Saturday, August 18, 2012

ከኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የፓትርያርክ ምርጫ ምን እንማራለን?


የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የምርጫ ሂደት በ1957 ዓ/ም ተሻሽሎ የወጣ ነው። ምርጫው የቤተክርስቲያኒቱ አባል የሆነው በሙሉ ያካተተ እንዲሆን የተሞከረበት ህገ ደንብ አለው። በእርግጥም ምርጫው በሲኖዶስ ፈቃድና እጣ የሚያበቃ  ሳይሆን ከየትኛውም ዘርፍ ያለውን አባሏን የሚያሳትፍ በመሆኑ እውነተኛ አባት ለመምረጥ አስቸጋሪ አልሆነባቸውም። ቢያንስ ቢያንስ አሁን ባለው የፖፕ ሺኖዳ ምትክ ምርጫ ላይ እንኳን ወደ 14 ሰዎች በግልና በጥቆማ ከቀረቡት የፓትርያርክ እጩዎች ውስጥ የማይፈለጉ ሰዎች ወደዚያ መንፈሳዊ ወንበር ሾልከው እንዳይወጡ ማስቀረት የሚችልበት የምርጫ ወንፊት ስላለው እስኪጣራ ድረስ ሂደቱን ሊያዘገይ አስችሎታል። መዘግየቱ ለመንበረ ሥልጣኑ ክፍት ሆኖ መቆየት አስቸጋሪ መሆኑ ባይካድም ክፍት እንዳይቆይ ተብሎ በሆይ ሆይ ቢሾም ደግሞ  የማይፈለጉ ሰዎች በቡድንና በድጋፍ ተጠግተው ሥልጣኑ ላይ ከወጡ በኋላ ሳያስለቅሱ ማውረድ እንዳይቸግር ከወዲሁ በወንፊት የማበጠሩ ጉዳይ መኖሩ ኮፕቶችን ቢጠቅማቸው እንጂ አይጎዳቸውም። ከዚያው ያገኘናቸው መረጃዎች የሚጠቁሙት ያንን ነው። እኛም የበሰለ ነገር ቢበሉት ሆድ አይጎረብጥምና ነገሩን አብስላችሁ ማቅረባችሁ ይበል የሚያሰኝ ነው እንላለን።
ወደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስንመጣ የራሷን ፓትርያርክ ስትሾም እድሜው እንደጥንታዊነቷ አይደለም። የዚያን እንዴትነት እስከነ ሰፊ ታሪኩ ትተን ፓትርያርክ መሾም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ሁኔታ በግብጽ አጽዳቂነት የተከናወኑትን ስንመለከት የድክመቶቻችን ውጤት እንጂ ስኬታችን ትልቅነት አድርጎ መመልከቱ ሚዛን አይደፋም። ራሳችን መሾም ጀምረናል ካልንበት ጊዜም ጀምሮ ቢሆን የመንግሥት እጅ በጓሮ በር ሳይገባበት የተከናወኑ ምርጫዎችን ለማግኘት ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ስለሚሆን አልፈነዋል። እንደዚያም ሆኖ በመገዳደል፤ በመከፋፈልና በመሰነጣጠቅ፤ በመወጋገዝ  የተሞላ መሆኑ የአሳዛኝ ገጽታው አንዱ ፈርጅ ሆኖ ዘልቋል። ዛሬም ከዚያ አዙሪት ስለመውጣታችን እርግጠኞች አይደለንም። ቤተክርስቲያኒቱን በማስቀደም ሳይሆን የሥልጣን ጥምን ለመወጣትና የመንፈሳዊ ማንነት ጉድለቱ ግዝፎ በመታየቱ ችግሮቻችን በአጭሩ የፕትርክና ታሪካችን ውስጥ የሺህ ዓመት ጥላሸትን አኑሯል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የፓትርያርክ አሿሿም ልምዷ ከጥንታዊነቷ ጋር የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ቢሆንም  እንኳን ፓትርያርኳን ለመሾም የግድ የ1000 ዓመት ልምምድ ያስፈልጋታል ወይ? ብለን እንጠይቃለን።
« ሞኝ ሰው ከራሱ ስህተት ይማራል፤ ብልህ ሰው ግን ከሞኝ ሰው ስህተት ይማራል» እንዲሉ  የሌሎችን ልምድ ቀምረን እኛ የተሻለ ሥራ ለመስራት እንደብልሁ ሰው መሆን ባንችል እንኳን እንደሞኝ ሰው ከስህተቶቻችን መማር ለምን እንደከበደን ሳስብ ግራ ይገባኛል።
በ21ኛው ክ/ዘመን ዲሞክራሲን ለመማር እንደአሜሪካ 200 ዓመት እስኪሞላ የምንጠብቅ ከሆነ ከሉላዊነት አስተሳሰብ ውጪ ነን ማለት ነው። አሜሪካ ውስጥ የተመረተ ሸቀጥ ኢትዮጵያ እስኪደርስ 200 ዓመት ይፈጅበታል ብሎ እንደማሰብ ይሆናል። እንደዚሁ ሁሉ ከኮፒቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የፓትርያርክ አሿሿም ሕገ ደንብ ለመማር የግድ የግብጽ ጳጳሳት እንደገዙን 1600 ዓመት ልንጠብቅ አይገባም።  የፓትርያርክነት የምርጫ አዙሪት  በመገምገም መፍትሄው በቅርቡ ሊሆን ይችል ይሆን? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ሩቅ ይሆንብኛል።
አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ሲሆኑ በምርጫው ላይ የነበሩ ጳጳሳት ዛሬም አሉ። አቡነ መርቆሬዎስ ሲባረሩም፤ የመባረራቸውን ተገቢነት የደገፉ  አሁንም አሉ። አቡነ ጳውሎስ በተባረሩት ምትክ ሲሾሙ የመረጡ አሉ። አቡነ ጳውሎስን የመረጡ ተመልሰው የጠሏቸው፤ አሁን ሲሞቱ ደግሞ ተመልሰው ለመመረጥ ወይም ለመምረጥ ያሰፈሰፉ አሉ። እንግዲህ አቋሟቸው ለመገለባበጥ እንጂ ሊኖር በሚገባ ሃይማኖታዊ ጽናት ለመቆም በማይችሉ ሰዎች በሞላበት ሲኖዶስ ተስፋ የሚጣልበትና እግዚአብሔር የወደደውን ምርጫ ለማካሄድ ገና መቶ ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል። ለዚያውም ሰማይና ምድር ሳያልፉ ከጠበቀን ነው። ዛሬ እንኳን ለምርጫው በውስጠ ምስጢር በመንግሥት በኩል የታለሙትና አውሬው ደግሞ በከተማይቱ እያስተጋባ የሚገኘውን ድምጽ ስናዳምጥ ነገም ልቅሶአችን ቀጣይ መሆኑን አመላካች ነው። በዚህ ዓይነት መልኩ ከሄድን ደግሜ እላለሁ፤ ነገንም ከእንባ አንላቀቅም።
የኛ ጉዳይ እንደዚህ ነው። የሚሆነውንና የሚመጣውን ከማያልቅበት እድሜ አይንፈገንና ሁሉን እናይ ይሆናል። እስከዚያው እስኪ ከኮፕቶች የፓትርያርክ ምርጫ ደንብ ጥቂት እንመልከት።
1/ ፓትርያርኩ ባረፉ በ7ኛው ቀን  የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና የጠቅላይ ምክር ቤት አባላት ባሉበት በጵጵስና ቀዳሚ የሆነው ሊቀጳጳስ ዐቃቤ መንበር ሆኖ ይሰየማል። የዐቃቤ መንበሩ ምርጫ እንዳበቃ  የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ይዋቀራል። አስመራጭ ኮሚቴው 18 አባላት ያሉት ሆኖ 9 ጳጳሳት ከሲኖዶሱ፤ 9 አባላት ደግሞ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ይመረጣሉ።
 ጠቅላይ ምክር ቤት ማለት በፓትርያርኩ ሊቀመንበርነት የሚመራ በመንበረ ፓትርያርኩ ስር የተዋቀረ ሲሆን  የሲኖዶስ አባላት፤ ቤተክርስቲያኒቱን በገንዘብ፤ በጉልበትና በእውቀት የሚደግፉ ምእመናን፤ አገልጋይ ካህናትና ዲያቆናት፤ የሰንበት ት/ቤት አባላት፤ ያሉበት የ24 አባላት ምክር ቤት ነው።
 
የዚህ ምክር ቤት አባላት በሌሉበት የዐቃቤ መንበሩና የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ አይዋቀርም።
2/ የፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር ከተፈጸመበት ከ40 ኛው ቀን ጀምሮ የእጩዎች ምዝገባ ይካሄዳል። እጩ መሆን የሚችል ሰው፣
ሀ/ ለ15 ዓመት ያህል ከገዳም ሳይወጣ የኖረና ይህንን ማስረጃ ማቅረብ የሚችል
ለ/ የግል እጩ ተወዳዳሪ መሆን የፈለገ የ6 ጳጳሳት ድጋፍ ማቅረብ ይጠበቅበታል።
ሐ/ ገዳማትና አድባራት ለእጩነት ወክለው የሚልኳቸው መነኮሳት
መ/ ሲኖዶስ ወክሎ የሚያቀርባቸው ሊቃነ ጳጳሳት
ሠ/ በምእመናን ጥቆማ የሚቀርቡ እጩዎች ናቸው።
3/ እጩዎችን የመቀበል ጊዜ ከ40ኛው ቀን እስከ 60ኛው ቀን ይቆይና በ60ኛው ቀን ማታ እጩ የመቀበሉ ሁኔታ በግልጽ ይዘጋል።
4/ የእጩዎቹ ማንነት ለሕዝብ ይገለጻል።
5/ በቀረቡት እጩዎች ላይ ከ60ኛው ቀን አንስቶ እስከ 75ኛው ቀን ድረስ ለ15 ቀናት ያህል የህዝብ ግምገማ ይቀርባል። የቀረቡት እጩዎች ስም ዝርዝር ለህዝብ ሚዲያ ማለትም በጋዜጣ፤ በቴሊቪዥን ይታወጃል። እጩዎችን የሚገመግም ኮሚቴ በአስመራጭ ኮሚቴው ስር ይዋቀራል። እጩዎቹ የፈጸሙት ጥፋት፤ ለእጩነት ብቁ የማያደርጋቸው ማንነት፤ ሰነድና ማስረጃ ለኮሚቴው በግል ወይም በህብረት ከማንኛውም ወገን ይቀርባል።  ኮሚቴው የቀረቡለትን ማስረጃዎች እጩው ተወዳዳሪ ባለበት ይገመግማል ። በቀረበለት ማስረጃ መሰረት ብቁ ያልሆኑትንና ብቁዎቹን ለይቶ ለአስመራጭ ኮሚቴው ያቀርባል። ያለአግባብ ውድቅ ተደርጌአለሁ የሚል እጩ፤ አቤቱታውን ለአስመራጭ ኮሚቴው ሊያቀርብ ይችላል።
6/ በ90ኛው ቀን በመጨረሻው የተመረጡት የእጩዎቹ ማንነት ተለይቶ ይታወቃል።
7/ በ150 ቀን በቀረቡት እጩዎች ላይ ድምጽ መስጠት ይካሄዳል። ድምጽ መስጠት የሚችሉት፤
ሀ/ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ለ/ የኮፕት ቤተክርስቲያን አባል የሆኑና እድሜአቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆነ
ሐ/ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገረ ስብከቶች ከተወከሉ ምእመናን፤ ካህናት፤ ዲያቆናት፤ የገዳማት መነኮሳት፤ መነኮሳይያት
መ/ ከታዋቂ ሰዎች፤ ከጋዜጠኞች፤ ምሁራንና  ያለውክልና ደግሞ በቀጥታ በመራጭነት መሳተፍ የሚችሉት የቤተክርስቲያኒቱ አባላት የሆኑ የመንግስት የፓርላማ አባላትና ሚኒስትሮች  ናቸው።በዚሁ መሰረት  በአቡነ ሺኖዳ ምትክ ምርጫ ላይ ለ14 እጩዎች 2500 መራጮች ተመዝግበዋል።
8/ ከድምጽ አሰጣጥና ቆጠራ በኋላ ከፍተኛ ድምጽ ያገኙት 3 እጩ ፓትርያርኮች ብቻ ቀርተው ምርጫው ባበቃ በመጀመሪያው እሁድ በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል በሚደረገው የቅዳሴ ሥነ ስርዓት ላይ እድሜው ከ7 ዓመት ያልበለጠ ህጻን ልጅ ዓይኑን በጨርቅ ታስሮ በአነስተኛው ሳጥን ውስጥ ተጠቅልሎ ከተቀመጠው ሦስቱ  እጩ ስሞች መካከል አንዱን እንዲያነሳ ተደርጎ  የወጣው ስም በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ባለው ሊቃነ ጳጳሳትና ምእመናን ፊት ተገልጾ ከተነበበ በኋላ 118ኛው የግብጽ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ማን እንደሆነ ይታወጃል። ሲመተ ፕትርክናው ይከናወናል።
ማጠቃለያ፤
 ኮፕቶች በምእመናን ቁጥር ትንሽ፤ በአብያተ ክርስቲያናትና፤ በገዳማት ቁጥር አነስተኛ፤ ያለባቸው የአክራሪና የመንግሥት ጫና ከባድ ሆኖ የመንፈሳዊ ምርጫ ሂደታቸው ግን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑ አይገርምም?
እኛ እንደዚህ እንዳናደርግ ምን የሚከለክለን ነገር አለ?  እንደዚህ እያበጠርን ብናደርግ ኖሮ አቡነ እገሌ እንደዚህ አደረጉ፤ እንደዚህ ሆንን እያልን በአእምሮ ድኩምነታችን የተነሳ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ድንጋይ የጫነብን አስመስለን ከማማረር እንድን እንደነበር እገምታለሁ።
ዳሩ ግን ይህ እንዲህ የማይፈልጉ ክፍሎች አሉ። ቀዳሚዎቹ ጳጳሳቶቹ እራሳቸው ናቸው። ከገዳም ለእጩነት የሚወከል ይኑር ቢባል እሺ የሚሉ ይመስላችኋል?  በአንገታቸው ገመድ ይገባል እንጂ  እነሱ እያሉ ይህ እንዲሆን አይፈልጉም። መንፈስ ቅዱስ ከገዳማት መነኮሳት ሳይሆን ከእኛ ከጳጳሳቱ ነው የሚመነጨው ብለው ስለሚያስቡ ተራ መነኮሳት ለውድድር እንዲቀርቡ አይፈልጉም።  የሚገርመው ግን ስልጡን አይደሉም የተባሉት አቡነ ተ/ሃይማኖት ከምንኩስና ተነስተው ፓትርያርክ የሆኑበት ዘመን ያውም በደርግ ዘመን መከራ ውስጥ ቤተክርስቲያን ጸንታ ለመኖር ከአሁኑ የተሻለች ነበረች። የቤተክርስቲያኒቱ ችግር የማያልቀው ቤተክርስቲያኒቱን መንፈስ ቅዱስ የመረጠው እንዲመራት ሳይሆን ሲኖዶስ የሚባለው በሥልጣን ጥመኞች ስለተሞላ ብቻ ነው።
ዛሬስ እነማን፤ ማንን ለፓትርያርክነት ከኋላ እየነዱ ይሆን? ከዚያም መንፈስ ቅዱስ መረጠልን ብለው በመንፈስ ቅዱስ አሰራር ላይ ሲዘባበቱ እናያቸው ይሆናል።  ያኔም መንፈስ ቅዱስ የሌለበት ምርጫ መሆኑ የሚታወቀው መራራ ነገር መታየት ሲጀምር ይሆናል።
ከኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የፓትርያርክ ምርጫ  ምን እንማራለን?