Sunday, September 30, 2012

ክርስቲያን በፖለቲካ ውስጥ በንቃት መሳተፍ ይኖርበታልን?

                                             ከተስፋዬ ሮበሌ
                                                              ወርኀ ጥር 2004 .
                                                                                                         እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቈጣጠር
                                                                                                         ግራንድ ራፒድስ ፣ ሚሽገን

በአንድ መስቀለኛ መንገድ ላይ በየቀኑ አሠቃቂ አደጋ ይከሠታል፤ ከአደጋው የተነሣም በርካታ ሰዎች ይሞታሉ፤ ከፍተኛ ንብረትም ይወድማል፡፡ ሁኔታው ያሳሰባት፣ በዚህ አካባቢ የምትገኝ አንዲት ቤተ ክርስቲያን፣ የአደጋው ሰለባ የሆኑትን ሰዎች የሚረዱ ሐኪሞችንና ነርሶችን በማሠማራት የአካባቢውን ማኅበረሰብ በንቃት ማገልገሉን ሥራዬ ብላ ተያያዘችው፡፡ የሕዝብና የመኪና ቊጥር ዕለት በዕለት እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት ግን፣ ችግሩ በዛው መጠን ተባብሶ ቀጠለ፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን እርዳታዋን በመጠንና በዐይነት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ መለስተኛ ሆስፒታል አደጋው በሚከሠትበት አካባቢ አቋቋመች፡፡ ይህ ሠናይ ምግባር የሰለባዎቹን ጤንነትና ሕይወት ከመታደግ አንጻር ብዙ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ ችግሩን ግን ከምንጩ ማድረቅ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም የችግሩ ምንጭ የተሳሳተ የመንገድ ዲዛይን ነውና፡፡ በመስኩ የሠለጠኑ መሐንዲሶች መንገዱ በአዲስ መልክ ዲዛይን ቢደረግ ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል የትራፊክ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቱን በቃልም ሆነ በጽሑፍ ቢያሳስቡም፣ ባልታወቀ ምክንያት ጽሕፈት ቤቱ ጆሮ ዳባ ልበስ አለ፡፡ በየዘመናቱ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ሰጠኝ የምትለውን ዐደራ ከዳር ለማድረስ፣ በሚያስፈልገው ሁሉ በመውተርተር ላይ ትገኛለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ነዳያንን በማብላት፣ የታመሙትን በማስታመም፣ ለመበለቶች ዳኛ በመሆን ጥልቅ ስም አላት፡፡ በርግጥም ቤተ ክርስቲያን የምስካየ ኅዙናን መንበር ናት፡፡ ወደ ፊትም ይህንኑ ግብረ ሠናይ ምግባሯን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የምትችለው የተሳሳተ ፖሊሲ ያስከተለውን ፍሬ በመልቀም ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት ትክክለኛ ፖሊሲ እንዲነድፍ ስታስተምር፣ መንግሥት ሲሳሳትም ስሕተቱን ስሕተት ነው ማለት ድፍረትና ክህሎት ሲኖራት ብቻ ነው፡፡
ፖለቲካ፣ የሕዝብ አስተዳደር መዘውር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የመዘውሩ ነገር ምን ተዳዬ የምትል ከሆነ ግን፣ በመዘውሩ እክል ምክንያት በሚከሠቱ ችግሮች ላይ ብቻ መጠመዷ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ውስጥ ሠርጾ በመዝለቁ ምክንያት፣ ወደ ፖለቲካው ዓለም የሚገቡ ወይም የፖለቲካ ሳይንስ የሚያጠኑ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ ከመንፈሳዊነት እንደ ጐደሉ ምናልባትም ክርስቶስን ከመከተል እንዳፈገፈጉ ይታሰባል፡፡ ክርስቲያን የዓለም ብርሃንነው፣ የዓለም ጨውነው የሚለው የቃለ እግዚአብሔር ትምህርት፣ በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ጨለማና አልጫ ነው ያለው ማነው? እንዲያውም ክርስቲያኖች በንቃት ሊሳተፉበት የሚገባ፣ ጨውነታቸውንና ብርሃንነታቸውን ሊገልጡበት የሚገባው የሕይወት ክፍል ፖለቲካ ነው፡፡ እንደ ንጉሥ ዳዊት፣ እንደ ንጉሥ ሰሎሞን ያሉ የእምነት አበው ፖለቲከኞች ነበሩ፡፡ እንደ ነቢዩ ናታን፣ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ነቢዩ ዳንኤል፣ ነቢዩ አሞጽ ወዘተ ያሉ ነቢያት ደግሞ መንግሥትን በማማከር አገልግለው እንዳለፉ ገድላቸው የናገራል፡፡ መንግሥት ሲስት ይገሥጹና ከስሕተቱ እንዲመለስ መንገድ የመላክቱ እንደ ነበር ቅዱስ ቃሉ ያስተምረናል፡፡ እንዲያውም ባልንጀራህን/ጐረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለው የክርስቶስ ቃል ከየትኛውም የትምህርት ዘርፍ ይልቅ ፖለቲካን የሚያመላክት ነው (ማቴዎስ 22÷39)፡፡ ለተጠቃው ከመጮኽ፣ የታረዘውን ከማልበስ፣ ፍትሕ ያጣውን ለፍትሑ ከመሟገት በላይ ምን ጐረቤትን መውደድ አለ? እግዚአብሔር አምላክ ለንጉሥ ሰሎሞን የሰጠው ስጦታ የፖለቲካ ስጦታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፖለቲካ የጸጋ ስጦታ መሆኑን የሚያጸና ነው፡፡
ወገኖቼ ክርስትና የማይዳስሰው የሕይወት ክፍል የለም፡፡ ክርስቲያኖች በፖለቲካው ውስጥ በመግባት ብርሃንና ጨው መሆን ካልቻሉ፣ ክርስቲያን ያልሆኑና እኵይ ሥነ ምግባር ያለቸው ሰዎች የፖለቲካውን መድረክ መቈጣጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ እየሆነም ያለ ይመስላል፡፡ ወገኖቼ፣ ኀጥኣን ከፍ ከፍ ሲሉ ሕዝብ ይጨነቃልየሚለው የጠቢቡ ሰሎሞን አነጋገር ፖለቲካን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ወዲህም ወዲያም ብታገላብጡት ሐቁ ይኸው ነው፡፡ ክርስትናና ፖለቲካ ዐይንና ናጫ ናቸው ወዘተረፈ የሚለው ወልጋዳ አስተሳሰብ የብዙዎችን ጐዳና አሰናክሏል፡፡ ከዚህም የተነሣ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ ስለ ፖለቲካ ያለን ዕውቀት በየጋዜጣው ላይ ከሚጻፉ መጣጥፎች አንዲሁም በየዜና አውታሮች ከሚተላለፉ ፕሮግራሞች የዘለለ አይደለም፡፡ ይህ ዐይነቱ ዕውቀት ደግሞ፣ ለፕሮፖጋንዳ ውዥንብር በቀላሉ ይዳረጋል፡፡ ቃላትን ቀምሮና እውነትን አስታኮ የመጣ ብልጣብልጥ ፖለቲካኛ ሁሉ ወዳሻው ቦታ ይዞት ይሄዳል፡፡ ወደድንም ጠላንም የአገሬ ጕዳይ ግድ ይለኛልየምንል ሰዎች ሁሉ፣ ቢያንስ መሠረታውያን የሚባሉትን የፖለቲካ መርሖች በቅጡ ልናውቃቸው ግድ ነው፡፡ ለምሳሌ ፖለቲካ በአገር ግንባታ ውስጥ ያለው ቦታ እስከምን ድረስ ነው? ሰብአዊ መብት ማለት ምን ማለት ነው? ኢሕአዴግ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲብሎ የሚጠራው የፖለቲካ አካሄድ፣ ከምዕራባውያኑ ለዘብተኛ (ሊብራል) ዴሞክራሲ በምን ይለያል?
ይህ የፖለቲካ ፍልስፍና በአገሪቱ ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት የሚያስከትለው አሉታዊ መዘዝም ሆነ አዎንታዊ እንድምታ እንዴት ይተነተናል? ክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ወይስ የዳር ታዛቢ መሆናቸው ብቻ ጥሩ ዜጋ ያሰኛቸዋል? ሕዝባዊና ማኅበራዊ ተቋማት ማለትም የመገናኛ ብዙኃን፣ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶችና የምርጫ ቦርድ ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ፍጹም ነጻ መሆን አለባቸውየሚባለው ለምንድን ነው? ነጻናቸው የሚባል ከሆነስ ደግሞ ነጻነታቸው በምን መስፈርት ይለካል? ፖለቲካ ለምጣኔ ሀብት ሕግጋት ይገዛል ወይስ ምጣኔ ሀብት ለፖለቲካ ሎሌ ያድራል? ወይስ ሁለቱም ለየቅል ናቸው? አንድ አገር ፖለቲካ ሰብአዊ መብትን እንዳሻው እየጨፈለቀ የምጣኔ ሀብት በረከት ሊያመጣ ይችላል? የማይቻል ከሆነ የቻይና ጕዳይ እንዴት ይታያል? የመናገር መብት፣ የመጻፍ መብት፣ የመደራጀት መብት ወዘተ የሚባሉት ጕዳዮች፣ በሰብአውያን ሕይወትና ዕድገት ውስጥ ያለቸው ስፍራ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፖለቲካ የሚያስተምረው ትምህርት ምንድን ነው

 አንድን የፖለቲካ ድርጅት ለመቃወመም ሆነ ለመደገፍ የፖለቲካ ፕሮግራሙንና የሥነ ምግባር ሕጉን እንዴት መፈተሽ ይቻላል? ቢያንስ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እነዚህን ርእሰ ጕዳዮች በሚገባ ማወቅ አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን የፖለቲካ መሠረታውያንን ለአባሎችዋ በሚገባ ማስተማር ይኖርባታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህን የቤት ሥራዋን መሥራቷ በአገር ግንባታ ውስጥ ተሳትፎ ማድረጓ እንጂ፣ ሃይማኖት በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባቱ ወይም ሃይማኖትንና ፖለቲካን ማጣቀስአይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ልጆችዋን በሥርዐቱ የማታሠለጥን ከሆነ ሌሎች በተጣመመ መንገድ ያሠለጥኑላታል፡፡ ድሮስ ጨው ጨውነቱን ካጣ መረገጥ እንጂ ምን ዕድል ፈንታ አለው?

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዐቅም ባጡበት ጕዳይ ላይ ሒስ የሚሰነዝሩ፣ አቅጣጫን የሚያመለክቱ፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ከፖለቲካ ከጫወታ ውጪ ነኝ፤ አይመለከተኝም የሚል አስተሳሰብ እንዳያድርባቸው ቃለ እግዚአብሔርን በመጥቀስ ወደ ጫወታው እንዲገቡ የሚሞክሩ ጸሐፍያን ያስፈልጉናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሆይ ተነሽየሚል ነቢያዊ ጩኸት የሚያስሙ የቊርጥ ቀን ልጆች የሚያስፈልጉን ይመስለኛል፡፡ መቼም የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ሁሉ በአንድ መፈረጅ አግባብ ባይሆንም፣ አብዛኞቹ መሪዎቻችን ልፍስፍሶች መሆናቸውን እንኳን ምዕመናን እነርሱ ጭምር የሚስማሙበት ይመስለኛል፡፡ አልታየሁምአልታወቅምነውሬ ተረስቶአልየሚሉ ካሉ ሞኞች ናቸው፡፡ ከታሪክ ዐይን የሚያመልጥ የለም፡፡ ይህ ግን እውን መሆኑን የሚያሳዩ ጸሓፍያን እንጠብቃለንእውነትን በፍቅር የሚገልጹ፡፡ አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ መስሎ ለመኖር ብቻ ውሃና ዘይትን ካለዋሃድን፣ እሳትና ጭድን ከላፋቀርን፣ ዐይንና ናጫን ከላስማማን የሚል አቋም ያላቸው ይመስላል፡፡ እውነትን ከጥቃት የምንጠብቀው ሐሰትን በግልጥ በመቃወም ጭምር ነው፡፡ በልፍስፍስ አቋሙ በባልንጀሮቹ በስፋት የሚታወቅ አንድ ወንድማችንን ሌላው ወንድማችን፣ ክርስቶስ ሰምራብሎ ይጠረዋል፡፡ አንድ ቀን፣ ወዳጄን ዳቦ ሳትቈርስ ክርስቶስ ሰምራብለህ ስም ያወጣህለት ለምንድን ነው? ለመሆኑስ ክርስቶስ ሰምራ ማን ነች?” ስል ጠየቅሁት፡፡ አታቅም እንዴ፣ ክርስቶስ ሰምራ የምትባል ክርስቶስንና ሰይጣንን ለማስታረቅ ሙከራ ያደረገች ብጽዕት ናት፤ እኔም ይህን ወንድም ከክርስቶስ ሰምራ ለይቼ አላየውም፤ ለመኖር ሲል ብቻ ሁሉም ትክክል ነው የሚል እርስ በርሱ የተምታታና የተውገረገረ አቋም ያለው ፍጥረት ነውአለኝ በሐዘንና በቊጣ፡፡ በርግጥ ስያሜው ወዳጄን በትክክል እንደሚመጥነው እቀበላለሁ፤ ገላጩ ስያሜው ግን አስቆኛል፡፡ 
መቼም መንግሥት ከእርሱ በተቃራኒ ዘውግ የቆሙትን ሁሉ ጸረየሚል የመነሻ ምዕላድ እየቀጸለ፣ ጽንፍ የነካ በመሰለበት በዚህ የታሪክ ጊዜ፣ መለሳለስ ጥሩ ስልት መስሎ ሊታይ ይችል ይሆናል፡፡ ግን የክርስቶስ ወንጌል የጀግኖች መለዮ እንጂ፣ የአልጮች ሙያ አይደለምና ልፍስፍስ አቋማቸውን መቀየር የግድ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ነው አንድ ወንድማችን ይህን አስመልክቶ፣ አቋም የለሽ አቋማችንእንዲስተካከል በአንድ ጽሑፉ የሚማጠነን፡፡ እውነት ነው አቋም የለሽ አቋማችንን እክ እንትፍ እንበለው፡፡ የአቋም ሰው መሆን ያስከብር ከሆነ እንጂ አያዋርድም (ቢያንስ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት)፡፡

ወንድሞችና እኅቶች በዚህ ረገድ የምትጽፉትን ጽሑፍ ማንበብ ጸሎቴም ምኞቴም ነው፡፡ ቸር ይግጠመን!

ተስፋዬ ሮበሌ
ግራንድ ራፒድስ ሚሽገን
ወርኀ ጥር 2004 .
በኢትዮጵያውያን የዘመን አቈጣጠር