Thursday, August 9, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን ምንቸት ግባ፤ ማኅበረ ቅዱሳንን የምትቃወም ምንቸት ውጣ!!!



ብጹእ አቡነ ገብርኤልን ከአስመራ ሊቀጵጵስና ዘመናቸው ጀምሮ ስለእሳቸው በሲኖዶሱ አካባቢ የተባለውን ነገር ብዙ ብዙ ሰምተናል። ከዓመታትም በኋላ ምድረ አሜሪካ ከኮበለሉ በኋላም  ቢሆን ወያኔ ወይም ሞት ብለው ከተቃውሞ ጎራ መሰለፋቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች አይተናል። አቡነ ጳውሎስን ቤተክርስቲያን እንደገባች እንትን…….  ሙልጭ አድርገው ሲያክፋፉ ተመልክተን፤ እንዴት ተደርገው ቢበደሉ ይሆን? ሊቀ ጵጵስናቸውን ግምት ውስጥ እስኪያገባ ድረስ ለዚህ ዓይነት አንደበት የበቁት ብለን ታዝበንም ነበር። በእርግጥ ይህ ተቃውሞ ሰልፍ በአሜሪካ ውስጥ እንደፖለቲካ ስደተኝነት የመኖሪያ ፈቃድ ለማስገኘት የሚያስችል የመረጃ ማጠናከሪያ መንገድ በመሆኑ ጥሩ ጥበብነቱን አድንቀን ተቀብለንላቸዋል።
የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት ከተቻለና የግል የገቢ ካፒታልን ማሳደግ የሚያስችል የቤተክርስቲያን ምስረታ ከተጠናቀቀ በኋላ ያገኙትን ገንዘብና ዝና ከጥሩ ነፋሻ አየር ጋር በነጻነት ለመተንፈስ ደግሞ በትውልድ ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ እንደመኖር ተመራጭና ለሚዛን የሚደፋ ሌላ ስፍራ ባለመኖሩ ብጹእ አባታችን አውጥተው፤ አውርደው ሁኔታዎችን ሲጠብቁ  የአሜሪካው ሲኖዶስ የጳጳሳት ሹመት የሚሰጥበትን ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው ወደ ውጤት በመቀየር፤ ሲኖዶስ ማለት በአቡነ ጳውሎስ የሚመራው ነው በሚል የተለመደ የተቃውሞ ጥበባቸው ከፓትርያርኩ ጋር የመደራደሪያ ሰነድ ለመጨበጥ ችለዋል።  በተቃዋሚነት ሰልፍ በመውጣት የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት እንደቻሉት ሁሉ፤ የአሜሪካውን ሲኖዶስም በመቃወም፤ ሲዘልፏቸው የነበሩትን የአባ ጳውሎስን ፓትርያርክነት 3600/ሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ/ ተገልብጠው ከእሳቸው ወዲያ ማንም የለም በማለታቸው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አዲስ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝተው ሀገር ቤት መመለሳቸውን አይተናል። ባንድ ጊዜ ሁለት መኖሪያ ፈቃድ ማግኘት ብልጠትንና የታክቲክ ስፖርትን ማወቅ ይጠይቃል።
ስለእሳቸው ባህርይ መምህር ጽጌ ስጦታው «ይነጋል» በሚለው መጽሐፉ «ዘክልዔ ልብ» ሲል በደንብ አድርጎ የገለጸበት ነገር በእውነትም አንድ ቦታ የማይረጉ እንደዓሳ ጎበዝ ዋናተኛ መሆናቸውን ነው ።
አባ ገብርኤል ምንም እንኳን በክብር ደረጃቸው ጳጳስ ቢሆኑ ስህተት የማይጎበኛቸው ፍጹምና ቅዱስ መልአክ እንዳይደሉ ስለምናምን፤ በተሳሳቱት ነገር ተጸጽተው ለደረጃቸው የሚመጥንና ሌሎችም እሳቸው መልካም ነገር እንዳላቸው በማመን ሊማርና ሊመሰክርላቸው እንዲችል ቢያደርጉ የሚጠላ ማንም ባለመኖሩ አየር ጠባዩ ሲደብር ወደ አሜሪካ መሄዳቸውና አየር ጠባዩ ደግሞ ሲስማማቸው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን በራሱ እንደስህተት አይቆጠርም።
ይሁን እንጂ አባ ገብርኤል ሀገር ቤት ከተመለሱና ወደ ሀዋሳ ከዘለቁ በኋላ ግን እየሆነ ያለውና የሚታየው ነገር ጥሩ እንዳልሆነ መታየት ከጀመረ ሰንብቷል። አባ ገብርኤል የሃዋሳ ሕዝብ ሊቀ ጳጳስ እንጂ የማኅበረ ቅዱሳን ሊቀ ጳጳስ  እንዳልሆኑ እየታወቀ፤  የሥራቸው መጀመሪያ አድርገው የፈጸሙት ነገር አስገራሚ ነበር።  «ማኅበረ ቅዱሳንን የምትቃወም ምንቸት ውጣ፤ የማኅበረ ቅዱሳን ምንቸት በኔ ሀገረ ስብከት ግባ» የሚል ቡራኬ ለመስጠት ጊዜ አልፈጀባቸውም። ሸምቆ ወጊው ማኅበር በዚህ ቡራኬ ያገኘውን ፈቃድ አሜን ብሎ በመቀበል፤ እነ እገሌን ምቱልኝ፤ እገሌንም ውጉልኝ ለማለት ጊዜ አልፈጀበትም። ይህ ነጋዴ፤ ከፋፋይ፤ መሰሪ፤ ሸቃጭና አስመሳይ ማኅበር እንደ ባህር ዓሳው/ Octopus/ ሰላሳ የመርዝ ጭራውን እያወራጨ፤ የቤተክርስቲያን ልጆችን ከመድረክ አስወገደ። ከሥራ አባረረ። ሺዎች እስከዛሬ ድረስ ከቤተክርስቲያን ተሰደው በየቤታቸው ተቀምጠዋል። ለጸሎትና ለጋራ የመማማር መድረክ እንኳን የግልና የህዝብ አዳራሾችን ለመጠቀም ተገደው ይገኛሉ። አባ ገብርኤል ስለነዚህ ተሰዳጆች ሲጠየቁ ምን የሚሉ ይመስሏችኋል? ጥቂት አፈንጋጮች!!!!!!!!!!
እውን እዚህ ፎቶ ላይ በአንድ ወቅት የተሰበሰቡትና በማኅበረ ቅዱሳን መሪነት አባ ገብርኤል ያባረሯቸው ምእመናን ጥቂቶች ናቸው?
የፎቶ ምንጭ፤dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com



ለመሆኑ እሳቸው የማኅበረ ቅዱሳን ሊቀጳጳስ ናቸው ወይስ ለእያንዳንዱ ሕዝበ ክርስቲያን?  ሕዝቡ ማኅበረ ቅዱሳንን አንፈልገውም ቢል እንዲቀበሉ የሚያስገድዱት ለምንድነው?
አዎ! በእርግጥም ማኅበሩን «ማኅበረ ቅዱሳን» ብለው ስም ያወጡለት እርሳቸው መሆናቸውን እናውቃለን። ማኅበሩን ባርከውና ቀድሰው ለጥፋት ያሰማሩት ሰው  እስከዛሬም ከጉያው አልተለዩም።   ማኅበሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ላደረሰው እያንዳንዱ በደል አባ ገብርኤል ባለእዳ ናቸው።  የማኅበሩ የጡት አባት ሆነው ዛሬም ሺዎችን ለማኅበሩ ህልውና ሲሉ አባረው ሲያበቁ፤ ጥቂቶች ሲሉ አያፍሩም። ለእርሳቸው ከማኅበሩ ውጪ ቤተክርስቲያኗ ራሷ ጥቂት ናት። የአቋም ማንነታቸው የተለመደ ባይሆን ኖሮ አባታችን ዛሬ ምን ነካቸው እንል ነበር። የቆየ ባህላቸው ስለሆነ ብዙም አያስገርምም።
ይህ ማኅበር በምድረ ኢትዮጵያ አባ ገብርኤልንና አባ አብርሃምን ለሚፈልጋቸው አገልግሎት መልእክቱን ማስተላለፍ ለእርሱ በቂው ነው። በእርግጥ ሐረር ላይ ይህንን ያህል  የሚያዋጣ ሆኖ አልተገኘም። ሐረሮች ጠንካሮችና አንድነት ያላቸው ስለሆኑ በራቸውን እስካሁን አልከፈቱም። ይህ ማለት ግን እንዴትና መቼ እንደሚከፈት ማኅበረ ቅዱሳን እያጠና፤ እየሰለለና ጊዜ እየጠበቀ ማለት እንጂ ችላ ብሏል ማለት ባለመሆኑ ነቅቶ መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ ማስገንዘብ እንወዳለን። ልክ ምድረ አሜሪካ ላይ አድባራቱን በመሰነጣጠቅ፤ አስተዳደራቸውን ለማፈራረስ ተግቶ እንደሚሰራው ማለት ነው። ለምሳሌ ያህልም በአሜሪካ ውስጥ በስለላ ሥራው የካህናቱን ውይይት በቄስ እንትና/ስሙ ለጊዜው ይቆየን/ ድምጽ ቀድቶ ሲያበቃ በደጀ ሰላም ገጹ እንዳወጣው ማለት ነው።በቴሌ ኮንፈራንስ የተደረገውን ውይይት በመቅዳት ለደጀ ሰላም የሰጠው ቄስ ለእርሱ ማኅበረ ቅዱሳን እንጂ ቤተክርስቲያን ምኑም አይደለችም። ቄሱና እሱን መሰሎች ፤ ወላጅ እናታቸው ገንዘብ ካወጣች ለማኅበረ ቅዱሳን ሲሉ ገበያ  ላይ አውጥተው ከመሸጥ የሚመለሱ አይደለም። ኅሊናቸውን እስከዚህ ድረስ የሸጡ ባለጌዎች ናቸው።
 ማኅበሩ አባ ገብርኤልን በሃዋሳ፤ አባ ገብርኤልን በአሜሪካ በኋላም በሐረር፤ በአሜሪካም አባ ኤዎስጣቴዎስን እና የእሱን ፍርፋሪ የሚለቃቅሙ ቄሶችን በመጠቀም የጥፋት ሥራው እያከናወነ ይገኛል።
ማኅበሩ በሃዋሳ፤ በአዶላ ወዩ፤ በዲላ፤ እና በነገሌ ቦረና ለሚያደርሰው በደል ሁሉ የአባ ገብርኤል ቡራኬ እስከዛሬ አልተለየውም። ይህ ሁሉ ሲሆን አባ ገብርኤል የሚሉት ጥቂት አፈንጋጮች ናቸው ነው። ለመሆኑ የአባ ገብርኤል ጥቂቶች ስንት ናቸው? በቁጥር ስንት ሲሆን ነው ብዙ የሚሆነው? ብዙ ለመባል የሚያበቃውን ቁጥር ይንገሩንና የተሰደዱት ቆጥረን እንንገርዎ!
እስከዚያው አቡነ ገብርኤል የእርስዎ ጥቂት ቁጥራቸው ስንት እንደሆነ ይንገሩን!