Thursday, September 13, 2012

«ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም!»

«እናንተ ብትገቡበት አያቅታችሁም፤በቤተ ክህነት አጽናኝም አሸባሪም መኖሩን የተናገሩት» አባ  ኤልሳዕ የደቡብ ጎንደር ሊቀ ጳጳስ

«ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ የሚጠብቅ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስፈጸም ረገድም ቋሚ ተጠሪ ነው»
አባ ማትያስ የካናዳ ሊቀ ጳጳስ
«የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይናጋ “በወርድም በቁመትም መሥራቱን” አጠናክሮ እንዲቀጥል» አባ ገብርኤል የሃዋሳ ሊቀ ጳጳስ
«ማኅበሩን መደገፍ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንደኾነ» ቄስ ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁ
ከ40 ሚሊዮን ተከታዮች በላይ ያሏትን ቤተክርስቲያን ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ የገጠሪቱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ የመምራትና የማስተዳደር ሥልጣን የተረከቡ ሊቃነ ጳጳሳት ከቤተክርስቲያኒቱ የምእመናን ማኅበር አንዱ አባል ለሆነው ለማኅበረ ቅዱሳን ይህን ያህል «ተቀመጥ በወንበሬ፤ ተናገር በከንፈሬ» ዲስኩር ለማሰማት መድረሳቸው በእርግጥም የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች እግዚአብሔርን ተስፋ ከማድረግ ወርደው፤ መንፈስ ቅዱስን አጋዥና መሪ ከማድረግ ወጥተው፤ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያኒቱ መንፈስ ቅዱስ ስለሆንክ አንተ ምራን ከሚሉበት ደረጃ መድረሳቸው አሳዛኝም ፤አሳፋሪም ነው።
አባ ኤልሳዕ የደቡብ ጎንደር ሊ ቀጳጳስ በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል ያለውን ቅራኔ ለመፍታት ማኅበረ ቅዱሳን ቢገባበት ምንም የሚያቅተው እንደሌለ መናገራቸው ሲሰማ በእርግጥ እኒህ አባት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይመራሉ? ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። የ21 ዓመቱ ክፍፍል ሊያበቃ ያልቻለው ለካ፤ በሥጋዊ መንፈስ እየተመሩና የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ታምነው እንዳልነበረ ከማሳየቱም በላይ ዛሬም ከዚያው ስህተታቸው ሳይላቀቁ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማስቀደም መድፈራቸውን ስንመለከት ቤተክርስቲያኒቱ የምትመራው በእነማን እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታየናል።  «እናንተ ብትገቡበት አያቅታችሁም» ማለታቸው የሚያሳየው እስከዛሬ የዘገውም ማኅበረ ቅዱሳን በእርቁ ውስጥ የማሸማገል ሚናውን ስላልተወጣ ነው ማለታቸው ነው። ሲኖዶሱ ደካማና ለእርቁ መፈጸም አቅም የሌለው በመሆኑ እስካሁን የመዘግየቱ ምክንያት እንዲህ ከተገለጸላቸው ታዲያ ለምን ማኅበረ ቅዱሳንን የሲኖዶሱ የእርቁ ቋሚ ተጠሪ አድርገው በመሾም ቶሎ እንዲፋጠን ያላደረጉ? በዚያውም ደግሞ በሲኖዶስ ጉባዔ ላይ እንደፓርላማ ደንብ በአጋር ድርጅትነት ወንበር የማይሰጡት?
ማኅበረ ቅዱሳን የራሱ የሆነ  የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ያለው ድርጅት ነው። በዚህ ስውርና ግልጽ የዓላማዎቹ ጉዞ ላይ የሚቀበሉትን እስከነጉድፋቸው ተሸክሞ ለመጓዝ የማይጠየፍ፤ የማይቀበሉትን ደግሞ ምንም እንኳን ንጹሐን ቢሆኑ አራግፎ ለመጣል ጥቂት የማያቅማማ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን እነ አቡነ ኤልሳዕን የመሳሰሉ ታማኞች  «አንተ ስላልገባህ እኛ አቅቶናል» የሚል ድምጸት ያለውን ቃል ቢናገሩለት ማን መሆናቸውን ከሚያሳዩ በስተቀር ስለማኅበረ ቅዱሳን ሁሉን አዋቂነትና የመፍትሄ ቁልፍነት መናገራቸው ማንንም አያሳምንም።
ሌላው አባትም ገና ከወደ ካናዳ ብቅ ከማለታቸው «እስመ አልቦ ነገር ዘይሰዓኖ ለማኅበረ ቅዱሳን» የሚል ትርጉም ያለውን ቃል ሲናገሩ መስማት ለጆሮ ይቀፋል። እሳቸው የተናገሩት ነው ተብሎ በደጀ ሰላም የሠፈረውን ይህን ቃል መዝኑት።
«ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ የሚጠብቅ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስፈጸም ረገድም ቋሚ ተጠሪ ነው»
ማኅበረ ቅዱሳን እውነት የሚታዘዝ ሆኖ ከሆነ ይታዘዛል፤ ይላካል፤ የሲኖዶሱን ትእዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ ሲጠሩት አቤት፤ ሲልኩት ወዴት ይላል ብሎ ታዛዥነቱን መግለጽ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳን፤ ቅዱስ ሲኖዶስን በዙሪያው ኾኖ ይጠብቀዋል ማለት ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኾኗል ማለት ነው።  ቅዱስ ሲኖዶስ ዙሪያውን ሆኖ የሚጠብቀው መንፈስ ቅዱስ ነው ወይስ ማኅበረ ቅዱሳን? የሲኖዶሱ አባል አባ ማትያስ ግን ሲኖዶሱ ዙሪያውን ሆኖ የሚጠብቀው ማኅበረ ቅዱሳን ነው ሲሉ በግልጽ መናገራቸው ማኅበረ ቅዱሳን ሁሉን ማድረግ እንደሚችል የማወጃቸው ነገር አስገራሚ ነው። ሲኖዶሱ በምን ዓይነት ሰዎች እንደተሞላ ከማሳየት አልፎ ፓትርያርክነቱን ለማግኘት ስለማኅበረ ቅዱሳን ታላቅነት መማል ፤ መገዘት የግድ ሆኗል ማለት ይቻላል።
አባ ማትያስ የሲኖዶሱ ጠባቂ ማኅበረ ቅዱሳንን ከማድረጋቸውም በላይ የሲኖዶሱን ውሳኔዎች ለማስፈጸም የሲኖዶስ ቋሚ ተጠሪ መሆኑንም አያይዘው አውጀውልናል። አሁን እንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ከማኅበር ጣሪያ በላይ ወጥቷል። ከእንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ድስት ያላጠለቀ ሲኖዶስ ነው ማለት ነው። በንግግር መሳት ካልቀረ እንደእነ አቡነ ማትያስ ጭልጥ ብሎ መንጎድ እግዚአብሔር ሲኖዶስን ይጠብቃል፤ ሥራውን ሁሉ ያከናውናል እስኪባል ድረስ የሲኖዶስ ጣዖት ሆኖ ማኅበረ ቅዱሳን ይቀጥላል ማለት ነው።
እነሱው በሰጡህ ፈቃድ መሠረት የሲኖዶስ ጠባቂ ማኅበረ ቅዱሳን ሆይ እነዚህን ጳጳሳት ጠብቅ፤ ከፍ ከፍም አድርጋቸው!!! እንላለን።
ሌላው ሊቀ ጳጳስ ደግሞ አባ ገብርኤል ናቸው። በመሠረቱ አባ ገብርኤል ከሲኖዶሱ ይልቅ በማኅበረ ቅዱሳን እንደሚታመኑና እንደሚመኩ ይታወቃል። አባ ገብርኤል ወደ ምድረ አሜሪካ ኰብልለው በመሄድ ኢህአዴግ ይውደም፤ አባ ጳውሎስ ይውረዱ በማለት የፖለቲካ ሰልፍ ሲመሩ እንደነበሩ መረጃዎቻችን ያሳያሉ። ከዚያም በድርድር ይሁን በእርቅ ለጊዜው በማይታወቀው ምክንያት ግሪን ካርዳቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ በሁለት ዜግነት መግባታቸውን ደግሞ አየን። በእርግጥ ሰው ከስህተቱ ቢታረም አያስገርምም። አባ ገብርኤልን ስንመለከት ከስህተት የሚማሩ አይመስሉም። ዛሬ ደግሞ የዳቦ ስሙን ላወጡለት ማኅበር እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ።
«የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይናጋ “በወርድም በቁመትም መሥራቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል»  ማኅበረ ቅዱሳን ያስፈልጋል ይሉናል።ኧረ ለመሆኑ  የቤተክርስቲያኒቱ አንድነት እንዳይናጋ፤ በወርዷም፤ በቁመቷም ለመስራት አልነበረም እንዴ አባ ገብርኤል ጵጵስና የተሾሙት?  በተሰጣቸው ጵጵስና መስራት ካቃታቸው ለሰጠቻቸው ቤተክርስቲያን መመለስ እንጂ ቤተክርስቲያንን እንዲመራ ውክልና ለሌለው ማኅበር ከወርድ እስከቁመቷ እንዲያዝባት እነሱ ደግሞ በተራቸው አሳልፈው እንዴት ይሰጣሉ?
ሲኖዶሱ ከመንበረ ፓትርያርክ አንስቶ እስከ ገጠሪቱ የሳር ክዳን አጥቢያ ድረስ መዋቅሩን የዘረጋው በወርዷም፤ በቁመቷም ለመሥራት አይደለም እንዴ?   አባ ገብርኤል ግን ያቃተቸው ይመስላል። ይልቁንም እኛ ስራውን ሁሉ ለማኅበረ ቅዱሳን እናስረክብና በወርዷም፤ በቁመቷም እሱው ይዘዝባት እያሉ አዋጅ ማስነገር ይዘዋል። አባ ገብርኤልስ የሌላ ሀገር ዜግነት ስላላቸው ነገር ዓለሙ መበላሸቱን ሲያዩ እብስ ብለው ወደ ጥንት የሰልፍ ሀገራቸው አሜሪካ ሊሄዱ ይችላሉ! ማኅበረ ቅዱሳን እንኳን በወርድ በቁመቷ፤ አንዲት ጋት በቤተክርስቲያን ላይ የማዘዝ መብት የለውም የሚሉ የቤተክርስቲያን ልጆችንስ ጅቡ ማኅበር ይዋጣቸው ማለት ነው?
እስከሚገባን ድረስ የቤተክርስቲያኒቱ ራስ እግዚአብሔር ነው። አንዳንድ ጳጳሳት ጠባቂያችን ማኅበረ ቅዱሳን ቢሉም እስከሚገባን ድረስ የሲኖዶሱ ጠባቂ መንፈስ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔርን ራስ አድርጎ ሲኖዶሱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና መገለጥ ቤተክርስቲያንን በወርድና በቁመቷ ይመራታል እንላለን። ከእነ አባ ገብርኤል የተገኘው አዲስ ግኝት ግን በወርድና በቁመቷ ለመሥራት ሥልጣኑ የማኅበረ ቅዱሳን ሆኗል። አባ ገብርኤል ፓትርያርክነቷ ተወርውራ እኔ ጋር ትደርሳለች ብለው አስበው ይሆን?
አንድ ጊዜ ሥልጣናቸው ተገፎ አቶ ኢያሱ የተባሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግመው ኮብልለው የፖለቲካ ሰልፍ ሲመሩ የነበረ፤ በኋላም ተመልሰው የወደዷቸውን ጸረ ኢህአዴጎችን ከአሜሪካ ከድተው ፤ የጠሉትን ኢህአዴግን ወደው፤ የጽዋውን ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳንን አነግሳለሁ እያሉ በአደባባይ በማወጅ የተጠመዱና በአንድ ቦታ በአንድ ቃል የማይረጉ አባ፤  እንኳን ፓትርያርክ ሊመረጡ ለእጩነትም ሊቀርቡ ተገቢ አይደለም። መጽሐፍ  «በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል» ይላልና። አባ ገብርኤል ለምንም ሹመት የሚበቁ አይደሉም እንላለን። « ሆያ ሆዬ ጉዴ ፤ብሯን ብሯን ይላል ሆዴ» እንደሚሉት የሆያ ሆዬ ጫወታ የእሳቸውም ሆድ ቁንጮዋን መጨበጥ ስለሆነ ሆዳቸውን እየቆረጠ እንዳይቸገሩ ቁርጣቸውን ማሳወቅ ተገቢ ነው።

በስተመጨረሻ የሰማነው ቃል ደግሞ ከቄስ ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁን ንግግር ነው። ቄሱ በመቀሌ ሥራ አስኪያጅ ሳሉ የነበራቸውን አድራጎት የዓይን ምስክሮችና የቅርብ ሰዎች ከአስገራሚ ትረካዎች ጋር ሲነግሩን ሰምተን ተደምመናል። ቤተክርስቲያን መቸም ጉድ መሸከም አይከብዳትምና ስለቄሱ የሰማናቸው እንዳሉ ሆነው  ዛሬ ደግሞ ስለማኅበረ ቅዱሳን ጉድ ወደመናገር ተሸጋግረዋል።
እኚህ ቄስ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። ምናልባት ማኅበሩ እየተጠናከረና የስለላ መዋቅሩን እያስፋፋ በመምጣቱ የቄሱን ሕይወት ታሪክ በእጁ ማድረጉ ስለማይቀር አቋሜን ለውጬ ደጋፊ ልሁን ከሚል የስነ ልቦና ግፊት የተነሳ ሊሆን ይችላል አሁን ስለዚህ ማኅበር ቅዱስነት አዋጅ ነጋሪ እስከመሆን የደረሱት። በስንት ሱባዔ እንደተገለጸላቸው አልነገሩንም እንጂ ድሮ ማኅበሩን ሳላውቀው እንደዚህ አይመስለኝም ነበር ይሉናል። ከመቀሌ እስከ አዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅነት ሲሰሩ ለዓመታት ያልተገለጸላቸው ማኅበር አሁን ምን አዚም ቀብቷቸው ይሆን እንዲህ የማኅበሩ ብርሃን የበራላቸው? አንዳንድ ጊዜ ትላልቅ የሚባሉ ሰዎች ውሸት ሲናገሩ ውሸቱ የሚታወቅባቸው አይመስላቸውም። እውነቱ ግን ቄስ ኃ/ሥላሴ ድሮም ሆነ አሁንም ማኅበረ ቅዱሳንን አሳምረው ያውቁታል። አሁን ያለው ልዩነት የአቋም ለውጥ ነው። ሰው አቅሙን አይቶ የአቋም ለውጥ ማድረጉ ባልከፋ፤ ነገር ግን ማኅበሩን በጣም እንደሚወዱት ማረጋገጫ ለመስጠት በየሄዱበት መቀባጠር ቢያስገምት እንጂ ሐቀኛ አያሰኝም። እንዲህ ማለታቸውን አሁን ሲያዩት ኅሊና ካላቸው ራሳቸውን ያሳፍራቸዋል።
«ማኅበሩን መደገፍ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንደኾነ»
እስኪ ይታያችሁ! ማኅበረ ቅዱሳንን የማይደግፉ እልፍ አእላፋት የቤተክርስቲያን ልጆች አሉ። ታዲያ እነዚህ ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳንን ስላልደገፉ ቤተክርስቲያንን አላገለገሉም ማለት ነው? ማኅበረ ቅዱሳን በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የራሱ ዓላማና እቅድ ኖሮት የሚንቀሳቀስ ማኅበር እንጂ የቤተክርስቲያኒቱ ጠቅላላ እስትንፋስ የሆነ ያህል ማኅበረ ቅዱሳንን መገደፍ እንዴት ቤተክርስቲያንን ማገልገል ሊሆን ይችላል? ቤተክርስቲያኒቱ ያለማኅበረ ቅዱሳን ሕያው ናት። ማኅበረ ቅዱሳን ግን ያለቤተክርስቲያኒቱ ከባሕር የወጣ ዓሳ ነው። ታዲያ በምን ስሌት ነው ማኅበሩን መደገፍ ቤተክርስቲያንን ማገልገል የሚሆነው? ማኅበረ ቅዱሳን በቤተክርስቲያኒቱ ስም ከብሯል፤ ሀብት አፍርቷል። ለቤተክርስቲያኒቱ ከሕውከት ውጪ የሰጣት ቤሳ ቤስቲን የለም።
ኧረ እባካችሁ፤ ሁለት ጸጉር ካበቀላችሁ በኋላ ለምትናገሩት ቃላት ምርጫ ይኑራችሁ። ውሸት ጥሩ ባይሆንም መልክ አብጁለት። ደግሞስ ምን ለማትረፍ ነው ይህ ሁሉ መወሻከት ? አቤት ዘመን! ይህም አልፎ በነበር የምንዘክርበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል።
ማጠቃለያ፦
ጳጳሳቱም ይሁን  ቀሳውስቱ ማኅበረ ቅዱሳንን ቅዱስ፤ ቅዱስ እያሉ ቢያሞካሹት እሱና ቅድስና ከስም በስተቀር የትም አይተዋወቁም። ማኅበሩ የዚህ ተፈጥሮም የለውም። ማኅበረ ቅዱሳን ብቃቱ በሰዎች ድካምና ኃጢአት የመጠቀም፤ ጠንካሮችን በመደለል የማስነፍና አገልጋይ የማድረግ ችሎታ፤ በለሰለሰና መንፈሳዊ ሽፋንን በተላበሰ ዘመናዊ ንግግር አጃጅሎ በቁጥጥር ስራ ማዋል፤ በጥቅም ማሸነፍ፤ መንፈሳዊ ሆኖ ለመገኘት የራሱን መንገድ በመምረጥ ሁሉም በሰራው መንገድ እንዲነጉዱ ማድረግ፤  ካልተመቸው እምቢ ማለት ማመጽ፤ ተንኰልና አዋጪ ስልቱን መንደፍ፤ መዋሸት፤ማታለል እስከዛሬ የተጓዘባቸው ስልቶቹ ናቸው።
ከዚያ ባሻገር ሲኖዶስን ጠብቅ፤ በወርድና በቁመት አንተ እዘዝ፤ አንተ ብትገባብን ሰላም ይሰፍናል ወዘተ ንግግሮች ሰዎቹ ስለማኅበሩ እውነት መናገራቸውን ሳይሆን የሚያሳየው ሰዎቹ ማኅበሩ ምን ያህል እንዳሰከራቸው የሚያረጋግጥልን እውነታ ነው። በማኅበረ ቅዱሳን ፍቅር የሰከሩ ሰዎች የቱንም ያህል ቢናገሩለት ማቅ የእውነት ሁሉ ጠላት እንጂ ከእውነት ጋር መስማማት የሚችል ድርጅት አይደለም።
ሌላው አሳፋሪው ነገር የውጪውን ሲኖዶስ የማስማማት ብቃት አለው የሚለው ማጃጃያ ነው። ብጹእ አቡነ መልከ ጼዴቅን መናፍቅ የሚልና የሚያስብል ድርጅት ዛሬ ተነስቶ «ብጹእ አባታችን» ብሎ በአክብሮት እንደሚጠራ መጠበቅ ጅልነት ነው። በየሚዲያው የፓትርያርኩ ድምጽ የታለ እያለ የሚያላዝነው የአቡነ መልከ ጼዴቅን ስምና ዓይን ለማየት ካለመፈለግ የተነሳ ካልሆነ በስተቀር አቡነ መርቆሬዎስ ለማኅበሩ ጩኸት ምላሽ ለመስጠት አቤት ወዴት! የሚሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ወሳኙ ነጥብ ለማኅበረ ቅዱሳን የሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ ሳይሆን እርቁ እውነት ሆኖ ቢፈጸም በእርቁ መካከል የእሱን አለመጎዳት በማረጋገጥ ተጠቀሚነቱን ማስቀጠል መቻል ነው።
ስለዚህም ከአሜሪካው ሲኖዶስ የማኅበሩ ህልውና ቀጣይ ስለመሆኑና ምንም ዓይነት ተቃውሞ እንደማይቀርብበት ማረጋገጫ እስካላገኘ ድረስ በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል ለሚደረገው እርቅ ቅንጣት ታህል ሚና መጫወት አይፈልግም።
የውጪው ሲኖዶስ ራሱን ለማኅበረ ቅዱሳን ለማስገዛት ከፊቱ ቃልኪዳን የመግባት ግዴታ ይጠብቀዋል። ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን ግዴታ በእርቁ ውስጥ ለመጨመር ከላይ ያቀርብናቸው ጳጳሳት ማኅበሩንና ሲኖዶሱን አንድ አድርጎ የማቅረብ ድምጽ ከምንም በላይ አረጋጋጭ ነው። የሲኖዶሱ ጠባቂ ማኅበረ ቅዱሳን ነው ማለት ለውጪው ሲኖዶስ ምን ማለት ይሆን?
ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም እንደተባለው ከሀገር ውስጡ ሲኖዶስ ጳጳሳት ገና ብዙ ጉድ እንሰማለን።