Wednesday, January 16, 2013

ሰበር ዜና፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ስድስተኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ ውሳኔ አሳለፈ

ጥር 8/2005 ዓ/ም  ምሽት ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባስተላለፈው ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥር 6 ጀምሮ ባደረገው ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ በሰጠው መግለጫ 6ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ ውሳኔ ማስተላለፉን ገልጿል።


ዜና ዘገባው አያይዞ እንደገለጸው በአሜሪካ ካሉ አባቶች ጋር ሲደረግ የቆየው ድርድር ሁሉ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ሲኖዶሱ በቀጥታ ወደምርጫ ለመግባት የተገደደ መሆኑን በመጠቆም፤ ነገር ግን የአሜሪካው ሲኖዶስ ወደእርቁ ተመልሶ አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ ከሆነ ለመቀበል ፈቃደኝነቱ እንዳለም አያይዞ አስረድቷል።
  ይህም ቀደም ሲል ሲነገር እንደቆየው አቡነ መርቆሬዎስ በፈለጉት ቦታ በጡረታ ከሚቀመጡ በቀር 5ኛ ፓትርያርክ ስንል ቆይተን፤ ቁልቁል ተመልሰን 4ኛ ፓትርያርክ በማለት የራሳችንን ሥራ የምናፈርስበት ምክንያት የለም የሚለውን ሃሳብ በደንብ ያንጸባረቀና ግልጽ ያደረገ መግለጫ ነበር። በሞት የተለዩትን ፓትርያርክ ሕገ ወጥ ናቸው በማለት የውጪው ሲኖዶስ ሲሞግት የቆየበትን ጥያቄ ተቀብሎ 4ኛውን ፓትርያርክ ወደመንበር መመለስ ማለት በ5ኛው ፓትርያርክ የተሰሩትና የተሾሙትን ጳጳሳትም በሕገ ወጥ ስልጣን የተገኘ ሹመት በማሰኘት ጥያቄ ውስጥ የሚከትና ወይም እንደገና ሊታደስ ይገባዋል የሚልን መንፈስ የሚያስነሳ ስለሆነ ከወዲሁ ስለአራተኛ ፓትርያርክ መመለስ ጉዳይ የሚነሳውን ፋይል ዘግተን ወደ 6ኛው ተሸጋግረናል በማለት እቅጩን የተናገረ ዘገባ ይመስላል። ይህም በፓትርያርኩ በራሳቸው አንደበት በቀጥታ  ባይሰማም በእነ አቡነ መልከ ጼዴቅ ይነሳ የነበረው የ4ኛው ፓትርያርክ ወደሥልጣን የመመለስ የእርቅ ክርክር እዚሁ ላይ ያቆማል ማለት ነው። 
የሀገር ቤቱን ሲኖዶስ እንደብቸኛ ሲኖዶስ በመቀበል፤ የውጪው ሲኖዶስ ከሀገር ቤቱ ጋር ለመቀላቀል ዝግጁ ይሆን? ያ ካልሆነ የእርቁ ፋይል እዚህ ላይ ይዘጋል!  ሁሉም ወገን ሥልጣን አይቅርብኝ የሚል ፈላጊ ስለነበር አንድ መሆን አልተቻለም። ሥልጣን የማያስጎመጅ አማራጭ ይኖር ይሆን?