Tuesday, January 1, 2013

ሁሉም ፓትርያርኮች የመንግሥት ጥገኞች ነበሩ!

ቤተክርስቲያኒቱ  ከምሥረታዋ ጀምሮ  የነገሥታቱ እጅ ተለይቷት አያውቅም። የሲሶ መንግሥትነት ድርሻዋም ከዚሁ ይመነጫል። የረጅሙን ዘመን የእንዴትነቱን ታሪከ ለጊዜው እንተወውና ስለፓትርያርኮቹ እውነታ ግን ጥቂት እንበል።

አጭር ምልከታ፡

1/ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ /አቡነ ባስልስዮስ/
ትውልድ መንደራቸው ከሸዋ መርሐ ቤቴ የሆኑት ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ /መምህር ገ/ጊዮርጊስ/ እየተባሉ በመናገሻ ማርያም፣ በኢየሩሳሌምና በኋላም በእጨጌነት የደብረ ሊባኖስ ሹም ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው በጣሊያን ወረራ ወቅት እስከ ማይጨው ድረስ ንጉሠ ነገሥቱን ተከትለው በመሄድ ውጊያውን አብረው ተካፍለዋል። በኋላም የጣሊያን ኃይል እየገፋ  ሲመጣ ከንጉሡ ጋር አፈግፍገው ንጉሡ ወደ ለንደን ሲሸሹ እጨጌው ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም ኮብልለዋል። ጣሊያንም ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በጎቻቸውን በትነው በምንደኝነታቸው የተነሳ ወደ ሀገራቸው በፈረጠጡት በግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ አባ ቄርሎስ ምትክ ከመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት መካከል መጀመሪያ አባ አብርሃምን፣ እሳቸው ሲሞቱ ደግሞ  አባ ዮሐንስን የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ ጣሊያን ሲሾም ሹመቱን አሜን ብለው በየተራ ተቀብለው ነበር። እንደነ አቡነ ጴጥሮስ የመሳሰሉት ጳጳሳት ለጣሊያን ወራሪ ኃይል ሕዝቡም፣ መሬቱም እንዳይገዙ ሲገዝቱና እስከ ሰማእትነት ሲደርሱ ሌሎቹ ጳጳሳት ደግሞ የጣሊያንን ሹመት እሰየው ብለው መቀበላቸው አይዘነጋም።
ከአምስቱ ዓመት የሕዝቡ መከራ በኋላ ጣሊያን ሲባረር የንጉሠ ነገሥቱን መመለስ ተከትለው እጨጌ ገ/ጊዮርጊስም ተመልሰው ወደ ሀገራቸው ገብተዋል።  ከዚያም በ1940 በግብጻዊው ፓትርያርክ አባ ዮሳብ እጅ ሊቀ ጳጳስ፡ እንደገናም ሌሎች ቀደምት ጳጳሳት እያሉ አጼ ኃ/ሥላሴ በተገኙበት ሥነ ሥርዓት በፓትርያርክ ቄርሎስ እጅ ካይሮ ላይ በሚገኘው ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፓትርያርከ ዘኢትዮጵያ ተብለው መሾማቸውን የቤተክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለ1600 ዓመታት በፈጠራ ሕግ በግብጾች የምንዳ አስተዳደር እጅ መቆየትዋን እንዲያበቃ ንጉሠ ነገሥት ኃ/ሥላሴ ከፍተኛ ሚና ቢጫወቱም የፈለጉትን ሰው ወደ  ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ  የሥልጣን እርከን ማምጣት መቻላቸውን ማስተባበል የማይቻል እውነት ነው። ኢትዮጵያውያን ጳጳሳትም ለጣሊያን ፋሺዝም ሳይቀር የስልጣን ሹመት ፈቃደኛነታቸውን በማሳየት አፍቃሬ ሲመታቸው እስከየት ድረስ እንደሆነ ማሳየታቸውንም  የሚዘነጋ አይደለም።
የሀገሪቱ ሕዝብ በገባር ሥርዓት ውስጥ በጭሰኝነት መከራ እየተጠበሰና ርስት አልባ ሆኖ  እየተሰቃየ  ሳለ በነገሥታቱ የተሾሙት የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ግልጽ ወገንተኝነታቸው ከነገሥታቱ ጋር  ነበር። ለምሳሌ ያህልም እንደ ደብረ ሊባኖስ ያሉ ትላልቅ ገዳማት  በርስትነት በተቆጣጠሩት ኩዳድ መሬት ላይ የገባሩ ሥርዓት አንዱ አካል በመሆን በክርስቲያን ሕዝባቸው ላይ ጭሰኝነትን መትከላቸው አይዘነጋም። ነገሥታቱ ሲያጠፉ የምትገስጽና የምትመክር ቤተ ክርስቲያን በአመራርዋ እስካሁን አልነበረችም። ይህ እውነት ቢዘገንነንም እውነት ነው። በሐብታምና በደሃ፡ በጨዋ ዘርና በባሪያ፣ በአሳዳሪና በገባር መካከል ያለውን የወንጌል እውነት ማንንም ሳትፈራና ሳታፍር ማስተማር ሳትችል ነጻነቷን ለነገሥታቱ አስረክባ መቆየትዋም አሌ የማንለው ሐቅ ነው። ከነገደ ዛግዌ ወገን ላይ በስመ ኢ- ሰሎሞናዊ ሽፋን ንግሥናን ከመቀማት አንስቶ  አይሁዳዊቷ  ሀገር እስራኤል ነጻነቷን ስታውጅ አናውቅሽም ያሏት፣ ነገር ግን  በስመ ነገደ ይሁዳ  ኢትዮጵያን ለሚገዙ ነገሥታት ታማኝ ሆና ቤተ ክርስቲያኒቷ  መቆየትዋም ለዛሬ የአስተዳደር ድክመትና የሌሎች ወገኖች ደጋፍ  መታጣት አንዱ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል። ይህንኑ ተከትሎ የመጡ መሪዎች ሁሉ ለመጠቀሚያነት እጃቸውን ለማስገባት መቻላቸውም  እርግጥ ነው።
2/  ሊቀ ሥልጣናት መልእከቱ/ አቡነ ቴዎፍሎስ

በዚህ የዘመናት ጉዞ አንዱ ክፍል ሆነው በንጉሡ ድጋፍ ፕትርክናውን የጨበጡት አቡነ ባስልዮስም በዚሁ ታሪክ ውስጥ አልፈው በእንደራሴነት ዘልቀው ፓትርያርክ የሆኑት አቡነ ቴዎፍሎስም ከንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ትልቅ ድጋፍ እንደነበራቸው አይካድም። አንዳንድ ጳጳሳት የሳቸውን ፓትርያርክ  መሆን አጥብቀው ከመቃወም አልፈው ደርግ  እርምጃ ሲወስድባቸው እንኳን ድጋፍ እስከመስጠት መድረሳቸው በተደገፈ መረጃ ጭምር የሚነገር እውነት ነው። አቡነ ቴዎፍሎስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ለልማትና ለመንፈሳዊ መነቃቃት መፈጠር ጉልህ ሚና እንዳላቸው ባይካድም ለንጉሡ ሥርዓት ቅርበት እንዳላቸውም  አይዘነጋም።  በአጼ ኃ/ሥላሴ ድርጊት ያቄሙ ጳጳሳት ከአዲሱ ሃይማኖት የለሽ መንግሥት ጋር ወግነው አቡነ ቴዎፍሎስ  እንዲታሰሩ መስማማታቸው ሳያንስ ፓትርያርኩ በእስር  እያሉ ሌላ ፓትርያርክ ለመሾም ራሳቸውን ለማጨት የፈለጉ ነበሩ።  ብልጡ ደርግ ግን አቋም የለሾች መሆናቸውን አይቶ ከወላይታ አንድ ደብር የተገኙትን ባሕታዊ አባ መልዓኩን ለፓትርያርክነት አቅርቦ ጳጳሳት ሳሉ ተራ መነኩሴው በአንድ ጊዜ አቡነ ተ/ሃይማኖት አሰኝቶ ለፓትርያርክነት ለማብቃት ችሏል። ብዙዎቹ ጳጳሳት በሹመቱ ቅሬታ ቢኖራቸውም አይምሬው ደርግ እንደሚሰለቅጣቸው ስላወቁ ባይወዱም ምርጫውን በመንፈ ቅዱስ  እንደተደረገ ቆጥረው ለመቀበል መገደዳቸው ይታወቃል። በምርጫው ላይ የደርግ ጣልቃ ገብነት እንደነበረ  ቢታወቅም  ከአምስቱም የፓትርያርኮች ዘመን በተሻለ  የአቡነ ተ/ሃይማኖትን ፓትርያርክነት ሕዝቡ ከልቡ ተቀብሎት እስከ ዛሬም በታሪካዊነቱ ያወሳዋል። ደርግም ሳያውቀው ከሥልጣን ጥመኞቹ ጳጳሳት እጅ መንጭቆ ለአንድ ባህታዊ አሳልፎ በመስጠት ቤተ ክርስቲያኒቱን ጠቅሟታል። ሌላው ቢቀር አቡነ ተ/ሃይማኖት ጸሎተኛ ባህታዊና መፍቀሬ ነዋይ እንዳልነበሩ  ይመሰከርላቸዋል። ከአለባበስ ጀምሮ እስከ አመጋገባቸው ብርቱ ሰው ነበሩ። ያም ሆነ ይህ በሹመታቸው ላይ የደርግ ፈቃደኝት እንደነበር አይካድም።

3/ አራተኛው ፓትርያርክና ለሁለት ሲኖዶሶች መፈጠር ምክንያት እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአባ ገ/ሊባኖስ /አቡነ  መርቆሬዎስ/ ወደ ፓትርያርክነት መምጣትም የደርግ እጅ እንደነበረበት ከጥርጣሬ በላይ በማስረጃ የሚናገሩ የወቅቱን አመራረጥ የተሳተፉት የሚናገሩት ነው። በተለይም የደርግ ማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የጎንደር ክ/ሀገር አስተዳዳሪ፣ በኋላም የክ/ሀገሩ የኢሰፓ 1ኛ ጸሐፊ የሆነው የጓድ መልአኩ ወሳኝ ድርሻ እንደነበረበት በሕይወት ያሉ ሰዎች ዘወትር የሚያነሱት ታሪክ ነው። በተለይም አባ መርቆሬዎስ የጎንደር ሊቀ ጳጳስ ሳሉ ዲቁናና ቅስና ለመቀበል ወደ እርሳቸው ዘንድ ይመጡ ለነበሩት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ካህናት የሚያቀርቡት ቃለ ቡራኬ “ይህ ሁሉ ወጣት ጠመንጃ ቢሸከም” ይሉ እንደነበር በሥፍራው የነበሩ ካህናትና መነኮሳት እማኞች ዛሬም ያስታውሱታል። ከኢህአዴግ መንግሥት ጥርስ ውስጥም የከተታቸው በአንድ ወቅት ለደርግ መንግሥት የጦርነት ድጋፍ የሚሆን ገንዘብ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በመስጠታቸውና ይህም በሚዲያ በመነገሩ እንደሆነ  ይገመታል። ከደርግ  ጋር ከምርጫ  እስከ ሃሳብ ድጋፍ ድረስ የተሰናሰሉ እንደነበር ቢያቅረንም በእውነቱነቱ መጋት የግድ ይሆናል።  በአባ መርቆሬዎስ ፓትርያርክነት ዘመን ቤተ ክህነቱ የጥቂት ወገኖቻቸውና ደጋፊዎቻቸው መፈንጫ እንደነበር ጊዜው ቢረዝምም እንዴት እንረሳለን የሚሉ ዛሬም አሉ። የእነ ሊቀማእምራን አበባው ይግዛውን አስተዳደር የሚያስታውሱ  ከደርግ ጋር እስከቆንስላነት የነበራቸው ትስስር በመዘንጋት ተበዳዮች ነበርን ባዮች፣ የእነሱ የግፍ አገዛዝ ይመለስልን ብለን እንዴት በተስፋ እንጠብቃለን? በማለት ጥያቄ ያነሳሉ። ምንም ይሁን ምንም የፓትርያርክ መርቆሬዎስ ቤተ ክህነት ከደርግ ጋር ቁርኝት እንደነበረው መካድ አይቻልም። ይህንን ቁርኝት ተከትሎ በደርግ ተበደልኩ የሚል ወገን የፓትርያርኩን በሥልጣን ላይ መመለስ ባይቀበል አያስገርምም። ያስደንቅ የነበረው ቤተ ክህነቱ በየጊዜው ከሚመጣ  የሀገሪቱ ባለሥልጣ ጋር ሳይለጠፍ ራሱን ችሎ ቢገኝ ነበር።

4/ የአባ ገ/መድኅን/ አባ ጳውሎስ/ ዘመነ ፕትርክና

ይህ ዘመን በብዙ እንከን የተሞላና በፖለቲካ ንፋስ የታመሰ ዘመን ነበር። በአንጻሩም አብያተ ክርስቲያናት በልማት ራሳቸውን ያሳደጉበትና አብዛኛው ካህናት የተሻለ የደመወዝ ተከፋይ መሆን የቻሉበትም ዘመን ነው። ያም ሆኖ ኢህአዴግና አባ ጳውሎስ እስከ ኅልፈታቸው ሳይከዳዱ በመደጋገፍ ጊዜያቸውን የፈጸሙበት ዘመን እንደነበርም  መዘንጋት አይቻልም። አቡነ  መርቆሬዎስን ከማባረር ጀምሮ  አቡነ ጳውሎስን እስከ ማስመረጥና ድጋፉ ሳይቋርጥ እስከመጨረሻው ድረስ ወዳጅነታቸው ሳይረግብ  መቀጠሉን መካድም ግልጹን እውነታ ወደ ውሸትነት አይለውጠውም። አቡነ ቴዎፍሎስ ሲታሰሩ እንደተስማሙት ሁሉ አቡነ መርቆሬዎስ ሲባረሩ በተመሳሳይ መልኩ የሊቃነ ጳጳቱ ብርቱ ድጋፍ ከኢህአዴጉ መራሽ መንግሥት ጋር ነበረ። በአቡነ መርቆሬዎስ ሥልጣንና አስተዳደር ቅሬታ የነበራቸው ጳጳሳትና ሠራተኞች በምትካቸው ሌላ ለመምረጥ ሲቻኮሉም ታይተዋል። ግማሹ እኔ እሾማለሁ በሚል ሂሳብ ሲሆን ገሚሱ ደግሞ  ማንም ይሾም ማንም፣ አባ መርቆሬዎስ ወርደው ብቻ ያሳየኝ ከሚል ጥላቻ የተነሳ ነበር። ስማቸውን መጥቀስ የማንፈልጋቸው ሰዎች አቡነ መርቆሬዎስ ወርደው ለማየት የቱን ያህል ፍላጎት እንደነበራቸው በወቅቱ ከማውረድ ጀምሮ  ለአዲስ ሰው ምርጫ ያደርጉት የነበረው ሩጫ አይረሳንም።
የአባ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና በአንጻራዊ ሰላምና ልማት  /የመንበረ ፓትርያርክ አዳዲስ ህንጻዎችን ልብ ይሏል/ የታየበት ዘመን ቢሆንም በአስተዳደር  ብልሹነትና  በገንዘብ ምዝበራ ረገድ ከየትኛውም ዘመን በተለየ  እጅግ የከፋ ነበር። በአባ ጳውሎስ ዘመን የጵጵስና ማእርግ የምርጫ ሥነ ምግባር ውጥንቅጡ የወጣበትና ለጵጵስናም የነበረ ክብር የወረደበት ዘመን መሆኑም አይዘነጋም።  መጋቤ ምስጢር ወ/ ሩፋኤል በአንድ ጽሁፉ እንዳለው እንደ ስምዖን ቀሬናዊ ከመንገድ እየተጎተቱ የተጫኑበትና “ብንድራቸው ይሻላል” የተባሉ ሁሉ ሥልጣን ላይ የወጡበት አሳዛኝ ዘመንም እንደነበር ይታወሳል። የእውነት ወንጌል ከመቼውም ጊዜ በላይ ዋጋ ያጣበት፡ ሥጋውያን ማኅበራት ነፍስ የዘሩበት ቢሆንም ብዙዎች የተጋረደውን እውነት ገልጠው ለማየት ይቻሉበትም ዘመን ሆኖ  አልፏል።


መጪው ፐትርክና እንዴት ይሁን?

ያለፉትን የፐትርክና ዘመናት ራሳችንን ለማሞኘት ካልሞከርን በስተቀር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሀገሪቱ መሪዎች እጅ እንደነበረበት አምነን መቀበል ተገቢ ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ ካላት የእምነቱ ተከታዮች ብዛትና አቅም አንጻር ቤተ ክርስቲያኒቱን ሳይቆጣጠሩ የሚመሩት ሕዝብ እጃቸው ላይ ስለሌለ በሚችሉት ሁሉ የሚስማማቸው ሰው እንዲሰየም ያደርጋሉ። በይበልጥም ቤተ ክርስቲያኒቱን የመንግሥት ጥገኛ የሚያደርጓት ሊቃነ ጳጳሳቱ ራሳቸው ናቸው። በራሳቸው አይተማመኑም። እግዚአብሔርን ሳይሆን የሚፈሩት ባለሥልጣናቱን ነው። ሥልጣንን እንደ ምድራዊ መሳሪያ እንጂ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደሚያገለግሉበት ኃይል አይቆጥሩትም። ስለዚህ በእነሱ መንፈሳዊ የመሆን ጉድለት የተነሳ እንደ ጎርፍ ከሚያልፉ መሪዎች ጋር ዘላለማዊቷን የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ለጥፈዋት ለችግር ሲያጋፍጧት ኖረዋል። ከዚህ የተነሳ መጪውንም ዘመን ፍቺ የሌለው አድርገን   እንድንመለከተው አወሳስበውብናል።
ይሁን እንጂ “ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም” እንደሚባለው ለችግሮቸ መፍትሄ በመፈለግ መንገድ መፍጠር አለብን። ከስሜቶች አስተሳሰብ  ይልቅ ከሚታዩ  እውነቶች ጋር መታረቅ የግድ ይለናል። ከዚህም ተነስተን አንዳንድ  መራራ እውነቶችን እንቀበል።

 ሀ/ የአቡነ መርቆሬዎስን ዘመነ ፕትርክና እንደነበረው ለመመለስ ከላይ ባቀረብናቸውና በሌሎች በብዙ ምክንያቶች የተነሳ እንደማይቻል ማመን ይገባናል።  በሥልጣን ላይ ሊመለሱ ይገባቸዋል የሚሉ ተሟጋቾች እንዳሉ ቢታወቅም  እነሱን ለማስደሰት ተብሎ የሚደረግ ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ አቡነ መርቆሬዎስ ስመ ማእረጋቸው ተጠብቆ በመረጡበት ይቀመጡ የሚለው ሃሳብ አሁን ባለው ሁኔታ  የተሻለው አማራጭ ነው። በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ የሚለው ማላዘን ዋጋ ቢስ የሚሆነው አቡነ ቴዎፍሎስ ክርቸሌ እያሉ አቡነ ተ/ሃይማኖት ተሹመዋልና ነው። ህጉ በሌለበት ህግ ማውራት ይሆናል።

ለ/  በእሳቸው የተሾሙ ጳጳሳት ከሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ጋር አንድ ሆነው ይቀጥሉ የሚለውም  ምትክ የለሽ ሃሳብ  ነው።
ሐ/  የአዲስ ፓትርያርክ ምርጫም መደረግ አለበት። እነማን? እና እንዴት? የሚለው ግን እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ነገር  ነው። ጳጳሳቱን ከረጅም ልምዳቸው እንደምናውቃቸው ለራሳቸው ሲራወጡ ለሌላ አሳልፈው የሚሰጡ ስለሆነ ሁሉም የእምነቱ ተከታይ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ክትትል ማድረግ አለበት። 

መ/ መቼም ቢሆን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ከመንግሥት ባይኖርም ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደ መንግሥታት ስትጠጋ እንደመኖሯ መጠን እንደሰጎን  ዓይኑን ከእንቁላሊቷ ሥልጣን ላይ ይነቅላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ ስውርና ግልጽ ፖለቲከኞችን፡ ዘረኞችን፡ ብዙ ጠማሞችንና ብዙ ደጎችን እንደመያዟ መጠን በምርጫ ሂደት ላይ ክትትል የለውም ማለት ከጅልነት ያስቆጥራል። ይሁን እንጂ በፖለቲካ ጉዳይ እጁን የማይነክር፡ ሃይማኖቱ የሚፈቅደውንና የሚያዘውን ብቻ ለመተግበር ዝግጁ የሆነ፣ ምእመናኑን በመንፈሳዊና በቁሳዊ ልማት ላይ ለማሰማራት ዝግጁ የሆነ ሰው ለመምረጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ በብቃት ብትንቀሳቀስ የመንግሥት ጫና እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም። ችግሩ የሚመጣው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ከራሷ ከውስጧ ነው። ይኸውም፣
·        በመንግሥት ብዙም የማይወደደው ማኅበረ ቅዱሳን በሚያደርገው የራሱን እጩ የማስመረጥ ሩጫ የተነሳ፡
·        ጃቸው በፖለቲካ ጉዳይ እንደነበረ የሚጠረጥራቸው  ጳጳሳት ለእጩነት ከቀረቡ፡
·        ጳጳሳቱ ለሹመት ካላቸው ጉጉት የተነሳ በሚፈጠረው የውስጥ ለውስጥ ሸኩቻ ምክንያት
ከመንግሥት ጋር ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ይገመታል።

ሠ/  ከዚህም ባሻገር መንግሥትን  ልናሳስበው የምንፈልገው ዐብይ ነገር  ደግሞ እጅህን በምርጫው ጉዳይ በማስገባት ለራስህም ለቤተ ክርስቲያኒቱም  መከራን ለመፍጠር አትፈልግ ለማለት እንወዳለን። የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን የሚደግፉት፡ በቅንነት፡ በእምነትና በመንፈሳዊ ብቃት ለመምራት የሚችልን አባት እንዲመርጡ ልትደግፍ ይገባል እንላለን። ከፖለቲካው የሚደባለቅ ፓትርያርክ መሪ ሳይሆን ሃይማኖቱን በማስተማር፡ ተከታዮቹን በልማት የሚደግፍና የሚያሳድግ አባት ያስፈልገናልና እንደ ሀገሪቱ መንግሥት በቤተ ክህነቱ አካባቢ ውር ውር የሚሉ ሥልጣን ነጣቂዎችን ተከታተል  በማለት እናሳስባለን። ያንን ነውጠኛ ማኅበር አደብ አስገዛልን ማለታችንም ሳይነዘነጋ ነው።
ከዚያ ባሻገር ሥልጣን በሚሰጡና በሚቀበሉ ምድራውያን ፈላጊዎች የተነሳ የተከፋፈሉት ሰዎቹ እንጂ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እስከ ዓለም ዳርቻ በበለጠ ከመስፋፋት ባሻገር አንድ ቦታ ያልቆመች ሆና ሳለ ቤተ ክርስቲያን ተከፋፈለች የሚለው ዜማ ከእውነታው ጋር የሚስማማ አይደለም። የሲኖዶሱ ሰዎች ቢታረቁም፣ ባይታረቁም አሜሪካና ኢትዮጵያ መቼም አይጣበቁም። የቤተ ክርስቲያንም አገልግሎት መቼም አይቆምም። የዶግማ ልዩነት በሌለበት ሁኔታ  ቤተ ክርስቲያን ተከፈለች በሚል ጩኸት ሥልጣንን የማስጠበቅ ትግል ከመሆን ያለፈ ነገር የለም።  ከዚያ ባሻገር እውነተኛ መንፈሳውያን ብንሆን ኖሮ የወንጌሉ ቃል አይሰወርብንም ነበር።
የሉቃስ ወንጌል 2226
እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን።