Sunday, August 26, 2012

የፓርትርያርክ የምርጫ ግርግር ለማኅበረ ቅዱሳንና ለወዳጅ ጳጳሳት ጥቅም እንዳይውል ያስፈራል!


ቅዱስ ፓትርያርኩ ቢቻል ከስልጣናቸው በሆነ መንገድ ቢነሱ፤ ባይቻል እንኳን ባሉበት ተሽመድምደው መስራት የማይችሉበት ገጠመኝ ቢከሰት ብዙ የደከመው ማኅበር፤ ማኅበረ ቅዱሳን እንደነበረ ይታወቃል። በየሲኖዶስ ጉባዔያት ፓትርያርኩም ይሁኑ ጽነት የሞላባቸው ጳጳሳት የየራሳቸውን ዓላማ የማስጠበቅ ህልም ለማሳካት ሲሉ ጥቅምትና ግንቦትን በቤተክርስቲያን አካባቢ የውጥረት ወራት አድርገው እንደሚያሳልፉ የምንረሳው አይደለም። ማኅበሩም ለውጥረቱ መባባስ አንዱ ምክንያት ሆኖ ለመቆየቱ ማሳያዎቹ፤ የሲኖዶስ ነደ እሳትና ጀግና እየተባሉ በስም የሚደገፉት ጳጳሳት ብዙ ጊዜ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር እሳትና ጭድ ሆነው በጉባዔው ላይ ውጥረት ፈጣሪዎች በመሆናቸው ነበር። ውጥረት ፈጣሪዎቹን ጳጳሳት ስንመለከት በእርግጥ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር እሳትና ጭድ ሆነው ጥቅምትና ግንቦትን የሚያጨሱት ለቤተክርስቲያን የሚቆረቆርና የሚመሰከርላቸው ሃይማኖታዊ፤ ሞራላዊና  ክርስቲያናዊ ማንነት ስላላቸው አልነበረም።  ስለምናውቀው ማንነታቸው፤ የኅሊና ጸጸት ስላላቸው ሳይሆን፤ ይልቁንም በውጥረቱ ውስጥ ብርቱ አሳቢና የቤተክርስቲያን ታጋይ ሆነው በመታየት የራሳቸውን ስብእና ለመገንባትና የስልጣን ጫናቸውን ለማሳረፍ ሲሆን በሌላ መልኩም ማንነታቸውን እንደመጽሐፍ የሚያነባቸውን ማኅበር ዓላማዎች በማስጠበቅ ውጪያዊ ስእላቸውን ለማሳመር ብቻ እንደነበር እንረዳለን።  አሁንስ?  አሁን እንግዲህ በማኅበሩም ሆነ በውጥረት ፈጣሪ ጳጳሳት ዘንድ የሚጠሉት ፓትርያርክ ጥሩም ሰሩ መጥፎ፤ ፍርዱን ለታሪክና ለትውልድ ትተው ላይመለሱ ሄደዋል። የቀሩት እነዚህ ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ገጾች ብቻ ናቸው።
   ማኅበሩና ውጥረት ፈጣሪ ነደ እሳት ጳጳሳት ከእንግዲህ ባዶ ቦታውን ለመሙላት ምን ማድረግ እንደሚገባቸው የእኛ ምክር የሚያስፈልጋቸው አይመስለንም። ልንናገረው የምንችለው ነገር ቢኖር  ከዚህ በፊት 7 ኰሚቴ አዋቅረው የፓትርያርኩን እጅ ለማሰር የሞከሩት እንቅስቃሴ የነበረ ቢሆንም  በፓትርያርኩ ብርቱ እርምጃ ተቀምተው የነበረውን ክፍተት ዛሬ ከሞታቸው በኋላ ያለ ከልካይና ተቃውሞ መሙላት መቻላቸውን ነው። ይህ አንድ ድል ሆኖ ሊመዘገብላቸው ይችላል። በእርግጥ የሲኖዶስን ውሳኔ የሚያስፈጽም በየሦስት ወሩ የሚመረጥ ቋሚ ሲኖዶስ አባላት እያለ ዛሬ  የ7 ኰሚቴ መኖር አስፈላጊቱ  ግልጽ አይደለም። ፓትርያርኩ በሕይወት እያሉ ያስፈለገበት ምክንያት ግን ስልጣን ለመንጠቅ ነበር። ዛሬ የሚነጠቅ ስልጣን ስለሌለ በቋሚ ሲኖዶስ ላይ ተደራቢ 7 የኮሚቴ  ሲኖዶስ መመደቡ አስፈላጊ አልነበረም። ይሁን እንጂ ይነጠቅ ዘንድ የተፈለገው ሥልጣነ ፓትርያርክ ባዶ ቢሆንም ይህንን  የሚጠብቅና የሚከላከል ኃይል ስለሚያስፈልግ እንዲቋቋም ተደርጓል። በመጪው ጊዜ ስልጣነ መንበሩንም ለመሙላት ይህ ኰሚቴ አመቻች ኃይል ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው። ከዚያም በላይ የዚህ ኰሚቴ አስፈላጊነት በፓትርያርኩ መንበር ላይ የተፈለገውን ሰው ለመሰየም ይቻል ዘንድ ፍርሃትና ጥርጣሬን ለመከላከል ብሎም በሃይማኖታዊ ነጻነታችን ውስጥ ጣልቃ መግባት ይቁም የሚል ተዋጊ ኃይል ሆኖ የተቋቋመ ስለመሆኑም እንገምታለን።  ጣልቃ ሊገባ ይችላል ተብሎ የሚፈራው ወገን ደግሞ አንድም ከውጪው ዓለም በፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራው ሲኖዶስ ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር በሚያደርገው ድርድር ምክንያት ሊመለስ ይችላል የሚል ፍርሃትና ስጋት አለ። በሌላ መልኩም ሁለቱ ቡድኖች ማለትም ማኅበሩና የማኅበሩ ታማኝ የጳጳሳቱ ኰሚቴዎች ያዘጋጁት እጩ በመንግስት ጣልቃ ገብነት ወደ መንበሩ እንዳይመጣ ሊደረግ ይችላል የሚልም ፍርሃት ታሳቢ ነው።  ስለዚህ ይህንን ውጥረት በማርገብ  ዓላማቸውን ለማስጠበቅ አስቀድሞ በሚዲያ ስራ የማንቃትና፤ የማደራጀት ላይ መስራት አስፈልጓቸዋል። ከዚህ ውስጥ አንዱ ማሳያ የማኅበሩ አፈ ብሎግ ደጀ ሰላም ደጋግማ የምታወጣው ጽሁፎች ሊጠቀሱ ይችላሉ። እስኪ ለአብነት እንመልከት።
“ቤተ ክርስቲያናችን አዲስ ፓትርያርክ ከመምረጧ አስቀድሞ አሁን ከገባችበት ዝብርቅርቅ ሁናቴ ለማገገም፣ ከሐዘኗም ለመጽናናት እና አሠራሯን በሥርዓተ አበው መሠረት ለማከናወን ጊዜ ያስፈልጋታል።”
መቼም ማኅበረ ቅዱሳን በአቡነ ጳውሎስ ኅልፈት  እንደሰውኛ ሃሳብ በሞት ደስ ባይሰኝም ሀዘን ላይ ወድቆ፤ ድንኳን ጥሏል ማለት መቀለድ ይሆናል።  ጥቅምትና ግንቦት በመጣ ቁጥር ነደ እሳቶቹ  ጳጳሳት በጉባዔ ላይ ፓትርያርኩን ከማብገን ወጥተው ከሞታቸው በኋላ  በአቡነ ጳውሎስ ሞት ደረታቸውን እየደቁ ሀዘን ተቀምጠዋል ቢባልም ማሾፍ ነው። ታዲያ እነደጀ ሰላም ከሀዘናችን ለመጽናናትና ከዝብርቅርቁ ለማገገም ጊዜ ያስፈልገናል ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? አዎ ሁኔታዎችን እስክናመቻች አታስቸኩሉን የማለታቸው ነገር የሚያሳየን፤ አስቸኩለው ኮሚቴ ማዋቀራቸውና ከፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር በኋላ ይደረጋል የተባለውን ዐቃቤ መንበር በማስቀመጥ ማጣደፋቸው፤ አታስቸኩሉን፤ ሁሉን እስክናመቻች የምትዘናጉበትን ጊዜ ስጡን ማለታቸው ነው። 
     ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው የቤተክርስቲያን አንዱ መጥፎ ገጽታ ባለፉት ዘመናት በሁለት ተከፍላ በአቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ የውጪ ሲኖዶስ መኖሯ ነው። ይህ አንድነት ሳይመጣ ኅልፈተ አቡነ ጳውሎስ መሆኑ ቢያሳዝንም አቡኑ በሕይወት እያሉ ለአንድነቱ አለመምጣት የእሳቸው ስልጣን ላይ መቆየት ምክንያት እንደሆነ ሲያሳጧቸው የኖሩት ኃይሎች ከሞታቸው በኋላ ማንነታቸው ገሃድ እየወጣ ነው። ማኅበሩና ነደ እሳቶቹ ጳጳሳት እንደቀደመው ጩኸታቸው እርቁ በአስቸኳይ ይፈጸም የሚል ድምጻቸው ጠፍቷል። እንቅፋት ናቸው የተባሉት ፓትርያርክ እንቅፋት መሆናቸው በሌለበት ሁኔታ አሁንስ ምን ይጠበቃሉ? ከጥልቁ ሀዘን ለመጽናናትና በአቡነ ጳውሎስ ሞት የተሰበረ ልባቸው እስኪያገግም ጊዜ አስፈልጓቸው ይሆን?  ነገሩ እውነትነት ባይኖረውም እንኳን እንደእውነት ብንቀበለው በሥርዓተ አበውም ይሁን በሲኖዶስ ሕግ ከቋሚ ሲኖዶስ ውጪ፤ ኰሚቴ የሚባል የሲኖዶስ አባላት ቡድን ይዋቀራል የሚል ስለሌለ ፓትርያርክ ሳይመጣ የፓትርያርኩን ስልጣን የመቀማት ስራ አስቀድሞ እየተሰራ ስለሆነ ጊዜ ያስፈልጋል የሚባለው የሀዘንና የመጽናናት ቃላት ተራ ማታለያ መሆናቸውን ተግባር ራሱ ያረጋግጣል።የራስን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ እንጂ ቤተክርስቲያኒቱ ወደ አንድነት እንድትመጣ ወይም እምነትና ፍቅር የሚጣልበት አባት ወደ መንበር እንዲመጣ ተፈልጎ አይደለም ብለን መናገር እንችላለን። ወደፊትም ቢሆን ቤተክርስቲያንን ወደ አንድነት ለማምጣት የማይጠቅም ኰሚቴ ስልጣን ለመቀማት የተደራጀ መሆኑን ከማስመስከር በላይ አንዳችም መልካም መስራት የማይችል ነው።
ይልቁንም አፈ ብሎጉ ለዓላማው መሳካት የሚያስፈራውን ኃይል እንዲህ ሲል ይጠቁመናል።
«በአዲሱ ፓትርያርክ ምርጫ ላይ የራሳቸው “ጥቅም” እና ፍላጎት ያላቸው አካላት፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች መኖራቸው እሙን ሲሆን ከነዚህ ሁሉ ኃይለኛው እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ እና ሥልት ያለው ግን መንበረ መንግሥቱን የተቆናጠጠው የኢሕአዴግ አስተዳደር ነው»
እርግጥ ነው፤ በኢትዮጵያ የቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ  ቤተክርስቲያንን ያልተጠጋ አይነግስም፤ ንጉሡም ቤተክርስቲያንን ለዓላማው ስኬት ካልተጠጋ መውደቁ አይቀርም። አፄ ቴዎድሮስን ለሞት ያበቃቸው አንዱ ምክንያት ከቤተክርስቲያን መጣላታቸው እንደነበር ታሪክ ይናገራል። የሩቁን ትተን የቅርቡን ብንመለከት አፄ ኃ/ሥላሴም ቤተክርስቲያን አንድ ክንዳቸው ነበረች። ፓትርያርክነትን በማስመጣትና ለሥልጣን በማብቃትም ውስጥ ንጉሡ እጃቸው ነበረ። ደርግም ቢሆን ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ባይችል፤ ከእጁ እንዳትወጣ የሚፈልገውን በማስሾምና የማይፈልገውን በመግደል ሚና ነበረው። የኢህአዴግም ረጅም ዓላማና እቅድ እንደፖለቲካ ጫወታ ሕግ ቤተክርስቲያንን በቁጥጥር ስር ማስገባት የሚጠበቅ እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም። መረሳት የሌለበት ነገር በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ ሳትቆጣጠረው በነጻ የምትለቀው ማኅበር ወይም ድርጅት እንደሌለ ነው። ስለዚህ በየትኛውም መንገድ ሚሊዮኖች አባላት ያሏትን የረጅም ዘመን ተቋም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በነጻ ይለቃታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ይልቁንም የመንግሥት እጅ በሰፊው እንዲናኝ እድል የሚከፍቱት ጳጳሳትና የቤተክርስቲያኒቱ ኃላፊዎች ራሳቸው ናቸው። ታሪክ የሚያሳየን ያንን እውነት ነው። አቡነ ቴዎፍሎስ ሲገደሉ የጳጳሳት እጅ ነበረበት፤ አቡነ ተ/ሃይማኖት ሲሾሙም ከመንግሥት ድጋፍ ነጻ አልነበሩም፤ የአቡነ መርቆሬዎስም ሹመትና ስደት የመንግሥትና የጳጳሳት የጋራ እጅ እንዳለው ይታወቃል። በአቡነ ጳውሎስም እንዲሁ!

ዛሬም ይኸው እንዳይቀጥል የሚያሳስባችሁ መንግሥት ለራሱ ዓላማ ሲል የእናንተን እቅድ በተለመደው እጁ እንዳያደናቅፍባችሁ እንጂ ለቤተክርስቲያን ልእልና ከማሰብ አንጻር አይደለም። ለቤተክርስቲያን ዓላማና ለእግዚአብሔር መንግሥት ታማኝ የሆኑ የቤተክርስቲያን መሪዎች «የቄሳርን ለቄሳር፤ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር» ብለው ሁሉን በየመልኩ ማድረግ ይጠበቅባቸው የነበረ ቢሆንም ለዚህ ስላልታደልን የመንግሥታት እጅ መግባቱ አይቀሬ ሆኗል። ይልቁንም ጳጳሳቱ በዘመናቸው እንደሥልጡን ባሌስትራ ሲተጣጠፉ የኖሩ በመሆናቸው መንግሥት እጁን ጫን አድርጎ ሲያስገባ አብረው ለመስራት የሚተጉ መሆናቸው ስለሚታወቅ ለቤተክርስቲያን ልእልና ማንም እንደማይቆም እናውቃለን። ስለዚህ አሁን የሚታየው የዓላማ ግጭት በመንግሥት ስውር እጅና በማኅበሩና ደጋፊ ጳጳሳት መካከል ይሆናል ማለት ነው። ለጊዜው አሁን ኃይልና ስልጣን ያለው  በእነዚህ ሁለቱ አካላት እንጂ በአባላቱ ላይ አይደለም።  አባላቱ የሚፈለጉት በፍጻሜው የጫወታ ሜዳ ላይ ለጭብጨባ  ነው።
እንደእውነቱ ከሆነ በማኅበረ ቅዱሳንና በደጋፊ ጳጳሳቱ ላይ ለቤተክርስቲያን የሚበጅ ነገር መጠበቅ አስቸጋሪ ነው። መስራት የሚችሉበት እድል እንዳለ ቢታመንም መስራት የሚችል ባህርይ የሌላቸውና የራሳቸውን ዓላማ ግብ ያነገቡ ኃይሎች ስለሆኑ ከእነዚህ የምንጠብቀው አስተማማኝ ነገር አይኖርም። አሁን ያለን ተስፋ ከመድኃኔዓለም በታች በመንግሥት ላይ ነው። ይልቁንም መንግሥት እጁን በመስደድ ከስልጣን ያስወገዳቸውን ፓትርያርክ በመንበር እንዲመለሱ በማድረግ  ሦስት  ነገር በአንዴ እንዲሰራ እንፈልጋለን። ይኸውም፤
1/ በዘመኑ ለሁለት የተከፈለችውን ቤተክርስቲያን አንድ በማድረግ መጥፎ ታሪኩን ማደስ ይችላል።
2/ በተከፈለችው የአንዲቱ ቤተክርስቲያን ሁለት ጎራ ውስጥ ችግሩን በማራገብ  ተከልለው የቆሙ የፖለቲካ ቡድኖችን ባዶ ማስቀረት ይችላል።  አልፎ ተርፎም ለእርቅና ሰላም በር ይከፍታል።
3/ የቤተክርስቲያኒቱን ከፍተኛ የሥልጣን እርከን በቡድን ለመቀማትና ለራሳቸው ግብ መሳካት ያሰፈሰፉትን የውስጥ ኃይሎች ዓላማ ማክሸፍ ይቻላል።
ስለዚህ መንግሥት ይህን እድል በመጠቀም ለቤተክርስቲያን ኅልውና የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እንፈልጋለን። ይህ አባባል ደስ የማያሰኛቸው ወገኖች እንዳሉ ብናውቅም አሁን ባለው ሁኔታ ቤተክርስቲያኒቱን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚፈልግ አካል በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ እንደሌለ ስለምናምን፤ ተቃዋሚ ወገኖች መንገዱን ያመላክቱን ዘንድ እንጠይቃቸዋለን።
ይልቁንም ለአንድነት ሳይሆን ለስልጣን ነጠቃ ያሰፈሰፉ ወገኖች አሉ። ፓትርያርክ ሳይሾም ኰሚቴ መዋቀሩ የፓትርያርኩን ስልጣን አስቀድሞ በመንጠቅና መጪውን ፓትርያርክ ወንበር ላይ አስቀምጦ የሙዚየም ቅርስ የማድረግ አንዱን እቅድ ሲፈጸም አይተናል።
የዚህ ኮሚቴ አስፈላጊነት የጳጳሳቱን ጀርባና ጥቃት ለመከላከል፣ ጥቅማችንን ያስነካል ብለው ባሰቡት ነገር ላይ ሁሉ አስቀድሞ ለመከላከል የተደራጀ መቺ ኃይል ነው። በሌላ መልኩም ከማኅበሩ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለመስራት ፈቃደኝነቱ ያለው፤ ከፓትርያርኩ በላይ ሊፈራ የሚችል አንጃ ነው። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያልታጠቀ  የፍርድ ሰጪ ምክር ቤት መሆኑ ነው። በንድፍ ሲቀመጥም ይህንን ይመስላል።