Saturday, August 4, 2012

በድንግል ማርያም ትንሣዔና እርገት ታሪክ ላይ ችግር አለ!


ቅዱሳንን ስለማክበር ምንም ጥያቄ የለንም። መታሰቢያ ማድረግም የነገሮችን ሁሉ ባለቤት እስካልተካ ድረስ የሚደገፍ ነው። ነገር ግን  «ጥቂት አሻሮ ይዞ፤ ዱቄት ወዳለው መጠጋት» የሚለውን ብሂል ለመተግበር መሞከር ግን ተቀባይነት አይኖረውም። በተለይም በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ወቅት ወንጌል እንደዚህ ስለሚል፤ እኔም እንደዚህ ብል ችግር የለውም የሚለውን ራስን መሸሸጊያ ምክንያት በማቅረብ ለመከለል መሞከር አያዋጣም። ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሱትና እነዚህ የመሳሰሉ የስህተት ችካሎች አልነቀል ያሉት በምክንያት ስር በመወሸቃቸው ነው። ራሱን የማርያምን እረፍትና ትንሣዔ ሳይሆን በማርያም እረፍት፤ ቀብር፤ ትንሣዔና እርገት ላይ ያሉ አስተምህሮዎችን ለመቃኘት እንሞክራለን።
ስለማርያም እረፍት፤ ትንሣዔና እርገት አብያተ ክርስቲያናት አንድ ዓይነት የእምነት አቋም የላቸውም። እንዲያውም ስለማርያም ሞትና የእርገት ዕለት በግልጽ የሚታወቅ ማስረጃ እንደሌለ በ5ኛው ክ/ዘመን  የኖረው የሳላሚሱ ኤጴፋንዮስ   ተናግሯል። [ 1 ] ዕረፍቷና እርገቷ በኢየሩሳሌም እንደሆነ  የሚናገሩ ቢኖሩም  ይህንን አባባል የማይቀበሉ አብያተ ክርስቲያናትና የቴኦሎጂ ምሁራን ሞልተዋል። በኢየሩሳሌም አርፋለች የሚለውን አባባል የማይቀበሉበትን ማስረጃ ሲያቀርቡም ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ እንደተናገረው «እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት»  ዮሐ19፤27 ባለው መሠረት ማርያም እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ከዮሐንስ ጋር ስለኖረችና ወንጌላዊው ዮሐንስም ከጌታ ሞት በኋላ በኢየሩሳሌም  ጥቂት ዓመታትን ከቆየ በኋላ በ37 ዓ/ም ገደማ ወደ ቤዛንታይን ከተማ ኤፌሶን ሄዶ ወገኖቹን ወንጌል እያስተማረ መቆየቱንና  ማርያም በሞት እስከተለየችው ድረስ  ከ48-52 ዓ/ም እዚያው እንደነበር ብዙ ተጽፏል። ከማርያም ክፍል ትይዩ ያለው የዮሐንስ መኖሪያ ቤት ፎቶ፤

 በኋላም  በቅርብ ርቀት ባለችው ደሴተ ፍጥሞም  በግዞት መኖሩ ይነገራል ።  አንዳንዶች ከዶሚኒሽን አገዛዝ ቀደም ብሎ የራእይ መጽሐፉን  ከ55-65 ዓም ገደማ እንደጻፈም  ይናገራሉ።
ዋናው ነገር  ማርያም በኤፌሶን ከዮሐንስ ጋር ኖራለች  ወይስ አልኖረችም ነው ጥያቄው።  በኢየሩሳሌም አርፋለች የሚሉ ሰዎች አንድም ጊዜ ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን ኖራለች ሲሉ አይደመጥም። ለምን?  ዮሐንስ ማርያምን እንደእናት ሊይዛት አደራ ተሰጥቶታል የሚባል ከሆነ ከዮሐንስ ጋር ኤፌሶን ስለመቀመጧ የማይነገረው ለምንድነው?  ዮሐንስ እስከ 96 ዓመቱ ድረስ ከኤፌሶንና ከደሴተ ፍጥሞ ውጪ ስለመኖሩ የተነገረ ነገር የለም። ማርያም ከዮሐንስ ጋር በኤፌሶን አልኖረችም ብሎ በመከራከርና በኢየሩሳሌም ኖራ፤ እዚያው ማረፏን በግልጽ በመናገር  መካከል ልዩነት አለ።  «እነኋት እናትህ» ባለው መሰረት አብረው ኤፌሶን ኖረው እዚያው ማረፏን የማይቀበሉና  ኢየሩሳሌም ኖራ አርፋለች የሚሉ ሰዎች እንደልጅና እናት አብረው የመኖራቸውን የወንጌል ቃል መካድ ሊሆንባቸው የግድ ነው። ያ ደግሞ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ በኢየሩሳሌም ኖራ እረፍቷም፤ ቀብሯና እርገቷ ሆነ ከሚለው አስተምህሮአቸው ጋር «እነኋት እናትህ» የሚለው  የወንጌል ቃል ስለሚጋጭባቸው ለዚህ ዓይነት ያፈጠጠ እውነት ምን እንደሚሉ አይታወቅም። ወይ ደግሞ ኤፌሶን ላይ እድሜውን ሙሉ የኖረው ዮሐንስና ኢየሩሳሌም ማርያምን ይዞ የኖረው ዮሐንስ የተለያዩ ናቸው ሊሉ ይገባል።
ሮበርት ክሬው የተባለ የነገረ መለኮትና የታሪክ ጸሐፊ ዮሐንስ ወንጌላዊ ዘመኑን ሁሉ በኖረበት ከኤፌሶን ከተማ 8 ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ ባለች ኰረብታ ላይ በተሰራ ቤት ውስጥ እንደኖረና ማርያምም እዚያ ማረፏን ጽፏል።  ይህንን በኤፌሶን ያለውን የማርያምን መቃብር የዓለም ክርስቲያኖች እንዲሆም ሙስሊሞች ሳይቀሩ ይጎበኙታል፤ ይሳለሙታል።  በቱርክ ግዛት ያለው ይህ ስፍራ በቱርካውያን ሙስሊሞች ዘንድ «ሜሪዬማና» ተብሎ ይጠራል።  ይህ ስዕል የሚያመለክተው ያንን ስፍራ ነው።

ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም የተለየችው መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት የምሥራቁና የምዕራቡ ጎራዎች የተለያየ አመለካከት አላቸው።
 በተወለደች በ58 ዓመቷ ዐርፋለች የሚሉ አሉ። በ72 እና 63 እድሜዋም አርፋለች የሚሉ መረጃዎች አሉ። እንደ ግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ግን የሚታመነው በ64 ዓመት እድሜዋ ማረፏ ነው።  ኖረችበት ተብሎ ከሚገመተውና አርፋለች ከሚባለው ቦታ ያለው ልዩነት እንዳለሆኖ በጥር ወር ከዚህ ዓለም ተለይታ በ40ኛው ቀን ማረጓን የሚናገሩ አሉ። በነሐሴ ወር አርፋ ከተቀበረች በኋላ ትንሣዔዋን ሳያዩ መቃብሯ ባዶ ሆኖ ስላገኙት ሐዋርያት ሱባዔ ይዘውበሦስተኛው ቀን ተገለጸችላቸው የሚሉም አሉ። እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ደግሞ በጥር ሞታ፤ በነሀሴ ተቀበረች የሚል ትምህርት አለ። በጥር ወር አርፋ፤ በነሀሴ ተቀብራለች የሚሉ ሰዎች ሥጋዋ በገነት ዛፍ ስር ለስምንት ወራት መቀመጡንና በሱባዔ ጸሎት በተደረገው ልመና የተነሳ ለመቀበር መቻሏን አስፋፍተው ይነግሩናል።

 
 በጥር ወር እንዳረፈች፤ ለመቀበር ያልቻለችውም ታውፋንያ የሚባል ሽፍታ፤ ጎራዴ ሲመዝባቸው ወደ ቀብር ሥጋዋን ተሸክመው ይሄዱ የነበሩት ሐዋርያት በመፍራት ጥለዋት በመሸሻቸውና ዮሐንስ ብቻውን ቀርቶ ወደ  መቃብር ሳትገባ ወደ ገነት ዛፍ ስር በመወሰዷ እንደሆነ ይነገራል።  ዮሐንስም ወደቤቱ ማምራቱንና ሸሽተው የነበሩትም ሐዋርያት ሥጋዋስ የታለ? ብለው ቢጠይቁት በገነት ዛፍ ስር መቀመጧን  ስለነገራቸው ዮሐንስን ገነት ዛፍ ስር ሬሳዋ መቀመጡን አይቶ ለምን እኛስ ይቀርብናል በማለት ነሐሴ 1/ ቀን የጾም የጸሎት ሱባዔ ጀምረው በ15ኛው ቀን ትኩስ ሬሳ ከገነት ዛፍ ስር እንደመጣላቸውና እንደቀበሯት ይናገራሉ። ይህ እንግዲህ በ49 ዓ/ም ገደማ መሆኑ ነው። ዮሐንስ ግን ኤፌሶን መኖር ከጀመረ 10 ዓመት አልፎታል።
ሌላው ጥያቄ የሚያስነሳው ነገር  በጥር ወር አርፋ  ከቀብር በፊት ወደገነት ዛፍ ስር ስለመወሰዷና  ዮሐንስ ወደ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ከነገራቸው በኋላ እሱ ያየውን እነርሱም ለማየት ሐዋርያቱ ለስምንት ወር ያህል የቆዩበት ምክንያት ግልጽ አለመሆኑ ነው። ሐዋርያቱ የልባቸውን ተምኔት ለማሳካት ሱባዔ ባያደርጉ ኖሮ የማርያም ሥጋ ከገነት ዛፍ ስር አይንቀሳቀስም ነበር ማለት ነው?
 ሌላው ደግሞ ይህ የማርያም ሥጋ አርፎበታል የሚባለው የገነት ዛፍ ምንነትና የሙት ሥጋ ማረፊያ ተብሎ የሚመረጥ የገነት ዛፍ ስለመኖሩ እግዚአብሔር  እንደዚህ ዓይነት አሰራር እንዳለው ለሰው ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ያላሰፈረ አዲስ ግኝት የመሆኑ ጉዳይ ነው። በሌላ መልኩም  የማርያም ሥጋ ለመቀበር የግድ የሐዋርያቱን ሱባዔ  በተስፋ እየጠበቀ የመቆየቱ ነገር አስገራሚ ይሆናል።
እንደሰዎቹ አባባል በጥር ወር አርፋ ሳይቀበር የቀረውን የማርያምን ሥጋ በስምንተኛው ወር ከገነት ወጥቶ ከተሰጣቸውና ከቀበሯትም በኋላ ቢሆን ሐዋርያቱ እርግቷን ለማየት አልቻሉም። ሐዋርያቱ ቀብረዋት ወደ ቤታቸው  ከገቡ በኋላ ቶማስ ሐዋርያው በደመና ተጭኖ ከህንድ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ማርያምን ሐዋርያት በቀበሯት በሦስተኛው ቀን ወደ ሰማይ ስታርግ የዳመናው ጎዳና ላይ ያገኛትና ቀድሞ የልጅሽን እርገት ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንቺን ሳላይ ልቀር ነው? ብሎ ቢያዝን ትንሣዔዬን ያላንተ ማንም አላየም ካለችው በኋላ የተገነዘችበትን ጨርቅ እና ሰበን ለምልክት ሰጥታው እንዳረገች ሰፊ ታሪክ ይነገራል።
ሰዎቹ ነገሩን ሁሉ ለማጣፈጥ የሚጠቀሙበት ነገር አስገራሚ ነው። የሰው ልጅ ከትንሣዔው በኋላ የዚህን ዓለም ጨርቅና ልብስ እንደተሸከመ ወደ ሰማይ ይገባል ማለት ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ነው ወይ? የሚል ጥያቄን ያስነሳልና ነው። ወንጌል ከትንሣዔ በኋላ ክርስቶስን ይመስል ዘንድ ሰው  ይለወጣል ይላል እንጂ የመቃብሩን ልብስና ሰበን እየተሸከመ ያርጋል የሚል አስተምሮ የለውም።
« 2ኛ ቆሮ 3፤18
እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን»
ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በመቃብሩ የተገነዘበትን ጨርቅ ትቶ መነሳቱን እንጂ  ያንኑ ለብሶ መነሳቱን አላነበብንም።
ዮሐ 20፤6-8 «ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ»
የሁላችን አማኞች ትንሣዔ የክርስቶስን ትንሣዔ መምሰል ካለበት በቀብር ወቅት ከዚህ ዓለም ጉድጓድ የገባ ጨርቅ ወደ ሰማይ አብሮን የሚያርግበት ምንም መንገድ የለውም።
ስለዚህ ተጠራጣሪ እንደሆነ ሁል ጊዜ የሚነገርበት ቶማስን በማርያም ትንሣዔ ላይ ግን የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ  ሲባል ማርያም ወደ ሰማይ ስታርግ የመቃብሯን ከፈን ተሸክማ የሄደች በማስመሰልና ለምልክት ይሆን ዘንድ ከፍላ  ሰጠችው የሚለው አባባል በአንዳችም ነገር  ከወንጌል እውነት የተጠጋ አይደለም።
ሌላው ነገር በመንፈስ ቅዱስ በመነጠቅ፤  በሌላ ስፍራ ወዲያውኑ መገኘት ስለመቻል ለሐዋርያው ፊልጶስ  ከተነገረው የወንጌል ቃል  በተለየ በዳመና ላይ ተቀምጦ ስለመሄድ ግልጽ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ባይኖርም የቶማስን ከህንድ ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ እንደፊልጶስ መነጠቅ አድርገን ብንቆጥረው እንኳን የቶማስ ሰብአዊነትና የማርያም የእርገት ማንነት የተለያየና ፈጽሞ የማይገናኝን ነገር ለማቀራረብ መሞከር ነው። የቶማስን የዳመና ላይ ውይይትን ከረቂቅ  ክርስቶሳዊ አዲስ ፍጥረት ጋር ለማገናኘት መሞከር የጥንቶቹን የግሪክ ወጎች/fable story/ እንድናስታውስ ያደርገናል።
በሞትና በትንሣዔ እንዲሁም በእርገት መካከል እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን እግዚአብሔር በሰውኛ ትረካ ይጫወታል ማለት እግዚአብሔር ስለሞትና ትንሣዔ በተናገረው መቀለድ ይሆናል።
ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ማርያምን በጥር ሞታለች ያሉ ሰዎች፤  በመጀመሪያው ሞት ዮሐንስ ብቻ እድለኛ ሆኖ በገነት ዛፍ ስር ለማየት በመቻሉ፤  በኋለኛውም ቀብር ቶማስ ብቻ ተጠቃሚ የሆነበትን የእርገት እድል፤  ሌሎቹ ሐዋርያት ለማግኘት ባለመቻላቸው በቀጣይ ዓመት ነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባዔ ለመያዝ መገደዳቸውንና በ16ኛው ቀን  ሁለተኛ  ትንሣዔና እርገትን ለማየት የመቻላቸው ነገር ነው። ቀብር ሳይኖር ትንሣዔዋንና  እርገቷን እንዴት ማየት እንደቻሉ ግልጽ አይደለም። በምሳሌ ይሁን በምትሃት እርግጠኝነቱን ያብራራ ማንም የለም።  ሁለት ጊዜ ትንሣዔና እርገትስ ማለት ምን ማለት ነው?
ሌላው  ደግሞ  ማርያምን መንበር፤ ጴጥሮስን ንፍቅ ቄስ፤ እስጢፋኖስን ገባሬ ዲያቆን አድርጎ በመቀደስ አቁርቧቸዋል የሚለው  ትረካ እርገቷን ተከትሎ የመጣ አባባል ነው። የማርያም ነፍስ እንዴት መንበር መሆን እንደሚችል? ምን የሚባለው ቅዳሴ እንደተቀደሰ? ለማወቅ የምናቀርባቸው ጥያቄዎችን ለጊዜው እንተዋቸውና፤  ሰራዔ ካህኑ ክርስቶስ የማንን ሥጋ  እንደቆረበ? እንዲነግሩን ግን እንጠይቃቸዋለን። ለየትኛው ድኅነት/መዳን/ እሱ ይቆርባል?  ክርስቶስ ቀደሰ እንጂ አልቆረበም  አንድ ነገር ነው።  ቆርቧል የሚባል ከሆነም ምክንያትና ውጤቱን የሚተነትን ትምህርት አያይዞ ማቅረብ የግድ ይላል። እሱማ የሕይወት ምግብ ሰጪ እንጂ ተቀባይ አይደለም የሚባል ከሆነም  ሰራዔ ካህናት በዚህ ምድር መቅደስ ውስጥ ከመቀደስ ባሻገር መቁረብ አይጠበቅባቸውም በማለት አብነታዊ የክህነት አስተምህሮን አያይዞ ማቅረብ  የተገባ ይሆናል።
እንግዲህ ማርያምን መንበር አደረጋት፤ ክርስቶስ ሰራዔ ካህን ሆኖ  ያልታወቀ ቅዳሴ ቀደሰ ማለት  ስለማርያም  ትንሣዔና እርገት ማጠናከሪያ በማቅረብ ትዕይንቱን  ተአማኒ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር አንድም እውነትነት የለውም። / እንደተለመደው አባባል ቅዳሴ እግዚእ ነው የተቀደሰው የሚል  ካለም ክርስቶስ ራሱን በሁለተኛ መደብ አስቀምጦ « ነአኩተከ አምላክ ቅዱስ፤ ፈጻሜ ነፍስነ፤ ወሀቤ ሕይወትነ ዘኢይማስን»  ሲል አይገኝም።  ራሱ ሕይወት ሰጪ ሆኖ ሳለ ሕይወት ይሰጠው ዘንድ አይለምንምና ነው። እንደዚህ ዓይነቱ አደገኛ ክህደት፤ ሰዎች ለማርያም ባላቸው ፍቅር ውስጥ ተደብቆ ለዘመናት ቆይቷል።
በጉ መስዋእቱን ለህይወታችን ሰጥቷል። ከዚያ ውጪ እሱ  በመንግሥቱ የፍርድ ሰዓት ዳግመኛ ሊመጣ ካልሆነ በስተቀር ከማእዱ አይካፈልም።«ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም፦ ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም። ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት» ሉቃ 22፤14-17
 በጉ መስዋዕቱን ሕይወት ይሆናቸው ዘንድ ለሰዎች ከሰጠ በኋላ፤ በፍርድ ቀን  የደሙን ምልክት ለተቀበሉት ሁሉ ዋጋቸውን ይሰጣቸዋል እንጂ እሱ የመስዋእቱ ተካፋይ ስላልሆነ፤ ክርስቶስ በቀዳሽነት  ቆርቦ፤ ማቁረብ የሚባል ታሪክ ከወንጌል ቃል ሊመጣ አይችልም። ይህም በማርያም ሞትና ትንሣዔ ላይ የተጨመረ ሌላ አሳዛኝ ትረካ ነው። በግ ለተራቡ ምግብ እንጂ እራሱን ተመጋቢ ሊሆን አይደለምና።
ወደዋናው ሃሳባችን ስንመለስ ለመሆኑ በማርያም ላይ ስንት ቀብር፤ ስንት ትንሣዔና ስንት እርገት ተደረገ? ብለን ብንጠይቅ እንደሚነገረው  ከሆነ ፤
1/ዮሐንስ ያየውና አፈር ያልነካው እርገት በገነት ዛፍ ስር
2/ አፈር የነካው የሐዋርያቱ ቀብር በነሐሴ 14 ቀን /ከስምንት ወር በኋላ/
3/ ቶማስ ያየው የትንሳዔ እርገት፤ ከቀብር በኋላ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16
4/ ከአንድ ዓመት በኋላ ሐዋርያት ያዩት የነሐሴ 16 ትንሣዔና እርገት ናቸው።
እንግዲህ በማርያም ሞትና እርገት መካከል አራት ትእይንት መከሰቱን ዛሬም ድረስ ከሚሰጡት የቃል አስተምህሮዎችና የተዘጋጁ ጽሁፎች ውስጥ በግልጽ እናገኛለን። ማርያምን መውደድ አንድ ነገር ነው። ማርያምን ግን እየቀበሩና እያነሱ ለማረጋገጥ መሞከር ደግሞ ሌላ አሳዛኝ ክስተት ይሆናል። እንዲያውም  ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት መሆን ከቻልኩ ሰባት ጊዜም ቢሆን እሞታለሁ ብላ ለልጇ ተናግራለች የሚሉትም  ተረት ተያይዞ ይነገራል።  የእሷ መሞት የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት መሆን ከቻለ የክርስቶስ ከእሷ መወለድ አስፈላጊ አይደለም የሚል ሃሳብን የሚያንጸባርቀው ይህ አባባል ከአሳሳች ትረካዎች ውስጥ የሚደመር ከመሆን አያልፍም።
እኛ  ማርያምን ብንወዳትና ብጽእት ብንላት «እናትህንና አባትህን አክብር»  ያለውን  የአምላክ ቃል መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለእርሷ  የተነገረ ቃል ስላለም ጭምር ነው። ነገር ግን የዘላለማዊ አምላክ የክርስቶስ ፤ እናቱ ስለሆነች  በማዳላት ወይም አምላካዊ ባህርይውን በሰውኛ ጠባይ በመለወጥ ከፍርድ ሚዛኑ በማጉደል  የእሷን ሞትና ትንሣዔ የተለየ ያደርጋል ብሎ ማሰብ የዋሕነት ይሆናል። የእሷ ሞትም የመድኃኒትነትን ውክልና ለሰው ልጆች የያዘ እንደሆነ ማሰብ ክህደት ነው። ብቸኛው መድኃኒት አንዱ በግ ኢየሱስ ብቻ ነው። ማርያምም ይህንን ስለምታውቅ « ነፍሴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ተስፋ ታደርጋለች» ብላ ነግራናለች።የትንሣዔ በኩር የሆነው ሁላችንም በሞቱ እንድንመስለው እንጂ የተለየ አድሎአዊ ጥቅምን/ faver/ ለተለዩ ሰዎች በመስጠት አይደለም።ወንጌል የሚናገረው ይህንን ነውና።
ሮሜ 6፥5
«ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን»
 ስለዚህ ደጋግሞ መሞት፤ መነሳትና ደጋግሞ ማረግ አለ ከተባለ ያ ነገር ከክርስቶስ ትንሣዔ ጋር ያልተባበረ ስለሆነ አንቀበለውም። እንዲያውን ይህ ኑፋቄና ወንጌልን መካድ ነው።  ሐዋርያው ጳውሎስም የተናገረው ስለክርስቶስ ወንጌል በሞቱም ክርስቶስን እንዲመስል ነበር።
ፊልጵ 3፥10-11  «እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ»
ማርያምን እንወዳለን እያሉ በጥር ሞተች፤ ገነት ዛፍ ስር ስምንት ወር በሬሳ ቆየች፤ በስንት ሱባዔ ስጋዋ መጥቶ ነሐሴ ተቀበረች፤ እስከነ ምድራዊ ልብሷ አረገች፤ በዳመናው ጎዳና  ላይ ከቶማስ ጋር ጨርቅ ተለዋወጠች፤ እድል ላመለጣቸው ሐዋርያት ዳግመኛ በስንት ሱባዔ በሌላ ትንሳዔና እርገት ተረጋገጠች፤ መንበር ሆና ተነጠፈች ወዘተ  በማለት እየገደሉና እያነሱ በማርያም ላይ መጫወት ተገቢ ነው ብለን አናምንም። የክርስቶስን ሞትና ትንሣዔንም ማፋለስና መካድ ይሆናል።

የማርያም ሞትና ትንሣዔ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ካዘጋጀው የትንሣዔው በኩር አንድያ ልጁ የተለየ አያደርገውም። ከመግቢያችን ላይ ጀምሮ ለመግለጽ እንደሞከርነው የኤፌሶኑና የኢየሩሳሌሙ ታሪክ እንዳለ ሆኖ አብያተክርስቲያናት ሁሉ የተለያየ የሞትና የትንሣዔ አስተምህሮ ከመያዛቸው አንጻር  ኤጲፋንዮስ እንዳለው ትክክለኛው ታሪክ ቀን አይታወቅም። [2 ] አሁን የሚደረገው ግን ልምድና ትውፊት ነው። ይሁን እንጂ የሆነውን ቀን ወስኖ መታሰቢያ ማድረጉ ባይከፋም እየገደሉና እያነሱ ከመጽሐፉ ቃል በተጻጻሪ የትንሣዔንና የእርገትን ነገር ዋጋ ማሳጣት ተገቢ አይደለም።
ለተጨማሪ መረጃዎች፣
_________________________________________________________________
[ 1 ]ይህንን ይመልከቱ
[ 2 ]ይህንን ይመልከቱ