተፈርሞ በአድራሻ ለጥበቃ አገልግሎት ክፍል የተላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው÷ ራሱንጉባኤ አርድእትበሚል የሚጠራው ቡድን ከቅዱስ ሲኖዶስ ይኹን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተሰጠው አንዳችም ዕውቅና የለውም፤ የጉባኤው አስተባባሪዎች በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ በውል ተለይቶ ላልታወቀና ላልተፈቀደ ዓላማ በኅቡእ መሰብሰባቸው ሕገ ወጥነት በመኾኑ የትኛውንም አዳራሽ ይኹን ቢሮ ለስብሰባ መጠቀም አይችሉም፤ የጥበቃ አገልግሎት ክፍሉም ይህንኑ ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ትእዛዝ ተሰጥቶታል፡፡  
በማለት የዘገበችው ዘገባ ሙሉ በሙሉ ውሸት እንደሆነ እና በደብዳቤው ላይ ስለጉባኤ አርድዕት የሚያወራው ነገር እንደሌለ የሰኔ 26 የሊቀ ኅሩያን አለም እሸት ደብዳቤ ያስረዳል።
 ደብዳቤውን በግልጽ ማየት እንደሚቻለውበቅዱሳን ፓትሪያርኮች ማረፊያ ህንጻ ማንም እንዳይገባ እና እንዳይሰበሰብየሚያግድ እንጂ ስለ ጉባኤ አርድእት የሚያነሳው ነገር የለውም። ደብዳቤውን ለማንበብ( እዚህ ይጫኑ ) 
ግን የማቅ ብሎጎች ደብዳቤውን ጠምዝዘው እና አቅጣጫ አስቀይረው ያልተጻፈበትን ነገር እንደተጻፈ አድርገው ማስነበባቸው እንዲህ እውነቱ ሲወጣ ትዝብት ላይ ከመውደቅ አያድናቸውም።
ደጋግመን እንደዘገብነው ውሸት የማኅበረ ቅዱሳን ተፈጥሮ ነው፡፡ ሀሳበ ሰንካላው ማኅበር በፊቱ የሚቆም ሌላ ማኅበር ካለ የጥፋት ማኅበር መሆኑ ጎልቶ እንደሚወጣ ስላወቀ የነገር ቀንዱን አሹሎ ያገኘውን ካልወጋሁ እያለ እያስቸገረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ገና በሀሳብ ደረጃ ያለ ማኅበርን የፈራውና ያርበተበተው ተደራጅቶ ስራ ቢጀምር የሚያመጣበትን ኪሳራ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ለሁላችንም ሳንጠይቀው ስለጉባኤ አርድዕት ያስተዋወቀን እና የጉባኤውን መመስረት ማኅበረ ቅዱሳን ከጠበቀው በተለየ መልኩ በርካታ የቤተክርስቲያን ልጆች በናፍቆት እንዲጠብቁት ያደረጋቸው ራሱ ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡
ስለ ጉባኤ አርድእት በተዘጋጀው እና ስለጉባኤው የሚተነትነው ጹሁፍ እንደሚያስረዳው የጉባኤው አላማ
 “… የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፣ ይህም አንድነትዋ በሃይማኖት፣ በቀኖናና በሥርዓት፣ በሕግ፣ በመዋቅር፣ በአስተዳደር፣ በአሠራርና በአመራር አንድነት የሚገለጥ ነው ብለን ስለምናምን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚያጠናክር ሁለንተናዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ አንድነት የበለጠ ጠቃሚ ነው ብለን ይህችን መንፈሳዊት ኅብረት ፈጥረናል፡፡ የሚል ነው፡፡ ይህንን አላማ ሰይጣን ካልሆነ ማን ሊቃወመው ይችላል? ሥራ ሳይጀምር አካሄዱ ሳይታወቅ እንዲሁ ብቻ ከማኅበረ ቅዱሳን ቁጥጥር ውጭ ነው ብሎ መርበትበት መደንገጥና ኡኡታ ማሰማት ምንድን ነው? ይህ ራሱ ማኅበሩ በስራው መተማመን እንደሌለው እና ሌላ ማኅበርም ከመጣ ያለ ብዙ ድካም ከማቅ የተሻለ ሥራ እንደሚሰራ የሚያሳይ ነው፡፡
መበለጥን ቀድሞ ለመከላከል ካልሆነ እንቅስቃሴ ሳይጀመር ይህን ያህል መደናበር ምን ማለት ነው? ሕዝቡን በስራ ሳይሆን በሽብር እኔ ከሌለሁ ዋጋ የለህም በማለት እራስን በእግዚአብሔር ቦታ አስቀምጦ ያለአቅም በመንጠራራት ከማሸበር ይልቅ አቅምንና ቦታን አውቆ የተሻለ ነገር ለማድረግ መሞከሩ የተሻለ ነው፡፡
ሌላው አስቂኝ ዘገባቸው ጉባኤ አርድእትን መንግስት ተቃውሞታል የሚለው ነው። እንዲያውም መንግስት ሐምሌ 3 ቀን የማኅበሩን አመራሮች ጠርቶ ባናገራቸው ጊዜ ያላቸው የተገላቢጦሹን ነው። መሰባሰብ እና መደራጀት መብት እንደሆነ የማንንም ሕገ መንግስታዊ መብት ማፈን እንደማይችሉ ማንም ተነስቶ ይህን እና ያን ማድረግ እችላለሁ ብሎ የሰዎችን የመደራጀት መብት ማፈን እንደማይችል እና ይሄ አካሄዳቸው ራሱ ጸረ ሕገ መንግስት መሆኑን እንደተገለጠላቸው የሚታወቅ ነው፡፡
የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ከባድ ስለሆነ፣  የመንግስትን ማስጠንቀቂያ ለማስተባበል እና አቅጣጫ ለማስቀየር ከጠፋን አይቀር ሁሉንም ይዘን እንጥፋ በሚል መሯሯጥ መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ጉባኤ አርድእት ግን ስራውን እንዳላቆመ እንዲያውም አካሄዱ እየተጠናከረ መምጣቱ ግልጽ ነው። ይህም ስላስደነገጣቸው አባላቱ ተከፋፈሉ ተገነጠሉ እያሉ ወሬ ማስወራትን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል።
ጉባኤ አርድዕት አሁንም ከማቅ የሚደርስበት ውርጅብኝ እንዳለ ሆኖ የታቀደለትን ወጥመድ እየሰባበረ ጉዞውን መቀጠሉ ታውቋል። አሁን ያለበት እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ እንደሆነ እና እንዲያውም የአባልነት ጥያቄውን ብዛት ከጠበቀው በላይ እንደሆነ በአጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናትና በሃገረ ስብከቶች የጉባኤ አርድዕት አባል ለመሆን እንደሚፈልጉ እና ቤተክርስታንን ካሁን በኋላ እነደ ማቅ ላለ የቀን ጅብ አሳልፈው መስጠት እንደማይፈልጉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ታዋቂ ሰባኪያን እና በቤተክርስቲያን ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች የጉባኤ አርድዕት አባላት እየሆኑ መምጣታቸው ታውቋል።
ማህበሩ የጉባኤው አደረጃጀት ስላስፈራው ወደ ታች ወርዶ አባላትን ማሳተፍ እንዳይጀምር ህዝብን ለማስደንገጥና ሲል በስምአ ጽድቅ ጋዜጣው እና በብሎጎቹ ጉባኤውን የተጠጋህ ወየውልህ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እየሞከረ ይገኛል።
እስካሁን ደረስ ባለው አደረጃጀት እንደ ጉባኤ አርድዕት አባቶቻችንን እንርዳ ብሎ የተነሳ ስብስብ የለም እነ ማኅበረ ቅዱሳን የጳጳሳትን ስራ ወስደው በእነርሱ ላይ እንደ ጳጳስ እየሆኑ ያልናችሁን ፈጽሙ ማለት እንጂ እንርዳችሁ የሚል አካሄድ የላቸውም። ጉባኤ አርድእት ግን ተልዕኮ እናሳካ እናንተን አንርዳ የሚል አካሄድ ነው ያለው። ይህንን አካሄድ ማንም ለቤተክርሰቲያን ቅን ልቦና ያለው ሰው የማይቃወመው ነው።  ማኅበረ ቅዱሳን ሀሳቡን በሀሳብ ደረጃ እያለ መቃመሙ እና ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ማድረጉ ማኅበሩ  ቤተክርስቲያንን በሞኖፖል የመቆጣጣር ህልሙን እና ከክርስቶስ ባሪያነት ለይቶ የሀሳቡ ባሪያ ለማድረግ የሚያደርገው ሩጫ አካል መሆኑ ግልጽ ነው።