እግዚአብሔር ይወድሃል! በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ
እያለህ መግቦቱን ያልከለከለህ ስለሚወድህ ብቻ ነው። ሰዎች በኃጢአት ውስጥ ስንኳ እያለን ዝም የሚለን በሕይወት እንድንኖር ጊዜ
የመስጠት ፍቅሩ ነው። ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም። ወይኑ የሚያፈራው
መራራ መሆኑን እያወቀ እንኳን ወይኑን ቶሎ አይነቅለውም። ወይኑን ይንከባከባል። ጣፋጭ ፍሬ እንዲያፈራ ይጠብቀዋል። ነገር ግን ወይኑ
በተደረገለትና በተሰጠው ነገር ሁሉ ፍሬያማ መሆን ካልቻለ «ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር
ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ?» ብሎ የወይኑ ባለቤት መራራውን ወይን ይነቅለዋል። የመራራው
ወይን መጨረሻም እጣ ፈንታ መራራ ይሆናል።
እናም ወንድሜ ሆይ! መግቦቱን፤ ፍቅሩንና ትእግስቱን እንድናውቅለት እግዚአብሔር
ይፈልጋል። በፍቅርና በምሕረት እንጂ በኃይልና በማስገደድ የሚገዛን እንዳልሆነም እንድንረዳ ይሻል። «በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት
ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ ድርቆሽም ጣልሁላቸው» እንዳለው የሚስበን በፍቅሩ እስራት፤ ከሸክምም ነጻ በማውጣት፤ መግቦቱን በፍቅር እንጂ
በማስገደድ አይደለም። ሆሴዕ 11፤4
ወንድሜ ሆይ፤ በሰውነታችን የወይን ተክል፤ መንፈስ
ቅዱስን ብናስመርረው ከበረሃ ላይ ወድቀው እንደቀሩት ዐመጸኞች፤ የዐመጻ ዋጋችንን መቀበላችን አይቀርም። ዐመጽን እንድንጸየፍ፤ ጽድቅን እንድንወድቅ አማራጭ የለው ምርጫችን ነው።
ዐመጽን ጠላሁ፤ ጽድቅንም ወደድሁ ብሎን የለ! ዐመጽን ልንጠላ፤ ጽድቅንም ልንወድ ይገባል።
ጥያቄው መቼ? የሚል ይሆናል። መልሱንም በቃሉ ይናገራል። «የመዳን ቀን አሁን ነው» ያለው ሐዋርያው ለመዳን ፈልገው፤ ጩኸታቸውን ለማሰማት
ለተነሱ የመራራ ነፍስ ባለቤቶች ሁሉ ነው። «በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን
ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው» 2ኛ ቆሮ 2፤6
ከዐመጻ ለመውጣት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደው
ሰዓት፤ ኃጢአትን ለመተው ውሳኔ ባሳለፍንበት ቅጽበት ነው። በዚያም በመዳን ቀን ረዳሁህ የሚል አስተማማኝ ኃይል ይሰጠናል። ሰዓቱም
አሁንና አሁን ብቻ ነው።
ምናልባት ተዘጋጅተንበትና ጊዜ ሰጥተን ሁኔዎችን
ካመቻቸን በኋላ ቢሆንስ? የሚል አስተሳሰብ ሊኖር ይችላል። ይሁን
እንጂ «ቀን የሚያመጣውን ምን እንደ ሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ» እንደተባለው ነገ የእኛ ቀን ስለመሆኑ ቀናቶቹን በእጃችን
የያዝናቸው ስላይደለ በሌለን ነገር ላይ ተስፋ እናደርግ ዘንድ የተገባ አይደለም። የእኛ ቀንና የተሰጠን ተስፋ አሁን ያለንባት የሕይወት
ጊዜ ብቻ ናት። እሷም ብትሆን «ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁና» ያዕ 4፤14 ተብሎ ስለተጻፈ እንኳን ለነገው ቀን ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሕይወታችን ላይ ለሚመጣው
ነገር የምናውቀው ምንም የለም። እናም መራራው ወይናችን የሚነቀለው ቀን ከመድረሱ በፊት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሳለን ለመገበን
አምላክ ጣፋጭ ለመሆን አሁኑኑ እንሠራ!! «እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን
ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ
መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ»
ከኃጢአት በመውጣት መንፈሳዊ ቤት ለመሆን የምንሠራው
በቁርጠኝነት እንጂ በጠባይ፤ በቀጠሮና በመለሳለስ አይደለም። ያልጀገነ ተዋጊ ጠላቱን ሊያሸንፍ እንደማይችል ሁሉ ጠላትም ድል ለማድረግና
በኃጢአት ምርኰ ይዞ ለማቆየት አይለሳለስምና ኃጢአትን በመተውና በመዳን መካከል ድርድር የለም። ጠላታችን በጀግንነት ካልተዋጋነው
በስተቀር ካለማመደን ኃጢአት ውስጥ በነጻና በፍላጎት አያሰናብተንም። ጠላት ምን ጊዜም ጠላት ነው። እናም ውጊያችን መራራና ጠንካራ
መሆኑን አውቀን መግጠም ይገባናል። በእኛና በጠላታችን መካከል ያለው ልዩነት ጠላታችን ውሱን ማንነት ያለው፤ ከኃይል በቀር ሥልጣኑን
የተቀማ ሲሆን በእኛ ዘንድ ያለው ሰይፍ ግን ሁሉን በእጁ የያዘ የፈጣሪ
ኃይል፤ የሁሉ ገዢና አስገኚ፤ የዘላለማዊ ሥልጣን ባለቤት በመሆኑ የውጊያው አሸናፊነታችን በምክንያትና በሁኔታ ላይ ያልተወሰነ፤
እርግጠኛና አስተማማኝ ነው። ግን ይህንን ኃይል እንዴት መታጠቅ እንደምንችል፤ መቼ መታጠቅ እንዲገባንና እንዴት መጠቀም እንዳለብን
ብዙዎቻችን እውቀቱ የለንም። ይህ አስተማማኝ አሸናፊነት እያለው የሰው ልጅ ሁሉ በኃጢአት የሚሸነፈው ታዲያ ለምንድነው?
እንደ ጳውሎስ ቁርጠኛና አሁኑኑ ወደውጊያው ለመግባት
የሚወስን ጀግና መሆን ባለመቻሉ የሰው ልጅ ለሚሸነፍለት ኃጢአት ተሸንፎ ይኖራል። ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ቀንቶ ክርስቲያኖችን ለማሳደድና
ወኅኒ ለመወርወር እንኳን ቅንጣት አላመነታም። ከኢየሩሳሌም ተነስቶ
217 ኪሎ ሜትር በእግሩ ወደ ደማስቆ ለመጓዝ ቅሌን ጨርቄን አላለም።
የጳውሎስ ጉዞ የክርስቶስን ቤት ለማፍረስ ቢሆንም እንደቁርጠኛ ውሳኔውን ግን ለእግዚአብሔር ከታሰረለት ፍቅር የተነሳ
ነበር። ለእግዚአብሔር ፍቅር ጠላትን የሚዋጋ ጊዜ መፍጀት እንደሌለበት ያመላከተ ሆኗል። ጳውሎስ በመንገዱ ላይ ያጋጠመው ብርቱ ኃይል ከእርሱ የሚበልጥ
በመሆኑም «አንተ ማነህ?» ማለቱም የጀግንነቱ ልክ መገለጫ ነበር።
እግዚአብሔርም ራሳቸውን ለእርሱ የሰጡትን እንደዚህ ዓይነቶቹን ሰዎች ይወዳል። ጀግናን ማን ይጠላል?