Friday, January 4, 2013

«የሦስት ልጆች አባት የሆነው አምላክ፤ የኢሬቻ በዓል»



12, 000 ሺህ ዓመት በፊት የኩሾች ፈርዖን፤ የሰማይና ጸሐይ   «አስራ» የተባለው አምላክ ሦስት ልጆችን ወለደ።  የመጀመሪያ ወንድ ልጁ «ሴቴ»፤ ሁለተኛው ልጁ ደግሞ «ኦራ» ሲባል የመጨረሻ ሴት ልጁ ደግሞ «አቴቴ» ወይም አድባር የምትባል ነበረች። ከጸሐይና ከሰማይ አምላክ «አስራ»  ልጆች መካከል ሴቴ የተባለው የመጀመሪያ ልጁ ታናሽ ወንድሙን ኦራን በድንጋይ ገደለው። በወንድሟ ሞት እጅግ ያዘነችው «አቴቴ»  ዐባይ ወንዝ ዳርቻ ባረፈው በሟች በወንድሟ መቃብር ላይ «ኦዳ» የተባለውን ዛፍ ለመታሰቢያነት ተከለች።
አቴቴ (አድባር) በመቀጠልም ያደረገችው ነገር በገዳይና በሟች ወንድሞቿ ቤተሰቦች መካከል በቀልና ጥላቻ እንዳይኖር ወደሰማይና ጸሐይ አምላክ አባቷ  ወደ አስራ በማመልከቷ የሰላም ምልክት እንዲሆን ከሰማያት ዝናብ ዘንቦ የተከለችውን «ኦዳ» የተባለውን በማለምለም ሰላም እንዲሰፍን አድርጎላታል።

ሟች ኦራም በኦዳ ዛፍ ልምላሜ የተነሳ በጸሐይና በሰማይ አምላክ አባቱ ሥልጣን ምክንያት ከሞት የተነሳና ያረገ ሲሆን ይኸው በኦዳ ዛፍ ስር ሟች ኦራን በማስታወስ የሚደረገው የሰላምና የምህረት አከባበር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ቀጥሏል። በቀደምት ኑቢያውያን የሚደረገው አከባበር  በጥንታውያን የአክሱም ስርወ መንግሥትም ዘመን የኦራ መታሰቢያን የሚያመለክት ቋሚ ድንጋዮችን በመትከል ሲታሰብ ኖሯል።

ከሙታን መነሳቱንና በኦዳ ዛፍ ልምላሜ  ምክንያት የተገኘውን ሰላም በማሰብ፤   የኦራን ሕያውነት የሚያመለክተው ይህ ትንሳኤ «ኦራ ኦሞ» /Ora-omo/ ሲቆይም «ኦሮሞ» ተብሎ ለመጠራት በቅቷል።  የሰማይና የጸሐይ አምላክ የኦራን አባት ከፍ ከፍ በማድረግ ለማመስገን በኦዳ ዛፍ ስር የሚደረገው በአንድነት ተሰብስቦ የማክበሩ ስርዓትም «ኢሬቻ» ይባላል።
አድባር የሁለቱ ወንዶች እህት ስትሆን ለወንድሟ ባደረገችው መታሰቢያ የተነሳ አምልኮ የሚፈጸምበት ዛፍ በስሟ አድባር እየተባለ እስከ ዛሬ ይጠራል። አድባር ስር ንፍሮ በመቀቀል፤ ቡና በማፍላት፤ እርድ በማድረግ ደም አፍስሶ ልመና ይፈጸማል።

የጸሐይና የሰማይ አምላክ የአስራ /Asra/ የመጀመሪያ ስሙ «ካኣ» ስለሆነ  ለስሙ የሚደረገው የወርሃ መስከረም የኢሬቻ በዓል «ኢዮ-ካኣ አባቦ» እየተዘመረ የሚከናወን ነው። ይህም የአበቦች አምላክ ካኣ አንተ ነህ በማለት ማመስገን ነው። «ኢዮ-ካኣ አባቦ»  የሚለውን የኦራ ኦሞ ዝማሬ ዛሬ «ኢዮሃ አበባ» በማለት ሰዎች እየጠሩት ይገኛል።
የክረምቱ መገለጥን ተከትሎ የችቦ መለኮስ እና የችቦው ስርዓት የደመራው በዓል መነሻው ኢሬቻ ነው። ይህም የኦዳ ስር ስርዓት ማቅረብ ሕይወት የተገኘበትና ሰላም የወረደበት የኦራ አምላክ ምስጋና ስለሆነ «ኢሬቻ» በኦራ-ኦሞዎች ዘንድ ትልቅ ሥፍራ አለው።
ኦራ-ኦሞዎች/ኦሮሞዎች/ በአንድ አምላክ የአምልኮ ጥላ ስር ለዘመናት፤ ከክርስትናና ከእስልምና ሃይማኖቶች መምጣት በፊት የሚያምኑ ስለነበሩ ለሃይማኖት እንግዶች አይደሉም።
ይህንን ለዘመናት የቆየ የኢሬቻን የአምልኮ ሥርዓት በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ ሐይቅ ዳርቻ / ቢሾፍቱ ማለት አስቀያሚ ወይም ማስጠሎ ማለት ነው/ በየዘመን መለወጫው በከፍተኛ ድምቀት ያከብሩታል።
ከብዙ በአጭሩ የሦስት ልጆች አባት የሆነው የሰማይ አምላክ «አስራ» ክብረ በዓል «ኢሬቻ» ይባላል