Saturday, January 26, 2013

አባ ሕዝቅኤል ለምን ስብሰባ ረግጠው ወጡ?

ዘመነ ካሣ
             ከጀርመን
የማንም አሿሿሚ አልሆንም የሥልጣን ጥመኞችን አላገለግልምበማለት አራት ወራት የቀረውን የሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነታቸውን የሚለቁ መሆናቸውን በደብዳቤ ገለጡ እየተባለ ሰሞኑን የሚወራላቸው አባ ሕዝቅኤል  ቀደም ሲልም ስብሰባ ረግጠው ቢወጡ የፈረሰው ቀኖና ይመለስ ብለው እንዳልሆነ መታወቅ አለበት።
አባ ሕዝቅኤልና በአዲስ አበባ የሚገኙት የሲኖዶስ አባለት ለእርቅና ለሰላም እንዲሁም ለሀያ ዓመታት የዘለቀውን የቤተ ክርስቲያን መለያየት ወደ አንድነት ለማምጣት በቅንነት እና ግልጽ በሆነ መንገድ ቢጓዙ ኖሮ ለዚህ ለከፋ መከፋፈል እንዲሁም ለመንግሥት ጣልቃ ገብነት ባልተዳረጉ ነበር ይልቁንም አባ ሕዝቅኤል  የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለ መባሉ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነና ቅዱስ ሲኖዶስ ለምርጫ የሚያስፈልጉ ደንቦችን ከማውጣት በቀር መንግሥት ጣልቃ አልገባም በማለት በአደባባይ ተናግረው ጸሐይ የሞቀውን እውነት የካዱ አባት ናቸው አቡነ ገብርኤልም ይሕንኑ ሀቅ ክደው በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ በሰጡት ቃል የአባ ሕዝቅኤልን ውሸት ደግመውታል።
ይልቁንም አባሕዝቅኤል በአፋቸው ስለ እርቅና ሰላም እያወሩ እሳቸውና መሰሎቻቸው  ከእኛም ወገን ይድረሰን ከሚሉት ግብረ አበሮቻቸው የሚፈልጉትን ፓትርያርክ ለማስመረጥ የሚሄዱበት መስመር እየተዘጋ በመንግሥት የሚደገፉት የነ አባ ሣሙኤል ክንድ እየበረታ ሲሄድ  ማንንም አሿሿሚ አይደለሁም፤ የሥልጣን ጥመኞችን አላገለግልም ማለቱ እና  አራት ወር የቀረውን የጸሀፊነት ሥልጣን እለቃለሁ ማለቱ ምክንያታዊነቱ  ፈጽሞ አይታይም።


በሐቅና በእውነት የአባ ሕዝቅኤል አቋም ሲታይ

1/የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከሁለትና ከዚያም በላይ ተከፋፍላ የምትገኘው ፓትርያርክ መርቆሬዎስ ያለ አግባብ በፖለቲካ ውሣኔ መንበራቸውን እንዲለቁ መደረጉን አምነው አይቀበሉም፣
2/ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተጥሶ ፓትርያርክ በሕይወት እያለ አባ ጳውሎስ መሾማቸው ቀኖና መሻሩን አምነው ለመናገር አይደፍሩም ታዲያ የአባ ሕዝቅኤል አቋም እና እውነት የት ላይ ነው ?

ሁሉም ማወቅ ካለበት እርቅ እንዲመጣ የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት እንዲመለስ ከተፈለገ ከእርቁ በፊት የምርጫ ሕግ ማውጣት ለምን አስፈለገ ? እርቁ መቅደም አልነበረበትም ? አውነት እንነጋገር ከተባለ የሰላሙን በር አስቀድመው የዘጉት አባ    ሕዝቅኤል  አይደሉምን?  ከመንፈስ ቅዱስ ሀሳብ ይልቅ የቁጥር ስሌት ገብተው አምስት ስንል ኖረን አራት አንልም ብለው መግለጫ ከመስጠት አልፈው ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በፓትርያርክነት ለመቀበል አንችልም ይልቁንም  ታሪክ ይፋለሳል አምስተኛ ፓትርያርክ እያልን ኖረን 20 ዓመት በኋላ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም፡፡ ይህ አስቸጋሪ ስለሆነ ቀኖናውንም ታሪኩንም የሚጥስ ስለሆነ ነው እንጂ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ቦታቸው እንዳይመጡ የጠላ ማንም የለም፡፡ ሁሉም ሰላሙን ፈልጓል፡፡ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ሃገር መጥተው በፈለጉበት ቦታ መቀመጥ ይችላሉ፡፡ ሰላሙ ተመስርቶ በውጭ የሚገኙ አባቶቻችን አዚህ መጥተው የመምረጥም የመመረጥም ዕድል ይኖራቸዋል፡፡በፈለጉበት ቦታ እንደማንኛውም ሰው ገብተው መቀመጥ ይችላሉ በማለት በአንድ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ደግመው አረጋግጠዋል።
አባ ሕዝቅኤል እውነት ለመናገር የማይደፍሩ በተለያዩ ሚዲያዎች እንኳን ለሚቀርብላቸው ጥያቄ አስተያየታቸውን  ለመናገር ቀጠሮ የሚያበዙ ነገሮችን በማድበስበስ ግልጽ አማርኛ ለመናገር ቋንቋ የሚያጥራቸው ግለሰብ ናቸው ታዲያ በምን መመዘኛ ነው አባ ሕዝቅኤልን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ቆሙ የምንለው?