Friday, August 17, 2012

በአቡነ ጳውሎስ እረፍት የማኅበሩ ምኞት ሰፋ ወይስ ጠበበ?



ፓትርያርክ ጳውሎስን እስከህይወታቸው ኅልፈት ድረስ ሲራገማቸው፤ ሲያዝንባቸው፤ ሲዘልፋቸው፤ ሲያሽሟጥጣቸውና በታመሙ ቁጥር አሁንስ የሚተርፉ አይመስልም እያለ ሲዘግብባቸው የቆየው ማኅበር አሁን እፎይ፤ ግልግል እንደሚል የደረሰበት የጥላቻው ጥግ ጽሁፎቹ ያረጋግጡልናል።
ደጀ ሰላም፤August 14, 2012
 እግራቸው ከጉልበታቸው በታች በከፍተኛ ደረጃ መጎዳቱንና የጤናቸው ኹኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ የሚነገርላቸው ፓትርያርኩ÷ ጤናቸውን ለመከታተል የሚያደርጉት ሳምንታዊ ወጪ ከስድሳ ሺሕ ብር በላይ ማሻቀቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የደጀሰላም ወዳጅ አስተያየት ሰጪ- August 16, 2012 2:06 PM
Anonymous said...ግልግል ለተዋህዶ የተስፋ ጮራ ነው!ፈርኦን ሆይ ህዝቤን ልቀቅ ሲባል ካልሰማ የእግዚአብሔር እጅ ትዘረጋለች። ከቁጣው እሳት ማምለጥ የሚቻለው ማን ይሆን?
የፓትርያርኩ ሕመም ሳይሆን ፓትርያርክ ሆነው ለህክምና 60 ሺህ ብር ማውጣቱ ያስቆጨውን ማኅበር ምን ይሉታል? ገንዘቡ ከወጪ እንዲድን ቶሎ ይሙቱልን ማለቱ አይደለምን? በሳምንት ይህንን ያህል እየወጣ ነው የሚለውን ገንዘቡን ወጪ ከህመማቸው ጋር ማነጻጸር ቆይታቸው ከወጪ በስተቀር ምንም ትርፍ የለውም ማለቱ ነው እስከሚገባን ድረስ።
ማኅበሩ ፓትርያርኩን እንደሚጠላ ይታወቃል፤ ግን አሳዛኙ ነገር እሳቸውን በሚያይበት ዓይን ወዳጆቻቸውንም እንደዚያው መመልከቱ አስገራሚ ነው።
ማኅበሩ እነ እገሌ ጳጳሳት ነደ እሳት ናቸው፤ እነ አቶ እገሌም መኪና ሸለሙኝ እያለ የራሱን ወዳጆች ከፍ፤ ከፍ እያደረገ ስማቸውን ለአፍታም ከአፉ እንደማያሳርፈው ሁሉ በተነጻጻሪው አቡነ ጳውሎስ ደግሞ ከወዳጆቻቸው መካከል አንዳንድ ሰዎችን ቢያቀራርቡና ቤተኛ ቢያደርጉ ይህ የሰው ባህርያዊ ፍላጎት መሆኑን በመካድ ማኅበሩ ፓትርያርኩን ሲያወግዝና ሲራገም፤ ወዳጆቻቸው ሲያጣጥል መገኘቱ ያሳዝናል።  ማኅበሩ የራሱን ወዳጆች እንደሚቀርባቸው ሁሉ አቡነ ጳውሎስ የልብ ወዳጆቻቸውን ማቅረባቸው ምን ክፋት አለው? ማኅበሩ የራሱ ስራ ሌላ፤ የሰዎቹ መወዳጀት ሌላ ! በየትኛው ርስቱ ላይ ነው፤ ይህ ማኅበር እንደዚህ አድርጎ የሚነጫቸው?
ከእነዚህ ተረጋሚ ሰዎች ከማኅበሩ ድረ ገጾች ስማቸው እስካሁን እረፍት ያላገኘውና ወደፊትም እንደ አቡነ ጳውሎስ በሞት ከሄዱም በኋላ የማኅበሩ እርግማን ይለያቸዋል ተብሎ የማይታሰበው ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፤ አባ ሠረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል፤ መጋቤ ሐዲስ በጋሻው ደሳለኝ፤መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፤ ሊቀ ስዩማን ኃ/ጊዮርጊስ ጥላሁን፤ መምህር አእመረ አሸብር፤ ንቡረ እድ ኤልያስ እና ሌሎች  ስማቸው ከማኅበሩ አገልጋይ ድረ ገጾች ላይ ለእረፍት አይወርዱም።
ማኅበሩ እነዚህን ሰዎች የሚረግማቸው ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ባላቸው ቅርበት እንጂ ማኅበሩ እንደማኅበር የሚንቀሳቀስበትና የሚሄድበት መንገድ ከእነዚህ ሰዎች ጋር የሚገናኝ ስለሆነ አይደለም። አንዳንዶቹም ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ገጥመዋል ብሎ ከሚጨነቅበት ባሻገር በምርኮኝነት እጃቸውን ሰጥተው የማኅበሩ አገልጋይ መሆን ስላልፈለጉ ቅናት እየሸነቆጠ ስላስቸገረው ነው። ለምሳሌም ያህል በጋሻውን፤ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤልንና ኃ/ጊዮርጊስ ጥላሁንን ማንሳት ይቻላል። ጥፋታቸው አንፈልግህም ማለታቸው ብቻ ነው።
ከደጀ ሰላም ስድብና እርግማን መካከል አንዱን እንመልከት።
ቅዱስ ሲኖዶስ በታሪክ እጅግ ሊያስመሰግነው በሚችል መልኩ በተሐድሶ ድርጅቶች እና አራማጆች ላይ የውግዘት ቃሉን ባስተላለፈ ማግሥት ቅዱስነታቸው ቀንደኛውን ተሐድሶ በአሜሪካ የሾሙበት ምክንያት የንፁሐን ኦርቶዶክሳውያንን ቅስም ለመስበር እንዲሁም ወደ ውጪ አገር ሰው በመላክ ሰበብ የሚያጋብሱትን ገንዘብ በታማኛቸው አማካኝነት ለማካሔድ በማሰብ መሆኑን ምንጮች አብራርተዋል። (ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 24/2004 ዓ.ም፤ ጁን 1/ 2012/
ቡነ ጳውሎስ ገንዘብ ለመዝረፍ ኃ/ጊዮርጊስን ወደ አሜሪካ ለመሾም የሚገደዱት በምን ስሌት ነው? የተሾሙ ሁሉ ገንዘብ ዘራፊዎች ናቸው? ኃ/ጊዮርጊስስ የማንን ገንዘብ ይዘርፋል? የማኅበሩ የጥላቻ ጥግ ጥቂት እንኳን ወደ እውነቱ አይቀራረብም።
ኃ/ጊዮርጊስ ቀድሞ የማኅበሩ ወዳጅ ነበር። ኃ/ጊዮርጊስ የጋብቻ ወረቀታችንን ቀደናል ባለ ማግስት ጀምሮ ማኅበሩ የዘመቻ ሰይፉን አንስቶበታል። ማኅበሩ ከእሱ የተለየ ሃሳብና መንገድ ያለውን ማንኛውንም ሰው እንደ ሰው የሚቀበልበት ተፈጥሮ የለውም። አሜን ብሎ የመገዛት ግዴታ፤ አለበለዚያም ከምድረ ገጽ እስኪጠፋ ድረስ የመዝመት ተልእኮ ያለው ማኅበር መሆኑን ስራዎቹ ራሳቸው ይመሰክራሉ።
ይህ ማኅበር በእሱ እርግማን ይሁን በእግዚአብሔር ፈቃድ የአቡነ ጳውሎስ ህልፈተ ህይወት የሆነበትም ምክንያት ለራሱ እንደመሰለው ቢያስብም፤  ነጋ ጠባ የሚጨቀጭቃቸው አባትከእንግዲህ በፊቱ የሉም።  በቀጣይ ወዳጆቻቸውን እስኪያጠፋ ድረስ ለጊዜው  ቤቱን ዘግቶ  የደስታ ከበሮ የመደለቅ መብቱ የተከበረ ነው። ይሁን እንጂ በአቡነ ጳውሎስ ሞት የተሰማውን ደስታ አጣጥሞ ሳይጨርስ፤ የፓትርያርኩ ወዳጆች ናቸው ብሎ የሚገምታቸውን ገና ካሁኑ ስማቸውን እየጠራ ዘመቻውን ጀምሯል።
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 10/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 16/ 2012
ፋውንዴሽኑ› መቋቋም ያስፈልጋል የተባለውን ገንዘብም እንደተለመደው ከስፖንሰርሽፕ፣ ከአድባራትና ገዳማት እንዲሁም ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ኢኮኖሚያዊ ምንጮች ለመሰብሰብ ሲዘጋጁ መቆየታቸውን የገለጸው የመረጃ ምንጩ÷ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነን፣ መልአከ ፀሐይ በቀለ ተሰማን (ቤቴል ቅዱስ ሚካኤል)፣ ሰሎሞን በቀለን (ቦሌ መድኃኔዓለም)፣ ቀሲስ ግሩም መልአክ ታዬን (ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤልን (ጠቅላይ ቤተ ክህነት) በዋና አደራጅነት ጠቅሰዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ በመንግሥት የፀጥታ ኀይሎች በመታገዝ ጠንካራ ክትትል በማድረግ የወይዘሮዋንና ሌሎች አካላትን ችግር ፈጣሪነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማቆም እየሠራ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡

የአቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር የማያስጨንቀው ይህ ማኅበር አስከሬናቸው ገና ከደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ሳይወጣ ፋውንዴሽን ሊቋቋም ይችላል በሚል የንብረት መሰብሰብ ዘመቻ ላይ በመጠመድ የፓትርያርኩን ቀራቢዎች በማዋረድና ስም በማጥፋት ላይ ተጠምዷል። በመሰረቱ የፋውንዴሽን ማቋቋምና አለመቋቋም ጊዜው አሁን ባይሆንም እንኳን ይህንን ለማድረግ ግን የማኅበሩ ፈቃድ የግድ ያስፈልጋል ማለት ነው? እኔ ያልፈቀድኩት ፋውንዴሽን መቼም አይቋቋም እያለ መሆኑ ነው።
የአባ ጳውሎስን ስም ከሞቱም በኋላ ከቂም በቀል አፉ አልተውም ብሎ እንጂ አድባራቱና ገዳማቱ ፓትርያርኩ በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ በማን ትእዛዝ ከካዝናቸው ገንዘብ በማዋጣት የአቡነ ጳውሎስን ፋውንዴሽን እንዲያቋቁሙ ይገደዳሉ? ከዚህ በፊትስ አቡነ ጳውሎስ እያዘዙ ገንዘብ ይወጣል በማለት ይወቅሳቸው ነበር አሁንስ? 
 እሳቸው በሞት ሲለዩላቸው፤ ይህንን የገንዘብ መዋጮ በአስገዳጅ እንዲወጣ ያስደርጋል የሚሉት ማንን ይሆን?
በቀሲስ በቀለ ተሰማ ወይስ በወ/ሮ እጅጋየሁ ወይስ በዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ትእዛዝ?
በህይወት እያሉ ሞታቸውን የሚመኝ ይህ ማኅበር ከሞቱ በኋላም ስም አጠራራቸው እንዳይታወስ ተግቶ የሚሰራ ብቻ ሳይሆን ወዳጆቻቸውን በመወንጀልና በማሳጣት ከመጠመድ ለአፍታም እንደማያርፍ ያመለክታል።  ቢያንስ ፓትርያርክ  ወይም የመንበረ ፓትርያርኩ ስራ አስኪያጅ ወይም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሳያውቅ ገንዘብ በቄስና በወ/ሮ ትእዛዝ እንደማይወጣ እየታወቀ አሁን ይህን ማንሳቱ ለገንዘብ ብክነት ታዝኖ ነው? ወይስ የጭቃ ውስጥ እሾክ ጥላቻን ለመበተን?
የቤተክርስቲያኒቱ ገንዘብ አላግባብ እንዳይጠፋ ይጠበቅ በማለት እንደቤተክርስቲያኒቱ አባልነት መቆርቆር አንድ ነገር ነው። ነገር ግን እኛ ያልወጠወጥነውና ያልጋገርነው ነገር ሁሉ ይደፋ ማለት ግን ክፋት ነው።
ፓትርያርኩ ከየትም ሰብስበው የሾሟቸውን በማኅበሩ በኩል ነደ እሳት ሲባሉ ነደ እሳት ለመሰኘት ያበቋቸው ፓትርያርክ  ግን ከሞቱም በኋላ የሚረገሙበት ምክንያት አይታየንም።
 አሁን የማኅበሩ ጉዳይ ሌላ ነው።  ጠላቴ የሚላቸውና ከቤተክርስቲያኒቱ ትልቅ የሥልጣን እርከን ላይ የነበሩት ሰው ላይመለሱ ሄደውለታል። አሁን የቀረው ነገር ይህንን ቦታ መሙላት ነው። ይህንን ቦታ ለመሙላት ደግሞ በአስተማማኝ ደረጃ የአቡነ ጳውሎስን ወዳጆች የሚጠራርግ፤ ጠላቶቼ የሚላቸውን ሁሉ የሚያስወግድለት ሰው መሆን ይገባዋል። ይህንን ከ20 ዓመት በኋላ ያገኘውን ወርቃማና እድሉን በቀላሉና  በዝምታ ያሳልፈዋል ተብሎ በእኛ በኩል አይታሰብም። የማይፈነቅለው ድንጋይና የማይቆፍረው ጉድጓድ አይኖርም። የቤተክርስቲያኒቱ አባላት ከሚጨነቁት በላይ የሚጨነቅ፤ የሲኖዶስ አባላት ከሚያስቡት በላይ የሚያስብ፤ መንግሥት ጉዳዩን ከሚከታተለው በላይ እንደቆቅ በመከታተል ይህን ማኅበር የሚያክለው እንደማይኖር እንገምታለን። እሱ የማይፈልገው እንዳይመጣ ይደክማል፤ የወደደው ደግሞ እንዲወጣ ሊተጋ እንደሚችልም እናስባለን።
እንዲያውም ለመሆኑ አቡነ ፋኑኤል ፓትርያርክ ሆነው ሊመረጡ በእጩነት ቀረቡ መባልን ቢሰማ ይህ ማኅበር ምን ይል ይሆን? 
እንኳን ለመመረጥ፤ መታሰባቸውን በራሱ  የተደረገ ያህል እንደሚቆጥረው እናውቃለን። ከተጠራቀመው የጥላቻ ስካር እየቆነጠረ ስማቸውን ከማጥፋት አለመታቀቡ እውነት ነው።

እኛን ከምንም በላይ የሚያሳስበን አሁን ባለው የጳጳሳት ማንነትና መንፈሳዊ ሚዛን ላይ ፓትርያርክ ሆኖ የተበተነውን ሰብስቦ፤ የተከፋፈለውን አንድ አድርጎ፤ ዘረኝነትን፤ ወገንተኝነትን፤ ምዝበራን በመታገል መንፈሳዊውን የእግዚአብሔር ቃል የሚመግብ፤ በጸሎቱና በትምህርቱ መፈወስ የሚችል አባት ማግኘቱ ላይ ነው።
ማኅበሩ ደግሞ የጳጳሳት ማንነት ጉዳዩ አይደለም። ስማቸውን እያነሳ የሚያሞግሳቸውን ስንመለከት የእሱ ምርጫ ምን ሊመስል እንደሚችል ስናስብ እንሰጋለን። እኛ  የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት በበቂ ሁኔታ የተማረው ሰው በመፈልግ ላይ እንጨነቃለን። ህዝቡ ከእውቀት ማጣት የተነሳ እንዳይጠፋ የሚያስተምር እንዲሆን እንሻለን። ማኅበሩ ድግሪ ሳይኖራቸው አለን የሚሉትን፤ ከወንበር ስር ከእግረ መምህራን ተቀምጠው ያልተማሩ ግን እሱን የሚደግፉትን ለማስመረጥ የሚደክም መሆኑ ያሳስበናል። ከዘመኑ እውቀት ጋር ቅርበት የሌላቸውና የ21ኛው ክ/ዘመን ተግዳሮቶችን መረዳት የማይችሉ ሰዎች መኖራቸው ሲታወቅ ፓትርያርክነቱን  ብቁ ባልሆኑ ሰዎች ሰይሞ የጎደለውን እኔ ሞላለሁ እንዳይሆን ያሰጋናል። ፖፕ ሺኖዳ በመንፈሳዊውም ሆነ በስጋዊው ትምህርት ሰዎች የደረሱበትን እርከን መድረስ የቻሉ እንደነበርና 41 ዓመት የመምራት ብቃታቸው ዝም ብሎ የተገኘ ባለመሆኑ በመንፈስም ጠንካራ፤ በእውቀትም የበሰለ አባት መኖሩ ያስጨንቀናል።
ሐዋርያት፤ ማትያስንና በርናባስን ለምርጫ ሲያቀርቡ ሁለቱም ለሐዋርያነት የሚያበቃ የማንነት መለኪያ እንደነበራቸው አይዘነጋም። የትኛው ለሹመቱ  የተገባ እንደሆነ መንፈስ ቅዱስ ቢያጸድቅም የሰዎች ምርጫ ግን ማንነታቸውን የሚለካ እንደነበር ይታወቃል።
ጳውሎስም ለጢሞቴዎስ የቤተክርስቲያን መሪ መሆን ያለበትን ሲነግረው ያለው ይህንን ነበር።
«በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል» 1 ጢሞ 3፤7
የሰዎች ቀና ምርጫና ማንነታቸውን የምንመዝንበት መለኪያ ቢኖረንም እንኳን የልባችንን መሻትና ቅንነት ተመልክቶ እጣውን እንዲያጸድቅ ለመንፈስ ቅዱስ መስጠት ይገባል።
ምእመናን፤ ካህናት፤ ጳጳሳት፤ መንግሥት ሁሉም በየድርሻው የኢትዮጵያ ኦርቶዶስክ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የሀገር ጉዳይ ነውና ነቅተን በመጠበቅ ከግርግር ፈጣሪዎችና ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም ተግተው ከሚሰሩ የጥፋት እጆች መከላከል ይገባናል።
ማኅበሩ ግን የአቡነ ጳውሎስ እረፍት ነገሩን ሁሉ  እንዳሰፋለት በማሰብ የልቡን ለመፈጸም መቼም አይመለስምና አቡነ ጳውሎስ ጥሩም ሰሩ መጥፎ ፍርዱን ለእግዚአብሔርና ለታሪክ ትተን ያለፉ ስህተቶች እንዳይደገሙ የመንፈሳዊ አባት አተካክ  ለቤተክርስቲያን የሚበጅ እንዲሆን በይበልጥም በሀገር ውስጥና በውጪ ያላችሁ ካህናት፤ መነኮሳት፤ ዲያቆናት፤ ታዋቂ ሰዎች፤ ምእመናንና ምእመናት፤ የመንግሥትም ድጋፍ ታክሎበት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅብናል። ጳጳሳቱ እንደሆነ እኔ፤ እኔ እያሉ የራሳቸውን ቡድንና ስልት ከመጠቀም ባሻገር እስካሁን ከዚህ ዓይነት ችግር ያልተላቀቁ ዛሬ ደርሰው አዛኝ ሊሆኑ አይችሉም።
የግብጽ ቤተክርስቲያን እስከዛሬ ፓትርያርኳን  ህገ ደንቡ ከሚያዘው ከ40 ቀን በኋላ ምትክ ሳታስቀምጥ የቆየችው በአንድ በኩል ስልጣኑን ለመረከብ አሰፍስፈው በቡድን የመጡ ፈላጊዎችና በሌላ በኩል ካህናቱ፤ ህዝቡና ታዋቂ ሰዎች  ባቀረቧቸው መንፈሳዊ ሰዎች መካከል ውጥረት በመንገሱ ነው። እስካሁን እልባት አላገኘም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥም ይህ ሊከሰት እንደሚችል እንገምታለን። በአንድ በኩል ማኅበሩና የማኅበሩ አቀንቃኝ ጳጳሳት ከነደጋፊዎቻቸው፤ በሌላ በኩል ማኅበሩንና የማኅበሩን አቀንቃኝ ጳጳሳትን የሚቃወሙ የሲኖዶስ አባላት፤ካህናቱና ምእመናኑ ናቸው። መንግሥትም የማይሆን እንዲሆን እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል ተብሎ አይታሰብም።  
ሊቃነ ጳጳሳቱ በስራ ያልተፈተኑ፤ የቤተክርስቲያኗን ችግር ሳይካፈሉ በቅንጦት የኖሩ፤ አንዳንዶቹም አንዴ ወደ ቀኝ፤ አንዴ ወደ ግራ ሲገለባበጡ የኖሩ፤  ይህችን ቀን ሲጠባበቁ ያደፈጡ ሁሉ አሁን ጆሮአቸውን ቢያቀኑ  እውነት እንዳይመስለን ልንጠነቀቅ ይገባናል። በተለይም በሁለት ዜግነት፤ ሁለት ሀገር ያላቸው እንኳን ለፓትርያርክነት ለዐቃቤ መንበርነትም መቅረብ አይገባቸውም። የበጎች እረኛ እንጂ ሞያተኛ አያሻንም። ከወዲሁ አጥብቀን እንድንጠነቀቅ ሃሳባችንን ለሚደግፉ ሁሉ ደግመን ደጋግመን እናሳስባለን። 
ለብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ነፍስ እግዚአብሔር መልካሙን እረፍት ይስጥልን! አሜን።