Wednesday, January 9, 2013

እውነቱ የቱ ነው? (ከዚህ በፊት የቀረበ)

መነሻ ሃሳብ «ገመና 81» መጽሐፍ

  ሀተታ

በኦርቶዶክሳውያን  ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከታች ጀምሮ እስከላይኛው እርከን ድረስ ያለው ሰው ስህተት ይኖርብናል ወይም ልንሳሳት እንችላለን ብሎ የሚያስብ ማግኘት አዳጋች ነው። በክርስቶስ ደም የተመሰረተችው ቤተክርስቲያን ፍጽምትና ንጽሕት መሆኗን በመቀበል እንዳለ መሪውና ተመሪው ራሱንም በዚያው ዓይን እያየ እኛ ፍጹማንና ንጹሐን ነን በሚል ከለላ ስር ራሱን በማስጠለል፤ ስህተትን አምኖ ለመቀበል አይፈልግም። የስህተት አስተምህሮ አለ፤ በእግዚአብሔር ቃል ሲመረመር አደጋው የከፋ ነው፤ የክፉ መንፈስ አሰራር ወደማወቅ እንዳንደርስ ቃሉን በክሏል ሲባል የሚሰጠው ምላሽ፤ 2000 ሺህ ዘመን የኖረችን ቤተክርስቲያን ዛሬ የተነሱ አፍቃሬ ተሐድሶ መናፍቃን ሊያርሟትና ሊበርዟት ይፈልጋሉ በማለት ታፔላ መለጠፍ ይቀናቸዋል። የስም ታፔላ መለጠፍ ብቻ ሳይሆን ሽልማት የሚያሰጥ ቢሆን ኖሮ የተመረጡና ለመስማት የሚዘገንኑ ስድቦችና ዛቻዎች ይዥጎደጎዳሉ።
በእርግጥ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ፍጽምትና ንጽሕት መሆኗ አያጠራጥርም። ምክንያቱም የመሠረታት በዓለቱ ላይ በፈሰሰው ደሙ ነውና። ይህ እውነት ቢሆንም በክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ አባል ሆነው የሚኖሩት የአዳም ልጆች መሆናቸውንም በመዘንጋት የቤተክርስቲያኗን መንፈስና ባህርይ እንዳለ ወደሰዋዊ ማንነት በመውሰድ እኛ ፍጹማንና ንጹሐን ነን በማለት ከስህተት አልባነት የቤተክርስቲያን ማንነት ጋር ራስን መቁጠር ትኩረት የሚያሻው መሆኑን ልናሰምርበት ይገባል። በእርግጥም የተጠራነው ፍጽምት በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ ፍጹማን እንድንሆን ነው። ነገር ግን ሰው ከተፈጠረበት ማንነት የተነሳ በፍጽምቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ ፍጹም ሆኖ መኖር የሚችል ማንነት የለውም።
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑን የሚችሉት የገላትያ ሰዎች ማንነት ነው። የገላትያ ሰዎች በክርስቶስ አዳኝነት አምነው ወደ ሕይወት መንገድ የተመለሱ ሕዝቦች ነበሩ። ፍጽምትና ንጽሕት በሆነች የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ተጨምረው የቆዩ ሆነው ሳለ ሰብአዊ ማንነታቸው አሸንፎአቸው ወደስህተት መንገድ በመግባታቸው በሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ የተወቀሱ ሕዝቦች ሆነዋል።
«የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነውገላ 31
ክርስቶስ ኢየሱስ በፊታቸው የተሰቀለ ሆኖ በእምነት ይታያቸው የነበሩት ሕዝቦች ከዚያ የቅድስና ማንነት ወርደውና እውነትን በመተው፤ የጠላት አዚም የወረደባቸው  ሕዝቦች እስከመሆን መድረሳቸውን ሲናገር እናያለን። ሥራቸውን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የጀመሩ ሆነው ሳለ ቁልቁል ተመልሰው የሥጋን ሃሳብና እውቀት ወደማመን መመለሳቸው በእርግጥም አሳዛኝ የሰው ልጆች ማንነት ማሳያዎች እንደሆኑ የሚያስገነዝበን  ነገር ነው።
«እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁንገላ 33 ይላል።
እንግዲህ ክርስቲያኖች ፍጽምትና ንጽሕት በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እምነታቸውን ሊጀምሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህንን ፍጽምና ወደአለማወቅ መመለስም ሊታይባቸው ይችላል። ምን ጊዜም ቢሆን የስህተት መንፈስ አገልግሎቱ፤ የእውነቱን መንፈስ ከሰው ልቡና ላይ በመውሰድ ወደስህተት መንገድ መምራት ስለሆነ በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሉ ሰዎች ውስጥ የስህተት አስተምህሮ እንደሚገባ እናረጋግጣለን።
ብዙዎች የአብያተ ክርስቲያናት አባላት በክርስቶስ ፍቅር ላይ ጸንተው ከመቆም ይልቅ ወደ ምድራውያንና ሰማያውያን ፍጥረቶች ፍቅራቸውን ስለለወጡ የሕይወት መንገድን ስተው መገኘታቸው እውነት ነው።
ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ልጁን ወደ ተሰሎንቄ የላከበት ዋናው ምክንያትም ተሰሎንቄዎች  ከእምነት ጽናታቸው ወደኋላ እንዳይመለሱ በመንፈስ ያበረታታቸው ዘንድ ነበር። ምክንያቱም ፈታኝ የምንጊዜም አዚሙን የሚያፈሰው  የአማኞችን ልቡና በማደንዘዝ ወደ አልሆነ አቅጣጫ መመለስ  ሥራው ስለሆነ ከዚህ ፈታኝ ይጠበቁ ዘንድ እንደላከላቸው ቅዱሱ ወንጌል ይነግረናል።
«ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ። ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ» 1 ተሰ 35

ከከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል ተብለው የሚጠሩ መነኮሳት በዋሻና በፍርክታ ገዳም መስርተው ሰው ሁሉ ወደዚያው እንዲከትም ከማድረግ ውጪ ሀገር ላገር ዞረው፤ እንደሐዋርያቱ ወንጌል ላልበራለት ሕዝብ ወንጌልን ስለማስተማራቸው የሚታወቅ ነገር የለም። ወንጌል ለሕዝቡ የበራ ቢሆንማ ኖሮ እስከዛሬ በዛፍ ስር ቡና የሚደፉ፤ ደም የሚያፈሱ፤ቅቤ የሚቀቡ፤በጨሌ፤ ቆሌና የቤት ጣጣ አምልኮ ሰርጾባቸው የሚኖሩ ባልኖሩ ነበር።  እምነት አለን፤ አውቀናል የሚሉት እንኳን እስከፕሮቴስታንት መምጣት ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን አያውቁትም። ደረትን ነፍቶ ኦርቶዶክሳዊ ስለመሆን አረጋጋጭ ከሆኑት ከድርሳናት ውጪ መጽሐፍ ቅዱስን ይዞ መገኘት በራሱ ኮትልኳል ወይም ጰንጥጧል የሚያሰኝ በመሆኑ ይዞ መገኘት ያሳፍር ነበር። ይህ በእድሜአችን ያየነው እውነት ነው። አንዳንዶች «ሳያዩ የሚያምኑ ብጹአን ናቸው» የሚለውን ቃል ጠምዝዘው ራሳቸው ለመሸንገያነት በመጠቀም አንድም ሐዋርያ ሳይመጣ ያመንን ስለሆንን ቃሉ እኛን ኢትዮጵያውያንን ያመለከታል ለማለት ቢፈልጉም የሐዋርያ ወይም የሰባኪ አለመምጣት እንደ ጉዳት እንጂ እንደጠቃሚ ነገር መቁጠር አለማወቃችንን የሚያሳይ ነው። መጽሐፍ የሚለን እውነት ይህንን ነው።
«እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉሮሜ 1014
እንደዚሁ ሁሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እውነተኛ ወንጌል በማስተማርና ሕዝቡን ከክርስቶስ ወንጌል ጋር በማስማማት እንዲኖር ለማድረግ እስከሞት ድረስ ከታገለው ከአባ እስጢፋኖስ በቀር ግብጻውያንም ጳጳሳት የሰሩት የወንጌል አገልግሎት አልነበረም። ወንጌል ሥራው በግጻዌ ምድቡ በጥቅስ ደረጃ በየሥርዓተ ቅዳሴው ላይ ተመርጦ ከሚነበብ ውጪ ከተአምረ ማርያምና ከድርሳናት እኩል መድረክ አልነበረውም። አቡነ ቴዎፍሎስ የወንጌልን አስፈላጊነት በማመን አዳሪ /ቤቶችን በማጠናከር፤ ሰንበት /ቤቶች በማቋቋምና በቃለ ዓዋዲ እንዲደነገግ እስኪያደርጉ ድረስ አብያተ ክርስቲያናት በግእዝ ቀድሰው፤ በግእዝ አንብበው፤ ለዓለመ ዓለም ካሉ በኋላ እግዚኦ መኀረነ ክርስቶስ እንበል 12 ጊዜ ብለው ጣት ከማስቆጠር ባለፈ ህዝቡ ወንጌልን እንደማያውቅ ጠንቅቀን እናውቃለን።
 እንዲያውም ወንጌል እቃ ግምጃ ቤት ገብቶ የሸረሪት፤ የአቧራና የአይጥ ቀለብ ሲሆን በአንጻሩ ልፋፈ ጽድቅ በየአንገት ላይ የሚንጠለጠል ክቡር መጽሐፍ ሆኖ ለዘመናት ኖሯል። ዛሬም እስከመቃብር ድረስ አብሮ የሚወርድ፤ ክቡር አዳኝ መጽሐፍ ሆኖ መቆጠሩን አላቋረጠም። የዲቁናም ይሁን የቅስና ማእርግ የሚሰጠው ሥርዓተ ቅዳሴውንና ኩሳኩሱን ከመልክዓ መልክዑ ጋር መሸምደዱ እንጂ ወንጌልን ተንትኖ ሕይወት የሚገኝበትን ቃል ማስተማር ስለሚችል አይደለም። 
ከዚህ በታች የምናቀርባቸው መጽሐፍ ቅዱሳችን በምንለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ ስህተቶች፤ ነገር ግን እውነት እንደሆኑ ቆጥረን የምንከራከርላቸው ሲሆኑ ችግሩን እንደችግር ያለመቁጠራችን ዋና ምክንያት ከላይ በሀተታ እንደዘረዘርነው አንድም እኛ ፍጽምትና ንጽሕት በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለን ስህተት አልባዎች ነን ከማለት የመነጨ ሰውኛ ማንነትን ካለመቀበል ችግር፤ አንድም- ክርስቶስ ከፊታቸው ተስሎ የነበሩት ገላትያውያን እንደሆኑት የሆነ አዚም አደንዝዞን እውነትን ለመቀበል ባለመፈለግ፤ አለያም ሳያዩ የሚያምኑ……በሚለው የሽንገላ ቃላት ተሸውደን እውነተኛውን የክርስቶስ ወንጌል የሚሰብክ እንዲኖረን ባለመፈለግ ራሳችንን ስናሞኝ በመኖራችን ይሆናል።

 የስህተት ትምህርት አስረጂዎች፤

ብዙውን ጊዜ «ከእውነተኛ የወንጌል አስተማሪዎች እጦት የተነሳ» /ከአስተማሪዎች እጦት የተነሳ አላልኩም/ ሕዝቡ እስካሁን ለወንጌል ቃል አዲስ በመሆኑ አሳማኝ መልስ መስጠት ስለማይችል እንደችግር መፍቻ መፍትሄ የሚጠቀምበት መንገድ በመሳደብ፤በማሳደድ፤በማሽሟጧጥ፤ በመደባደብ ብሎም በመግደል  ልዩ ለሆነ ሃሳብ ሁሉ ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል። አሁንም ይህ አድራጎት አላቋረጠም። ከዚህ በታች ለሚቀርቡ አስረጂዎች ምላሽ መስጠት የሚችል አንድም ሰው እንደሌለ እርግጠኞች ስንሆን የሚሳደብ ወይም የሚያንቋሽሽ ክርስቲያኖችን ግን በሺህዎች እንጠብቃለን።
 
   1/ ስለታቦተ ጽዮን ትረካ፤
1,1  ስለታቦተ ጽዮን አመጣጥ ታሪክ የሚናገረውን  «ክብረ ነገሥት» የተባለውን መጽሐፍ ማኅበረ ቅዱሳን ውሸታም ብሎታል።

ማኅበረ ቅዱሳን ትውፊትንና ባህልን፤ ልምድንና አምልኰትን ለይቶ የማያውቅ የጅምላ እምነት አራማጅ መሆኑ ሲታወቅ፤ ራሱ እገዛበታለሁ የሚለውን ትውፊት ሲሽር እንጂ ሌሎች ሲሽሩ ዓይኑ ደም የሚለብስ አስቸጋሪ ድርጅት ነው። እንደሚታወቀው ግራሃም ሐንኰክ የተባለ እንግሊዛዊ ምሁር /The sign of the seal/ በሚል ርእስ // 1992 / ያሳተመውን መጽሐፍ ይህ የትውፊት ጠበቃ ነኝ የሚለው የጅምላ እምነት አራማጅ ማኅበር፤ /ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ/ በሚል ርእስ በጌታቸው ተስፋዬ አስተርጉሞ ያሳተመው መጽሐፍ  እንደሚተርከው ታቦተ ጽዮን በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን በልጁ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ በቀዳማዊ ምኒልክ እጅ ሳይሆን ወደኢትዮጵያ የመጣው በግብጽ ኤሌፋንታይን አቋርጦ ከዓመታት ቆይታ በኋላ የዓባይን ሸለቆ ተከትሎ ቀስ በቀስ በጣና አድርጎ ነው የገባው በማለት ይናገራል። ስለዚህ «ክብረ ነገሥት» ስለታቦተ ጽዮን አመጣጥ የሚተርከው የእነ ቀዳማዊ ምኒልክ ታሪክ በውሸታምነቱ ተመዝግቧል ማለት ነው። ማኅበረ ቅዱሳን የታቦተ ጽዮንን አመጣጥ በግራሃም ሃንኰክ አተራረክ መሰረት የሚያምን ከሆነ ክብረ ነገሥትን ትረካ ዋጋ ቢስ ያደርገዋል። የሚገርመው አንድም የሊቃውንት ጉባዔ ይሁን የጳጳሳቱ ዓለም የክብረ ነገሥትን ትረካ የሚቃወመውን የማኅበረ ቅዱሳን እትም መጽሐፍ ሲያወግዝ ወይም ታሪካችንን አፋልሷል ሲል አልተሰማም። ስለዚህ የክብረ ነገሥትን ውሸታምነት አጽድቆታል ወይም የማኅበረ ቅዱሳንን የትርጉም አተራረክ ለመከላከል አቅም አጥቷል። ከዚህ አንጻር ስለታቦተ ጽዮን አመጣጥ የሚናገር የተለያየ ሃሳብ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ስላለ እውነተኛው የትኛው እንደሆነ ለጊዜው አይታወቅም ማለት ነው።
 
1,2/ ታቦተ ጽዮን ወደኢትዮጵያ አልመጣችም በማለት መጽሐፈ እዝራ ካልዕ ይናገራል።

ከላይ እንዳስቀመጥነው ማኅበረ ቅዱሳን ክብረ ነገሥትን ውሸታም በማለት በግብጽ በረሃ አድርጋ ነው ታቦተ ጽዮን የመጣችው የሚለውን የግራሃም ሃንኰክን መጽሐፍ ለተከታዮቹ ሲያከፋፍል የምንረዳው ሁለት የተለያየ የአመጣጥ ትረካ መኖሩን ነበር። ይሁን እንጂ ሰማንያ አሀዱ በተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጽሐፈ እዝራ ካልዕ ምዕራፍ 1 ቁጥር 54 ላይ እንዲህ በማለት ከላይ የቀረቡትን ሃሳቦች ሁሉ ውድቅ በማድረግ ታቦተ ጽዮን ወደኢትዮጵያ እንደመጣች ሳይሆን ወደባቢሎን መሄዷን በግልጽ ይናገራል።
«እግዚአብሔርን የሚያገለግሉበትን ንዋየ ቅድሳቱንና ጥቃቅኑንና ታላላቁን ዕቃ ሁሉ የእግዚአብሔር ማደሪያ ታቦትንም፤ ከቤተመንግሥት ዕቃ ቤት ያለውን ሣጥኑንም ሁሉ ማርከው ወደ ባቢሎን ወሰዱ» እዝራ ካልዕ 154
ናቡከደነጾር 634-562 / የነበረ የባቢሎን ንጉሥ ሲሆን እርስ በእርሳቸው ያልተስማሙት የክብረ ነገሥትና የታቦተ ጽዮንን ፍለጋ መጻሕፍት ትረካ ውድቅ በማድረግ ወደ ባቢሎን ማርኰ ስለመውሰዱ ሰማንያ ወአሀዱ የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ አፖክሪፋ መናገሩ ነገሩን ሁሉ መያዣ መጨበጪያ የሌለው አድርጎታል። አሁን እንግዲህ ሊነሳ የተገባው ጥያቄ፤

Ø  ክብረ ነገሥት የተባለው መጽሐፍ ነው ትክክል?
Ø  ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ የተባለው መጽሐፍ ትረካ ነው ትክክል? ወይስ
Ø  የለም! ሁለቱም የሚሉት ትክክል አይደለም፤ ታቦቱ ወደባቢሎን በምርኰ ተወስዷል የሚለው የመጽሐፈ እዝራ ካልዕ ቃል ነው ትክክል?

 1,3/ መጽሐፈ ነገሥትም እስከ ባቢሎን ምርኰ ድረስ ታቦቲቱ ኢየሩሳሌም እንደነበረች ይናገራል።

 ሌላው ስለ ታቦተ ጽዮን በንጉሥ ሰሎሞን  ዘመን ወደኢትዮጵያ መጣች የሚለውን አባባል ውድቅ የሚያደርገው አስረጂ 300 ዓመት ቆይታ በኋላም በኢዮስያስ ዘመን/ 649-609 // ኢየሩሳሌም  እንደነበረች መጽሐፍ ቅዱስ መናገሩ ነው። የሕጉ መጽሐፍ መነበቡን/ 2 ነገ 228/ ንጉሡ የሕጉን መጽሐፍ ሲሰማ ልብሱን መቅደዱን /2 ነገ 2211/ የእግዚአብሔር ቤት ይጠገን ዘንድ ማዘዙን /2 ዜና 3410/ ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት በመቅደሱ እንዲያኖሩት ማድረጉን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
«እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለእግዚአብሔርም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ፦ ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ» 2 ዜና 353
እንደእኛ እምነት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ስለማይሳሳት መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃወሙ መጻሕፍት ሁሉ ስሁታን ናቸው።

    2/ ዲያብሎስ  የወደቀው በትዕቢቱ  አምላክ  ለመሆን ስለፈለገ ነው ወይስ  ለአዳም ስገድ ተብሎ  እምቢ በማለቱ ነው?

 እንደቤተክርስቲያን አስተምህሮ ሰይጣን እስከነሠራዊቱ የወደቀው በመታበዩ ምክንያት እንደሆ ነው። ትንቢተ ኢሳይያስ 1412
«አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህይለዋል።
ራሱን የሁሉ ገዢ ለማድረግ ልቡናው ስለተነሳሳ በስሁት መንፈሱ ለውድቀት ተዳርጓል የምትል ቤተክርስቲያን፤ «የለም! ሰይጣን የወደቀው ለአዳም አልሰግድም ስላለ ነው» የሚል አስተምህሮ ይዛ መገኘቷ ነገሩን ሁሉ አስገራሚ ያደርገዋል።

2,1 መጽሐፈ መቃብያን ለአዳም ስላልሰገደ ዲያብሎስ ወደቀ ይለናል።

 እንደዚህ የሚል ትምህርት በቤተክርስቲያናችን የለም የሚል ሰው ቢኖር ቁጥሩ ከአፖክሪፋ የሆነውንና እንደመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክፍል እንዲቆጠር በግድ የተበየነበትን መጽሐፈ መቃብያንን አያነብም ወይም ስለተሸከመው ብቻ የገባው ይመስለዋል ከማለት ውጪ ምን ልንል እንችላለን።
«የሚጠፉ በኔም የሚስቱ ሰዎች ፈጽመው ይበዙ ዘንድ፤ የአዳምም ልጆች ይጠፉ ዘንድ፤ ይህንን በተናገሩ ጊዜ እኔ ደስ ይለኛል፤ ለሚዋረድልኝ ለአዳም አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለአባታቸው ስለአዳም ከማዕረጌ አዋርዶኛልና፣ 3 መቃ 115
«ክሳደ ልቡናውን በማጽናትና ራሱን በማኩራት ፈጣሪው ለፈጠረው ለአዳም መስገድን እንቢ እንዳለ» 2 መቃ 91-3
ዲያብሎስ የወደቀው ለአዳም አልሰግድም ብሎ እምቢ በማለቱ ነው የሚል ይህ እንግዳ ትምህርት ከእውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር በፍጹም ተቃራኒ ነው። በባለፈው ጽሁፋችን ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር በመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ቁጥርና ዓይነት የምንለያይበትን መንገድ ለመጠቆም መሞከራችን አይዘነጋም። ግብጾች ወርቁንና ብሩን ከጫንላቸው የቱንም የስህተት መንገድ ብንከተል ጉዳያቸው እንዳልነበር የሚያሳይ ነገር ነው። እነሱ ይህንን የመቃብያን መጽሐፍ ከቅዱስ መጽሐፍ አካል ያልቆጠሩት ይህንን የመሰለ ስህተት እንዳለበት ስለሚያውቁ ይሆናል።
ዲያብሎስ የወደቀው ለአዳም አልሰግድም በማለቱ ነው የሚለው የመቃብያን መጽሐፍ የሚመሳሰለው ከቁርዓን ጋር ነው። ቁርዓን እንዲህ ይላል።
 
2,2 ቁርዓንም  እንደመቃብያን ይናገራል።

ሱረቱል አልበቀራህ ወይም የላም ምዕራፍ 2 34
وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ أَبَى وَاسْتَكْبَرَ وَكَانَ مِنَ الْكَافِرِينَ ንባቡም ይህንን ይመስላል።
Waith qulna lilmalaikati osjudoo liadama fasajadoo illa ibleesa aba waistakbara wakana mina alkafireena
ወደአማርኛ ሲመለስ፤
«ለመላእክትም ለአዳም ስገዱ ባልን ጊዜ (አስታውስ) ሁሉም ወዲያው ሰገዱ። ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ኮራም ከከሀዲዎቹ ሆነ» ማለቱ ነው።
እንግዲህ ቁርዓንና መጽሐፈ መቃብያን ዲያብሎስ እንዴት እንደወደቀ አንድ ዓይነት ቃል ይዘዋል። እሱም  ለአዳም ስገድ በተባለ ጊዜ እምቢ በማለቱ  ነው ይሉናል።  ሊቃውንቱ ስለመቃብያን መጽሐፍ  ከቁርዓን ጋር መመሳሰል ምን ይላሉ? ግብጻውያን እነሱ  ያልተቀበሉትንና  ያልፈለጉትን  መጽሐፍ  ጭነውብን  ነው ወይስ  ለእኛ ለኢትዮጵያኖች ለብቻችን መቃብያን መጽሐፍ ከሰማይ የወረደልን ሆኖ ይሆን?
ዲያብሎስ  ለአዳም  እንዲሰግድ  የታዘዘውስ  መቼ ነው? ይህስ  ከየት የተገኘስ  አስተምህሮ  ነው?

    3/ ለሰዎች በጥቁርና ቀይ ቀለም መጻፍ ያስተማረው አጋንንት ነው?

ለዚህ ጥያቄ  መቼም አዎን! የሚል ምላሽ ቢሰጥበት ሰዎች መቃወማቸው እርግጥ ነው። ምክንያቱም  ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ በጥቁር ወይም  በጥቁርና  ቀይ መጻሕፍት  እያዛነቁ  መጻፍ የተለመደ ስለሆነ የጥቁርና  ቀይ ቀለማትን ምንጭ  ከአጋንንት ጋር ማያያዝ ትክክል ነው  ማንም  ሊል እንደማይችል ይታሰባል። ይሁን እንጂ የግብጽ ኦርቶዶስክ ቤተክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የማትቆጥረው መጽሐፈ  ሄኖክ  የተባለው  አፖክሪፋ / */በቀይና በጥቁር ቀለም መጻፍ ለሰው ልጆች ያስተማረው አጋንንት ነው ይለናል። መጽሐፈ ሄኖክ 1922-24 ይመልከቱ። እንግዲህ ለመልካም ይሁን ለጥፋት በዚህ ዘመን የሰው ልጅ የሚጠቀምበት የመጻፊያ ጥቁርና ቀይ ቀለም ተጠቃሚዎች ሁሉ የአጋንንት ተማሪዎች ናቸው ማለት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ተስፋ /ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋና ትንሣዔ ዘጉባዔ ማተሚያ  ቤቶች ይበልጥ ተጠያቂ ናቸው ማለት ነው።
ይሁን እንጂ የጽሕፈት፤ የፊደላትና የእውቀት ባለቤት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንጂ  አጋንንቶች ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። ሰዎች የተሰጣቸውን እውቀት ላልተፈለገ  ዓላማ ሊገለገሉበት  ይችላሉ እንጂ አጋንንት የአዳምን ልጆች የጽሕፈት እውቀት አስተማሩ ማለት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ሰውን የአጋንንቶች ወዳጅ አድርጎ የሚያቀርብ  የክህደት አስተምህሮ ነው። ቋንቋን ለሰጠ እግዚአብሔር፤ የቋንቋ መጻፊያ ቀለማትን ሰይጣን በመፍጠር በምንም መልኩ አጋዥ ሊሆን አይችልም።  ቤልሆር ከክርስቶስ ጋር ምንም ኅብረት የለውምና።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር  ለነቢያቱ ይህን  ጻፉ፤ እንዲህም ጻፉበት እያለ የጽሕፈት ባለቤትነቱን  ይመሰክርለታል።
     «ሙሴም  የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ ማለዳም ተነሣ» ዘጸ 244
    «ሙሴም በዚያ ቀን ይህችን መዝሙር ጻፈ፥ ለእስራኤልም  ልጆች አስተማራት» ዘዳ 3122
    «አንድ  የመጽሐፍ  ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም  ከተናገርሁበት  ቀን ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ  በእስራኤልና በይሁዳ ላይ በአሕዛብም  ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት» ኤር 362
    «ዳግመኛም  ሌላ  ክርታስ ውሰድ፥ የይሁዳም  ንጉሥ ኢዮአቄም  ባቃጠለው  ክርታስ  ላይ የነበረውን  የቀድሞውን ቃል ሁሉ ጻፍበት» ኤር 3628

እጅግ ብዙ አስረጂዎችን  ማቅረብ ይቻላል።  እውነትን  ለመግለጥ በቂ ነውና በሄኖክ ስም ራሱን በእግዚአብሔር ቦታ አስቀምጦ እኔ ለሰው ልጆች እውቀትን የሰጠሁ ነኝ የሚለው ክፉ መንፈስ ግን በእግዚአብሔር ቃል የተሳሳተ አስተምህሮ ነው። አጋንንት ጽሕፈትን እንዴትና መቼ  እንዳስተማሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ  የሚያቀቡ አስረጂ ወዳጆች ካሉት  ለመስማት ዝግጁ ነን። ይሁን እንጂ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  እጅግ  የምታደንቀው  የሃይማኖት አባት አትናቴዎስ የማያውቀውንና የኮፕት ቤተክርስቲያንም  እንደቅዱሳት መጻሕፍት የማትቀበለውን መጽሐፈ ሄኖክ   የመምህርነቱን ስፍራ  ለአጋንንት ሰጥቶት ይገኛል። የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንስ ያልተቀበለችው ለምን ይሆን?

 3/ ዲያቆናት ጥርስ  ማፋጨትና እሳቱ ወደማይጠፋ ቅጣት ይወርዳሉ የሚል ትምህርት ዉሸት ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ላይ የተሰጣቸውን መክሊት አራብተው ለባለቤቱ ዋናውን የመለሱ ሠራተኖችን ማንነት የሚገልጽ ቃል አለ።
(የማቴዎስ ወንጌል 2514-30 ያለውን ይመለከቷል)
በቁጥር 15 ላይ «ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ» ይላል። እነዚህ ሰዎች በተሰጣቸው መክሊት አትርፈው ዋናውን ለባለዋናው መመለስ በሚገባቸው ወቅት የተገኘባቸው ትጋት እንዲህ ተቀምጧል።
« አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ፈራሁም ሄጄም  መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ»
በዚህ ውስጥ ያተረፉት ሲሾሙና ሲሸለሙ፤ ያላተረፈውን ባለአንድ መክሊት ባሪያ  ግን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት እሳት መጣሉን ቃሉ ይናገራል። ይህንን ቃል አንድምታ በተባለው ትርጉም  ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል ተቀምጧል።
ባለአምስት መክሊቱ  ሊቀጳጳስ ነው፤ ባለሁለቱ መክሊት በቄስ  ይመሰላል፤ ባለአንድ መክሊቱ ደግሞ በዲያቆን ይመሰላል በማለት እጣ ፋንታውን በቤተክህነቱ የስልጣን  እርከን መሠረት ይደለድላል። በዚህ ድልደላ መሠረት ዲያቆናት « ወለገብርሰ ዘእኩይ» ተብለው እድል ፈንታቸውም  የዘላለም እሳት እንደሆነ የተቀመጡበት የሥልጣን እርከን ድልድል በፍጹም ትክክል አይደለም። (ወንጌል ቅዱስ ንባቡና ትርጓሜው 1916 /)
 በዚህ ዘመን ያለውን ግብር  ተመልከተን ብንመዝን በያዙት ሥልጣንና ኃላፊነት ደረጃ ተጠያቂ በመሆን የሚወዳደራቸው የማይኖረው ለራሳቸው የባለአንድ  መክሊቱን ሥፍራ  ቆርሰው የያዙት በሆኑ ነበር። ለተልእኰ  በመፋጠንና ከሙጋድ ጭስ  ጋር ሲታገል የሚኖረውን ዲያቆን ገብር ሀካይን ደረጃ ሰጥተውታል።  ለምን?
ስናጠቃልል እስካሁን ለዘረዘርናቸው መጠይቅ  መላሾች እውነቱ የቱ ነው? በማለት እንጠይቃለን።  ስህተት ካለብን ያለ እውቀት  ስለሃይማኖት በማክረር  ከማሽሟጠጥ ይልቅ ምራቅ ዋጥ እንዳደረገ ሰው እውነቱን ይገልጥ ዘንድ ይፈለጋል። ያ መሆን ካልቻለ እውነቱን ለመቀበል ባንፈልገውም  እውነት ምን ጊዜም  እውነት  እንደሆነ ሲኖር ውሸትም ለእውነት ጊዜውን ጠብቆ ሥፍራውን መልቀቁ አይቀርም።
«ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና» 2ኛ ቆሮ 13፤8