Wednesday, September 5, 2012

ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው 2ኛ ተሰ 3፤5


ስለትዕግስትና ታጋሽነት ብዙ ብዙ ሰምተናል። ትዕግስት መራር ናት ፍሬዋ ጣፋጭ ነው፤ በለሷን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል ፤ የመሳሰሉት ጥቅሶች የትዕግስትን አስፈላጊነት የሕይወታችን አንድ ክፍል የማድረግን ነገር የሚያሳስቡን ኃይለ ቃሎች ሆነው አገልግለውናል ወይም ለተገልጋዮች ተናግረናቸዋል። ትዕግስትን ብዙ ምሁራን፤ሊቃውንትና መሪዎችም በገባቸው መጠን በማሳያነት ጠቅሰው ከትበውልናል።
ሚልን የተባለው ምሁር ትዕግስትን በወንዝ ጉዞ ስዕላዊ መንገድ ሲነግረን  «ወንዞች እንዴት እንደሚፈሱ ስለሚያውቁ ቁልቁል ይፈሳሉ፤ ብዙውን ጠመዝማዛ መንገድ በረጅም ትዕግስት አቋርጠው ከመጨረሻቸው ይደርሳሉ» ይለናል። ሚልን ስለትእግስት በምሳሌ የነገረን ነገር በእርግጥም ትልቅ እውነት ነው። ዓባይን የሚያክል ወንዝ በእርጋታ ከጣና ተነስቶ በረሃውንና ቁልቁለቱን አቋርጦ፤ ሀገራትን አካልሎ ከሜዲተራንያን ገብቶ እረፍት ለማድረግ ብዙ ትዕግስት ማድረጉ በእርግጥም አስገራሚ ነገር  ነው።
«The book thief» የተባለውን መጽሐፍ የደረሰው ማርከስ ዙሳክ ደግሞ ስለትዕግስት እንዲህ ብሏል። «ትዕግስት የሌለው ሰው የራሱን ምስል በጥቁር ቀለም የሳለ የእአእምሮ ንክና  ዓለምን ማሸነፍ ያልቻለ ሰው ነው» ሲል ገልጾታል።
«ፓውሎ ኮልሆ» ደግሞ ስለትዕግስት አስፈላጊነት እንዲህ ሲል ይመከረናል። «ትዕግስት ለምን እንደሚያስፈልግ ታውቃላችሁ?» በማለት ይጠይቅና ለጥያቄው ምላሽ ራሱ እንዲህ ሲል ይሰጣል።  «ምክንያቱም የትዕግስት ማጣት ለነገሮች ተገቢውን ትኩረት እንዳናደርግ ይከለክለናል» ሲል አስቀምጦታል።
ጃሮክ ክኒትዝ ደግሞ  የትዕግስትን አስፈላጊነት ሲገልጸው« ወንድሜ! ውሃው ሳይፈላ፤ እንፋሎት አይወጣምና ታገስ» ሲል እጥር ምጥን ባለ ቃል ገልጾታል።
እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ የዘመኑ ምሁራንና ፈላስፎች ስለትዕግስት አስፈላጊነት በየመድረኩ ሳይናገሩ የቀሩበት ጊዜ የለም።  ጥቅሶቻቸውን ከማነብነብ ውጪ ምን ያህላችን የትዕግስትን አስፈላጊነት ገላጭ ምክሮቻቸውን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ እንዳደረግን ቤቱ ይቁጠረው። ይሁን እንጂ ትዕግስት አስፈላጊ ስለመሆኗ ሁላችንም በአንድ ቃል እንስማማለን። አባቶቻችንም የትዕግስትን አስፈላጊነት ሲገልጹ «ለዚሁ ነው በሬዬን ያረድኩት» ያለውን ሰው ምሳሌ የሚያቀርቡት የመታገስ አቅምን ከማጣት ጋር አስተሳስረው ሲነግሩን ኖረዋል። በትዕግስት ማጣት ብዙ ችግር ሊመጣ እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው። ግን የትዕግስት መጠኑ እስከየት ድረስ ነው? ይሄም ብዙ ያነጋግራል። ስለዚህም ብዙ የተባለ እንደሆነ ይታወቃል።  የርእሳችንን መነሻ ያሰፋዋልና ትተነዋል።
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ በምሁራን የትዕግስትን ገላጭ ቃላትና የትዕግስትን የገደብ ጣሪያ እስከየትነት ለመተንተን ሳይሆን በሕይወት ዘመናችን ውስጥ ዓለማውያን ሊቃውንቶች ምክርና ተግሳጽን በመስጠት ትዕግስትን ገንዘብ እንድናደርግ የለገሱንን በማንሳት፤ ዓለም የዚህን ያህል ተራምዳ ስለትዕግስት አስፈላጊነት ከተናገረች መንፈሳዊ ሕይወትስ እንዴትና እስከየት እንደተናገረችን ለመዳሰስ በመሻት መንደርደሪያ ይሆን ዘንድ አስቀምጠነዋል።
ወደ ርእሳችን ስንመለስ እንዲህ ይላል።
«ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው» 2ኛ ተሰ 3፤5
ወደ ክርስቶስም ትዕግስት እግዚአብሔር እንዲያቀናው የሚፈለገው ትዕግስት ምን ዓይነት ይሆን?
በመንፈሳዊው ዓለም ከክርስቶስ የሆነ ትዕግስት የሌለው ሰው ክርስቲያን ሊሆን አይችልም።  በመባልና በመሆን መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ልናስተውል ይገባል። ብዙ ሰዎች ክርስቲያኖች ሊባሉ ይችላሉ። ክርስቲያኖች የተባሉ ሁሉ ግን ክርስቲያን ሆነዋል ማለት አይደለም። የሚወዷቸውን የሚወዱ ክርስቲያኖች ሞልተዋል፤ ነገር ግን የሚጠሏቸውን የሚወዱ ክርስቲያኖች ማግኘት አዳጋች ነው።  እነዚህ ክርስቲያኖች ይባላሉ ግን ክርስቲያን መሆን ያልቻሉ ቀራጮች ናቸው። ወንጌል እንዲህ ካለ እነዚህ ሰዎች ቀራጭ ክርስቲያኖች የማይባሉበት ምክንያት የለም።
የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ማቴ 5፤46
ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ክርስቶስም ትዕግስት ልባችንን ያቅናው ያለበት ምክንያት መውደዳችን በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኘንበትን ምስጢር ከቀራጭነት ሚዛን እንድናወጣው መሆኑ ግልጽ ነው። ክርስቶስ እኛን የወደደበት ትዕግስት ሚዛን የለውምና ነው።
የክርስቶስ የፍቅሩ ትዕግስት እኛን ለማዳን መፈለጉ ብቻ አልነበረም። እኛን ለማዳን ከመጣና ከኃጢአት ብቻ በቀር  በሥጋ  ከተዛመደን በኋላ ማዳኑን በደስታ ለመቀበል ከእኛ የተገባ ማንነት የሚጠበቅ ሆኖ ሳለ ሊያድነን የመጣበት ትዕግስት ሳያንስ እንዲያድነን መግደላችንን መታገስ መቻሉ እጅግ አስገራሚ ያደርገዋል።
ማንም ሰው መልካም ስጦታ ይዞለት የመጣውን ሰው በድሎት ሲያበቃ ከተበዳዩ ሰው ፍቅርን መጠበቅ አስቸጋሪ እንደሚሆንበት መገመት አይከብድም። ክርስቶስ ኢየሱስ ሌላ መድኃኒት በስጦታ አላመጣም፤ ይልቁንም ራሱን ሞት ለሚገባው ሰው፤ ምትክ ሆኖ ለመሞት ፍቅሩ ፍጹም በሆነ ትዕግስት የመጣ መድኃኒት ነበር። ለዚህ የሞት ምትክ መድኃኒት የቀረበለት መስዋእት የደስታ ምስጋና ሳይሆን እስከሞት የሚያደርስ መከራ ነበር። የሚገርመው ነገር ይህ ሁሉ ሆኖ ትዕግስቱ ምን ጊዜም ሞት በሚገባቸው ሰዎች ላይ የጸና መሆኑ ነው።
«ኢየሱስም፦ አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ» ሉቃ 23፤34 እንደዚህ ዓይነት ትዕግስት ከወዴት ይገኛል?
ዛሬ አንዱን ክርስቲያን በቅጽበታዊ ንዴት ሌላውን ክርስቲያን፤ ጉንጩን በጥፊ ቢመታው  ከመ ቅጽበት አጸፋዊ ምላሹን ከመንጋጋው ወይም ዓይነ ስቡን በተጠናከረ ምት የማይሰጥ ለማግኘት  ከተአምር ቢቆጠር አይገርምም። እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ ወይም ወንድምህ ሆኜ ሳለሁ እንደዚህ የመታኸኝ ምን በደልኩህ? የሚል ቢኖር በእውነት ክርስቲያን ማለት እሱ ነው።
በየሚዲያው፤ በየጉባዔውና በየመድረኩ  የምንወራወራቸው የቃላት ናዳዎች ያልፈነከቱት ወይም ያላሳመሙት ለማግኘት ከባድ ነው። እንደዚያም ሆኖ በማስተዋል ላይ ሆነን ነገሮችን ከክርስቶስ ትዕግስት አንጻር ባለመመልከት ናዳዎቹ ከየአእምሮአችን ጓዳ እየተፈነቀሉ ቀጥለዋል። ከሁሉም የሚከፋው እኔ ያልኩትና የተናገርኩት ብቻ ትክክል ነው የሚለው ናዳዎች እየተፈነቀሉ መወርወራቸውን አለማቋረጣቸው ነው።  እንደዚያም ሆኖ ክርስቲያኖች እንባላለን። ግን እስከመቼ?

አይሁዳውያን ክርስቶስን ሲከሱና ለስቅላት ሲያደርሱት ድርጊታቸው ለእነሱ ትክክላቸው ነበር። ለእነሱ ትክክል የመሰላቸው ነገር ግን የክርስቶስን ትክክለኛ ማንነት የሚሸፍን አልነበረም።  በሁለት ጽንፍ ያለው ሁለት ነገር በአንድ ጊዜ ትክክል ሊሆን አይችልም። የአይሁዳውያን የራሳቸው ትክክለኛነት፤ በሌላው ትክክል አለመሆኑ የሚታወቀው የእነሱ ትክክል «ስቀለው ስቀለው» የሚል ጩኸት የጎበኘው ሲሆን የክርስቶስን ትክክለኛነት የሚገልጸው እውነተኛው ትክክል ደግሞ « አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው» የሚለው ልመና ነበር።ትዕግስት የለሽና ትዕግስት የሞላበት ማንነት ሚዛናዊ መስፈሪያ ሆኗል። ጳውሎስም ይህንኑ ቃል ተቀብሎ ለተሰሎንቄ ሰዎች እግዚአብሔር ልባችንን ወደክርስቶስ ትዕግስት ያቅናው አለ። ዛሬ «ስቅሎ፤ ስቅሎ» የሚሉ ቀራጭ ክርስቲያኖች በበዙበት ዘመን ልባችንን ወደክርስቶስ ፍቅር እንዲያቀናውና ሰቃዮቻችንን ይቅር እንዲላቸው የመቻልን ትዕግስት ከማግኘት በላይ ምን ልመና ሊኖር ይችላል? ብዙውን ነገር ማድረግ እየቻልን ትዕግስትን ግን ከስሟ ወዲያ በእኛ እጅ ማቆየት አልቻልንም።
አዎ! ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው!!
ምክንያቱም ይላል፤ ጠቢቡ መክብብ በመጽሐፉ፤ ትዕግስት ኃጢአትን ጸጥ ያደርጋል፤ የመጣውንም ቁጣ ሊያቆመው ይችላል ሲል ያስተምረናል።
«ትዕግሥት ታላቁን ኃጢአት ጸጥ ያደርጋልና የገዢ ቍጣ የተነሣብህ እንደ ሆነ ስፍራህን አትልቀቅ» መክ 10፤4
ትዕግስታችን ከእኛ መውደቅና መዋረድ፤ ክብርን ማጣትና መጎሳቆል ጋር ሊያያዝ መቻሉ ድል ማድረግ ለምንችለው ድክመታችን ትልቅ ኃይልና መንፈሳዊ ጉልበትን ይዞልን ይመጣልና ነው። ክርስቶስ ወደ ጥልቁ ጉድጓድ እስኪጣል ድረስ መታገሱ፤ በትንሣዔው ከፍ፤ ከፍ ከማለት አልተከለከለም። እኛም ስለክርስቶስ ሁሉን በትዕግስት ብንቀበል ለነፍሳችን እረፍትንና ከፍታን ማግኘታችን እሙን ነው።
«ወበትዕግስትክሙ ታጠርይዋ ለነፍስክሙ»  በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ። ሉቃ 21፤19 እንዳለው በቅዱስ ወንጌል።
መታገሳችን መዳናችን ነው። በትዕግስት ሁሉን ችሎ ያዳነን ክርስቶስ ኢየሱስ ትዕግስትን መዳናችን አድርጎታልና። ሐዋርያው ጴጥሮስም ይህንኑ ቃል አስረግጦ ሲናገር እንዲህ ይለናል።
«የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ» 2ኛ ጴጥ 3፤15
ስለክርስቶስ ብለን የምንታገሰው ነገር መዳናችን እንዲሆን፤ ኃጢአታችን ጸጥ እንዲል፤ ከገዢና ከዘመኑ የስመ ክርስቲያን መስፍኖች ቁጣ ሁሉ ማዕበሉ እንደረጋ ወደብ ጸጥ ብለን በእርጋታ እንድንቀበል ኃይል የሚሆን ብርታታችን ነውና ትዕግስትን ገንዘባችን እናደርግ ዘንድ ይገባናል።  ለዚሁም ከጳውሎስ ተምረን እንዲህ እያልን እንጸልይ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ይነግረናል።
ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው። አሜን!