Thursday, August 16, 2012

ሰበር ዜና፤ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አረፉ።



ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ያገኘነው ዘገባ አረጋግጧል። በሳምንቱ መጀመሪያ ገደማ ለሕክምና ዳጃች ባልቻ ከገቡ በኋላ አንዳንዶች ህመማቸውን እንደህመማቸው ቆጥረው ሳይሆን መታመማቸው ይፋዊ ዜና እንዲሆንላቸውና መጨረሻቸውም በሚፈልጉት መንገድ ሲያበቃ ለማየት የቋመጡ  ያህል ሲዘግቡ የሰነበቱበት እውን ሆኖ   በ9/12/ 2004  ዓ/ም ንጋት ላይ  አርፈዋል።
የቅዱስ ፓትርያርኩን ሞት ለረጅም ዘመን ሲጠብቁ የቆዩ ደስ ሲላቸው እስከ ሰውኛ ድክመታቸው ፓትርያርኩ ለዚህች ቤተክርስቲያን የሚችሉትን ያህል ሰርተዋል የሚሉ ደግሞ ማዘናቸው አይቀርም። ደጀ ብርሃን ብሎግ አቡነ ጳውሎስ ከስህተትና ከሰውኛ የድካም ጠባይዓት ፍጹም ነጻ ነበሩ ብላ ባታምንም  ቤተክርስቲያኒቱን ደከመኝ፤ ሰለቸኝ ሳይሉ በማገልገል፤ የተወረሱባትን ሃብትና ንብረት በማስመለስ ረገድ ትልቅ ስራ መስራታቸውን፤ በቅዳሴ አገልግሎት በህመም ውስጥ እንኳን እያሉ ማገልገላቸውን ትመሰክራለች።
አቡነ ጳውሎስን በአስተዳደር፤ በገንዘብ ጉዳይ፤ በዘረኝነት የሚወቅሱ ወገኖች አሁን በሞት ሁሉን ነገር ትተውላቸው ሲሄዱ ፍላጎታቸውን ሊያሟላ የሚችል ጳጳስ በመፈለግ «ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ» እንዳይሆን ከወዲሁ ትልቅ ፍርሃት አለን።
 በቀጣይ ጽሁፋችን ሙሉ ታሪካቸውን ይዘን የምንቀርብ ሲሆን እግዚአብሔር የወደደውን እንዲያደርግ ከማሰብ ባሻገር በጥላቻም ይሁን መጠን ባለፈ ምስጋና ውስጥ እንዳንሆን አንባቢዎቻችንን ለማሳሰብ እንወዳለን።
እግዚአብሔር በዐጸደ ቅዱሳን እረፍቱን ይስጥልን!