Saturday, September 29, 2012

በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሃይማኖት ብሔርተኝነት አደገኛ ነው!

«መጪውን ጊዜ በሃይማኖት ብሔርተኝነት መዋጀት» ይገባል። (ማኅበረ ቅዱሳን )

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁጥር 1 2005 ዓ.ም.
ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት ማለት ምን ማለት ነው?
በሳንዲያጎ ግሮስሞንት ኰሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጆን ኦክስ የሃይማኖት ብሔርተኝነትን በተነተኑበት ጽሁፋቸው እንዲህ ሲሉ ያስቀምጣሉ። የሃይማኖት ብሔርተኝነት /Religious Nationalism/ የሚከተሉትን አራት ባህርያት ያሟላ ወይም ለማሟላት የሚሰራ ሲሆን በአንድ ሀገር ውስጥ ህልውናው ይረጋግጣል ይላሉ።
1/ የሀገሪቱ መንግሥት ለአንድ የተለየ  የሃይማኖት ተቋም ብቻ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጥ ከሆነ፣
2/ የሃይማኖቱ ተቋም፦ ሞራልን፤ ግብረ ገብንና ሥነ ምግባርን በተመለከቱ በመንግሥታዊው ጉዳዮች ላይ ጫና ማሳረፍ ከቻለ፤
3/  በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሌሎች ሃይማኖቶች በመንግሥት የሚደገፈውን ሃይማኖት መብት መጠበቅ ከተገደዱ፤
4/ መንግሥታዊ ድጋፍ ያለው ይህ ልዩ ሃይማኖት በፖለቲካው መስክ የመንግሥቱ ደጋፊ ሲሆን  በአንድ ሀገር ውስጥ የሃይማኖት ብሔርተኝነት አለ ማለት ይቻላል በማለት ያብራራሉ።
ለምሳሌ ኢራን፤
በኢራን ውስጥ ክርስቲያኖች፤ ቡድሂስቶችና አይሁዳውያን ያሉ ቢሆንም መንግሥታዊው ሃይማኖት ግን እስልምና ነው። እስልምናው በመንግስት በጀት ይደገፋል፤ ሃይማኖታዊውን ተቋም የሚጻረር አንድም ሕግ አይወጣም፤ ሌሎች ሃይማኖቶች የእስልምናን ብሔራዊነት የበላይነት የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው ( ከእስልምና ሰው ሰብከው ቢወስዱ ይቀጣሉ፤ እስልምና ግን ከእነሱ ሰብኮ ቢወስድ አይጠየቅም)፤ መንግሥታዊው ሥልጣን  ከእስላም ሰዎች እጅ እንዳይወጣ ሃይማኖቱ ድጋፍ ይሰጣል።
ግሪክና፤ ራሺያም በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት ይታይባቸዋል። በሀገሪቱ ውስጥ ብዙ ሃይማኖታዊ ሰዎች ቢኖሩም የመንግሥቱን ስልጣን የሚረከበው ሰው ቃለ መሃላ የሚፈጽመው በመንግሥቱ ተቀባይነት ባለውና በሚደገፈው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እጁን ጭኖ እንጂ በፌዴራሉ ዳኛና በዱማው ፊት ብቻ አይደለም።
የሃይማኖት ብሔርተኝነት /Religious Nationalism/ በራሱ ሃይማኖታዊ ተቋም ውስጥ የተለየ ሃሳብና ጥያቄን ለማስተናገድ በፍጹም ቦታ አይሰጥም ብቻ ሳይሆን ባለው የኃይል ተደማጭነት የተነሳ ልዩ ሃሳብና ጥያቄ ወይም ተቃውሞ አቅራቢዎችን የመጨፍለቅና የማስጨፍለቅ አቅም አለው።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ሃይማኖት ብሔርተኝነት ጎዳና እያዘገመ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን የተለየ ሃሳብና አቋምን የማይቀበልና እንደነዚህ ዓይነት ልዩነቶች ለማስተናገድ ስለማይችል የሚወስደው እርምጃ  ማስደብደብ፤ ማሳሰር ብሎም ከተመቸው ማስገደል ነው። በመምህር ጽጌ ስጦታውና በዲ/ን ሙሉጌታ ወ/ገብርኤል ላይ የደረሰውን ድብደባ ማስታወስ ይሏል።
ብሔር ማለት በቁሙ ወሰን፤ ክልል፤ድንበር፤ ጠረፍ ያለው  ሀገር ማለት ነው። የሃይማኖት ብሔርተኝነት ማለትም የራሱ ድንበር፤ አጥር፤ክልል ወሰን ያለው የሃይማኖት ተቋም  ማለት ነው። የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የስነ ሃይማኖት ሌክቸረር ማይክል ኤሪክ ዳይሰን ስለሃይማኖት ብሔርተኝነት እንደዚህ ይላሉ። "No religion has a particular right on the nation»  በሀገሪቱ ውስጥ የተለየ መብት ያለው ሃይማኖት የለም»
ታዲያ የሃይማኖት ብሔርተኝነትን ማኅበረ ቅዱሳን የሚያቀነቅነው ለምንድነው? ምናልባት ከአባ ጳውሎስ በኋላ የፓትርያርክነቱ  ተራ የወሎዬዎች ነው እየተባለ የሚዘፈነውን በመስማቱ ሃይማኖታዊ ብሔር እንጂ ጎጣዊ ብሔር በቤተክርስቲያን የለም ለማለት ፈልጎ ይሆን?  የብሔር ድጋፍና ጥላቻ እንግዳ ነገር አልነበረምና ሹመቶቹን ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ ማላከክ ተገቢ አይደለም። የእግዚአብሔርን ፈቃድና እውቅና ማቀላቀል አይገባም። ሰዎች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሲከተሉ፤ ፈቃዱ ይፈጸምላቸዋል። የልባቸውን አሳብ ሲከተሉ ደግሞ  የልባቸውን መንገድ እንዲሄዱ እግዚአብሔር እውቅና ይሰጣቸዋል እንጂ በሁሉም ሹመቶች ላይ የእግዚአብሔር ፈቃድ የለም።
እንደ ልባቸው ሥራ ተውኋቸው፥ በልባቸውም አሳብ ሄዱ» መዝ 81፤12
እስራኤላውያን ሳኦል ይነግስ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ባይሆንም የልባቸውን አሳብ አይቶ ሳሙኤል ቀብቶ እንዲያነግስላቸው እግዚአብሔር እውቅናውን ሰጥቷል።
« እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ» 1ኛ ሳሙ 8፤7
ስለዚህ ሰዎች በቡድንና በጎጥ እየተደራጁ የሚያደርጓቸውን ሹመቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደተፈጸመ ለማድረግ ቢሞክሩ ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር ሚዛን አይደፋም።  እንደማኅበረ ቅዱሳን ዜና ዘገባ ከዚህ በፊት በቡድንና በፖለቲካ ድጋፍ የተደረገ የፓትርያርክ ሹመት እንዳልነበረ  በመቁጠርና ዛሬ እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ መከሰቱን በሚያሳብቅ መልኩ የሃይማኖት ብሔርተኝነትን ወደማራገብ መሸጋገሩ ጉንጭ አልፋ ስነ ሞገት ከመሆን አያልፍም። ምክንያቱም በሁላችንም ዘንድ ያለው እውቀት ያንን አያሳይምና ነው። ያለን መረዳት ከዚህ በፊት የቡድን ወይም የፖለቲካ ድጋፍ እንደነበረ ሲሆን የከዚህ በፊቱ የቡድንና የፖለቲካ ድጋፍ ምርጫ መቀጠል የለበትም ነው ሊባል የሚችለው። ይህ እውን ሊሆን የሚችለው ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ በመታመን እንደ ሐዋርያው ማትያስ ምርጫ በመንፈስ ቅዱስ እጣ ሰጪነት  ላይ በመጽናት ብቻ ነው። (ሐዋርያም ማትያስ አልኩኝ እንጁ አባ ማትያስ ዘካናዳ ወይም አባ ማትያስ ዘአሜሪካው አላልኩም)። ምርጫ ምንም ዓይነት «የሃይማኖት ብሔርተኝነት» ሳይጨመርበት መሆን ይገባዋል። ሃይማኖታዊ ብሄርተኝነት የሚታመነው በሃይማኖታዊ ወግና ባህል ላይ እንጂ በእግዚአብሔር አሠራር ላይ ስላይደለ የከዚህ በፊቶቹ  ስህተቶች እንዳይደገሙ ለማድረግ ዋስትና አይሰጥም።
ከዚህ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን በሃይማኖት ብሔርተኝነት እንቁም በማለት ጥሪ ሲያቀርብ ምን ማለቱ ነው?
ሁሉም ሃይማኖት የየራሱን እምነት አጥብቆ መያዝና መከተል ባህርያዊ ነው። ነገር ግን ችግሩ የሚመጣው «የኔ ብቻ» የሚል ጽንፍ ሲከተለው ነው። እግዚአብሔር አሜሪካና ሕዝቧን ይባርክ ማለት ለራስ የማሰብ አንድ አካል ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር አሜሪካና ሕዝቧን ባርኳል ማለት ሌላ ነገር ሲሆን ይህም «እኔ ብቻ» የሚለው ጽንፍ «ኢራንን አልባረከም» እንደማለት በመሆኑ ራስን በሁሉን ዓቀፍነት ዓይነት ማየት አደገኛ ነው በማለት የኮርኔሉ ሌክቸረር ዳይሰን ያሰምሩበታል።
« Religious nationalism can also give a sense of exclusivity»

ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት «ከእኔ በቀር» የሚልና ሌላውን ለመቀበል የማይፈልግ  አደገኛ ጽንፍ ነው፤ በማለት አጥብቀው ይገልጻሉ። የሃይማኖት ብሔርተኝነት ከሌላው ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ አይሆንም። የራሱን አጥርና ድንበር አበጅቶ የሚኖር ስለሆነ የህብረ ብሔር አመለካከት የለውም። ሌሎቹን ሃይማኖቶች እንደትናንሽና አላስፈላጊ ተኮናኝ ሃይማኖቶች ቆጥሮ በራሱ የፍርድ መዝገብ ስላሰፈራቸው በብሔሩ ውስጥ እንደመጤና የጥፋት ኃይል ያስቀምጣቸዋል።
ከእነዚህ  ሀገር በቀል የሃይማኖት ብሔርተኝነት ታጋይ የሆነው አንዱ ማኅበረ ቅዱሳን ነው። የዚህ ማኅበር አፈቀላጤ የሆነው አንድ አድርገን ብሎግ «ቀዩ መብራት» በሚል ርእስ እንዲህ ብሎ ነበር።
  • ·        አንደኛ ……….. ጠቅላይ ሚኒስትር …….   ONLY JESUS (የሐዋርያ እምነት ተከታይ)
  • ·        ሁለተኛ ……….ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ….. MUSLIM
  • ·        ሶስተኛው …. ጠቅላይ ሚኒስር ለመሆን የታጩት ሰው ….. MUSLIM
(አንድ አድርገን መስከረም 10 2005 ዓ/ም)፡-
ይህ አጻጻፍ ከሃይማኖት ብሔርተኝነት አንጻር ተገቢ ነው። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ታሪክ ከኦርቶዶክስ ውጪ ሌላ ሰው መሾሙ ያሳምማል፤ በእርግጥም ራሱን በጽድቅ ረድፍ ላስቀመጠ ሃይማኖት ቀይ መብራት ነው። ችግሩ የሚመጣው የኮርኔሉ ዩኒቨርሲቲ መምህር ያሉትን በንጽጽር ብናስቀምጥ «ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን እግዚአብሔር ይባርክ» ከማለት ይልቅ «ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን እግዚአብሔር ባርኳል» ከሚል የእኔ ብቻነት ማእቀፍ አስተሳሰብ የሚመነጭ መሆኑ ነው። ይህ አባባል እግዚአብሔር የረገመው የትኛውን ነው? የሚል ጥያቄን ስለሚያስከትል የሃይማኖት ብሔርተኞች፤ ጽንፈኞች መሆናቸውን ያመለክታል። ከሌላ እምነት ረድፍ ወደ ሥልጣን መምጣት እንደቀይ መብራት ይቆጠራል።   እግዚአብሔርን ለሚታዘዙና እሺ ብለው ፈቃዱን ለፈጸሙ በምድር በረከት ሁሉ ማትረፍረፍ አምላካዊ ፈቃዱ መሆኑን ስንመለከት ስለምን የባርኮቱን ምልክት ከማየት ከልክሎአቸው «በቀይ መብራት» አስደነገጣቸው?
«እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ» ኢሳ 1፤19
ብሔርተኞች ለራሳቸው የሃይማኖት ሕግ እንጂ ለእግዚአብሔር ሕግ የሚገዙ አይደሉም።  ሌሎቹን የሚያዩበት የዓይናቸው መነጽር የተንሸዋረረ መሆኑ የሚገለጸው እንደ እግዚአብሔር ሃሳብና እቅድ ሳይሆን እንደሃይማኖታዊ ህጋቸው ወግ ለማየት ስለሚሞክሩ ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑን ፈሪሳውያን አይሁዶች ናቸው። በሃይማኖት ሕጋቸው ሳይታጠቡ መብላት ነውር ነው። ውስጣቸው የቆሸሸና ለእግዚአብሔር ማደሪያነት ያልተሰራ ሆኖ ሳለ እጃቸውን ለማንጻት ትጉሃን ስለሆኑ እጅን ባለመታጠብ ብቻ ሌላውን ሲኮንኑ ይታያሉ። የተለሰነ መቃብር ውስጣቸውን ማንጻት ሲገባቸው አፍአዊ ክርስትናቸውን ለሃይማኖታዊ ማንነታቸው ትክክለኛነት ማረጋገጫ አድርገው ለማቅረብ ይዳዳሉ።
ማኅበሩ የሃይማኖት ብሔርተኝነት ስብከቱን ለማንሳት የወደደው ለምርጫ ያሰፈሰፉትን የጎጣቸውን ባለተረኛነት ጥያቄ  አቅራቢዎችን በአንድ የወግና የባህል ሙቀጫ /መውቀጫ/ ውስጥ ገብታችሁ ከምንወቅጣችሁ በስተቀር እኛን አታስቸግሩን የሚል ድምጸት ያለውን መልእክት ለማስተላለፍ የፈለገ ይመስላል።  ለወጋችንና ለባህላችን የሚመቸንን ከምንመርጥ በቀር ደጋፊያችን እንኳን ቢሆን በጎጥ ድርሻ ውስጥ ገብተን ጊዜያችንን አናጠፋም እንደማለት ነው። ይሁን እንጂ የሃይማኖት ብሔርተኝነት ጠቃሚነት ለመግለጽ ከተፈለገበት ለምርጫ አገልግሎት እናውለው ከሚለውም  በዘለለ ትልቅ መልእክት ያለው ቃል ነው። እኔና እኔነትን በማሳደግ፤ እኛና እኛነትን ማዳከም፤ ከሌሎች ጋር መስማማትን በመዝጋት ግላዊ የሃይማኖት ባህልን ማሳደግ ማለት ይሆናል።
ስለዚህ ለምክክር፤ ለመወያየት፤ ለመነጋገር፤ ለመጠያየቅ፤ ለመመካከር ምንም በር የሌለው የሃይማኖት ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ አደገኛ ነው። እስልምናው ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነትን በሸሪአ ሕግ ሊያረጋግጥ ይፈልጋል። በውስጡ የሚነሱ አስተሳሰቦችን በዚህ ማእቀፍ ውስጥ ይጨፈልቃል። ማኅበረ ቅዱሳንም በዚሁ ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት ከረጢት ውስጥ ልዩ ልዩ አስተሳሰብና አመለካከት ያላቸውን ሁሉ በመክተት ሃይማኖቱ በሚፈቅደውና ለክቶ በሚሰጣቸው መንገድ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው። ለምሳሌ ማኅበረ ቅዱሳን ጎጂ ድርጅት ነው ብሎ መናገር ወንጀል ይሆናል ማለት ነው። ዐቃቤ መንበሩ የፕሮቴስታንት ሰው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መምጣቱ ስጋት መሆኑን እንደመናገራቸው መጠን ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ሁሉ በሃይማኖት ብሔርተኝነት ጥላ ሥር ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦርቶዶክሳዊ ባለመሆኑ  እውቀቱን ወይም ፖለቲካዊ አስተሳሰቡን ሳይሆን እምነቱን ብቻ ተመልክቶ ውድቅ እንዲሆን በመሰለፍ ለመስራት ይጠበቅበታል ማለት ነው። በሃይማኖት ብሔርተኝነት የተሰለፉ ኃይሎች ማንም ወደ ሥልጣን መምጣት ያለበት በፖለቲካ እውቀት ሳይሆን በሃይማኖት አባልነቱ ሚዛን ነው የሚል አስተሳሰብ አላቸው።
ለዚህም ነው ዳይሰን « Religious nationalism can also give a sense of exclusivity» በማለት በአጭር ቃል ያስቀመጡት። ሌላውን ያካተተ ነገር እንዴት ይታሰባል?  እንደማለት ነው። የእነ አንድ አድርገን «ቀዩ መብራት» እና የማኅበሩ የሃይማኖት ብሔርተኝነትን ማቀንቀን በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን በውስጣቸው የሚመላለሰው እኔነት ጎትቶ ያወጣው የወግና የባህል ጽንፈኝነት ውጤት ነው። ስለሆነም ማኅበረ ቅዱሳን የሚወረውረው የሃይማኖት ብሔርተኝነት እጅግ አደገኛ አስተሳሰብና ከእስልምናው ሰለፊ ርእዮት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን ልናሰምርበት እንወዳለን።