Wednesday, January 16, 2013

«ሐራ» ነኝ ማለትህ ቅጥፈትይሆንብሃል!



የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ሆነውና ያሉበትን ሥፍራ ተተግነው እንደልዩ የመረጃ ምንጭ መስለው ቅጥፈት የሚዘሩ ብሎጎች ብቅ ብቅ ማለታቸውን ስናይ ቆይተናል። ከእነዚህም አንዱ «እኔ የቤተክርስቲያን ወታደር ነኝ» በማለት ራሱን ያስተዋወቀው አንድ ብሎግ ወታደርነቱን እጠብቃታለሁ ለሚለው ቤተክርስቲያን ዓላማ ብቻ ማዋል ሲገባው ሲፈልግ ለግለሰቦች ጋሻና መከታነቱን የሚያሳይ፤ ዛሩ ሲነሳበት ደግሞ ጋሻ የሆነላቸውን ሰዎች ቆሌ በመግፈፍ ካርታው እንደጠፋበት ወታደር እዚህም፤ እዚያም የሚዳክር ሆኖ ይስተዋላል።
በእጃችን ያሉ መረጃዎችን መሠረት አድርገን፤ ነገር ግን መረጃዎቹን ትተን ጥቅል ችግሮቹን ብቻ ከዚህ በፊት ስለዝዋይ ገዳም አስነዋሪ ተግባራት በዘገብን ጊዜ ይህ ወታደር ነኝ ባዩ ብሎግ ሽንጡን ገትሮ ለሊቀጳጳሱ በመከራከር እንባ ቀረሽ ልቅሶውን በጽሁፍ ባስነበበን ጊዜ ወታደር ነኝ የሚለው ዲስኩሩን ትተን «የዓይጥ ምስክር ድንቢጥ» በማለት አልፈነው ነበር።
ይኸው የቤተክርስቲያን ወታደር ነኝ ባዩ ብሎግ ስለዝዋዩ ሊቀጳጳስ ጠበቃ መሆኑን በጽሁፉ ባሰፈረ ጊዜ በልማት፤ በማኅበራዊና በመንፈሳዊ  እድገት ትልቅ እመርታ ማሳየታቸውን ጠቅሶ ሊቀጳጳሱ ላይ የስም ማጥፋት እርምጃ ለመውሰድ የፈለጉ ወገኖች መነሻ ምክንያታቸው «የኦሮሞ ፓትርያርክ ለማሾም የሚራወጡ ቡድኖች ጠባብ አስተሳሰብ ያመጣው ችግር ነው»  በማለት ነጭ ውሸቱን በድጋፍ ዘመቻው በማከል ጠበቃነቱን ማሳየቱ አይዘነጋም። ጽሁፉን ያነበብን አንዳንድ ወገኖች  የኦሮሞ ፓትርያርክ ዝዋይ ላይ መሾም እንዴት እንደሚቻል አዲሱን ግኝት አያይዞ ባለማብራራቱ ግር ብንሰኝም እንደአስፈጋጊ ቀልድ እውነታውን ስለምናውቅ በወቅቱ አልፈነው ነበር። ይኼው ብሎግ ለሊቀጳጳሱ በወቅቱ ከሰጠው ምስክርነት ጥቂቱን ጠቅሰው ወደሌላው «በአንድ ራስ ሁለት ምላስ» ጽሁፉ እናመራለን።
«ሁለቱም አካላት በተለያዩ መንሥኤዎች የገዳሙንና የብፁዕነታቸውን ስም ለማጥፋት ይሞክሩ እንጂ በአንድ ጎራ ያሰለፋቸው ስጋት ተመሳሳይ እንደኾነ ምንጮቹ ጨምረው ያስረዳሉ፡፡ ይህም ስጋት ብፁዕነታቸው በቀድሞው ፓትርያሪክ እንደ እንደራሴም እንደ ተተኪም መታጨታቸውና ለዚህም ዓላማ ፓትርያሪኩ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ እንዳስተዋወቋቸው የሚነገርላቸው ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ ስድስተኛው ፓትርያሪክ  ለመኾን በመንግሥት ታጭተዋል በሚል የመነገሩ ወሬ ነው»
ይህ ከላይ በቀይ የተቀመጠው ጽሁፍ የቤተክርስቲያን ወታደር ነኝ ባዩ ብሎግ የሊቀጳጳሱ ወታደር ሆኖ በወቅቱ የጽሁፍ ምስክርነቱን በመስጠት በብሎጉ ላይ ያሰፈረው ነበር። ይኼው ብሎግ  ከወራት በኋላ ማለትም ጥር 6/2005 ጀምሮ የተደረገውን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ተከትሎ በሚወጡ ዘገባዎች ላይ የሊቀጳጳሱ ጫና እያየለና ተሰሚነታቸው እየተጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ ወደ ፓትርያርክነት የሚያደርጉትን የእጩነት ጉዞ በማጥላላት ዘመቻ ውስጥ ገብቶ፤በመዘገብ ላይ መጠመዱ ነገሩን ሁሉ አስገራሚ ያደርገዋል። 

ከታች የሰፈረውን ጽሁፍ በተቃራኒው ያስነበበን ይኼው የሊቀጳጳሱ ወታደር ሆኖ ሲከላከልላቸው የቆየው ብሎግ ነው።
«ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ (ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ የሚሉ አባቶችን በሃይለ ቃል በማሸማቀቅና ከምርጫው አኳያ የሚከናወኑ ተግባራት እንዲፋጠኑ እየሠሩ ናቸው፤ ለረጅም ጊዜ በቆዩበት ሀገረ ስብከት አጥጋቢ ተግባር ባለማከናወናቸው ብቻ ሳይኾን በችግሮች አፈታታቸው የሚተቿቸው ቀራቢዎቻቸው ለፓትርያሪክነት በዕጩነት እንደሚቀርቡ ከዚህም በላይ ቀጣዩ ፓትርያሪክ ሊኾኑ እንደሚችሉ በመስማታቸው ብቻ እንኳ ይሣቀቃሉ»
ወታደሩ ብሎግ ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለግለሰቦች ጠበቃ የመሆን መብት እንዳለው ብናምንም ይህንን መፈጸም ያለበት ሲያምረው  እውነቱን እየደበቀ፤ ስሜቱ ሲቀሰቀስ ደግሞ ሀሰት ያለውን እውነት ለዓላማው መጠቀሚያ እያዋለው መሆን የለበትም እንላለን። ከላይ ያቀረብነው «ከአንድ ራስ ሁለት ምላስ» ጽሁፉ የምንረዳው ነገር ሲመቸው ገመናን በመሸፈንና ዛሩ ሲነሳበት ደግሞ ድክመትን ለዓላማው ማስፈጸሚያ በማዋል የሚታወቀው ማኅበር አባላት እንደሆኑ ግምታችን ከፍ ያለ ነው። አቡነ ሳሙኤልንና አቡነ አብርሃምን ተጠግቶ ብዙ እንቅስቃሴ የነበረው ማኅበረ ቅዱሳን ሰሞኑን ሁለቱንም ጳጳሳት እርቅ እንደማይፈልጉና ለፓትርያርክ ምርጫ የሚሮጡ አድርጎ አንዳንድ የጽሁፍ ዘገባ ማቅረብ መጀመሩ ማኅበሩ ማንን ለምን እንደሚቀርብና መቼ ደግሞ ጠላት መሆን እንደሚችል እቅድ ይዞ የሚጓዝ መሆን የሚያመላክት አስረጂ ነው። እንደዚሁ ሁሉ የቤተክርስቲያን ወታደር ነኝ በማለት በቅርቡ ወደ መረጃ መረብ ብቅ ያለው አዲሱ ብሎግም ስለዝዋዩ ሊቀጳጳስ ጠበቃ ሆኖ ሲከራከር እንዳልቆየ ሁሉ ቀደም ሲል የተወራው ነገር እውነት እየሆነ መምጣቱ ሲታየው «አባ ጎርጎርዮስ እንኳን ፓትርያርክ መሆን ይቅርና ለእጩነት መቅረባቸውን ራሱ ሲሰሙ የሚሳቀቁባቸው አሉ» ሲል አስገራሚ ምስክርነቱን የቀድሞ ምስክርነቱን አፍርሶ አስነብቦናል። እባክህ የቤተክርስቲያን ወታደር ነኝ የምትለው አንተ ብሎግ በነካካው እጅህ ለእጩነት መቅረባቸው በራሱ የሚያሳቅቀው ለምን እንደሆነ ምስጢሩን ግለጥልንና የቀድሞ ጠበቃነትን እንደንስሐ ጊዜ ተጠቀምበት። ያለበለዚያ የቤተክርስቲያን ወታደር «ሐራ» ነኝ ማለትህ ቅጥፈትይሆንብሃል።