Saturday, January 19, 2013

እንኳን ለ1975ኛው ዓመት በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ!




ውሃ ለሥጋችን ሕይወት ነው። ከዚያም በላይ የፍሳችንን መዳኛ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት የምናዘክርበት ትልቅ ተስፋችን ነው። ውሃ በዘመነ ኖኅ የኃጢአት በትር ሆኖ የሰው ልጆችን የቀጣ ቢሆንም ነገሮችን አዲስ ማድረግ የባህሪው የሆነው እግዚአብሔር ውሃን በልጁ  ሞት ሞተን ፤ በኃይል ስለመነሳታችን  የምስክርነት ተስፋ አድርጎ ሰጥቶናል።
ውሃ የሞት መሣሪያ በሆነበት ዘመን «ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ» 2ኛ ጴጥ 2፤5  ካጠፋቸው በኋላ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የትንሣዔው ኅብረት ምልክት ሆኖ፤«በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ» ቆላ 2፤12 በማለት  በትንሣዔው  ያለንን አንድነት ነግሮናል።
እንደዚሁ ሁሉ በክርስቶስ ያመኑቱ ሁሉ ሊያደርጉት የሚገባና የሕያውነት ምስክርነታቸውን የሚሰጡበት የጥምቀት ዝክረ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከከተራው ጀምሮ የጌታ ጥምቀት ተፈጽሞበታል ተብሎ እስከሚታሰበው እለት ድረስ ብዙ ሺህ ሕዝብ በተገኘበት፤ የውጪ ቱሪስቶች ለጉብኝት በሚገኙበት ሥርዓት ጥር 11/2005 ዓ/ም በጃንሜዳና በየአድባራቱ ተከብሮ እንደሚውል ይታወቃል።  በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የተከናውነውን ሥነ ሥርዓት  ከፊል ምሥል አቅርበናል።