Wednesday, January 23, 2013

የውጪው ሲኖዶስ ድርድሩን ቅድሚያ ከመንግሥት ጋር ቢያደርግ ሳይሻል አይቀርም!

ከከፈለኝ ምስጋናው

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዘመንዋ ሁሉ ከነበሩ መንግሥታት ጋር እጅና ጓንት ሆና መቆየትዋ እውነት ነው። ከነገሥታቷና ከሹማምንቷ ጋር መሆንዋ በአንድ በኩል ጠቅሟታል። ይኸውም በፈለገችበት የሀገሪቱ አድማስ እንድትስፋፋ፤ በኢኮኖሚ አቅሟ እንድትደላደል፤ ተሰሚነት ያለው ድምጽ እንዲኖራት አግዟታል። በተቃራኒው ደግሞ ከመንግሥታት ጋር ተጠግታ መኖርዋ ራሷን ችላ እንዳትተዳደር፤ ሉዓላዊ የሆነ ሥልጣን እንዳይኖራትና ጉዳይዋን ባላት አቅም እንዳትፈታ በግልጽም፤ በቀጥታም ሲቆጣጠሯት መቆየታቸው አሁን ለደረሰችበት ፖለቲካንና ሃይማኖትን የማቀላቀል ዘመን ላይ እንድትደርስ አድርጓታል። ነገሥታቱ ሌላው ቀርቶ የአድባራትና የገዳማት አለቆችን እስከመሰየም ድረስ ግልጽ ሥልጣን እንደነበራቸው ታሪክ ይነግረናል። እስከ ደርግ መውደቅ ድረስ የጠቅላይ ቤተክህነቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሚሾምላት በቤተ መንግሥቱ ነበር። በዘመነ አፄ ኃ/ሥላሴ መነኮሳቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነው በማገልገል በሕዝባቸው ላይ የገባር ሥርዓት እንዲቀጥል ታማኝ አባል በመሆን የነገሥታቱ ባለሟልም ነበሩ።  

  በዚህም ይሁን በዚያ ከመንግሥታቱ ጋር መጣበቅዋ መልካም ገጽታዎችና አሉታዊ መልኮችም አብረዋት እንዲኖር ማድረጉም እውነት ነው።
ይህንኑ ተከትሎ 4ኛው ፓትርያርክ አባ መርቆሬዎስም እንደቀደመው ታሪክ ሁሉ በደርግ መንግሥት ድጋፍና ተቀባይነት ነበራቸው።  ደርግን የሚጠላ ደግሞ እርሳቸውን ቢጠላ አይደንቅም። መደገፍ እንዳለ መቃወምም ሰውኛ ጠባይ ነውና። ገለልተኛ መሆን በማይቻላቸው የቤተክርስቲያን መሪዎች የተነሳ  አንዱ ሄዶ አንዱ ሲመጣ መንግሥታት እንደምትመቻቸው ለማድረግ በመድከም ቁጥጥራቸው ለቤተክህነቷ ቅርብ ነው።  ከዚህም የተነሳ ለደርግ የነበራቸውን አቋም በመመልከትና በእሳቸው ላይ የነበረውን ጥላቻ በራሱ መንገድ ለመፍታት በመፈለግ  ከደርግ ውድቀት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው የኢህአዴግ መንግሥት እንደቀደሙት መንግሥታት በቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ እጁን ማስገባቱ አልቀረም።  እውነት እውነቱን ስንነጋገር፤ የአባ መርቆሬዎስን ከሥልጣን መልቀቅ ይፈልግ የነበረው ተረኛው መንግሥት ብቻ ሳይሆን የመንበረ ፓትርያርኩ ብዙዎቹ ኃላፊዎችና ሊቃነ ጳጳሳቱም ጭምር እንደነበር በወቅቱ ከስልጣን የማባረር ተሳታፊዎችን ዘመቻና ግርግር ያስተዋለ አይዘነጋውም። 
  መንግሥትም ሆነ አባ መርቆሬዎስን ለመጣል ጊዜው አሁን ነው ባዮች የዘመቻው አባላት መጻኢውን የቤተክርስቲያን መከፋፈል ከግምት ውስጥ ባለማስገባታቸው የፈጸሙት ስህተት እስከአሁን ላለው ልዩነት ዳርጓል። ቤተክርስቲያን ነጻነቷን ሳታስደፍር እንዳትኖር መሪዎቿ ከመንግሥታት እየተለጠፉ ከመኖራቸው የተነሳ ደርግ መራሹ ቤተክህነት ወደኢህአዴግ መራሽ ተለውጧል። ለዚህ ድጋፍ ሥልጣን ናፋቂ አባላቶችዋ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።
በእርግጥ ቤተክህነት ውስጥ የተሰገሰገው እውነተኛ አማኝ ብቻ አይደለም።  በቆብና በቀሚስ ስር የተሸሸገ አደገኛ ፖለቲከኛም በመኖሩ መንግሥታት በሌላኛው  ዓይናቸውን ቤተክርስቲያኒቱን ቢከታተሏት ሊደንቀን አይገባም። በዘመነ ደርግ የፓርቲው አባላት ቤተክህነቱ ውስጥ ሥልጣን ሲኖራቸው ሌሎቹ ቀን እስኪያልፍ ሳይወዱ እየሳቁ ቀኑን ማሳለፋቸው አይዘነጋም።  የቤተክርስቲያኒቱ መለያየት ለሃይማኖታዊ ፖለቲከኞችም ሆነ ለግልጽ ፖለቲከኞች መሸሸጊያ  ዋሻ በመሆንዋ መንግሥታት በፖለቲካዊ ፍርሃት የተነሳ እጃቸውን እንዲያስገቡ በመደፋፈር ትንፋሿን ይቆጣጠራሉ።  የእግዚአብሔርን መንግሥት ብቻ የሚያገልግሉ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መንግሥትንም አጣምረው የሚያገለግሉ ሞልተውባታል። ቤተክህነት ለሁለት ጌቶች ከተገዛች ደግሞ አንዱንም ማጣትዋ የግድ ነው። የሃይማኖተኛ ሰው ፖለቲካው ሃይማኖቱ ብቻ መሆን ነበረበት። ዛሬ የሚታየው ሃይማኖተኛ ግን ፖለቲካዊ ሃይማኖተኛ እንጂ ሃይማኖተኛ አማኝ አይደለም። 


ዛሬም በሀገር ቤትም ሆነ በውጪው ዓለም ቤተክህነቱን የወረሩት ሁለቱንም አጣምረው የሚያራምዱ ሰዎች ናቸው። አንዳንዶቹ ኢህአዴግ የነፍሴ ምትክ ብለው በጭፍን ይሞግቱለታል። አንዳንዶቹ ደግሞ አህአዴግ ወደሲኦል ይውረድ ብለው ጨልጠው ፍርድ ይፈርዱበታል። ቤተክህነቱን የሞሉት እንደዚህ ዓይነት ሃይማኖተኞች ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሃይማኖተኞች ሳይሆኑ በሃይማኖት ስር የተጠለሉ ፖለቲከኞች ናቸው። ኢህአዴግን የሚጠላ አብዛኛው ፖለቲከኛ የማያውቃትን ቤተክርስቲያን መከፈል የቆጨው መስሎ በየሜዳው ያላዝናል። ገሚሱ ደግሞ ለችግሯ ከእርሱ በላይ የሚከራከር እንደሌለ ራሱን አቅርቦ  የፖለቲካ የድጋፍ ትርፉን ለመሰብሰብ ይፈልጋል።  በእውነት ግን ቤተክርስቲያን አታውቀውም፤ ወይም እርሱም አያውቃትም።  

  ጾምና ጸሎት ምን እንደሆነ የማያውቅ ፖለቲከኛ ለቤተክርስቲያኒቱ ችግር የፈውስ መንገድ አንድነቱ ብቻ እንደሆነ ቢለፍፍ  እንኳን እግዚአብሔርን ሰዎችን ማሳመን አይችልም። እንደነዚህ ዓይነተኞቹ አስመሳይ ሃይማኖተኞች የሚያስተጋቡት የአንድነት ጩኸት ችግሩን ከሚያስረዝም በስተቀር  የእግዚአብሔርም ምህረት እንዲቀርብ፤ የመንግሥትም ልብ እንዲላላ አያደርግም። አንዳንዶች ደግሞ የእርቁ ነገር እጅግ እንዲወጠርና ብዙ ጆሮ እንዲያገኝ የሚተጉት፤ ነገር እውን እንዲሆን ስለሚሹ ሳይሆን  በዚያ መሃከል የፖለቲካ ትርፍ በማግኘት ይኼው እኛ ለእርቅ ይህንን ያህል ብንታገል የሚሰማን ጠፋ በማለት ሀቀኛ ከዚህ ነው ያለው በማለት የስሙልኝ ጅራፍ ለማጮህ እንደሆነ ያሳለፍናቸው የፖለቲካው ባህል ያስረዳናል።
 በሌላ መልኩም ከፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ ኅሊና በሀገር ቤት ይሁን በውጪው ዓለም ያሉ በቅንነትና በእውነት የቤተክርስቲያን መከፈል የሚያንገበግባቸው ጥቂቶች ቢኖሩም የእነዚህን ድምጽ በፖለቲከኛ ሃይማኖተኞች ድምጽ በመዋጡ ቤተክርስቲያኒቱም ሆነ የኢትዮጵያው መንግሥት ሊያዳምጧቸው አይፈልጉም። እነዚህኞቹ ለቤተክርስቲያን ባላቸው መቆርቆር የተነሳ ከሥልጣን በላይ መንፈሳዊ እሳቤ በየትኛውም ወገን ልቦና ውስጥ እንዲኖር የሚሹ ናቸው። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢም የአቡነ መርቆሬዎስ መመለስ ለቤተክርስቲያኒቱ አንድነት ጠቃሚ እንደሆነ ሲያምን መመለስን ከሥልጣን ጋር በማጣመር አንድነቱ እንዳይመጣ ከመፈለግ ይልቅ ሥልጣኑን ለእግዚአብሔርና ለቤተክርስቲያን ሰጥተው በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የክብርና የማእረግ ሥፍራ አግኝተው ቢቀመጡና በእሳቸው እጅ በአንብሮተ እድ የተሾሙትም ሆነ ሌሎቹ ሊቃነ ጳጳሳት ተመልሰው በአዲስ መንፈስ፤ በአንድነት የጋራ የሆነ አዲስ ፓትርያርክ ቢመርጡ ይመኝ ነበር። ቅድሚያ ወደሥልጣን ለሚል ማንኛውም ሥነ ሞገትና ሊቀርቡ በሚችሉ አጸፋዊ ምላሾች ከመኖራቸው የተነሳ በክርክር ከማክረር ይልቅ ሁሉ  እያለው ሁሉን እንዳጣው የክርስቶስ ምሳሌ ይዘን አንድነታችንን እናምጣ የሚለውን አሳብ የሚቀበል ስላልተገኘ የተመኘነው አንድነት እንዳይሆን ሆኗል። ያለሥልጣን አንድነት የሚለው ድምጽ በአፍንጫችን ይውጣ የሚለው ድምጽ በማየሉ የተመኘነው አልሆነም።  
 በእርግጥ አቡነ መርቆሬዎስ ሥልጣኔን ካላገኘሁ አንድነቱን አልፈልግም ይሉ ይሆን?  ይላሉ ብሎ ለማሰብ ይከብዳል። የእሳቸው ሥልጣን ቤተክርስቲያንን  አንድ ማድረግ ከቻለ የሰማዩን ብልጫ ያስቀድማሉ እንጂ ስልጣኔ ይበልጥብኛል ይላሉ ብዬ አላስብም።  እንዲሉ የሚያስገድዷቸው ፖለቲከኞች፤ ደጋፊዎችና የጳጳሳቱ ተጽእኖዎች እንደሚኖሩ ግን ይገመታል።
አንዳንዶቹ ጳጳሳት በሀገር ቤትም ይሁን በውጪው ካሉት ውስጥ ፖለቲከኞች መኖራቸው እውነት ነው። የሀገር ቤቱ ጳጳሳት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ስላሉ በዚያው አስተዳደር  ይገዛሉ፤ ፈሪዎቹም እንደጥንቱ ደረቅ ሳቅ እየሳቁ ቀኑን በዝምታ ያሳልፉታል። የውጪዎቹ ፖለቲከኞች ጳጳሳት ግን በአንድነቱ ስም ወደሀገር ቤት ለመመለስ ከመንግሥት ጋር ካልተደራደሩ በቀር ቤተክህነቱ ብቻውን ሊመልሳቸው እንደማይችል ስለሚያውቁ ድርድሩን የሚፈልጉት ለፍጆታ ነው። በዚህም የተነሳ አቡነ መርቆሬዎስ ወደሥልጣናቸው ካልተመለሱ አንድነት የሚባል ነገር አይታሰብም በሚለው ሥነ ሞገት ላይ ሙጭጭ ማለትን መርጠዋል። አቡነ መርቆሬዎስ በጡረታና በክብር ተቀምጠው ጳጳሳቱ ግን በአንድነቱ ውስጥ የሚስማማቸውን ፓትርያርክ በአንድነት ቢመርጡ እግዚአብሔር ይቆጣል?  በፍጹም! ሥልጣኑን ሸሽጎ በጎል የተኛው የአዲስ ልደት አምላክ ያንን አላስተማረንም።
ይሁን እንጂ የአሜሪካው የጳጳሳት ቡድን አባ መርቆሬዎስን ኢህአዴግ  አባሯቸዋልና  ወደመንበራቸው ይመለሱ እያለ ቤተክህነቱን ይጠይቃል። ዳሩ ግን አባሯል ከተባለው ከኢህአዴግ ጋር ከማድረግ  ይልቅ ከቤተክህነቱ ጋር ማድረግ ምን እንዲመጣ  ነበር? ብለን ብንጠይቅ በቤተክህነቱ ከለላ የኢህአዴግን ጣልቃ ገብነት በማጋለጥ የራስን መደላድል ለማስተካከል ከመጣር ያለፈ አይደለም። እየሆነ ያለውም ይህ ነው። ከድርድሩ ምን ነገር ጠብ ላይል የአዲስ አበባውን ሲኖዶስ በሁለት ሀሳብ እንዲከፈል አድርጓል፤ የመንግሥት ሚና የት ድረስ እንደሆነ አሳይቷል።  ለቤተክርስቲያኒቱ ሳይሆን የውጪው ሲኖዶስ ያደረገው ስልታዊው ድርድር ለራሱ ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል።  «ሁለት ባላ ትከል አንዱ ሲነቀል ባንዱ ተንጠልጠል» ማለት ይሄ ነው።  የድርድሩ ማጠቃለያን የፖለቲካ ትርፍ በየሚዲያዎቹ ስናነብ «እኔ ፓትርያርኬን መርጫለሁ፤ እናንተስ?» ወደሚለው ማምራቱ የሚጠቁመን ነገር የውጪውን ቤተክህነት ወደ ውጪው ሲኖዶስ የመጠቅለል ዝንባሌ አንዱ ማሳያ ነው።  
በአንድ በኩል መንግሥት አባሮናል ብሎ በሌላ በኩል ካላባረቻቸው ቤተክርስቲያን ጋር መደራደር ምን ይሉት ፈሊጥ ነው? የጠራ መንገድ የሌለው የድርድር ጉዞ ነበር።  

 ወደፊትስ የሀገር ቤቱ ከ45 ሚሊዮን በላይ የቤተክርስቲያን ምእመን በውጪው ሲኖዶስ  ይተዳደራል ተብሎ ይታሰባል? ወይስ ምእመኑ ኢህአዴግን ጥሎ የ4ኛውን ፓትርያርክ ስልጣን በኃይል ይመልሳል? ይህ መቼም እንደማይሆን እርግጥ ነው። በውጪው ስር አይጠቀለልም ማለት ነው፤ ስለዚህ አዲስ ይመረጣል።
አይሆንም እንጂ ቢሆን የሀገር ቤቱ ምእመን እንደሙስሊሞቹ ዘመቻ አህባሽን በቤተክህነት እንዲፈጥር የሚፈልግ ጥሪም ሲስተጋባ ይሰማል።  መቼም ቢሆን የቤተክርስቲያን አንድነት በእግዚአብሔር ፍቅር እንጂ በዘመቻ አይመጣም። መንግሥት የፖለቲካ ትርፉን እያሰበ ብቻ የሚያደርገው እርምጃ እንዳለ ሆኖ  በኢትዮጵያ ያለው የሰለፊ እንቅስቃሴ ግን በቀጥታ ከአክራሪነት ውጪ ምንም ሌላ ዓላማ የለውም። ከዚህ አንጻር በምእራብና ሰሜን አፍሪካ እየተስፋፋ ያለውና በመካከለኛው ምሥራቅ እየተፈበረከ ወደየሀገራቱ የሚሰራጨው የሰለፊ አክራሪ እንቅስቃሴን  ዓይነት የሃይማኖት መብት እንደተጣሰ ቆጥሮ የውጪው ሲኖዶስ ተመሳሳይ ዐመጽ በሀገር ቤቱ በቤተክህነት ውስጥ እንዲያቀጣጥል ጥሪ ማድረግ ከሃይማኖት ፖለቲከኝነት በዘለለ የእብደት ሃሳብ ከመሆን ያለፈ አይደለም።
 ድርድሩ እውን ሆኖ አባ መርቆሬዎስ ወደስልጣናቸው እንዲመለሱ ወሳኝ ድርሻ ያለውና አባሯል የተባለው መንግሥት ፈቃደኝነቱ እንደሌለው እያወቁ የውጪዎቹ ሲኖዶሶች ወደ ድርድር መምጣታቸው በእርግጥም አንድነቱ ይመጣል ብለው አልነበረም ማለት ይቻላል።  ኢህአዴግስ 4ኛው ፓትርያርክ ወደሥልጣናቸው እንዲመለሱ ይፈልግ ነበር? አይመስለኝም!  ኢህአዴግ ጠብ መንጃና ፖለቲካ ይዞ የመጣ ተዋጊ እንጂ የወንጌል ሐዋርያ አይደለምና ቤተክህነቶቹ በትህትናና በየዋህነት መንፈስ ቤታቸው ውስጥ ተመልሰው በጥበብ መስራት እስካልቻሉ ድረስ አንድነቱ ቅርብ አይሆንም። እንደእርግብጥ የዋህ፤ እንደእባብ ብልህ ሁኑ ለሚለው የወንጌል ቃል ዝግጁ አይደሉምና በክርክር የተነሳ የአንድነት ጊዜው ሩቅ ነው። የዱሮን ምሳሌ እያቀረቡ በዘመኑ ዓይን ለመፍታት መሞከርም የእውቀት ጉድለት ነው።
ኢህአዴግ የውጪዎቹን ጳጳሳቱን ይኮንናል ተብሎ ከሚታሰቡ ምክንያቶች አንዳንዶቹ ጳጳሳት ፖለቲከኞችና እኔን ለመጣል ከሚያሴሩ ድርጅቶች ጋር ቁርኝት አላቸው በማለት ነው።  እንደኤልያስ በጸሎቱ የሰማይን መስኮት መክፈትና መዝጋት ከሚችል መንፈሳዊ ኃይል ጋር ኅብረት በማድረግ የኢህአዴግን ጉልበት አድክም፤ ዓይኑንም አፍዝዝ በማለት ከተቻለ በጸሎት ኃይል እንደማሰር በፖለቲካ ሰልፍና ዘመቻ ኢህአዴግን ለመጣል እንደሚቻል በማሰብ አደባባይ የሚወጣ ጳጳስ ስናይ ለጽድቅ ብሎ የማይገዛን ፖለቲከኛው ኢህአዴግ ይቅርና እኛንም አስገርሞናል። አሳፍሮናልም። በረሃ ወርዶ ጠብ መንጃ የሚባርክም ተመልክተናል። ይህ ሆኖ ሳለ በምን ችሎታዋ ነው ቤተክህነት እርቁን ያለመንግሥት ድጋፍ ወደአንድነት ማምጣት የሚቻላት? ስለሆነም ከኢህአዴግ ጋር መደራደር ያልቻለ የውጪው ሲኖዶስ መቼም ቢሆን ኢህአዴግ በሥልጣን ላይ እያለ ወደአዲስ አበባው ሲኖዶስ በአንድነት መምጣት አይችልም። ኢህአዴግ ደጋፊዎችን እንጂ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን በቤተክህነት ውስጥ ሰግስጌ በራሴ ላይ እሳት አላነድም ቢል ሊያስገርመን አይገባም። መንግሥት ከጥፋቱም ሆነ ከታሪክ ባለመማር በእልከኝነት የጸና ይመስላል። ግልጽ ፖለቲከኛ ሃይማኖተኞችን ትቶ አንድነቱን ለሚፈልጉ እውነተኛ ወገኖች የቤተክህነቱ መከፋፈል ለማቆም ያለውን አቋምና ድጋፍ በግልጽም፤ በስውርም ማሳወቅ ነበረበት። ይህን አላደረገም፤ ለምን? ብለን እንጠይቃለን። ከሰልፈኞቹ፤ ከጠብመንጃ ባራኪዎቹና ከአንዳንድ ተቃውሚዎች ጳጳሳት የተነሳ የመጣው ይምጣ እንጂ እነዚህን አልመልስም ብሎ ይሆን?  መቼም በሃይማኖት ጉዳይ መንግሥት ጣልቃ አይገባም ብሎ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ በመጥቀስ በዚህ ጉዳይ እኔ የለሁበትም እንደማይለን ተስፋ እናደርጋለን። ዲስኩርና ተግባር ለየቅል ናቸውና። በመሪዎች ከማን አንሼ የተነሳ ምእመኑ ታመሰ፤ የዝሆኖች ጥል ሳሩን እንደጎዳው መሆኑ ነው።
አቡነ መልከጼዴቅ በአንድ ጽሁፋቸው ጽድቅና ሃይማኖትን የማያውቅ ኢህአዴግን ያወገዙበትንና የረገሙበትን ጽሁፍ ብታነቡ ለኢህአዴግ ጭከና እንደምክንያት አይቆጠርም? (ጽሁፉን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)
የውጪዎቹ ጳጳሳት ድርድሩን ቅድሚያ ከመንግሥት ጋር ማድረጉ ሳይሻላቸው አይቀርም።