Wednesday, September 19, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን የጥናት እና ምርምር ማእከል ባዘጋጀው በ፬ኛው የኢትዮጵያ ቤተ- ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ ላይ የተደረገ አጭር ደሰሳ፡፡



   ፍቅር ለይኩን ለደጀ ብርሃን የላከው ጽሁፍ
[fikirbefikir@gmail.com/befikir12@yahoo.com

‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ!›› የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሕያው ቃል ባለ አእምሮ የሆነ ሰው ሁሉ በማስተዋልና በጥበብ መንፈስ ሆኖ መልካሙን ከክፉ ለመለየት ጥናት እና ምርምር በእጅጉ አሰፈላጊ መሆኑን የሚያሳስበን ኃይለ ቃል/ምክር ይመስለኛል፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአይሁድ ምኩራብ ተገኝቶ በተደጋጋሚ ስለ ጌታችን፣ አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት፣ ጌትነት እና አዳኝነት የሰበከላቸው ልበ ሰፊዎቹ የቤሪያ ሰዎች፡- ‹‹ነገሩ እንዲህ ይሆንን በማለት መጻሕፍትን በመመርመር ቃሉን በሙሉ ልብ ተቀበሉ ይለናል፡፡›› (ሐዋ  ፲፯፣፲፩)   
የሥልጣኔ ምንጭ፣ የሺህ ዘመናት ባለ ታሪክ እና የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ለሆነችው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጥናት እና ምርምር ሥራ ታላቅ ፋይዳ ያለው መኾኑ አያጠራጥርም፡፡ በኢትዮጵያ ባሕልና ቱሪዝም ሚ/ር በቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ ጳጉሜን ፫ እና ፬ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ‹‹ኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ›› አንገብጋቢ እና ወቅታዊ በሆኑ ሀገራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ምሁራን፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመጡ፣ ከተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ መሥሪያ ቤቶች በተጋበዙ እንግዶች በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሰባት የጥናት ወረቀቶች የቀረቡበት ጉባኤ ነበር፡፡
ጥናት እና ምርምር በሳይንሳዊ ዘዴ ለችግር መፍትሔ ለማፈላለግ፣ አዳዲስ ግኝቶችን ለመፍጠር፣ ተጨማሪ እውቀትን ለማግኘት፣ አስፈላጊውን መረጃ ተገቢውንሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ዐቢይ ተግባር ነው፡፡ ዛሬ አንቱ የተባሉ፣ ዓለምን ያስደመሙ ጥበባት ኹሉ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ናቸው፡፡ በዘመናችን በዓለም ላይ የተጋረጡ በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ፣ ፖለቲካዊ እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ዋነኛው መንገድ ጥናት እና ምርምር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
ስለሆነም በሀገራችን ይህን የሚያስፈጽሙ አያሌ የጥናት እና ምርምር ተቋማት ተመሥርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን የረጅም ዘመን የሥነ መንግሥት/ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ኑሮ፣ ታሪክ፣ ባሕል እና ሥልጣኔ እንዲሁም ፍልስፍና፣ ሕግ፣ ሥነ ጹሑፍ፣ ኪነ ጥበብ እና ሥነ ሕንጻ/አርክቴክቸር ሰፊ እና ጉልህ አሻራ ያላት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ሰፊ የሆነ ምርምር እና ጥናት በማድረግ ረገድ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሀገራችን ለትምህርት መጀመር ከተጫወተችው ግንባር ቀደም ሚና እንዲሁም ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት እና ወንጌላዊት እና በበርካታ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናን ያሏት ተቋም የመሆኗን ያህል በበቂ ሁኔታ የተደራጀ የጥናት እና የምርምር ማእከል የላትም፡፡
ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድ ለእናቱ ሊባል የሚችለው በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ደረጃ አለ የሚባለው የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅም በብዙ አካዳሚያዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ እንደ አንድ አካዳሚያዊ ተቋም በበቂ ሁናቴ የተደራጀ እንኳን ቤተ መጻሕፍት የለውም፡፡ በየጊዜው በአኀተ አብያተ ክርስቲያናትም ሆነ በክርሰቲያኑ ዓለም የሚወጡ አዳዲስ መጻሕፍቶች፣ የጥናት እና የምርምር ጆርናሎች እና ፐሮሲዲንጎች በዚህ ተቋም ውስጥ እጅጉን ብርቅ ናቸው፡፡ እናም ይህ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብቸኛ እና አንድ የሆነ የሥነ መለኮት ተቋም የሚጠበቅበትን ያህል ለቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ ለሀገር መፍትሔ አመላካች የሚሆኑ ብቁ እና ወዳዳሪ የሆኑ ምሁራንን በብዛት እና በጥራት ለማፍራት ቀርቶ ተቋም እራሱ በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ የሌሎችን ብርቱ እገዛ ወደሚፈልግበት ደረጃ የደረሰ ይመስላል፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማለት ይቻላል የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በማጥናት በኩል ከእኛ ይልቅ ምዕራባውያኑ እና አሜሪካውያን ምሁራን ሰፊውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን ብቻ ሳይሆን በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ስለ ችግሮቻችን አጥንተው መፍትሔ አሳብ የሚያቀርቡልን ፈረንጆቹ መሆናቸው ነገሩን እንቆቅልሽ ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ በተለይም በቤተ ክርስቲያናችን ጥናት እና ምርምርን የሚያበረታቱ አመቺ ሁኔታዎች እና ተቋማት አለመኖራቸውና ለረጅም ዘመናት የቆየው የቤተ ክርስቲያኒቱ ባሕላዊ የሆነ የትምህርት ሥርዓትም ያለውን ከማስጠበቅ አልፎ አዲስ እውቀት ለማምረት (Knowledge Production) የሚያስችል የጥናት እና ምርምር በር ለመክፈት አለመቻሉ እንደ አንድ ምክንያት ሊወሰድ የሚችል ይመስለኛል፡፡
ፊደል ቀርፃ፣ ቀለም በጥብጣ፣ ብራና ዳምጣ የድንቁርና እና የአለማወቅን ጨለማ ለመግፈፍ ገና ከጥንት ከጠዋቱ ታጥቃ የተነሳች ቤተ ክርስቲያናችን በጀመረችው ፍጥነት መጓዝ ተስኗት እና ይባስም ሲል በምርምር እና በጥናት እጅጉን የተራቀቁ እና የመጠቁ የሥነ መለኮት እና የፍልስፍና ሊቃውንቶችን ያፈራች ቤተ-ክርስቲያን በዘመናችን በብዙ ችግሮች ተተብትባ መንገዷ ሁሉ ባለህበት እርገጥ መሆኑ ሁላችንንም ሊያስቆጨን የሚገባ ጉዳይ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም፡፡
ይህን ቤተ ክርስቲያኒቱ እና የትምህርት ተቋማቶቿ ኅብረተሰቡ ከእነዚህ ተቋማት የሚጠብቀውን ያህል አለመንቀሳቀሳቸው፣ ያሉባቸውን እና የተጋረጡባቸውን ሁለተናዊ እንቅፋቶች እና ቤተ-ክርስቲያኒቱ በዚህ ረገድ እጅግ ወደ ኋላ መንደርደሯን የታዘቡ አንድ ምሁር እና ፖለቲከኛ በአንድ ወቅት ‹‹ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጭ›› በሚል በመጽሐፋቸው ላይ፡-
በአንድ ወቅት በምድረ አውሮፓ እና በአረቢያ ከነበሩ ተመሳሳይ የመንፈሳዊ እውቀት ተቋማት ጋር መወዳደር የሚችል የትምህርት ዓይነቶች ያስተምር የነበረ ቤተ ክህነት፣ አውሮፓውያኑ እነዚህን ተቋማት ወደ ትላልቅ እና ዝነኛ የጥናት እና የምርምር ማእከላት እና ዩኒቨርስቲዎች መቀየር ሲችሉ የእኛው ቤተ ክህነት ተቋማት እንዴት ከነ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቀባይነታቸው እና ክብራቸው ጋር የእርግማን ሰባኪ ተቋም ብቻ ሆኖ እንደቀረ እኔም ሆነ ትውልዴ ለማወቅ አልጣርንም፣ አልፈለግንም በማለት ቁጭታቸውን ገልጸው ነበር፡፡
ዛሬ በዓለማችን ያሉ ትላልቅ የሃይማኖትም ሆኑ ዓለማዊ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ወጪ የሚመድቡት ሰፊ እና ጥልቅ በሆነ ጥናት ለታገዙ የምርምር ስራዎች እና አማካሪዎች/መማክርት ነው፡፡ በሀገራችንም ሆነ በቤተ ክርስቲያናችን ለተጋረጡብን ሁልቆ መሣፍርት ለሌላቸው ችግሮቻችን በዚህ ዘመን ጥልቅ የሆኑ በእግዚአብሔር ጥበብ እና ማስተዋል መንፈስ የተቃኙ ጥልቅ የሆኑ አሳቢዎች/ተመራማሪዎች (Great Thinkers) በእጅጉ ያሰፍልጉናል፡፡
በቀደመው ታሪካችን ዘመን በሀገራዊ እና በቤተ ክርስቲያን አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ጊዜ በመውሰድ የሚያሰላስሉ፣ የሚጸልዩ፣ በጽሞና መንፈስ ሆነው በእግዚአብሔር ፊት በጽናት እና በትዕግስት የሚቆዩ አባቶች እንደነበሩን የታሪክ ድርሳናቶቻችን ይመሰክራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተጋድሎ እና መንፈሳዊነት ዛሬ በታሪክ ብቻ በነበር የምናወሳው የሩቅ ዘመን ትዝታችን ሆኖ መቅረቱ ሁላችንንም ሊያንገበግበን ይገባል፡፡ አውሮፓውያን እና አሜሪካውያን ዛሬ ለደረሱበት እጅግ ለመጠቀ ሥልጣኔ፣ የአስተሳሰብ ምጥቀት፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገቶች እና ለውጦች ትልቅ መሠረት የጣሉ በሃይማኖት ተቋማቶቻቸው የነበሩ ጥልቅ አሳቢዎች እና ተመራማሪዎች እንደ ነበሩ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡
በአውሮፓውያኑ ዘንድ ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ቅርስ፣ ፍልስፍና፣ ኪነ ህንፃ እና ኪነ ጥበብ በሰፊው እንዲጠና በመካከለኛው ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያውን መነኮሳት እና ሊቃውንት በተለይ በአውሮፓ ለኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር መከፈት ምክንያት መሆናቸውን ታሪካችን ያወሳል፡፡ በተለይ አባ ጎርጎሪዎስ ዘመካነ ሥላሴ የተባሉት መነኩሴ ጀርመናዊውን ሉዶልፍን የግዕዝን ቋንቋ፣ የሀገራችን እና የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በማስተማር በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ ምድር የኢትዮጵያ ጥናት እንዲጀመር በቀደምትነት መሠረትን የጣሉ  ኢትዮጵያዊ ሊቅ እንደሆኑ የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ሀገር ምሁራን ይመሰክራሉ፡፡
በእነዚህ ኢትዮጵያውያን መነኮሳትና ሊቃውንት በአውሮፓ የተጀመረው ጥናት እስከ አሁን ዘመን ድረስ ቀጥሎ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ትላልቅ ዩኒቨርስቲዎች፣ የጥናት እና ምርምር ማእከሎች በኢትዮጵያ ጥንታዊ ቋንቋ በሆነው በግዕዝ፣ በሀገሪቱ የረጅም ዘመን ታሪክ እና ሥልጣኔ ዙሪያ ሰፋ ያለ ጥናት በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ ለአብነትም ያህል በፈረንሳይ፣ በኢጣሊያን ፍሎረንስ እና ኔፕልስ ዩኒቨርስቲዎች፣ በጀርመን ሀምቡርግ ዩኒቨርስቲ፣ በለንደን School of Oriental and African Studies እና በአሜሪካ በሚገኙ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች በጥንታዊው የኢትዮጵያ ቋንቋ በግዕዝ እና በሀገራችን ጥንታዊ ሥልጣኔ እና ታሪክ፣ ባሕል እና ቅርስ ዙሪያ ጥናቶች ይደረጋሉ፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ዙሪያ ጥናት እና ምርምር የሚያካሂዱ የውጭ ሀገር ምሁራን መሆናቸው ቀስ በቀስ እየተለወጠ ቢገኝም እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ እራሳችን በጥናት እና በምርምር በተደገፈ ሁኔታ በልበ ሙሉነት ለመናገርም ሆነ በተለያዩ ቋንቋዎች የዳጎሱ የጥናት መጻሕፍቶችን በማቅረብ ረገድ ገና ብዙ የሚቀረን ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም የዚህ የማኅበረ ቅዱሳን የምርምር እና የጥናት ማእከል በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ዓመታዊ ጉባኤም በከፊል የዚህ ቁጭት እና ቅናት ውጤት የወለደው ነው ለማለት የሚቻል ይመስለኛል፡፡
የጥናት እና ምርምር ፋይዳውን የተረዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፍሬዎች የሆኑ እና በተለያዩ የትምህርት መስክ እስከ ፒ ኤች ዲ የተማሩ ልጆቿ ጥረት ለአራተኛ ጊዜ በማኅበረ ቅዱሳን የምርምር እና ጥናት ማእከል የተዘጋጀው አራተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ፣ በጥናት እና በምርምር በመታገዝ በቤተ ክርስቲያናችን ያሉትን ችግሮች በሚገባ አጥንቶ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ ተያያዥ በሆኑ፣ በወቅታዊ የሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለማፈላለግ የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት በሚል ከአራት ዓመታት በፊት የተጀመረ ጉባኤ መሆኑን የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ የሆኑት ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡
ለአራተኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁለት ቀናት በተደረገው የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን የጥናት ጉባኤ ላይ በቀረቡት የጥናት ወረቀቶች እና ከተሳታፊያን በተነሱ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶች እና ውይይቶች ዙሪያ መጠነኛ የሆነ አጭር ደሰሳ በማድረግ ይህችን አጠር ያለች ጹሑፍ ለአንባቢያን ለማቅረብ ወደድሁ፡፡
ይህ ጹሑፍ እግረ መንገዱንም በተለይ በማኅበረ ቅዱሳን እና ከማኅበረ ቅዱሳን በተቃራኒ በቆሙ ማኅበራት እና ግለሰቦች ደጋግመው ማኅበረ ቅዱሳንን ስለሚከሱበት፡- ‹‹ማኅበሩ የወንጌል ጠላት ነው፣ ማኅበረ ቅዱሳን የፖለቲካ ድ/ት ነው፣ ማኅበሩ በመንፈሳዊነት መጋረጃ ጀርባ የለየለት ዘራፊ እና ነጋዴ ሆኗል፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላለፉት ሃያ ዓመታት ለገባችበት ቀውስ በከፊልም ቢሆን የማኅበሩ ተጠያቂ ነው…ወዘተ፡፡›› በማለት ማኅበሩን የሚከሱትን ቡድኖችንም ሆነ ግለሰቦች በሩቅ ቆመው ከመካሰስ እና እርስ በርስ ከመፈራረድ ይልቅ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል አሉ የሚሏቸውን ችግሮች እና ትዝብታቸውን በተጨባጭ መረጃ፣ በጥናት እና በምርምር በማስደገፍ ማቅረብ ቢችሉ እንዴት መልካም በሆነ ነበር፡፡ እንዲሁም በእንዲህ ዓይነቶቹ እና በተመሳሳይ የጥናት ጉባኤ መድረኮች ላይ በመገናኘት፣ በመቀራረብ እና በግልጽ በመነጋገር ልዩነቶችን አሰውግዶ በአንድነት መሥራት የሚቻልበት መንገድ እንዲኖር በሚል በቅንነት መንፈስ ያቀርብኩት ደሰሳ እንደሆነ ከወዲሁ ለአንባቢዎቼ በአክብሮት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
በዚህ አራተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ ላይ ከቀረቡት እና በጨርፍታ ዳሰሳ ላደርግባቸው ከመርጥኳቸው የጥናት ወረቀቶች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፕሬስ ባልደረባ፣ የታሪክ ምሁር እና ተመራማሪ እንዲሁም በሀገራችን በሚታተሙ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የታሪክ ነክ መጽሐፎች ላይ ሰፊ እና ጥልቅ የሆኑ ዳሰሳዎችን (Book Reviews and Critics) በማድረግ የሚታወቀው አቶ ብርሃኑ ደቦጭ፡-

‹‹የማኅበረ ቅዱሳን የኅትመት ውጤቶች በቤተ ክርስቲያን እና በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን የአዘጋገብ ሂደት›› በተመለከተ ባቀረቡት የጥናት ወረቀት ላይ በተለይ በስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጾች፣ ዜናዎች እና ሐተታዎች ላይ አጥኚው ሰፋ ያለ ትንታኔ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ ጋዜጣዋ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባዎች፣ ሂደቶች እና ውሳኔዎች ላይ፣ በሃይማኖታዊ ግጭቶች መንስኤዎች ዙሪያ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ በሆኑ ወቅታዊ እና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚወጡ ዘገባዎች በአብዛኛው ፍርሃት የሚንጸባረቅባቸው ቢሆኑም ስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ችግሮች በማሳየት ረገድ አዎንታዊ ሚና እንዳላት ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ተግባራዊ የሚሆን መፍትሔን በማቅረብ ረገድ ግን ጋዜጣዋ ድካም እንደሚታይባት ገልጸዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ባቀረቡት የጥናት ወረቀት ላይ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት እና በቅርስ ጥናት እና ጥበቃ የሥራ ባልደረባ የሆኑ ሰው በሰጡት አስተያየት፡- ‹‹ስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ እንደ ስሟ እውነትን በመናገር ረገድ ብዙም የተዋጣላት አይደለችም፡፡›› የማኅበረ ቅዱሳን ኅትመት ውጤቶች፡- ‹‹የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልእኮ የሆነው ወንጌልን ገሸሽ ያደረጉና የወንጌሉ ዐቢይ መልእክት እውነት፣ መንገድ እና ሕይወት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በሚገባ የማይገልጽ ነው በሚል አስተያየታቸውን አጠናክረዋል፡፡›› በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች፡- ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን የኅትመት ውጤቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባዎች እና ውሳኔዎች ላይ እንዲሁም ሀገራዊ በሆኑ ወቅታዊ እና አንገብጋቢ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ላይ ግልፅነት እና ተጠያቂነት የሚያንሰው ነው ሲሉ…›› ሌሎች በግል ያነጋገርኳቸው ተሳታፊዎች ደግሞ በዋነኝነት፡-
‹‹በቤ/ን እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የማኅበረ ቅዱሳን የኅትመት ውጤቶች መንፈሳዊ ወኔ እና ድፍረት የሚጎድለው አዘጋገብ እንደ ሚንጸባረቅበት…›› አስተያየታቸውን ሰጥተውኛል፡፡ 

በእነዚህ እና በመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተነሱ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶች እና ጥቆማዎች ላይ በማኅበሩም ሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ የኅትመት ውጤቶች ላይ በእርጋታ መንፈስ ጠቃሚ እና በጎ የሆነ ውይይት የተካሄደበት ነበር፡፡ በቀረበው የጥናት ወረቀት ላይ ከተሳታፊያን የቀረቡት ጥያቄዎች እና የተደረጉ ውይይቶች ብሩህ ተስፋዎችን የተሞሉ እንደ ነበሩ በግሌ ታዝቤያለሁ፡፡
ሌላኛው ጥናት አቅራቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሙስናን ለመዋጋት/ለመከላከል ያለው ሚና›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታቸው መግቢያ ላይ ጥንታዊት እና ሐዋርያዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውልድን በሥነ ምግባር እና በሃይማኖት ታንጸው እንዲያድጉ የተጫወተችው ሚና ትልቅና ሰፊ መሆኑን ተጨባጭ ማስረጃዎችን እና ምሳሌዎችን በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡
የመድረኩ አወያይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፡- በሀገራችንም ሆነ በተቀረው ዓለም ለዘመናዊው ሕግ፣ የሥነ ምግባር ደንቦችና ሥነ ሥርዓቶች መነሻ የሆኑት የሃይማኖት ተቋማት መሆናቸውን በመግለጽ በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ትጠቀምበት የነበረው ፍትሐ ነገሥት የተባለው መጽሐፍ፣ የቆየው ክርስቲያናዊ ባሕል እና ግብረ ገብ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕግ መወለድ ያላቸውን ጉልህ ድርሻ አንስተዋል፡፡
አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዓለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በሀገራችን ትልቅ አደጋ የሆነውን ሙስናን በመዋጋት ረገድ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ያላቸውን በጎ አስተዋዕፆ አጽንዖት በመስጠት ገልጸዋል፡፡ በዚህ አንገብጋቢ ርዕስ ጉዳይ ላይ ከመድረክ አስተያየታቸውን ያቀረቡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፡- ‹‹በዘመናችን የሃይማኖት ተቋማት፣ መሪዎች እና መምህራን እንደ ጥንቱ ዘመን በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር ቀርቶ እራሳቸው አስከፊ በሆነ የሞራል ውድቀትና ሙስና ውስጥ መገኘታቸው የሚያሳፍር እና የሚያሸማቅቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡››
እንዲሁም ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች፡- ‹‹በቤተ ክህነቱ በእጅጉ ተንሰራፍቶ ያለውን ሙስና፣ ዝርፊያ እና የንብረት ብክነት ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደ መንግሥት ሁሉ የጸረ ሙስና ተቋም ማቋቋም ወደ ሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡›› በማለት በምሬት እና በቁጭት ሆነው ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በእሁዱ ዕለት የሁለተኛው ቀን ጉባኤ ላይ ‹‹The Role of Folklore in Controlling Sexual Behavoiur in Christian Context›› በሚል ርዕስ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ የቋንቋ እና የባሕል ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ የሻው ተሰማ ባቀረቡት ጥናታዊ ጹሑፋቸው ኢትዮጵያዊ የሆኑ የሥነ ቃል ሀብቶቻችን ሥነ ምግባርን፣ በኢትዮጵያዊ ባሕል እና ጨዋነትን ወጣቶችን ኮትኩተው በማሳደግ ረገድ ያላቸውን ፈይዳ በሰፊው አስረድተዋል፡፡ በተለይ በዘመናችን በዘመናዊነት እና በሥልጣኔ ስም ወጣቶቻችን በምዕራቡ ዓለም መረን የለቀቀ ባሕል ምርኮኛ በመሆን ትውልዱ ማንነቱን ታሪኩን እና ክቡር ሕይወቱን ጭምር እያጣ ያለበትን ሁኔታ በጥናታቸው ገልጸዋል፡፡
ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ ከሚነሳበት ራብተኝነት፣ ድርቅ እና ድህነት ባልተናነሰ ዜጎቿ በኤ ች አይ ቪ/ኤድስ የሚያልቁባት ምድር ተብላ የመጠራቷ ምክንያቱ ይኸው በሥልጣኔና በዘመናዊነት ስም በትውልዱ ላይ የተጫነው ልቅ ባሕል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሥነ ቃል ትውፊታዊ ሀብቶቻችን ወጣቱን ትውልድ በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ጨዋና በባሕሉና በታሪኩ የሚኮራ ሰብእናን እንዲያዳብር ለማድረግ እንዚህን ጥንታዊ ሀብቶቻችን ዙሪያ ጥናት እና ምርምር ማድረግ ያለውን ፋይዳ በጥናታዊ ጹሑፋቸው በአጽንዖት ገልጸዋል፡፡
ተሳታፊዎችም በዘመናችን አንገብጋቢ እየሆነ በመጣው የሞራል ውድቀት፣ የቤተሰብ መፍረስ፣ ልቅ የሆነ የልጆች አስተዳደግና ቤተሰባዊ ግንኙነት ዙሪያ እየተከሰተ ያለውን ማኅበራዊ ምስቅልቅል እና ቀውስ ለመቀነስ ሃይማኖታዊ ተቋማት እና እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ የወጣት ማኅበራት ያለባቸውን መንፈሳዊ ኃላፊነት በሚገባ እንዲወጡ አደራ ጭምር ያስተላለፉ ሰዎች ነበሩ፡፡
በሁለቱ ቀናት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ ላይ በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች ጥናቶች ያቀረቡ ሰዎች ነበሩ፡፡ በመድረኩ የቀረቡ ጥናቶች አንገብጋቢና ወቅታዊ የሆኑ ሀገራዊ አጀንዳዎች የተነሱበትም ነበር፡፡ በሀገራችን ታሪክ፣ ባሕል፣ ቅርስ፣ ቱሪዝም፣ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና፣ ሕግ ዙሪያ የቀረቡት ጥናቶች ላይ ከማኅበረ ቅዱሳን፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከመንግሥታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
አንዳንድ በግል ያነጋገርኳቸው አስተያየት ሰጪዎች፡- ‹‹የጥናት እና ምርምር ማእከሉ ለወደፊቱ በሀገራችን ከሚገኙ የተለያዩ እምነት ተቋማት የሚገኙ ምሁራንን ጭምር በመጋበዝ በሃይማቶች መካከል መቀራረብ እንዲኖርና ለሀገራችን ሰላም፣ አንድነት እና እድገት የሃይማኖቶት ተቋማት እና አማኞች ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ እንዲህ ዓይነት የውይይት መድረኮች ከሲቪል ማኅበራት እና የሃይማኖት ተቋማትም እገዛ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለግሰውኛል፡፡››
በጥናቱ ማጠቃለያ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የጥናት እና ምርምር ማእከሉ ዳይሬክተር ማእከሉ ጥናት እና ምርምር ለማቅረብ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዕለቱም በተለያዩ ምሁራንና የኢትዮጵየ ቤተ ክርስቲያን ተመራማሪዎች በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔት/Journal of Ethiopian Church Studies ለሽያጭ ቀርቧል፡፡ ለሁለት ቀናት የተካሄደው ጉባኤም የጥናቱን አቅራቢዎች ና ተሳታፊዎች በማመስገን በአባቶች በምስጋና ጸሎት፣ በመጪው አዲስ ዘመን ለሀገራችን እና ለቤተ ክርስቲያናችን ፍፁም ሰላም እና አንድነት እንዲሆንላቸው በጸሎት በመማለድ ተዘግቷል፡፡
በቀጣይ ጹሑፌም የማኅበረ ቅዱሳን የጥናት እና ምርምር ማእከል ባዘጋጀው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት ጉባኤ ላይ የጀመርኩትን ዳሰሳ በዚሁ ታትሞ በሽያጭ በቀረበው በሁለተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጆርናል ላይ ‹‹የኦሮሞ ብሔር ባሕል ሥርዐተ አምልኮ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቁርኝት›› በሚል ርዕሥ በማኅበራዊ ሳይንስ የከተማ ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዋቅቤካ ኤርፓ የተባሉ ሰው ባቀረቡት የጥናት ወረቀት ዙሪያ ደሰሳዬን እንደምቀጥል ለአንባብያን ላስታውስ እወዳለሁ፡፡ በቀጣይ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔት (ቅጽ.፪) በቀረቡት የጥናት ወረቀቶች ላይ የምቀጥለው ዳሰሳ ብዙዎቻችንን የሚያነጋግረንና የሚያወያየን ርዕሰ ጉዳይ እንደሆነ አስባለሁ፤ ስለዚህም ከወዲሁ ሁላችንም አስተያየት በመስጠት፣ በቅንነት እና በጨዋነት መንፈስ በመወያየት ተሳታፊ እንድንሆን አደራ እላለሁ፡፡
አዲሱ ዘመን እርስ በርሳችን ከመካሰስ እና ከመፈራረድ በመውጣት፣ በቅንነት እና በበጎ ኅሊና በመቀባበል፣ በእግዚአብሔር ፍቅር እና በሰላም ለቤተ ክርስቲያናችን ፍፁም የመንፈስ አንድነት የምንሰራበት የተባረከ ዘመን እንዲሆንልን በመመኘት ልሰናበት፡፡
ሰላም! ሻሎም!