Saturday, January 12, 2013

ያቆመንና ሊያቆመን የሚቻለውን ትተን ማንን ስንይዝ መቆም ይቻለናል?

ብዙ መጠላላትና መነቃቀፍ ብዙ ቦታ ተሰጥቶት መገኘቱን በየእለት ውሎአችን እናያለን።  እውነት፤ እውነቱን መነጋገር ቢቻልም መነቃቀፍ በበዛበት ዓለም እውነቱን በእውነታ ለመቀበል የሚቸገርም ሞልቷል። የሚቀበል ቢኖርም፤ ባይኖርም እውነት ነው ብለን ያመንበትን መናገር እንዳለብን ስለምናምን መናገራችንን አናቋርጥም። ዛሬም በዚህ ጽሁፋችን የምናውቃቸውን እውነታዎች፤ አንዳንዱ እውነት ነው ብሎ እንደሚቀበልና የዚህ ተጻጻሪው ደግሞ ጥላሸት በመቀባት ልምዱ የቆመበትን ስፍራ በቃሉ እንደሚያሳየን በማሰብ ጥቂት ለመግለጽ  የምፈልጋቸው ነገሮች አሉን። ጽሁፋችንም በቤተክርስቲያናችን ዙሪያ ያጠነጥናል።

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእምነት ዓምድ /ዶግማ/ ማለትም ምሥጢረ ሥላሴን አብርታ፤ አምልታና አስፋፍታ በማስተማር፤ እንዲሁም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሥጋ የለበሰበትን ረቂቅ ምሥጢር ፤ ምሥጢረ ሥጋዌውን አብራርታ በመስበኳ የታነጸችበትን ሃይማኖታዊ አለት/ ኰክሕ/ ስንመለከት በእውነትም የእግዚአብሔር ደጅ ናት ብንላት ቢያንሳት እንጂ አይበዛባትም። በክርስቶስ መሠረት ላይ የታነጸች፤ በሐዋርያት ትምህርት ያደገችና በሊቃውንቱ በእነአትናቴዎስ፤ ባስልዮስ፤ ጎርጎርዮስ ወዘተ የምሁራን አስተምህሮ የበለጸገች መሆኗን ማንም ሊክደው የማይችል የታሪክ እውነት ነው።

ዳሩ ግን ይህንን መሠረቷን የሚንዱ፤ ወንጌሏን ወደጎን የሚገፉ፤ አጋንንታዊ ልምምዶችን በስመ ሥሉስ ቅዱስ የሚያስፋፉ፣ ተከታዮቿ ዓይናቸውን ከክርስቶስ ላይ ነቅለው በየምናምኑ ላይ  እንዲተክሉ የሚያበረታቱ ብዙ አሳዛኝ መጻሕፍት በተረት፤ በእንቆቅልሽ፤ በወግና በአስማት ተሸፍነው የቤተክርስቲያኒቱን የወንጌል አስተምህሮ ማእድ በመበከል መርዛቸውን ታቅፋ እንድትኖር መገደዷን አስተዋዩ በደንብ ሲረዳው፤ እልከኛውም  በአፉ ለመመስከር ያቅተው እንደሆን እንጂ ችግር እንዳለ ልቡናው እንደሚመሰክርበት እናስባለን። 

ልበ ጠማሞች ደግሞ «በድሮ በሬ ያረሰ የለም» የሚለውን ብሂለ አበውን ከአፋቸው ሳያወርዱ ፤ በዚያው መራር አፋቸው ደግሞ በድሮ ስር ለመደበቅ «የቀደመውን ድንበር አታፍርስ»  ከማለታቸውም በላይ ከእኔ ወዲያ ለአባቶቼ ርስት ቀናዒ የለም! በሚል የኩራት ካባ በመደረብ የቤተክርስቲያኒቱን የወንጌል ማእድ የመረዙትን ህጸጾች መነካት የለባቸውም በማለት የግብር አባታቸውን ሥራ ተረክበው ሳያስተጓጉሉ  ለማስጠበቅ ሲታገሉ ኖረዋል፤እየታገሉም ይገኛሉ ። ደግሞ እናንተ እነማን ናችሁ? በማለት ለጥያቄዎች መልስ የመስጠት ብቃቱ ሳይኖራቸውና መልስ ይሰጡ ዘንድ ማንም ሳያስቀምጣቸው ራሳቸውን ሰይመው መገኘታቸውም የሚገርም ነው።
 
ቀጥተኛይቱን አርቶዶክስ ያጎበጡ ሸክሞች በቃለ እግዚአብሔርና በሊቃውንቱ ይመርመሩ፤ ይታረሙ ማለት ቤተክርስቲያኒቱን እንደማፍረስ አድርገው የሚቆጥሩ ቢኖሩ አያስገርምም። ምክንያቱም እነዚያን ጉድለቶች ባሉበት እንዲኖሩና ወደቀደመው ውበቷ እንዳትመለስ የሚፈልገው መጻሕፍቱን ያስገባው ክፉ መንፈስ በሰዎች አድሮ እስከመጨረሻው ድረስ እንደሚከራከር ይታወቃልና ነው። እንኳን በሥጋ ድካም የምንሸነፈው እኛን  ይቅርና ሰማያዊ አምላክ የሆነው ክርስቶስን፤ ሥጋ በመልበሱ ብቻ እንደደካማ ሰው ቆጥሮ፤ ጠላት ፵ መዓልት ከፆመበት ተራራ አንስቶ እስከ ቤተመቅደሱ ጫፍ ድረስ በፈተና ለመጣል ትግሉን አለማቆሙን ያነበብነው ቃል ብዙ ያስተምረናል። ዛሬም ቦታዬን ለቅቄ የትም አልሄድም በማለት የሚያደርገውን መታገል የሚያስፈጽሙለት ሊኖሩ የግድ ነው። ሌላው ወገን ደግሞ የስህተት አስተምህሮ አለ፤ የሚለውን ለመቀበል የማይፈልገው ከስህተት ጋር ተስማምቶ ለመኖር ስለፈለገ ሳይሆን ከእውቀት ማነስና ለቤተክርስቲያኒቱ ካለው ጅምላ ፍቅር የተነሳ ነው።

እዚህ ላይ የራሳችንን ድርሻ  ጥርት አድርገን መግለጹ አስፈላጊ ይመስለናል። የቀደመችውና ቀጥተኛዋ ኦርቶዶክስ ወንጌልን መሠረት ያደረገ አስተምህሮ እንዳላት ቅንጣት ያህል አንጠራጠርም። ለተሳሳቱ መልስ መስጠት የምትችል፤ ላላመኑ የምታሳምንበት ዶክትሪን ያላት መሆኗን ያለማመንታት እንቀበላለን። ክርስቶስን ማእከል አድርጋ የምታስተምር ቤተክርስቲያን እንደነበረች እውነት ነው። ወንጌል የሚያስተምሩ ገበሬዎች የተወለዱባት ቢሆንም የወንጌል ጠላት ለምድራዊ ሞት አሳልፎ መስጠቱንም ታሪክ ይነግረናል። አምልኮና ስግደት ለእግዚአብሔር ብቻ ያሉ እነእስጢፋኖስ በሰይጣን ጉዳይ ፈጻሚዎች ኢ-ክርስቲያናዊ ግፍ ተፈጽሞባቸው የወንጌል ፋይል ሳይዘጋ በፊትና ወንጌል ሥፍራውን ሰይጣንን እናስታርቃለን ለሚሉ ጸረ ወንጌል ስብከቶች ቦታውን ሳይለቅ በፊት ወንጌል ብቻውን ነግሶ ነበር።  ሰይጣን መነኮሰ፤ሰይጣን ተገዘረ፤ ሰይጣን ቀለም አስተማረ፤ ጀጀጀ፤ ጨጨጨ፤ ኤኮስ፤ ለማስ፤ኤነከምካም ………ወዘተ ዓይነት ትምህርት ቦታውን ተረክቦ ትምህርቱ ሁሉ በሚያስደነግጥ መልኩ ስለሰይጣን ደግነት የሚወራበትና ምንጩ ያልታወቀ አስማት የሚጠራበት ከመሆኑ በፊት ያለውን የቤተ ክርስቲያናችን ሕይወት መልካም ውበት እንደነበረው እናምናለን። 

ምንም እንኳን ያልታወቁ፤ ያልታረሙ፤ የተሳሳቱና አጋንንታዊ ልምምዶችን የሚያስፋፉ ስሁት ትምህርቶች የወንጌል ቦታውን የተረከቡ ቢሆን ወይም ከወንጌል ጋር እየተቀላቀሉ እንዳይታወቅባቸው በስመ ሥሉስ ቅዱስ ተሸፍነው ሲተላለፉ በመገኘታቸው ብናዝንም የቤቱ ቅናት የበላቸው እውነተኞቹ ሊቃውንቶች እንዲመለከቱትና እንዲያስተካክሉት ከመጣር በስተቀር ቤተክርስቲያንን ለጠላት አሳልፈን የምንሰጥ የማንም ቅጥረኞች አይደለንም። ክርስቶስን በምታውቅ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ልጆቿ  እናት ቤታቸውን ለቀው እንዲኮበልሉ በምንም መልኩ የምንፈልገው አይደለም። እንዲያውም «ኢየሱስን ተቀበሉ» እየተባሉ ድክመቶቿን እያዩ ሌሎች ያስከበለሏቸው፤ ልጆቿ ወደእናት ቤታቸው እንዲመለሱ እንታገላለን።  «አንድ ሳር ቢመዘዝ፤ ቤት አያፈስም» በሚል እልከኛና ትምክህተኛ መፈክር የተነሳ ልጆቿ ሲኮበልሉ ግድ ከማይሰጣቸው የሰይጣን መልእክተኞች በስተቀር አንድም ኦርቶዶክሳዊ ሲኮበልል ምንም የማይስማንና ግድ የማይለን ምንደኞች አይደለንም።  «ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም» እንደተባለው እናት ቤታችን የነፍስ ማእዱ ሞልቶላት ሳለ ጠላት የበተነውን አፈር የሚያነሳ በመጥፋቱና የመንፈስ እንጀራ የሚመግብ እውነተኛ መሪ ባለመገኘቱ የተነሳ የሚኮበልል በዝቶ ስናይ «ጌታ ሆይ ይህ እስከመቼ?» ብለን ወደሰማይ ማንጋጠጣችንን ስንናገር፤ እውነታውን የሚመለከት ዳኛ በሰማይ ስላለን አናፍርም። 

በሌላ መልኩም የቤተክርስቲያኒቱን  ምእመናን የሚጠብቅ፤ ንጹህ ውሃና ለምለም ሳር ወዳለበት የሚያሰማራ እረኛ በመጥፋቱ በላይ ያሉቱ እርስ በእርሳቸው የሚነካከሱና የሚካሰሱ ሆነው ሁለትና ሦስት ጎራ ለይተው ለየራሳቸው የአሸናፊነትን ሰይፍ ሲመዙ ስናይ ይበልጥ  እናዝናለን። ቤተክርስቲያኒቱ የስንዴ ክምር ሆና የዝንጀሮ መንጋ ትውልድ ሰፍሮባት እያፈረሰ ከመጋጡ በላይ የሚዘርፈው፤ የሚሸጠው፤ የሚለውጠው፤ እንደአፍኒንና ፊንሐስ በቅጽሯ የሚያመነዝር የአስነዋሪ ትውልድ መፈልፈያ ሆና ስናይም ልባችን ያለቅሳል። ተወልደን፤ባደግንባት ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደዚህ ዓይነት የመከነ ትውልድ ሆነን የመገኘታችን ምስጢር ምን ይሆን? ብለን እንጠይቃለን።

ለጥያቄያችን መልስ ያለውና መንገዱን የሚነግረንን ቃል ስንመረምር  ይህንን አግኝተናል። ደረቱን በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ፤ ጸጉሩም እንደበረዶ ነጭ የሆነ፤ ዓይኖቹም እንደእሳት ነበልባል የሚያበሩ፤ እግሮቹ እንደእቶን እሳት የነጠረ፤ የሰባቱን ከዋክብት ምስጢር የፈታው ንጉስ ለሰርዴስ ቤተክርስቲያን ጥፋቷ ከመምጣቷ በፊት እንዲህ ብሎአት ነበር።
«እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ፤ እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም።» ራእይ 3፤2  የሚለው ቃል ዛሬም መልእክቱ ለእኛ የሚሆን ይመስለኛል።
ቤተክርስቲያናችን የወንጌልን እውነትን እንዴት እንደተቀበለች እናውቃለን። ይህንን ጠብቃው መቆየት የተሳናት ደረጃ ላይ    ደርሳለች የሚያሰኙ ኩነቶች ቤተክርስቲያኒቱን ከበዋታል።   ስለዚህ ምን ይሻላል?  በቃሉ እንደተናገረን መፍትሄው ወደተቀበልነው እውነት መመለስ ብቻ ነው። ለዚህም በመመለስ ንስሐ እንግባ!  የሰርዴስ ቤተከርስቲያን ብዙ አባላት የነበሯት ቢሆንም ቃሉን ሰምተው ወደተቀበሉት እውነት ለመመለስ ንስሐ የገቡት ጥቂቶች ነበሩ። «ስሙን ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም» የተባለላቸው እነዚህኞቹ የድሉ ባለቤቶች መሆናቸውን የሰባቱ ከዋክብት ምስጢር ባለቤት  ይናገራል። የድሉ ባለቤቶች፤ ከሚዋሹ የሰይጣን ማኅበር የአንዳንዶቹን ልብ ማሸነፍ እንደሚችሉም ተነግሯል።

ያኔ ነው፤መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ» ሲል ለዛሬውም ጭምር እንደተናገረ ጆሮአችንን ከፍተን መስማት የምንችለው። ጆሮ ያለው ማንም ወደቀደመው እውነት እንመለስ የሚለውን ቃል ቢሰማ ለእውነት የሚከፍለው ዋጋ ነው፤ የቀደመውን የሚያስጥለንን እንጣልና ንስሐ እንግባ! ያኔ ችግሮቻችን ሁሉ ወድቀው እኛ እንደቀድሞው እንቆማለን፤ ያኔ ክፍፍላችን አክትሞ በአንዱ ጌታ ፈቃድ ስር ተሰባስበን በቤቱ እንተከላለን። ያለበለዚያ የሰርዴስ ቤተክርስቲያን የተነገራትን ስላልሰማች የሆነችውን ያየ በወንጌል ቃል መፈጸም ቢጠራጠር ለታሪክ ያለው እውቀት ዝግ መሆኑን ያሳያል። እኛም እየሄድን ያለንበት መንገድ የስምምነት፤ የፍቅር፤ የእውነት፤ የንስሐና የወንጌል መንገድ ባለመሆኑ ከታሪክ አለመማርም ይሆናል። «ብልጥ ከሰው ስህተት ይማራል፤ ሞኝ ግን በራሱ ስህተት ይማራል» እንዲሉ የሰባቱን ከዋክብት ምስጢር ከፈታውና መንፈሱ ለአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ጆሮ ያለው ይስማ! ካለው ቃሉ እንማር!
ያቆመንና ሊያቆመን የሚቻለውን ትተን ማንን ስንይዝ መቆም ይቻለናል?