Tuesday, September 11, 2012

በአዲሱ ዓመት አዲስ ሰው እንሁን!


ለነፍሳችን እረፍትን የሰጠን እግዚአብሔር የታመነ ነው። ይሁን እንጂ ይህንን የነፍስ እረፍት ባለማግኘታችን በረከትና የኃጢአት ሥርየት ፍለጋ ከቦታ ቦታ የምንዞር ኢትዮጵያውያን ስፍር ቁጥር የለንም። ዘመናቱን እያፈራረቀ መግቦቱን ያላቋረጠ እግዚአብሔር ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለውን እነሆ ይመግባል። ነገር ግን ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የእለት እንጀራችንን ከእርዳታ ለጋሽ ሀገራት ምጽዋት በመጠበቅ የወፍ ጫጩት ከመሰልን ዓመታት አለፈን። ገሚሶቻችንም ምጽዋቱ ሲቀንስ፤ እድሜና ሆዳችን በማደጉ ረሃብና ጠኔ ከሚገለን የበረሃው ሃሩር ያቅልጠን፤ የባሕሩ ዓሳ ይብላን እያልን ዳቦ ፍለጋ መንጎዳችን ቀጥሏል።
እንግዲህ በነፍሳችን በረከት፤ ቃል ኪዳን፤ ሥርየት፤ ምሕረት፤ እረፍትና መድኃኒት መፈለግ ከጀመርን፤ ለሥጋችንም ዳቦ፤ ለእርዛታችን እራፊ መሻታችን ማብቂያ አለማግኘቱ የሚጠቁመን ነገር በእኛ በቃል ተቀባዮቹና በቃል ሰጪው በእግዚአብሔር መሃከል የሆነ ችግር አለ ማለት ይቻላል። እግዚአብሔር ለነፍስ እረፍትን ለሥጋ መግቦቱን ስለመስጠቱ ከተማመንን ከዚህ ስጦታ የኛው ድርሻ የጎደለው ለምንድነው? ብለን መጠየቁ ተገቢ ነው።
መጽሐፍ እንደሚለው በእርሱ የሚታመኑ ሁሉ ሕያው ቃሉን እየታመኑ ይህንን ለማለት ይደፍራሉ። «ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና» መዝ 3320
ይሁን እንጂ ለነፍስ እረፍት የሚሰጠው እግዚአብሔር ያጎደለው ነገር ያለ ይመስል ኢትዮጵያውያን የነፍስ እረፍት ፍለጋ ሀገሪቱን ስናስስ እድሜአችንን ኖረናል። ዛሬም ፍለጋችን እነሆ አላቋረጠም። መሻታችንን ከምንፈልግበት ቦታ ደርሰን በማግኘት የረካነው ስንቶቻችን እንሆን? ብዙዎች ግን ዛሬም ተስፋው እንደሞላ ሰው ረክቶ ከመቀመጥ ይልቅ የተሻለ መተማመኛና እረፍት ፍለጋ ላይ ናቸው። በረከት፤ ምሕረት፤ ሥርየት፤ ቃል ኪዳን፤ አስተማማኝ ቃል ፍለጋ፤ ፍለጋ.........ግን መገኛው የት ይሆን?
እስካሁን አስተማማኝ ነገር ላለመገኘቱ እለታዊ ሕይወታችን ግን ይመሰክርብናል። እኛም አላረፍንም፤ ሀገራችንም ከችግር አላረፈችም።
መዝሙረኛው እንዳለው «ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቍላለችና፥ ሆዳችንም ወደ ምድር ተጣብቃለች» መዝ 4425 እንዳለው እየሆነብን መሆኑ እርግጥ ነው።
ሚሊዮኖች በሀገራቸው ባለው ነገር ተስፋ በመቁረጣቸው ተሰደዋል። ወለተ ማርያም ከድጃ፤ አመተ ማርያም ፋጡማ ወዘተ እየተባሉ የማያውቁትን እምነት እምነታቸው አድርገው ለባርነትና ከሰው በታች ለሆነ ኑሮ እራሳቸውን በመሸጥ የሚኖሩትን ብዙ ሺዎችን ስናይ እግዚአብሔር ተስፋችን ባርኮታል ማለት እጅግ ይከብዳል። እኛ እንደምንለው፤ እውነት ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ከሆነች የተሰጠው አጸፋ እንዲህ ዓይነት ፈተና ሊሆን ይገባው ነበር? ወይስ እግዚአብሔር ስለሚወደን እኛን ለመከራ አሳልፎ በመስጠት ሊፈትነን ስለፈለገ ይሆን?
ይህንን ቃል ለመቀበል ያስቸግራል። እየተራበ፤ ያስራበኝ እግዚአብሔር ስለሚወደኝ ነው የሚል ሰው እግዚአብሔርን አያውቀውም፤ አለበለዚያም እግዚአብሔር ቃሉን ለሚጠብቁ አጠግባችኋለሁ ካለው እኛን የሚበድልበትን ምክንያት ሊያሳየን የግድ ይሆናል።
እውነታው ግን እግዚአብሔር ቃሉን እንደሰው አይለዋውጥምና ለሚታዘዙት በረከትን፤ ለሚቃወሙት ቁጣን እንደሚሰድ ስለምናውቅ ራሳቸውን እየደለሉና ሕጉን ሳይጠብቁ እኛ ሀገረ እግዚአብሔር ነን የሚሉቱን አስመሳዮች አንቀበላቸውም።
ረሃብ፤ እርዛት፤ ህመምና ሞት ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጡ ገጸ በረከቶች አይደሉም። ሰው ራሱ በራሱ ላይ ወዶና ፈቅዶ ያመጣቸውና የሚያመጣቸው ጉድለቶች ስለመሆናቸው ቃሉ ይናገራልና።
«ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፥ በልባችሁም ባታደርጉት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እርግማን እሰድድባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማታለሁ አሁንም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና እኔ ረግሜአታለሁ» ሚል 22




እግዚአብሔር የሚታዘዙትን ይታደጋቸዋል የሚል የተጻፈ ስለሆነ ስሙን እየጠራን ፈቃዱን ለመፈጸም ፈቃደኛ ባልሆንበት ሁኔታ ውስጥ ሀገረ እግዚአብሔር ነን ማለቱ ከንቱ ነው።
«በሥርዓቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም፥ ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቍረጥ ይደርሳል፥ የወይኑም መቍረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በጸጥታ ትኖራላችሁ። በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ። ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም አሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።ፊቴም ወደ እናንተ ይሆናል፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። ብዙ ጊዜ የተቀመጠውንም አሮጌውን እህል ትበላላችሁ ከአዲሱም በፊት አሮጌውን ታወጣላችሁ። ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ ነፍሴም አትጸየፋችሁም» ዘሌ 263-11
እግዚአብሔር ቃሉን ለጠበቁና ለወደዳቸው የሰጠው ቃል እውነት ነው። ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ይህ አልሆነም። ብዙ ጊዜ የተቀመጠውን ለመብላት ይቅርና የእለቱንም እንጀራ ለማግኘት ልመና እንደአንድ የስራ መስካችን ሆኗል። በባእዳን መዝገበ ቃላት ረሃብ የሚለውን ቃል «ኢትዮጵያ» የሚለውን ስም መግለጫ እስከማድረግ መደረሱ የውርደታችን ልክ የት እንደደረሰ ማሳያ ነው። የችጋራችን ደራሾች አሁን አሁን እነዚህ ፈውስ የሌላቸው ሕዝቦች በማለት ሰልችተውናል። እንደዚያም ሆኖ ዛሬም ዳቦ ከእጃቸው እንጠብቃለን።
እንግዲህ በእኛ ሀገረ እግዚአብሔር ባይነትና በእውነተኛው የእግዚአብሔር ሀገር መሆን መካከል ክፍተት አለ። እኛ በምንለውና እየሆነብን ባለው መካከል ያለው ልዩነት የትየለሌ የሆነው በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል።
1/ እግዚአብሔርን እናውቀዋለን፤ ግን ፈቃዱንና ቃሉን አልፈጸምንም።
2/ እግዚአብሔር ለም ሀገር ሰጥቶናል፤ ግን ተስማምተን ማልማትና መስራት አልቻልንም።
*ቃሉንና ፈቃዱን ለመፈጸም ሰዎች በቅድሚያ የራሳቸውን ፈቃድና ቃል ማራገፍ አለባቸው። የተጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ፤ ትእዛዝ፤ፍርድና ሥርዓት እያለ በምንም መልኩ ሰው የራሱን ህግ፤ ስርዓትና ትእዛዝ መጻፍ የለበትም። የሰው ሥርዓት የእግዚአብሔርን ይቃወማልና።
«አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፥ ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴን ሕጌንም ጠብቆአልና» ዘፍ 265 እንዳለው።
* ሥራን በበዓልና ድግስ ቆጠራ ማሳረፍ የለበትም።
«ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ» ዘጸ 209
ለዚህ የኢትዮጵያ ችግር መስተካከል ዋናው የእኛ መስተካከል ስለሆነ የለበስናቸውን ብዙ ልዩ ልዩ ልብሶችና ድካም የሚስማማቸውን ምድራዊ መታመኛዎችን ትተን ሁል ጊዜ አዲስ የሆነውን አዲሱን ሰው ለብሰን አዲስ እንሁን።
«ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ» ኤፌ 424 ያለውን ልንፈጽም ይገባል።