Sunday, August 19, 2012

ፓትርያሪክ መርቆሪዮስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ!



ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል 
የፓትርያሪክ ጳውሎስ ሞት ከአወዛጋቢነት አልፎ አስደንጋጭ ዜና እየተሰሙ ነው። ፓትሪያሪኩ ህይወታቸው ለህልፈት እስከተዳረገች ዕለት ድረስ በተለይ የዕለቱ ውሎአቸው እስከ ሥርዓተ ቁርባን ድረስ ምንም ዓይነት ችግርና እንዲሁም የድካም መንፈስ ያልታየባቸውና ያልተስተዋለባቸው ሲሆኑ ቅዱስቁርባኑን ከወሰዱበት ቅጽበት ጀምሮ ግን በሰውነታቸውን ላይ የመዛል፣ በሚታይ የሰውነት ክፍላቸውም በላብ የመጠመቅ ዓይነት ምልክት እንደታየባቸው በትናት ዕለት ካነጋገርቸው በዕለቱ አብሮአቸው ቤተ- መቅደስ ውስጥ ነበሩ ከተባሉ ካህናት ተጨባጭ ምስክርነት ለማግኘት ተችለዋል።
በሁኔታው ግራ የተጋቡ የዓይን ምስክሮች ጨምረው እንዳወሱልኝም ከሥርዓተ ቁርባኑም ሆነ ከዚያ በፊት የነብሩ ቀናት ፓትሪያሪኩ እንደ ወትሮ የዕለተ ዕለት ግዴታዎቻቸውን በሚገባ ሲያከናውኑ እንደሰነበቱና ምንም ዓይነት ለሞት ሊዳርግ የሚያስችል ዓይነት ሕመም እንዳልነበራቸውም ለማወቅ ተችለዋል። ታድያ ገዳያቸው ማን ሊሆን ይችላል? ቤተ- ክርስቲያን እነሆ ደመ ክርስቶስ ብላ ለስዎች ልጆች ሕብረት በምታቀርበው በጽዋ ላይ ገዳይ መርዝ ጨምሮ ጭቃኔ በተሞላበት አረመንያዊ ድርጊት የሰው ነፍስ ለህልፈት ዳርጎ ሲያበቃ ተጠቃሚ የሚሆነው ማን ሊሆን ይችላል? የቤተ- ክርስቲያኒቱ አባቶችና ሊቃውንት መምህራን በመግደልስ የጥቅም መርበቡን በቤተ- ክርስቲያን ላይ የመዘርጋትና እውን የማድረግ ዓላማ አነግቦ የተነሳ ነፍሰ ገዳይ ማን ይሆን? ለሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች በሰፊውና በተጠናከረ መልኩ ሳምንት እመለስበታለሁ።
በዛሬው ዕለት ግን ህልፈተ ሥጋ ፓትርያሪክ ጳውሎስ ተከትሎ በብዙሐን ዘንድ አነጋጋሪ ከሆኑት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል በቀዳሚነት እያነጋገረ የሚገኘውን የፕትርክና መንበሩ/መቀመጫው ማን ይተካው? የሚለው ጥያቄ ዙሪያ ላይ አጭር መልስ/መፍትሔ ለመጠቆም ነው። ስህትት በስህተት ለማረም ወይንም ደግሞ ለማስተካከል እንደማይቻል ከሌላው በተሻለ ኢትዮጵያውያን ብዙ ማለት እንደምንችል አመናለሁ። ይኸውም ስህተትን በስህተት ለማስተካከበል በሞከርናቸው ዘመናት ሁሉ እርምጃዎቻችን ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አመዝኖ ዛሬ ምድራችንም ሆነ ሕዝባችን የሚገኝበት አሳፋሪ ገጽታና የተመሰቃቀለ ህይወት ማየቱ በቂ ማስረጃ ነው ብዬ አምናለሁ።
እዚህ ላይ አጽንዖት ሰጥቼ ለማስተላለፍ የምወደው መልዕክት ቢኖር ቤተ- ክርስቲያን በተለይ በሀገር ውስጥ የሚገኘውን ሲኖዶስ ከቀድሞ ስህተት ይልቅ የባሰ ስህተት እንዳይሰራ ከወዲሁ እርምጃዎችን ይመረምር ዘንድ ነው የሚጠየቀው። ፓትሪያሪክ ጳውሎስ አልፈዋልና አዲስ መሾም ያስፈልጋል በማለት በጥድፍያ የሚሆን ነገር እንደሌለ በመገንዘብ በተለይ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መካከል የተጀመረውን የዕርቀ ሰላም አጀንዳ በሁለቱም አካላት በጎ ተነሻሽነት በአስቸይ ፋይሉን በመክፈት ቤተ -ክርስቲያኒቱ አንድ የምትሆበትና ወደ ቀድሞ አንድነትዋ የምትመለስበት እንዲሁም የቀድሞ ፓትሪያሪክ ወደ መንበራቸው የሚመለሱበት መንገድ በርትቶና ተግቶ መስራት እንደሚጠበቅበት ነው የማምነው። ይህን አይነቱ እርምጃ ደግሞ ከየትኛውም አቅጣጫ ለማየት ቢሞከር ሀገራዊም ሆነ መንፈሳዊ ጠቀሜታውም የጎላ ነው
በተጨማሪም የመንፈሳዊያን መሪዎችም ሆነ የቤተ- ክርስቲያን አጀንዳ ሰላምና ሰላም እስከሆነ ድረስ ለዓመታት የዘለቀውን ቀውስና ትርምስ መግታትና ማስቆም የሚቻለው መንበሩ ከፖትሪያርክ መርቆርዮስ አልፎ ለማንም ሊሆን እንደማይችልና እንደማይገባ በማመን ፓትሪያሪክ መርቆሪያስ ወደ ቀድሞ መቀመጫቸው ለመመልስ በሚሳየው በጎ ተነሳሽነት ነው። ይህም የምለው ያለ ምክንያት አይደለም። በቤተ- ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ የሚመለከተውም የማይመለከተውም አፉን በከፈተ ቁጥር ለዚህ ሁሉ ዕንቅፋትና መሰናክል መዋቹ ፓትሪያሪክ ጳውሎስ ብቸኛ ተጠያቂ ያደርግ እንደነበረ ማናችንም አንስተውም። ታድያ አሁን ማንን ተጠያቂ ልናደርግ ነው? በህይወት ባሉ ፓትሪያሪክ ላይ ፓትሪያሪክ ለመሾም አይደለም ሊሞከር ፈጽሞ ሊታሰብም አይገባውም። ፓትርያሪክ መርቆሪዮስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ!
መቀመጫው አሜሪካ ላያደረገ የአበው ጉባኤ (ሲኖዶስ):
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ብጹዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሆይ! ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕ 12 :17 በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ ሲል እንደ ጻፈላቸው ዛሬ ደግሞ እኛ ባለተራዎች በእኩል ኃይል ሥልጣንና መንፈስ ቃሉ ከፍ ባለ ድምጽ ሰላምን እናወርድ ዘንድ አፍ አውጥቶ እየጮኸ ይገኛል። ሳሙኤል ገና ብላቴና በነበረበት ዘመን እግዚአብሔር በስሙ ይጠራው ነበር። ሳሙኤልም ገና የእግዚአብሔር ድምጽ ለይቶ ካለማወቁ የተነሳ እግዚአብሔር በጠራው ቁጥር ብድግ እያለ ወደ ኤሊ በመሄድ እነሆ የጠራኸኝይለው ነበር። ታድያ ከዕለታት አንድ ቀን ነገሩ የገባው ሊቀ ካህን ሳሙኤልን ሄደህ ተኛ ቢጠራህም አቤቱ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር በለው በማለት አሰናብቶታል። 

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ብጹዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት:በተፈጠረው ሁኔታ ሳቢያ ክፍተቱን ለሞምላት ማንም ዘው ብሎ በመግባት መጻኢ የሀገሪትዋም ሆነ የምድሪትዋ ዕጣ ፈንታ የሚያበላሽበት በእናንተ በመሪዎች በኩልም እንደሆነም ከሥጋውያንና ፍጥረታውያን ሰዎች ስልክ የምትቀበሉበትና ምላሽ የምትሰጡበት በአንጻሩም በመደወል ምን እንድርግ? የምትሉበት ጊዜ ሳይሆን የሥጋ ሃሳብ፣ የሰዎች ጉትጎታ፣ የሁኔታዎችንም ድምጽ ወደ ጎን በመተውና ካለፈውንም ታሪክ ትምህርት በመቅሰም ከራሳችን አልፎ ለሀገርና ለወገን የሚተርፍ መልካም የሆነውን ሃሳብ የምታስቡበት እንደ ሳሙኤል በልዑለ ባህሪ እግዚአብሔር ፊት በመውደቅና ድምጾችንም በመለየት ባሪያ ይሰማልና ተናገር በማለት ድምጹን ለመስማት የምትሹበትና ድምጹንም ሰምታችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም በፍቅርና በመተሳሰብ ተቃቅፈን እንደ ጨው የተበተነውን በልዩ ልዩ ምክንያትም አንድ ሆኖ ሳለ እርስ በርሱ ሆድና ጀርባ የሆነውን ሕዝብ የምትሰበስቡበትና የምታስተቃቅፉበት የምሕረት ዝናብም የምህረት አምላክ ከሆነው ከእግዚአብሔር እጅ የምናስለቅቅበት፣ ምድሪትዋ ታሪክ በሚለውጥ ቅባት የምናርስበት በር እነሆ ወለል ብሎ ተከፍተዋልና በመንፈሳዊ ልጅነቴ ለዚህ በታላቅ ጩኸት እየተስተጋባ ያለውን ድምጽ ይሁንታችሁን ትሰጡ ዘንድ ሰላምንም ታወርዱ ዘንድ ጥሬን አቀርባለሁ።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ብጹዓን አበው ሊቃ ጳጳሳት:ሰው ከሰው ጋር ተላትሞ ታግሎም ያጣና የተሸነፈ እንደሆነ ትልቅ የሞራል የሥነ ልቡናና የአካል ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል ሁላችን የምንስማማበት እውነት ነው። ዳሩ ግን ከሰው እጅ አልፎ ፋይሉ በእግዚአብሔር እጅ በገባ ጉዳይ ግን ስለ እግዚአብሔር መሸነፈንና መተው ውርደትና ሽንፈት ሳይሆን በአንፃሩ ከብርና ሞገስ የጽድቅም አክሊል የሚያቀዳጅ እንደሆነ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት አንድ ብለን ቆጥረን አንዘልቀውም። ስለሆነም
አንደኛ:ቅዱስ ሲኖዶስ በፓትሪያሪክ ጳውሎስ ሞተ ሥጋ/ህልፈት በማስመልከት ሳይውል ሳያድር የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ለቤተሰቦቻቸውንም መጽናናት በመመኘት ይፋዊ መግለጫ ይሰጥ ዘንድ በእግዚአብሔር ሥም እጠይቃለሁ። ስለ ምድሪትዋ ከመስማት አልፈው አይተዋት የማያውቁ እንግዶች፣ የሌሎች ቤተ እምነት የኃይማኖት መሪዎች ሐዘናቸውን ለመግለጽ ከየአቅጣጫው እየጎረፉ በሚገኙበት ሰዓት በአካል ለመገኘት ለጊዜው ሁኔታዎች ባይፈቅዱም ካላችሁበት ስፍራ ሐዘናቹን መግለጽ በምትችሉበት መንገድ በመጠቀም መንፈሳዊ ግዴታሁን በመወጣት ድምጻችሁን አሰሙ። ይህን ካለ ማድረግ ብትቆጠቡ ግን ለሰሚ ጆሮም ጸያፍ ነው የሚሆነው።
ሁለተኛ: ክፉም ሆነ ደግ የአንድ መሪ ከስፍራው በሞት መለየት ሊያስከትለው የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ ቤተ- ክርስቲያኒቱሰለባ ላለመሆንና አንድ ጊዜ በተፈጸመው ስህተት ለረጅም ዓመታት የታመሰችውንና የተበታተነውንም የቤተ እምነቱ ተከታዮች ልብ መጠገንና አንድ የማድረግም ኃላፊነቱ አላችሁና የተጀመረውን የዕርቀ ሰላም አጀንዳ እንደተጠበቀ ሆኖ ቅዱስ ሲኖዶስ ፓትሪያሪክ መርቆሪያስ ወደ ቀድሞ መንበራቸውን በመመለስ ረገድ ቀጣዩን ወሳኝ ምዕራፍ ለመጫውት ፍላጎት ማሳየት፣ የጎላ እንቅስቃሴ ያደርግም ዘንድ በመንፈሳዊ ልጅነቴ በድጋሜ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
United States of America
August 18, 2012