Friday, July 6, 2012

በውኑ፣ ክርስቶስ ያማልዳልን?


 አንዳንዶች ስለክርስቶስ የማማለድ ሥራ ለመቃወም ሲሉ መጽሐፍ ቅዱስን እስከመደለዝ ደርሰዋል። ሰብዓ ሊቃናትና ዐበይት የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤያት ያጸደቋቸውን የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜ በመሰረዝ የራሳቸውን ክልላዊ መጽሐፍ ቅዱስ እስከማሳተም የደረሱት የክርስቶስን ሥጋ የመልበስን ምስጢርና አሁንም በአብ ቀኝ የተቀመጠበትን አምላክ ሰው የሆነበትን ማንነት ለመጠበቅ ሲሉ የግሪኩንና እብራይስጡን ትርጉም ሰርዘውታል። በአንድ በኩል መናፍቃን ለራሳቸው እንዲያመቻቸው የወንጌል ቃልን ይሰርዛሉ፤ ይደልዛሉ እያልን በሌላ መልኩ ወቃሾች፤ የተወቃሾችን ታሪክ መድገም መደለዝ በመሠረቱ አሳዛኝ ነገር ነው። አበው ያቆዩትንና የተጻፈልንን እውነት ይዞ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ቃል ግልጽልጽ አድርጎ መመለስ ሲገባ፤ የተጻፈውን ሰርዞ፤ ከማስተማር ለመደበቅ መሞከር አስደንጋጭ ነው። ይህንን ከእውነት የመሸሽ ተግባር በማብራራት ከታች የቀረበው ጽሁፍ አንድ ነገር ይጠቁመናል። መሰረዛቸውን የማይክዱ ግን በመሰረዛቸው ከሲኖዶሳውያት ጉባዔያት ጋር ለምን እንደተለያዩ ማሳመን የማይችሉ ሰዎች ይህን ጽሁፍ ሲያነቡ ጆሮአቸውን ሊያስክክ፤ ዓይናቸውንም ሊያጨልም ይችላል።
የጽሁፉ ባለቤት «አድነው ዲሮ» ይሰኛሉ። መልካም ንባብ ይሁንልዎ!

I. መግቢያ፡- የሰው ልጅ ውድቀት

የዚህ ጽሁፍ አቢይ አላማ በየዕለቱ ስለ ሚገጥሙን የሕይወት ውጣ ወረዶች አንጻር፣ ስለታመሙ ሰዎች፣ በእስር ስላሉ ሰዎች፣ ስለ መሪዎች፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ አገር፣ ስለ አገልግሎት፣ ወዘተ አንዱ ለሌላው ወደ ፈጣሪው የሚያደርሰው የምልጃ ጸሎት፣ ክርስቶስ ለእኛ ባደረገው የማማለድ ሥራ ላይ ጥላውን እንዳያጠላበት ጥንቃቄ እንድናደርግ ለማሳሰብ ነው፡፡ እንደነዚህ አይነቶቹ - አንዱ ስለ ሌላው የሚጸልየው ጸሎት - ክርስቶስ ለእኛ ከፈጸመው የምልጃ ሥራ ጋር ምንም ዝምድና እንደሌለው ማሳሰብና እነዚህ ሁለት ነገሮች ሊነጻጸሩም ጭምር እንደማይገባ ማሳየት፣ የማንም ሰው የጸሎት ምልጃ የክርስቶስን የመስቀል ላይ ምልጃ ሊተካው እንደማይችል መግለጽ፣ እንዲያውም አንዳችን ለአንዳችን የመጸለይ (የመማለድ) ፈቃድ ያገኘነው በክርስቶስ የምልጃ ሥራ ከእግዚአብሔር ጋር ስለታረቅንና ከተቆጣን ፈጣሪ ጋር ሰላም ስለፈጠርን መሆኑን ማስገንዘብ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህንን አሳብ ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ ከችግሩ መነሻ ማለትም ከሰው ልጅ የውድቀት ታሪክ እንነሳና ጉዳዩን በጥልቀት እንመልከት፡፡ 

የሰው ልጅ፣ አጽናፈ ዓለሙ፣ የምድር አራዊት፣ የሰማይ ወፎች፣ የባሕር ዓሶች ከተፈጠሩ በኋላ በፈጣሪው አምሳል በስድስተኛው ቀን የተፈጠረ ልዩ ፍጥረት ነው፡፡ ከእርሱ ቀድሞ የተፈጠሩትን ይገዛና ያስተዳድር ዘንድ ሃላፊነት ጭምር የተሰጠው ይህ ሰው፣ ይኖርበት ከነበረው ኤደን ገነት የአንዲቷን ዛፍ ፍሬ እንዳይበላ ከፈጣሪው ትእዛዝ ተሰጠው፡፡ በፈጣሪው ላይ መታመን ያልፈለገው የሰው ልጅ በትዕቢት ከፍሬዋ ቀጥፎ በላ፡፡ ከፍሬዋ በበላህ ጊዜ ሞትን ትሞታለህ ያለው አምላክም ጻድቅ ፈራጅ እንደ መሆኑ፣ የጽድቅ ብያኔውን በራሱ ላይ ተደግፎ ለመኖር በወሰነው በዚህ የሰው ልጅ ላይ አስተላለፈ፡፡ ከብያኔዎቹ መካከል አንዱ እንዲህ ይነበባል - «... የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፣ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና፣ ምድር ካንተ የተነሳ የተረገመች ትሁን፤…´ (ዘፍ. 317)፡፡

የሰውና የፈጣሪ ጠብ እንግዲህ ከዚህ መጥፎ ጊዜ ይጀምራል፡፡ ከዚህች ቀንና ሰዓት ጀምሮ ሰውና ፈጣሪው ጥለኞች ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያዘጋጀውም መልካም ሃሳብ በሰይጣን ፈታኝነት፣ በሰው ልጅ ተባባሪነት እንቅፋት ገጠመው፡፡ አግዚአብሔር ሕግ ሰጠ፣ የሰው ልጅ ተላለፈው፣ ፈጣሪም የጽድቅ ፍርድ አስተላለፈ፡፡ ይህም ፍርድ ሞት ይባላል፡፡ የሰው ልጅ በሞት ፍርሃት ውስጥ እየማቀቀ ለበርካታ ዓመታት በምድር ላይ የስቃይ ኑሮ መግፋት ጀመረ፡፡

ይህን ፍርድ ያስተላለፈው አምላክ ጻድቅ ብቻ ሳይሆን የፍቅር አምላክ በመሆኑ፣ ከእስትንፋሱ የተካፈለው ሰው በምድር ላይ ሲሰቃይ ማየት አላስቻለውም፡፡ በዚህም ምክንያት ጻድቅ ፈራጅነቱንና የፍቅር አምላክነቱን አዋህዶ የሚያሳይ ሌላ የደኅንነት መንገድ ለሰው ልጅ አዘጋጀ። ይህ የደኅንነት መንገድ ጽንፍ የሚመስሉትን የአምላክ ሁለት ባሕሪያት (ፍርድና ምሕረት) በአንድ መስመር ያገናኘ አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው ዘር ሁሉ ላይ ያሳለፈው ሊታጠፍ የማይችል የሞት ፍርድ ሳይቀለበስ የሰው ልጅ ከተቆጣው አምላኩ ጋር ታረቀ፡፡ የአገራችን የእምነት ሊቃውንት ይህንን ሁኔታ ግሩም በሆነ መንገድ እንዲህ በማለት ይገልጹታል፡፡ «እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ ተጠበበች፡፡´ የዚህ አስገራሚ ትእይንት ጀማሪና ፈጻሚው ደግሞ ምንም በደል ያልተገኘበት ኢየሱስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ላይ የተቆጣውን ቁጣ በኢየሱስ ላይ አሳረፈው፤ ፍርዱን አሳየ፡፡ ኢየሱስ ስለ ኃጢአተኞቹ ስለ እኛ ሞተ፡፡ በእርሱም ምክንያት የሰው ልጅ ምሕረትን ተቀበለ፡፡ ከፈጣሪውም የፍርድ ቁጣ ተረፈ (ሮሜ. 59)፡፡

የብሉይና የሐዲስ ኪዳናት መሰረታዊ ጭብጥም ይኸው ታላቅ ሥራ ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን የሐዲሱ ኪዳን ጥላ/ምሳሌ እንደ መሆኑ፣ የሰው ልጅ የደኅንነት መሰረት የሆነው (1ቆሮ. 310-11) ክርስቶስ ዘመኑ ደርሶ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እስኪመጣ ድረስ፣ የሰው ልጅ በታላቅ ምጥ ውስጥ ነበር፡፡ ጥላ የነበረውንና የሰውን ልጅ ፍጹም ሊያደርገው የማይችለውን የእርቅ ሥርዓት (ዕብ. 9910) እየፈጸመ ከአምላኩ ጋር ሊያስታርቀው የሚችለውን የደኅንነት ተስፋ መጠበቅ ጀመረ፡፡ አንዳንዶች ይህን ተስፋ በሩቅ ተሳለሙት (ዕብ. 1113 114940) ሊሎች ደግሞ ይህን ተስፋ በዓይናቸው አዩት (ሉቃስ 229-32)፡፡ የዚህ ጽሑፍ አንባቢ እርስዎና እኔ ደግሞ በዚህ የምሕረት ዘመን ውስጥ ለመገኘት የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ሆነ፡፡
የሰው ልጆች ሁሉ ተስፋ የነበረው፣ የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት የሚቤዠው፣ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያስታርቀው፣ የተዋረደውንና በውድቀት ከእግዚአብሔር ቁጣ ስር ለሞት የሚጠበቀውን የሰውን ዘር የሚታደገው ብቸኛ አዳኝ እስኪመጣ ድረስ፣ የሰው ልጅ የዚህን ፍጹም ተስፋ ጥላ እየተከተለ አካሉን ናፈቀ፡፡ ጥላው የነበረውን የብሉይ ሥርዓት እየፈጸመ የአካሉን መገለጥ ለእልፍ ምዕት ዓመታት በናፍቆት በጠበቅ ግድ ሆነበት፡፡ ከዚህ በታች ባሉት ጥቂት አንቀጾች ከሰው ውድቀት አንስቶ እስከ መሲሁ መምጣት ድረስ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ተቀባይነት ያለውን ሕብረት ለማድረግ፣ የኃጢአት ሥርየትን ለማግኘትና የምስጋና መሥዋዕት ለማቅረብ ምን ነገሮችን ይፈጽም እንደነበረ አለፍ አለፍ እያልን እናያለን፡፡ ይህ የብሉይ ሥርዓት ሊመጣ ያለው እውነተኛ አካል ጥላ/ምሳሌ እንደሆነ አንባቢ ልብ ይበል፡፡ በዚህ ስር የምናያቸው ቁም ነገሮች ግልጽ ከሆኑ፣ ኋላ ላይ የምናየው የሐዲስ ኪዳኑ አካል ፍሬ አሳብ ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡


II. የብሉይ ኪዳን ክህነት

የክህነት አገልግሎት የእስራኤል ሕዝብ በሙሴ መሪነት ከግብጽ ባርነት ከወጣ በኋላ የተጀመረና ለአንድ ሺህ አመታት የዘለቀ ታላቅ አገልግሎት ነው፡፡ እነዚህ የክህነት ሕግጋቶች ለእስራኤል የተሰጡት በሲና ተራራ ላይ ሲሆን (ዘሌ. 738 251 2646 2734) የአገልግሎቱም አስፈላጊነት እስራኤል የኃጢአት ስርየትን በመቀበል ከርኩሰት ነጻ እንዲሆን ነበር (ዘሌ. 1145)፡፡ ይህ የአምልኮ ሥርዓት አንዳንዶች የብሉይ ኪዳን ወንጌል በሚሉት የዘሌዋዊያን መጽሐፍ ላይ በስፋት ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡

ካህን የሰው እንደራሴ በመሆን መባና መሥዋዕት በማቅረብ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ አገልጋይ ነው፡፡ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል በመቆም የሚማልድ ነው፡፡ «ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማል´ (ዘጸ. 281 ዕብ. 51-4) የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የካህናትን አጠራርና ተግባር በግልጽ ያሳያል፡፡ የዘሌዋዊያን መጽሐፍ ጭብጥ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚቻለው በመሥዋዕት አማካኝነት ብቻ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ይህም ምሥዋዕት በእስራኤል የአምልኮ አገልግሎት ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዳለው ያሳያል፡፡ እስቲ አሁን በአጭሩ የአሮን ክህነት ባሕሪን እንመልከት፡፡


II.1 የአሮን ክህነት

የሰው ልጅ በኃጢአት ከወደቀ በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ዳግም ተቀባይነት ያለውን ኑሮ ለመግፋትና እግዚአብሔርን ለማምለክ የክህነትን ሥራ ተጠቅሞበታል፡፡

እግዚአብሔር የነገድ ምርጫ ሳያደርግ የእስራኤልን ሕዝብ ባጠቃላይ የእርሱ ካህን የማድረግ ውጥን ቢኖረውም (ዘጸ. 196) ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ሕግና ትዕዛዛት የድንጋይም ጽላት ለመቀበል አርባ ቀንና ለሊት ከእግዚአብሔር ጋር የቆበትን አጋጣሚ በመጠቀም የወርቅ ጥጃ ሰርተው በማምለካቸው ምክንያት ለዚህ ክህነት አገልግሎት የሌዊን ነገድ ብቻ ለመምረጥ ተገደደ፡፡ ከዚህ ነገድ ደግሞ የመቅደሱን ውስጠኛ አገልግሎት ለመፈጸም የተፈቀደለት የአሮን ቤተሰብ ብቻ ነበር (ዘኁ. 310)፡፡

ስለ መሥዋዕቶቹ ስንመልከት ደግሞ፣ በመጀመሪያዎቹ ሰባት የዘሌዋውያን መጽሐፍ ሃሳብ መሰረት አራት ዋና ዋና መሥዋዕቶች እናያለን፡፡ እነዚህም የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የኃጢአት መሥዋዕት፣ የበደል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት በመባል ይታወቃሉ፡፡

ሊቀ ካህናት 4 ዋና ዋና ተግባራት ሲኖሩት እነዚህም በእግዚአብሔር ፊት የእስራኤል እንደራሴ መሆን (ዘጸ. 2817-29) የነቢይነትን አገልግሎት በአግባቡ መወጣት (ዘጸ. 2830) ለሕዝቡ ቡራኬ መስጠት (ዘኁ. 622-27) በማስተስረያ ቀን ሥርዓቱን መፈጸም እና ለሕዝቡ መጸለይ (1ሳሙ. 1223) ናቸው፡፡ የመሥዋዕት አቀራረቡን በተመለከተ ደግሞ ካህናት በየዕለቱ የሚቀርቡ መሥዋዕቶችን የሚያሳርጉ ሲሆኑ፣ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት መሥዋዕት ማቅረብ የሚፈቀድላቸው ግን ሊቀ ካህናት ብቻ ነበሩ፡፡ 

ሊቀ ካህኑ በአመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚገባበትና የማስተስረያ ቀን በመባል በሚታወቀው ልዩ ዕለት የሚሆነው ነገር ይህን ይመስላል፡- አሮን ሊቀ ካህናት ሆኖ ለመሥዋዕትነት ከሚቀርቡት ከሁለቱ ፍየሎች አንዱን «ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የሚሰዋውንፍየል ያርዳል፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል በወይፈንም ደም እንዳደረገ በፍየሉ ደም ያደርጋል፤ በመክደኛውም ላይና በመክደኛውም ፊት ይረጨዋል´፡፡ ይህንም ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ «ሕያውን ፍየል ያቀርባል፤ አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ የጭናል፤ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ፣ መተላለፋቸውንም ሁሉ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፤ በተዘጋጀውም ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል፡፡ ፍየሉም ኃጢአታቸውን ሁሉ ወደ በረሃ ይሸከማል፤ ፍየሉንም በምድረ በዳ ውስጥ ይለቅቀዋል´ (ዘሌ. 1615-22)፡፡ እነዚህ ሁለቱም ፍየሎች በአንድነት በዚህ ቀን የሚሰዉ የኃጢአት መሥዋዕቶች ነበሩ (ዘሌ. 165)፡፡ በመጀመሪያው ፍየል አማካኝነት የእስራኤል ሕዝብ የኃጢአት ቅጣት ሞት መሆኑን ሲገነዘብ፣ በሁለተኛው ፍየል ደግሞ እንስሳው እነርሱን ተክቶ (ኃጢአታቸው ከእነርሱ ተወስዶ በፍየሉ ላይ እንደሆነ) የኃጢአታቸውን ቅጣት እንደተቀበለ በእርሱም ምክንያት እነርሱ ከቅጣት ነጻ እንደሆኑ ይገነዘባሉ፡፡ ይህ ሥርዓት የክርስቶስ መሥዋዕትነት ጥላ ሲሆን፣ እኛም ክርስቶስ ኀጢአታችንን በመሸከሙና በመሞቱ ከኃጢአት ቅጣት ነጻ የወጣን መሆናችንን ያበስረናል (1ጴጥ. 224 ዕብ. 97 1528)፡፡

II.2 የመልከ ጼዴቅ ክህነት

የዚህ ሰው ክህነት ከአሮን ክህነት ፍጹም የተለየ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ካህን የሚናገረው እንግዳ ነገር የትርጓሜ ግርታን መፍጠሩ የተለመደ ስለሆነ እስቲ እነዚህን እንግዳ ቁም ነገሮች እንመልከት፡፡ ስለዚህ ካህን የትውልድ ቁጥር እና ዘመን የእብራዊያን ጸሐፊ ሲተርክ እንዲህ ይላል፡- «አባትና እናት የትውልድም ቁጥር የሉትም፣ ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፣ ዳሩ ግን ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል፡፡´ (ዕብ. 73)፡፡ ይህን ገለጻ ሰውየው መልአክ ነው ወይስ የተለየ ፍጥረት እንድንል ይጋብዘን ይሆናል፡፡

«አባትና እናት የሉትም´ ማለት እንዲሁም «ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም´ ሲባል ስለ እርሱ በቀረበው ጽሁፍ ወይም ታሪክ ውስጥ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የተጻፈ ነገር የለም ማለት ነው እንጂ ፍጹም  አባትና እናት የሌሉት እንግዳ ፍጥረት ነው ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ነገሮች ሳይጻፉ የቀሩበትም ምክንያት መንፈስ ቅዱስ መልከ ጼዴቅ ክርስቶስን እንዲመስል በእርሱም የክርስቶስን ስዕል አግኝተን የክርስቶስ ክህነት ለዘላለም እንደሆነ እንድናስተውል ስለ ፈለገ ነው፡፡

በኦሪት ሕግ መሰረት ክህነት የተሰጠው ለአሮን ልጆች ብቻ መሆኑን ከላይ ተመልክተናል፡፡ ትውልዱ በትውልድ መጽሐፍ ያልተገኘ ማንኛውም ሰው እንደ ካህን ሊያገለግል አልቻለም (ዘኁ. 310 819-22)፡፡ ይህ አባባል፣ ክህነት በዘር ተወስኖ የነበር አገልግሎት መሆኑን ያሳየናል፡፡ መልከ ጼድቅ ግን የትውልድ ቁጥር የለውም፡፡ ማለትም ትውልዱ በትውልድ በጽሐፍ አልተገኘም፡፡ ዘሩ ከየት እንደሆነም አልተጻፈም፡፡ በዚህ ምክኒያት ክህነቱ በዘር ላይ አለመመስረቱንና ይህም የእግዚአብሔር ልዩ ጥሪ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ስለሆነም የመልከ ጼዴክ ክህነት ከሌዊ ክህነት የተለየ መሆኑን እናያለን፡፡

«ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፣ ዳሩ ግን ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል´ የሚለው አሳብ ደግሞ መልከ ጼዴቅ ስለ ኖረበት አመት ብቻ ሳይሆን ስለ ክህነቱም ዘመን ጭምር ያሰበ ይሆናል፡፡ ሌዋዊያን ለአገልግሎታቸው የተወሰነ ዘመን ነበራቸው፡፡ ይህም 25 እስከ 50 አመት የሚዘልቅ ሲሆን (ዘኁ. 446-47 824-26) የዚህ እድሜ ስሌት ክህነታቸው የሚጀመርበትና የሚያከትምበት የዘመን ቁጥር መኖሩን ያሳየናል፡፡ክህነታቸው «ለዘላለም´ አልነበረም፡፡ መልከ ጼዴቅ ግን ክህነቱ የተወሰነ መጀመሪያና መጨረሻ ስለሌለው «ለዘላለም´ ተብሎለታል፡፡ ይህም ማለት ይህ ሰው በእድሜው ዘመን ሁሉ ካህን ሆኖ ኖሯል ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የሌዋዊያን ክህነት መጀመሪያና መጨረሻ የሚታወቅ ሲሆን የመልከ ጼዴቅ ክህነት ግን የሚጀምርበትና የሚጨርስበት ዘመን አልተቆጠረምና «ለዘላለም´ ካህን ሆኖ ይኖራል ተብሎለታል፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ለኢየሱስ ክህነት ምሳሌነት የሚያገለግለው የአሮን ክህነት ሳይሆን የመልከ ጼዴቅ ክህነት ነው፡፡ ለምን ቢሉ ኢየሱስ ከይሁዳ ነገድ እንጂ ሌዋዊ አይደለምና፡፡ ክህነቱም ቢሆን እንደ አሮን ልጆች በሞት የተገደበ ሳይሆን ዘላለማዊ ነውና፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የዕብራዊያን ጸሃፊ ሲናገር «...አንተ (ክርስቶስ) እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ…´ (ዕብ. 717) «እነርሱም (ካህናት) ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ (ኢየሱስ) ግን ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና…´ (ዕብ. 723-25) ይላል፡፡

 III. የሐዲስ ኪዳን ክህነት

በብሉይ ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች የራሳቸው የሆነ ትርጉም ነበራቸው፡፡ ይህ ትርጉም ደግሞ መሥዋዕቶቹ በራሳቸው ከሚኖራቸው ትርጉም በላቀ፣ ለሐዲስ ኪዳን ዘመን ያላቸው ፋይዳ ጉልህ ነበር፡፡ እነዚህ ጥላ ወይም ምሳሌ የሆኑት የመስዋዕት ሥርዓተቶች አካሉ የሆነውን የኢየሱስ ሥራ በማሥረዳትና በመግለጥ ረገድ ያላቸው ሚና አስደናቂ ከመሆኑ በተጨማሪ እግዚአብሔርን የሰውን ልጅ ለማዳን የሄደውን የጥበብ ጎዳና የሚዘክሩ ናቸው፡፡

እስቲ አሁን የእነዚህን ጥላዊ መሥዋዕቶች ትርጉም ከሐዲስ ኪዳን አካላዊ ፍጻሜ አንጻር በጥቂቱ እንመልከት፡፡በብሉይ ለመሥዋዕትነት ይቀርብ የነበረው እንስሳ ነውር የሌለበት መሆን ነበረበት (ዘሌ. 13 31)፡፡ የዚህ ጥላ ሥርዓት አካል የሆነው ኢየሱስም እንዲህ እንደነበረ ሐዋሪያው ጴጥሮስ ሲመሰክር - «... ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ፡፡´ ይላል (1ጴጥ. 118-19)፡፡ ሌላው ደግሞ በመሥዋዕቱ ሥርዓት ወቅት የሰው ኃጢአት ወደ መሥዋዕቱ መተላለፍ ነበረበት (ዘሌ. 14 1621)፡፡ ይህም የሰው ሁሉ ኃጢአት በክርስቶስ ላይ የመሆኑ ምሳሌ ነበር (ኢሳ. 536-12 1ጴጥ. 224 318 ዕብ. 928)፡፡ መሥዋዕቱ ኃጢአትን በመሸከምና በኃጢአት ምክንያት ለኃጢአተኛ ምትክ ሆኖ መሞት ነበረበት (ዘፍ. 227-8 ዘሌ. 1615)  የዚህ ምሳሌነቱ ደግሞ ክርስቶስ በኃጢአተኞች ምትክ መሞቱን ለማመላከት ነበር (ኢሳ. 535-6 ማር. 1045 ሮሜ 58 2ቆሮ. 521 ገላ. 313 ዕብ. 928 1ጴጥ. 318 1ዮሐ. 22 316)፡፡ የዚህ ነገር መጨረሻው የሰውየው መንጻት ነውና፣ ከመሥዋዕቱ የተነሳ የሰውየው ኃጢአት ይደመሰሰ ነበር (ዘሌ. 426 3135 1621-22 መዝ. 511-9 ኢሳ. 4422 ሕዝ. 3625)፡፡ ምሳሌነቱም በክርስቶስ ሞት ምክንያት የሰው በደል ተደመሰሰ የሚል ይሆናል (1ቆሮ. 611 ዕብ. 914 1ዮሐ. 17 ራዕ. 14-5 714)፡፡

በብሉይ ይቀርቡ በነበሩት የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት አሳብ መሰረት እንስሳት ሰውን ተክተው ይሞቱ ነበር፡፡ ይህም ማለት የሰውየውን ሞት እነርሱ ሞተው፣ መሞት የሚገባውን ሰው ከኃጢአት ቅጣት ፍርድ ማለትም ሞት ያስመልጡ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ አስደናቂ የመተካት ጽንሰ ሃሳብ የክርስቶስን ሥራ ለማስረዳት ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡ ሐዋሪያው ጴጥሮስ፣ ክርስቶስ በኃጢአታችን ምክንያት መሞት የሚገባን ሰዎች ምትክ ሆኖ ኃጢአታችንን በመስቀሉ ላይ እንደተሸከመልንና ከሚጠብቀን የሞት ፍርድ እንዳዳነን ሲገልጽ እንዲህ አለ፡- «እርሱ (ክርስቶስ) ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ´ (1ጴጥ. 224)፡፡

ክቡር ስለሆነው የኢየሱስ ደም፣ በሰው ልጆች መታረቅ ውስጥ ያለውን ሚና ስንመለከት ደግሞ ሁለት የብሉይ ኪዳን መሰረታዊ ጥቅሶች መቃኘት ይኖርብናል፡፡ እነዚህም «ደም ሳይፈስ ሥርየት የለም´ (922) የሚለውና «የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና´ (104) የሚሉ ናቸው፡፡  የመጀመሪያው ጥቅስ ያለ ምትክ፣ እርቅ አይገኝም፡፡ ያለ ምትክ ከእግዚአብሔር ቁጣ መሸፈን መከለል አይቻልም የሚለውን ለመናገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የብሉዩ መሥዋዕት የሐዲሱ ጥላ ወይም ምሳሌ እንደነበረ ያሳያል፡፡ በነገራችን ላይ ሥርየት ማለት መሸፈን ማለት እንደሆነ ልብ ይበሉ፡፡ እንግዲህ፣ የበደለ ሰው ነውና ምትኩም ሰው ሊሆን ግድ ነው፡፡ ይህም ሰው ደግሞ ነውር የሌለበት ሊሆን የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰው ደግሞ አምላክም ሰውም ከሆነው ከኢየሱስ በቀር ማን ሊሆን ይችላል?  ስለዚህ ለሰው ደኅንነት ዋጋ የሚኖረው ክቡር የሆነው የክርስቶስ ደም ብቻ ነው፡፡ (1ጴጥ. 118-19)፡፡ ያለ ነውር የሆነ ሰው በዚህ ምድር ላይ ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ ይህን የመተካት ሥራ መስራት ስለሚችል አምላክ ሰው መሆን ባላስፈለገው ነበር፡፡ ነገር ግን፣ በምድር ላይ በአዳም ዘር ውስጥ አንድ «ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ የለም፤…´ (ሮሜ. 311)፡፡ ከአዳም ውድቀት በኋላ በምድር ላይ ካለ የሰው ዘር ያለ ኃጢአት የተገኘ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡

ክርስቶስ ፋሲካችን ነው (1ቆሮ. 56-7)፡፡ 400 አመታት በላይ በግብጽ ባርነት ውስጥ የነበረው የእስራኤል ሕዝብ ከዚህ ባርነት ሲወጣ እግዚአብሔር የተጠቀበመት የመጨረሻው ተአምር በግብጽ አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኩርን ሁሉ መግደል ነበር (ዘፀ.1212)፡፡ «ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፣ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም፡፡´ (ዘፀ. 1223) «ደሙን ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤…´ (ዘፀ. 1213) ይህ ታሪክ ደኅንነት በምትክነት የሚገኝ ስለመሆኑ ጥሩ አስረጅ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ የዳኑት ሰዎች ምንም ምን ስለሆኑ ሳይሆን የበግ ደም በቤቶቻቸው ላይ ስለ እነሱ ስለታየላቸው ነው፡፡ ይህም ዛሬ ከእግዚአብሔር ቁጣ ሰዎች የሚድኑት የክርስቶስ ደም በእነርሱ ፈንታ በሕይወታቸው ላይ የታየላቸው ሰዎች ብቻ ስለመሆናቸው ግልጽ ምሳሌ ነው፡፡ የበጉ ደም በበር ላይ መረጨት ነበረበት፡፡ ደሙን እግዚአብሔር እንዲያየው አስፈላጊ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ደሙን ሲያይ ከእነርሱ ዘወር ይል ነበር፡፡ ይህ ትዕይንት የክርስቶስ ምሳሌው ስለሆነ (1ቆሮ. 56-7) ለሐዲስ ኪዳን ሕዝቦች ያለው ፋይዳ እንደምን ይገለጣል ከተባለ  ምላሹ ዛሬም ለመዳን የሚፈልግ ሰው ሁሉ በክርስቶስ ደም መሸፈን አለበት (1ጴጥ. 11-2 1ዮሐ. 17-9) የሚል ይሆናል፡፡

ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ክህነትና መሥዋዕት ፍጻሚ ነው፡፡ ይህም ለሐዋሪያቱ ምልጃን በማቅረብ (ሉቃስ 2231-32) ለደቀ መዛሙርት ሌላ አጽናኝ እንደሚሰጣቸው አብን እንደሚለምን ቃል በመግባት (ዮሐ. 1416) ከመያዙ በፊት በሰፊው ለተከታዮቹ በመጸለይ (ዮሐንስ 17) ተገልጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር «የመዓዛ ሽታ የሚሆን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ´ ራሱን አሳልፎ በመስጠት (ኤፌ. 52) በእግዚአብሔር ቀኝ ሆኖ ስለ እኛ በመማለድ (ሮሜ. 834) ጠበቃ በመሆን (1ዮሐ. 21) እና መካከለኛ በመሆን (1ጢሞ. 25) የመልከ ጼዴቅ ክህነት ፍጻሜ መሆኑን አሳይቷል፡፡ እርሱ በመስቀል ላይ ከፈጸመልን ሥራ የተነሳ አሁን ሁላችን በእርሱ ሥራ ወደ አብ «መግባት´ አግኝተናል (ኤፌ 218 312)፡፡ በሐዲስ ኪዳን አሳብ መሰረት ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን በመሆኑ፣ እኛ ምእመኖቹ ሁላ ደግሞ የእርሱ ካህናት (አገልጋዮች) ሆነናል (ራዕ. 15-6 1ጴጥ. 29)፡፡

IV. የተሳሳቱ አመለካከቶች፡-

IV.1 አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ያደረገውን ይህን የክርስቶስ የአማላጅነት አገልግሎት ትምህርት ለመቀበል ለምን ተቸገሩ?

መልካምም ይሁን ጎጂ፣ የሰው ልጅ አንዴ የያዘውን አስተሳሰቡን፣ ልማዱንና ወጉን መተው ይቸገራል፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች በአንድ ለሊት የተገነቡ ስላልሆኑ፣ በአንድ ለሊት ሊፈርሱ አይችሉም፡፡ ነጮች አሮጌ ልማዶችን የመሻር አስቸጋሪነትን «Old habits die hard!´ በማለት ይገልጻሉ፡፡ ትርጓሜውም አሮጌ ልማዶች በቀላሉ አይሞቱም እንደማለት ነው፡፡ አንዴ ለዘላለም የሆነው የክርስቶስ ምልጃ፣ ምንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በአገራችን የእምነት ትውፊቶች በግልጽ የተነገረ ሥራ ቢሆንም በእኛ አገር ክርስትና አሁንም ድረስ በቀላል ቁጥር በማይገመቱ ምእመናን ዘንድ በከፊል ተቀባይነት ለማግኝት አልቻለም፤ ወይም ግልጽ አይደለም፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ስለ ጉዳዩ ለማሰብ፣ መጽሐፍ ቅዱስን አስረጅ አድርጎ ከማቅረብ ይልቅ ለሰው አመክንዮ (logic) እና ልማድ ትልቅ ሥፍራ መስጠት እንደሆነ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያምናል፡፡ ለምሳሌ «እንዴት አምላክ የሆነው ኢየሱስ ያማልዳል?´ «ምልጃ የፍጡራን ሥራ መሆን አለበት!»´ «ከማለደልንም፣ ክርስቶስ ሊማልድልን የሚችለው በምድር ላይ ሳለ ብቻ መሆን አለበት!»´ የሚሉቱ አመክንዮዎች ለፍጥረታዊ ሰው አስተሳሰብ ተቀባይነት ለማግኘት ቀሊሎች መስለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ መታሰብ ያለበት ትልቅ ቁም ነገር ግን፣ የትኛውም ውብ ተፈጥሮአዊ መነሻ አሳቦች ወደ ትክክለኛ መንፈሳዊ/መለኮታዊ /ማጠቃለያ ላይ እንደማያደርሱን ሊታወቅ ይገባል፡፡ እንዲያውም ብዙዎቹ የእግዚአብሔር ሥራዎች -መዳናችንን ጨምሮ- ለእኛ ፍጥረታዊ አመክንዮ ግራና ሊቀበሏቸው የሚያስቸግሩ ናቸው (1ቆሮ. 118-21)፡፡ ለዚህ ነው የእግዚአብሔርን ነገር መረዳት ለፍጥረታዊ ሰው ሞኝነት የሚሆንበት፡፡ «ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም´ (1ቆሮ. 214)፡፡ ስለዚህ በመንፈስ የሚመረመረውን የእግዚአብሔርን አሳብ በራሱ ቃል መሰረት ለማረጋገጥ ከማጥናት ውጪ ከራሳችን አመክንዮና ሐይማኖታዊ ቅናቶች በመነሳት ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የምናደርገው ማንኛውም ጥረት ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የሰማሁትን አንድ የእምነት ንግግር ላካፍላችሁና ይህን ሃሳብ ልቋጭ፡፡ አንድ የእግዚአብሔርን መኖር የማያምን ሰው አንዱን አማኝ እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፡- «እንዴት ዮናስ በታላቅ ዓሳ ሆድ ውስጥ 3 ቀንና ለሊት ቆየ ብለህ ማመን ትችላለህ፤ ይህ ከሣይንስ ጽንሰ ሃሳቦች አኳያስ እንዴት ያስኬዳል? ብሎ ቢጠይቀው፣ «ወዳጄ አንተ የቸገረህ ይህን ማመን ቢሆንም  እንኳን ዮናስ በዓሳ አንበሪው ሆድ ውስጥ ማደር ይቅርና፤ ዓሣ አንበሪው ራሱ በዮናስ ሆድ ውስጥ ለ3 ቀናት አደረ የሚል ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ ባገኘው ለማመን አልቸገርም»´ አለውና ውይይቱ በዚያው ተጠናቀቀ፡፡ የቱንም ያህል ለአእምሮአችንና ልማዶቻችን ይክበደው እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ግልጽ አሳቦች በመቃወም የራሳችንን የስሜት ሃሳብ ልናምን አይገባም፡፡      «ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል» ዕብ 7፤25 የሚለውን ግልጽ ቃል ያልተቀበለ «ዓሳ አንበሪ በዮናስ ሆድ ውስጥ አደረ» የሚል አስገራሚ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢያገኝ በእርግጥም አይቀበልም።

IV .2 የክርስቶስ የምልጃ አገልግሎት ከአብና መንፈስ ቅዱስ እንዲያንስ ያደርገዋልን?

ኢየሱስ ይህን የምልጃ ሥራ በመስራቱ ከአባቱም ሆነ ከመንፈስ ቅዱስ አያንስም፡፡ ለነገሩ፣ በግብር ላይ ተመስርተን የተግባሩን ባለቤት ክብር ወይም ሥልጣን መመዘንና ደረጃ ማውጣት የሰው ሥርዓት ስለ ሆነ ይህንን እርኩሰት የተሞላበትን ባህላችንንና አስተሳሰባችንን ለፈጣሪ ፍጹም ሥራ ምዘና ስናውለው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን መዘንጋት የለብንም፡፡ በዚህም ምክንያት ነው እግዚአብሔር ወልድ ያለማንም አስገዳጅነት በፈቃዱ በፈጸመው የምልጃ ሥራየተነሳ ወልድ፤ ከአባቱ እና ከመንፈስ ቅዱስ እንደሚያንስ እንድናስብ የምንገደደው፡፡ እንግዲያው ሥላሴ በስልጣን፣ በገዢነት፣ በአምላክነት፣ ወዘተ አንድ ሲሆኑ በግብር ግን እንደሚለያዩ ያስቀመጥነው የቤተክርስቲያኒቱ  የእምነት አቋም ፋይዳው ምኑ ላይ ነው?  በግብር አንጻር፡- አብ በመውለዱ፣ ወልድ ደግሞ በመወለዱ ምክንያት አብ ወላጅ ስለሆነ የሚበልጥ፣ ወልድ ደግሞ ልጅ ስለሆነ የሚያንስ እንዳልሆነ መቀበል ካልከበደን፣ ለምን በመስቀሉ ሥራ ላይ በግብር፡- አብ ተማላጅ ወልድ ደግሞ ማላጅ መሆኑን መቀበል ከበደን? ዛሬስ ወልድ የአብ ልጅ መሆኑን እናምናለን? ወይስ ልጅ መባሉ ከመስቀሉ በኋላ አብቅቷል? እንላለን። ልጅ የመባሉ ምስጢር ለአባቱ  የመታዘዙ ነገር ነው ካልን፤ የወልድን ማነስ እያመንን ነው ማለት ነው? ይህ አደገኛ ስህተት ነው። አብ ተማላጅ፤ ወልድ ማላጅ ነው ሲባል የአባትና የልጅነት ግብርን መናገራችን እንጂ የመለኮታዊ ዕሪና /እኩልነት/  ሚዛን እየሰፈርን አለመሆኑን ለመገንዘብ አለመቻል አስቸጋሪ ነገር ነው።
ኢየሱስ በመለኮቱ (በአምላክነቱ) ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ስለመሆኑ የሚናገሩ በርካታ ጥቅሶች ቢኖሩም ለአብነት የሚከተሉትን ይመልከቱ፡- «… ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ፡- እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፣ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉትይፈልጉ ነበር´ (ዮሐ. 518)፡፡ «እኔና አብ አንድ ነን´ (ዮሐ. 1030)፡፡ «… እኔን ያየ አብን አይቷል´ (ዮሐ. 149)፡፡ «ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው´ (ዮሐ. 1615)፡፡ «በመጀመሪያ ቃል ነበር፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፣ ቃልም እግዚአብሔር ነበር´ (ዮሐ. 11)፡፡ «… እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው´ (1ዮሐ. 520)፡፡

ኢየሱስ እንደ አምላክነቱ ጸሎትን የሚሰማ ተማላጅ አምላክ ቢሆንም እንደ ሰውነቱ በግብሩ (ሊቀ ካህንነቱ) ደግሞ ሥለ እኛ በሰማያዊት መቅደስ ያለ ብቸኛ አማላጅ/አስታራቂ/መካከለኛ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ያለው የኢየሱስ ምልጃ በምድር ላይ ከነበረበቱ ልዩ የሚሆነው ምልጃው  በተፈጸመ ሥራው ስለ እኛ በአብ ዘንድ አንዴ የቀረበ ብቻ መሆኑ ነው (ዕብ. 92428)፡፡ ስለዚህ እኛም በምስጋናም በልመናም ሆነ በምልጃ ወደ እግዚአብሔር በኢየሱስ በኩል ስንቀርብ ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱ ከአባቱ ጋር ጸሎታችንን የሚሰማና የሚቀበል ሲሆን በትስብእቱ ደግሞ ከእኛ ጋር ሆኖ ጸሎታችን ተሰሚነት እንዲኖረው በአባቱ ፊት ስለ እኛ ብቁ ሆኖ የሚታይ አማላጅ እንደሆነ ኅሊናችን ሊቀበለው ይገባል፡፡ ደም ሳይፈስ ስርየት እስከሌለ ድረስ ሃይማኖት የሌለው ሰው ወደክርስትና በእምነት ቢመጣ የሚታረቀው በማን ደም ነው? በአብ ዘንድ ተቀባይነት ባገኘው በእርቁ ደም በክርስቶስ በኩል ብቻ ነው።

IV.3 ክርስቶስ ያማለደው በሥጋው ወራት (በምድር ሳለ) ነው፡፡

ኢየሱስ በምድር ላይ በሰነበተበት 3አመት ተኩል ጊዚያት፣ በተለያየ ሁኔታ የምልጃ ሥራን ሰርቷል፡- ሉቃስ 2231-32 ዮሐ 1721 ሉቃስ 2334 ዕብ. 57 - ነገር ግን አሁን በአባቱ ቀኝ በተቀመጠበት ጊዜ ይህ ቆሟል የሚሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ አስተያየት የክርስቶስን የክህነት ባሕሪ ጠንቅቆ ካለመረዳት ወይም ከባዶ ቅንዓት የሚመነጭ ነው የሚሆነው፡፡ የክርስቶስ ክህነት እንደ አሮን ሞት የሚከለክለውና የሚቋረጥ አይደለም (ዕብ. 717)፡፡ ሞት ያላስቀረው ሊቀ ካህናችን ስለ ሆነ ስለ እኛ «...ሲያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል፡ ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል´ (ዕብ. 725)፡፡ የኢሱስ ክህነት/ምልጃ ዘላለማዊና የማይለወጥ ክህነት/ምልጃ ነው «… እርሱ (ኢየሱስ) ግን የማይለወጥ ክህነት አለው፤…´፡፡ «... የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሳው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡´ (ሮሜ. 834) ይህ ጥቅስ የክርስቶስ ምልጃ/ክህነት በመሞቱ ምክኒያት ያልተቋረጠ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ ይህ ክህነት በምድር ላይ እያለ ብቻ ሳይሆን ከትንሳኤው በኋላ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦም ሳለ አብሮት ያለ የዘላለም ሹመት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ «አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ´ (ዕብ. 56) ያለውን ትንቢት መዘንጋት የለብንም፡፡

«ልጆቼ ሆይ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህንን እጽፍላችኋለሁ፤ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ክርስቶስ ነው፡፡´ (1ዮሐ. 21) የሚለው ጥቅስ የኢየሱስን የጥብቅና ማዕረግ በጉልህ ያሳያል፡፡ ይህም ጥብቅና ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ሰዓት ብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብም ሆነ የኃጢአት ይቅርታን ለመቀበል ትምክህት ሊሆነን የሚችል ጠበቃ ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ የበስረናል፡፡ ጠበቃ አለን እንጂ ጠበቃ ነበረን አለማለቱን አንባቢ ልብ ይበል፡፡

«እርሱ (ክርስቶስ) … ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ …´ (ዕብ. 1012) ስለ ተቀመጠ ምልጃውም አንዴ ለዘለዓለም የቀረበ የምልጃ/የክህነት ሥራ ስለሆነ ክርስቶስ ዛሬ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት እንደነበረው ሥርዓትና እንደ አሮን ክህነት በየአመቱ ወደ ቅድስት መስዋዕት ይዞ መግባት አያስፈልገውም (ዕብ. 925)፡፡ በእግዚአብሔር ቀኝ ሆኖ ስለ እኛ ይማልዳል ማለት በመስቀል ላይ የፈጸመውን ሥራ ይደጋግማል ማለት ሳይሆን በኢየሱስ በኩል ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ እርሱ ስለ እኛ ይታያል ማለት ነው እንጂ፡፡ «ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ» ዕብ 9፤24

IV.4 ኢየሱስ ካረገ በኋላም እንደሚማልድ የትውፊት መጽሐፍት ይናገራሉ፡-

«ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የእኔ ስለ ሆኑት ምህረትን ወደ ምለምንበት ወደ ሰማይ ወደ አባቴ አርጋለሁ አላቸው፡፡´ (መጽሐፈ ዚቅ ዘሰኔ ሚካኤል፣ ገጽ 189)

አብ ሆይ ስለ ኢየሱስ እርዳን፤ ክርስቶስ ወደ ቸር አባትህ አማጽነን/አማልደን የአብና የወለድ መንፈስ አጽናናን (ሰዓታት ዘሌሊት ወዘንግህ፣ ገጽ 222)

IV.5 መዳናችንን/መጽደቃችንን/መታረቃችንን ከዚህ የክርስቶስ ሥራ በተለየ መንገድ የምናገኘው ነው ወይ?

መዳናችንን/መጽደቃችንን/መታረቃችንን ከዚህ የክርስቶስ ሥራ በተለየ መንገድ እንደምናገኝ ማሰብ ወይም ለማግኘት መሞከር የእግዚአብሔርን የማዳን መንገድ ለማሻሻል ከመሞከር ሌላ የተለየ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ ጽድቅ በሕግ በኩል ከሆነ፣ መዳን በሰው ምልጃ በኩል የሚገኝ ከሆነ፣ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ሌላ የተሻለ መንገድ ካለ፣ እንግዲያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ (ገላ. 221)፡፡

IV.6 እኔ ኃጢአተኛ ስለ ሆንኩ በእግዚአብሔር ፊት ልቀርብ አልችልም፤ ስለዚህ መካከለኛ ሰዎች ያስፈልጉኛል?

ከአዳም ውድቀት በኋላ፣ ሰውን ከሰው ሳይለይ ሁሉ (ሮሜ. 39-11) በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ አይችልም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ጻድቅ ስለ ሆነ እርሱ ፊት ሊቀርብ የሚችለው ልክ እንደርሱ ቅዱስ የሆነ ሰው ብቻ ነው፡፡(ማቴ. 548)፡፡  «እንግዲያስ ከሰው ዘር እንደ እርሱ ቅዱስ የሆነ ማን ሊገኝ ይችላል? የሚል ጥያቄ ያነሱ ይሆናል፡፡ መልሱ በእርግጥ ተችሏል የሚል ነው! ይህም ሰው ኢየሱስ ይባላል፡፡ «እኛ በእርሱ ሆነን (በክርስቶስ ሆነን) የእግዚአብሔር ጻድቅ እንባል ዘንድ ኀጢአት ያላወቀውን እርሱን (ክርስቶስን) ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው» (2ቆሮ. 521)፡፡ ይህ አስደናቂ የልውውጥ ሥራ ኃጢአተኞቹን እኛን ጻድቅ፣ ጻድቁን ጌታ ደግሞ ኃጥእ ያሰኘ መለኮታዊ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ሥራ አማካኝነት (በእርሱ በኩል) ሁላችን እንደ ጻድቅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ድፍረት አግኝተናል (ዕብ. 1019-20 ኤፌ. 213 216)፡፡ እንግዲህ ከአዳም ዘር የሆንን ሁላችን ማንንም ከማንም ሳይለይ ኃጢአተኞችና በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ የማንችል ብንሆንም በክርስቶስ በተደረገልን ቤዛነት፣ በእርሱ ፍጹም ሥራ በኩል ወደ እግዚአብሔር መቅረብም ሆነ መጸለይ እንችላለን፡፡ ወደ እግዚአብሔር የመቅረቢያ ድፍረታችን የለበስነው የኢየሱስ ጽድቅ እንጂ የእኛ መልካም ነገር አይደለም፡፡ በራሴ መልካም ሥራ በኩል ወይም ከእኔ በተሻሉ በምላቸው ሌሎች ሰዎች በኩል ወደ እግዚአብሔር መድረስ እችላለሁ የምትል ነፍስ ራሷን ከቅዱሱ ኢየሱስ ጋር እያወዳደረች መሆኗን ልትገነዘብና ንስሀ ልትገባ ይገባታል፡፡ ስለዚህ ከእርሱ ሌላ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብባቸው ሌሎች መካከለኞች፣ ሌሎች አማላጆች ፈጽሞ የሉንም፡፡ ወደእግዚአብሔር የምንደርስበት ሌላ መንገድ ራሱ ክርስቶስ በወንጌል ነግሮን ሳለ እኛ ግን ሌሎች ሰዎች ያደርሱናል ማለት  ክርስቶስን ተሳስተሃል ማለት ይሆናል። «ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም» ዮሐ14፤6

IV.7 ልክ እንደ ብሉይ ኪዳን በሐዲስ ኪዳንም ለክህነት የተመረጡ ጥቂት ግለሰቦች አሉ?

በሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንን የመምራት፣ የማስተዳደርና ምእመኑን የመመገብ ኃላፊነት የተሰጣቸው አማኞች ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት፣ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ዲያቆናት (ሐዋ. 2028 1423 ፊሊ. 11) ተብለው ስያሜን ከማግኘት ውጪ ከምእመናን በተለየ መልኩ ካህን ወይም ሊቀ ካህን የሚል ሹመት አልተሰጣቸውም፡፡ ይህንን የሚያሳይ አንድም ገጽ የለም። መጽሐፉ እንደሚል የሐዲስ ኪዳን ብቸኛ ሊቀ ካህን ኢየሱስ ብቻ ሲሆን (ዕብ. 217 96-11) በእርሱ ያመኑ ምእመናን ሁሉ ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ የትምህርት ደረጃ ሳይለይ የእርሱ ካህናት ተብለዋል (1ጴጥ. 25-9 ራዕ. 510)፡፡  አሁንም የብሉይ ኪዳን ክህነት አለ ብለው የሚያስቡ ካሉ እንግዳው ይህም ክህነት ቢሆን ለአሮን ቤተሰብ ብቻ የተሰጠ መሆኑን ማስታወስ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለ ክህነት እግዚአብሔር የማያውቀው ክህነት አይደለም፡፡ ቃሉ የሚናገረውን አለመበቀል መብት ቢሆንም የሰዎች አለመቀበል ግን የወንጌልን ቃል እውነተኛነት አይቀይረውም። «እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ» 1ኛ ጴጥ 2፤5
ሊቀ ካህናት ክርስቶስ ኢየሱስ በመሐላ የተሾመ ዘላለማዊ ሊቀካህን ነው ካልን ሌላ በመሃላ የሚሾም፤ ዘላለማዊ ሊቀ ካህን ከየት ይመጣል?

V. ማጠቃለያና የንስሃ ጥሪ፡-

ወዳጆቼ ሆይ የኢየሱስ መካከለኛነት አንድ ሰው ለሌላው ሰው ጸሎት የማድረስ አገልግሎት አይነት ብቻ ነውን? «ፈጽሞ! ምልጃ ስለ ሌላው ሰው መሞትንም የሚያጠቃልል ነው እንጂ´ የሚሉኝ ከሆነ እንግዲያው ከኢየሱስ ውጪ ስለ ሰው የሞተ ማን ነው? ስለ ምልጃ ስናወራ ምሉእ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ መሥዋዕት መሆን፣ መጸለይና ምትክ መሆን እያወራን መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ከዚህ ምሉእ አገልግሎት ውስጥ ስለ ሌሎች መጸለይ የምትለዋን ብቻ በማውጣት ምልጃን ለመተርጎም ስለሚሞክሩ የተሳሳተ ማጠቃለያ ላይ ይደርሳሉ፡፡
የጸሎት ምልጃን በተመለከተ ማንም ሰው ለማንም መጸለይ ይችላል (ያዕ. 514 ቆላ. 42-4 12)፡፡ እርግጥ ነው እግዚአብሔር የሚፈሩትን ሰዎች ጸሎት ይሰማል ፡፡ ይህ ማለት ግን የእግዚአብሔር ጆሮዎች መቁጠር ለምንችላቸውና  እኛ ለምናውቃቸው ቅዱሳን ብቻ የተከፈተ ነው ማለት አይደለም፡፡ ማናችንም ብንሆን እግዚአብሔርን በመውደድና በእምነት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጸሎታችንን በኢየሱስ ስም ብንጸልይ እግዚአብሔር የሁላችንን ጸሎት ያለ ልዩነት ይሰማል፡፡ የማናችንም ሥራ በእርሱ ፊት ብቃትን ሊሰጠን አይችልም። ከክርስቶስ ውጪ ስንታይ እንኳን ዐመጻችን ጽድቃችንም ቢሆን የመርገም ጨርቅ ነው፡፡ እንግዲያውስ ሁላችንም፣ ገና ዛሬ እግዚአብሔርን ያወቀ አዲስ ክርስቲያን ቢሆን፣ የሰነበተ ዲያቆን፣ ጀማሪ ቄስ ይሁን፣ የበቃ ጳጳስ፣ የአንድ አመት መጋቢ ይሁን የቆየ ሽማግሌ፣በእግዚአብሔር ፊት ለመጸለይና ወደ ፊቱ ለመቅረብ የምንችለው በክርስቶስ ሥራ ብቻ ነው፡፡
ይህን ለራሳችንም ሆነ ለሌላ ሰው የምናደርሰው ጸሎት፣ ጸሎትን ወደ ሚሰማና ወደ ሚመልስ እግዚአብሔር ሊደርስ የሚችለው በአንድ መንገድ ብቻ ነው (ዮሐ. 146)፡፡ ሊሎች አማራጮች የሉንም፤ አያስፈልጉንምም፡፡ ይህም መንገድ ኢየሱስ ነው፡፡ በስሙ (በኢየሱስ ሰም) የምንለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰማና እንደሚመልስ ተጽፏል (ዮሐ. 1413-14 1623-24)፡፡
«እኔም እላችኋለሁ። ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።
የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል» ሉቃ 11፤9-10
ይህ ሁኔታ በአገራችን የትውፊት መዛግብት ላይ ሳይቀር እንግዳ አለመሆኑን ከድርሳነ ማኅየዊ የተወሰደውን የሚከተለውን ክፍል ይመልከቱ «አቤቱ ጌታችን ተቀዳሚ ተከታይ ስለ ሌለው ስለ ልጅህ ስለ ወዳጅህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አማኑኤል ብለህ ይቅርታህን ከእኛ አታርቅ፤ መሀላህንም አታፍርስ´ (ድርሳነ ማኅየዊ፣ ምዕራፍ 1 ቁጥር 13 ገጽ 5)፡፡
በመጨረሻም፣ በዚህ ጽሁፍ የቀረቡትን አሳቦች በመጠቅለል መቋጫ እናበጅና እንለያይ፡፡ የሰው ዘር ከውድቀት በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ መቅረብ ባለመቻሉ፣ ክርስቶስ ለዚህ ተስፋ ቢስ የሰው ዘር ወኪል በመሆንና በመታዘዝ ጻድቅ ሕይወቱን በሰው ልጅ ፈንታ ለእግዚአብሔር አቀረበ፡፡ የሰው ልጅ ሊሸከማት ያልቻለውን የኃጢአት ቅጣት በእርሱ ፈንታ በመሸከም የኃጢአት ስርየትን አስገኘለት፡፡ ከዚህም የተነሳ ሰው በእግዚአብሔር ፊት እንደ ጻድቅ ተቆጠረ፤ ክርስቶስ ግን እንደ ኃጢአተኛ ተቆጠረ፡፡ ሐዋሪያው ይህን ታላቅና አስደናቂ ልውውጥ «እኛ በእርሱ (በክርስቶስ) ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን (ክርስቶስን) ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው´ በማለት ገልጦታል (2ቆሮ. 521)፡፡ በአንድ በኩል ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር እርቅና ሰላም የሚኖረው ክርስቶስ በእርሱ ስፍራ የሕግን ቅጣትና እርግማን በመሸከሙ ሲሆን (ገላ. 313) በሌላ በኩል ደግሞ በክርስቶስ ጽድቅ ውስጥ በመቆሙ ነው (1ቆሮ. 130-31)፡፡ አንዳንዶች የክርስቶስን የማዳን ስራ ለመሸርሸር ሲፈልጉ ቶሎ ብለው ቅዱሳን ተብለው ከሚጠሩ ሰዎች ማንነት ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራሉ። ሰዎች የክርስቶስን ምትክ አልባነት ሲነግሯቸው ቅዱሳንን በክርስቶስ ቦታ በመተካት የመዳን ሊቀ ካህናት እንደሆኑ ለመስበክ ይፈልጋሉ። ቅዱሳን በማስተማር፤ በመስበክ፤ በመምከርና  በመገሰጽ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ፈለጋቸው ወደ እምነታችን ጥንካሬ ሊያመጣን ካልሆነ በስተቀር የክርስቶስን የማዳን ሥራ ሊተኩ አይችሉም። ይህንን የሚልም ማንም ቅዱስ የለም።
ቅዱስ ጳውሎስ ከመሰከረው እውነት ውጪ የሚናገር ማን ይሆን? እኛ ወይስ ቅዱሳኖቹ?  ቅዱስ ሰው የወንጌል አገልግሎቱ ሰው ሁሉ በክርስቶስ ፍጹም እንዲሆን እየገሰጸ፤ እያስተማረ፤ በጥበብ እየሰበከ የሚያቀርብ ማለት እንጂ ራሱ አዳኝ የሆነ ማለት አይደለም።
«እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው» ቆላስ 1፤28
እናም የክርስቶስ ሞት የእኛ ምትክ መሆኑ የሚያስገነዝበን ነገር ቢኖር እርሱ በእኛ ምትክ መሞቱን፣ የእኛን ህማም መታመሙን፣ የእኛን በደል መሸከሙን (ኢሳይያስ 53) ነው፡፡ ኢየሱስ ስለ እኛ ቆሰለ፣ ስለ እኛ ተዋደረ የማይገባውን ያውም የመስቀል ሞት ለመሞት የታዘዘ ሆነ (ፊሊ. 28)፡፡ ጤነኛ የሆነ አእምሮ ሁሉ የህን ካነበበ በኋላ «ግን ለምንብሎ ሊጠይቅ ይገባዋል፡፡ መልሱም ሊያድነን፣ ከፈጣሪያችን ጋር ሊያስታርቀን፣ ቅዱስ ሕዝብ ሊያደርገን፣ ቀድሞ ወደ ነበርንበቱ ክብር መልሶ ሊያመጣን የሚል ይሆናል፡፡ ይህ የመዳን መንገድ ብቸኛው የመዳን መንገድ ነው (ዮሐ. 14 6) ከዚህ የተሻለ የመዳን መንገድ ለመፈለግ ማሰብም ሆነ ማድረግ ከእግዚአብሔር ይልቅ ጥበበኛ ነኝ ከሚል ትእቢተኛ ልብ የሚመነጭ ከመሆኑ ባሻገር የኢየሱስን ሞት ከንቱ ማድረግ ይሆናል (ገላ. 221) ደሙንም ማክፋፋት ይሆናል ፡፡
ኢየሱስ ይህን ሁሉ ከፈጸመልኝ የእኔ ድርሻ  ምንድር ነው? አንተን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ የሚቀር ሌላ መሥዋዕት እንደሌለ እወቅ፣ የኢየሱስ መሥዋዕት ፍጹም፣ ንጹህ፣ ቅዱስ፣ በቂ በመሆኑ አንተን ለማዳን የሚችል እንደሆነ እመን፡፡ ይህንን የማዳን መንገድ ሙሉ ለማድረግ ከእምነት ውጪ ከአንተ ምንም እንደማይጠበቅ እመን፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም ነገር ለማድረግ በምትንቀሳቀስበት ቅጽበት የኢየሱስ የመስቀል ሥራ ጎዶሎና ያለእኔ እርዳታ በራሱ ሊቆም የማይችል ደካማ ሥራ ነው እያልክ እንደሆነ አትዘንጋ፡፡ «ለመዳን (ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ) ከማመን ውጪ ከኔ የሚጠበቅ እኔ የማዋጣው ነገር የለም ነው የምትለኝየሚሉኝ ከሆነ፣ እኔ ደግሞ በተራዬ አንድ ጥያቄ እንድጠይቅዎ ይፍቀዱልኝ፡- «ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ እርስዎ ሊያደርጉት የሚችሉት አንዳች ነገር ቢኖር ኖሮ እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ለዚህ ሥቃይ አሳልፎ የሚሰጠው ይምስልዎታል?
እኔ ግን እላለሁ፤ እመን ትድናለህ? ከዳንክ ደግሞ ተመልሰህ እነበርክበት እንዳትገባ እምነትህን በስራ አሳይ! ክርስቲያናዊ ሕይወት ማለት ያ ነው።
ጸሎት መጸለይ፣ ጦም መጦም፣ ችግረኛ መርዳት፣ በቅድስና ለመኖር ራስን መግዛትና የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ ከአምላኩ ጋር ከተታረቀና የዘላለም ሕይወት እንዳለው ከሚያምን አማኝ ሁሉ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እያንዳንዱ ሰው ሽልማት የሚቀበልበት መመዘኛዎች ናቸውና የሚናቁ ነገሮች አይደሉም (ራዕ. 2212)፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ነገሮች ለድኅነት በአንድ ላይ ተከምረው እንደተራራ ቢከመሩ ክርስቶስ ለእርስዎ ካደረገልዎ የመስቀል ሥራ አንጻር የኢምንት መጠን እንኳ ዋጋ የሚቸራቸው አይደሉም፤ ፈጽሞም ከእግዚአብሔር ጋር ሊያስታርቁ አይችሉም፡፡ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከእርስዎ ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡


ዋቢ መጻሕፍት
የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ፣ .
የአዲስ ኪዳን መካከለኛ
ሃይማኖተ አበው
ትምሕርተ ክርስቶስ፣ በቄስ ኮሊን ማንስል