Tuesday, December 17, 2024

ኪዳነ ምሕረት ኢየሱስ ነው!

ኪዳነ ምሕረት ኢየሱስ ክርስቶሰ ነው! ከዚህ በላይ የሚታየው ስእል የጣኦት አምላኪዎች እንጂ የሌላ የማንም ስእል አይደለም። በጣኦት አምላኪዎቹ ልብ ሰይጣን ያስቀመጠው ትርጉም እንደምንገምተው ልጅ እግሩ ሰው የኢየሱስ፣ ሽማግሌው ደግሞ የአብ መሆኑ ነው። በእግዚአብሔር መንግስት ሦስት ምስሎች በአኀዝ የሚቀመጡበት ወይም በወጣትና በሽማግሌ የሚመሰልበት መለኮታዊ ማንነት የለም። ከእግዚአብሔር ያልሆነ የሰው ልብ ያመነጨው ስእል ሁሉ ከተመለከ፣ ከተወደሰ እሱ ጣኦት ነው የሚባለው። “እንዳትረክሱ፥ የተቀረጸውን ምስል የማናቸውንም ነገር ምሳሌ፥ በወንድ ወይም በሴት መልክ የተሠራውን፥” (ዘዳግም 4፥16) አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ምሕረትና ይቅርታ የአዳም ልጆች እንዲያገኙ ለማንም ኪዳን አልሰጡም። መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ልጆች የምሕረትን ኪዳን ሞታችንን ከሞተልን ከኢየሱስ በቀር ለፍጡራን እንደሰጡ አንድም ቦታ ተጽፎ አናገኝም። “ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።” ነው የተባለው። (ይሁዳ 1፥25) እውነቱ ይህ ከሆነ የመዳን ኪዳን ያገኘነው እንዴት ነው? ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ፣ የሥርየት ቃል ድምዳሜ ወይም ፍጻሜ ማለት ነው። ምሕረት የማይገባው ጥፋተኛ፣ በምሕረት አድራጊው እቅድ ከእዳ፣ ከበደል፣ ከወንጀል ነጻ አድርጌሃለሁና የነጻነትህን አዋጅ በዚህ ደብዳቤ አረጋግጬልሃለሁ ብሎ የሚሰጠው የአርነት ሰነድ ነው። የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ወደሆነው ዝርዝር ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ራሱ "ኪዳን" የሚለው ቃል ምንን ያመለክታል የሚለውን ለመመልከት እንሞክር! ውል በሁለት ተዋዋይ ወገኖች መካከል በቃል ወይም በፅሑፍ የሚደረግ አሳሪ ሕግ ነው። በውሉ ላይ ተዋዋይ ወገኖችን መብትና ጥቅም በማካተት የሚደርሱበት ስምምነት ሲሆን መሠረታዊው የውል አስፈላጊነት ጥቅምንና መብትን ለማስከበር መርህ አድርጎ የሚነሳ ቢሆንም ውል ሁልጊዜ አዋጭ ወይም ዘላቂ ላይሆን ይችላል። ውል በዓለማችን ላይ እየተሠራበት ያለው የተዋዋይ ወገኖች አሳሪ ስምምነት ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ኪዳን በጣም የተለየ ነው። የእግዚአብሔር ኪዳን ወይም (Covenant) በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የሚደረግ የአቻ ስምምነት አይደለም። ኪዳን ማለት በጥሬ ትርጉሙ ውል:ስምምነት ቢሆንም ኪዳኑ በምድር ላይ ሰዎች እንደሚያደርጉት በሁለት እኩል ተዋዋይ ወገኖች መካከል እንደተደረገው አይደለም። በውል ሰጪ(በእግዚአብሔር) እና በውል ተቀባይ (በሰው ልጆች) መካከል የተደረገው ኪዳን እግዚአብሔር መብትና ጥቅሙን ለማስከበር ወይም ከሰው ልጆች የሚያገኘው የተለየ መብት እንዲጠበቅለት የተደረገ ኪዳን ሳይሆን እግዚአብሔር በባህርይው ፍቅር ስለሆነ የጠፋውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ በክንዱ ተጠብቆ እንዲኖር ሲል እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለፀበት መንገድ ነው። ሌላውን ወገን የሚጠቅም ኪዳን ማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር የሚገባው ኪዳን አምላክነቱን አስገድዶ ለመጫን ሳይሆን ጌትነቱን ለተቀበሉት ሁሉ ከአምላክነቱ በረከት እንዲትረፈረፍላቸው ከፍቅሩ የተነሣ የሚደረግ ኪዳን ነው። “በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው።” (ኢሳ 63፥9) እግዚአብሔር አዳምን የፈጠረው ማንንም ሳያማክር ከአምላካዊ ክብሩ ሕያውነት እንዲካፈልና በዘላለማዊ ፍቅሩ እንዲኖር ነው። “ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። (1ኛ ዮሐ 4፥10) ለአዳም የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ያሟላለት በአዳም ጥያቄ አልነበረም። እንዲያውም አዳም የተፈጠረው የአምላክን ባሕርይ ተካፋይ እንዲሆን፣ ክብሩ በሱ እንዲታይ በአርአያውና በምሳሌው ነው። እግዚአብሔር ከፈጠረውና ገዢ እንዲሆን በፍጥረቱ ላይ ካሰለጠነው ከአዳም ጋር የገባው ኪዳን ከሰጠሁህ እልፍ አእላፍ ፍጥረት መካከል ይሄን አንዱ ከበላህ ሞትን ትሞታለህና እንዳትበላው የሚል ትእዛዝ ነበር። አዳም ሞትን የሞተው ባልተነገረውና በማያውቀው ነገር ሳይሆን ራሱ ሞትን በመምረጡና የእግዚአብሔርን ድምጽ በመጣሱ የተነሳ ነው። ይህ የመጀመሪያ ኪዳን የፈረሰው ውል ተቀባዩ ውሉን በማፍረሱ ስለሆነ ውሉ የሚያስከትለው ቅጣት በአፍራሹና በልጆቹ ላይ ሞት ተግባራዊ ሆኗል። ከአዳም ውል አፍራሽነት በኋላ እግዚአብሔር ከአዳም ልጆች ጋር የገባው ሌላኛው ኪዳን ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ በኮሬብ ተራራ ነው። ልቅሷችሁንና ጩኸታችሁን ሰምቻለሁ ከባርነት አወጣችኋለሁ፣ ወተትና ማር የምታፈስ ሀገር አወርሳችኋለሁ ብሎ በታላቅ ድንቅና ተአምራት ከግብጽ ከወጡት እስራኤላውያን ጋር ያደረገው ኪዳን ኮሬብ ላይ ተገልጿል። (ዘጸ19፣4—5) ❝በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤❞ ብሏል። ይህ ኪዳን ዘላለማዊው ኪዳን እስኪፈጸም ድረስ በምድራዊ ርስት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከሌሎች ለይቶ የሚያቆይበት የኪዳን ሕግ ተሰጥቶ ነበር። እግዚአብሔር ከመረጠው፣ ራሱ ከሚመራው፣ የተሻለ ሀገር አወርስሃለሁ ካለው ከዚህ ሕዝብ ጋር ኪዳን አደረገ። ይህ ኪዳን እግዚአብሔር የመረጠው ሕዝብ ከአህዛብ የሚለይበት፣ ደግሞም ከእግዚአብሔር ጋር በድምፅና በመልእክት የሚገናኝበት የሕግ ኪዳን ነበር። በአድርግና አታድርግ የተሠጠው የኪዳኑ ስምምነት በተጻፈው የጽሌ ሠሌዳ ላይ እንዲህ የሚል ተፅፎበት እንመለከታለን። 1/ ከኔ በስተቀር ሌሎች አማልክት አታምልክ፣ 2/ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ፣ 3/ የሰንበትን ቀን አክብር፣ 4/ እናትና አባትህን አክብር፣ 5/ አትግደል፣ 6/ አታመንዝር፣ 7/ አትስረቅ፣ 8/ በሀሰት አትመስክር፣ 9/ የባልንጀራህን ገንዘብ አትመኝ፣ 10/ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚል የኪዳን ሕግ ነበረ። ይህ ኪዳን ይጠበቅ ዘንድ የሚከናወንበት መንገድ የኃጢአት፣ የደኅንነት፣ የሚቃጠል መስዋዕት በማቅረብና ትዕዛዛትን በመጠበቅ ነበር። “እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል፤” ( ዘዳግ 7፥12) ይህ ሕግና ትዕዛዛቱ ምድራዊ ሥርየትን ያስገኝለታል እንጂ አዳም ትቶ ወደወጣበት ገነት መልሶ የሚያስገባ አልነበረም። ይህንን በእግዚአብሔር ቁጣ የተዘጋውን የገነት በር መልሶ በመክፈት አዳምንና ልጆቹን ማስገባት የሚችል ከሰው ልጆች አንድም ሰው ስላልነበረ በሌዊ ወገን በሚሾሙ ካህናት በኩል ደም በመርጨት ጊዜያዊ ሥርየትን እያገኙ እስከአማናዊ የተሻለ ኪዳን ድረስ ለመቆየት ችለዋል። ምክንያቱም ሰው በጥፋት ሥራው የተረገመ በመሆኑና ምድርም በተረገመው ሰው ምክንያት የተረገመች በመሆኗ ከሰው ልጆች መካከል ከእርግማን ነጻ የሆነ ሰው ስላልነበረ ዘላለማዊ ድነት ማስገኘት የሚችል አንድም ጻድቅ አልነበረምና ነው። “አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤” (ዘፍ 3፥1) እግዚአብሔር ሌሎች ንዑሳን ኪዳናት ከወደዳቸው ጋር ኪዳን አድርጓል። ከኖኅ ጋር በቀስተ ደመና (ዘፍ9፣11-12)፣ ከሙሴ ጋር (ዘጸ34፣27)፣ ከአብርሃም ርስቱን ሲሰጠው(ዘፍ15፣28)፣ የቁልፈታቸው ግርዛት እንዲወድቅ (17፣11)፣ ከይስሐቅ (ዘፍ17፣19)፣ ከያዕቆብ (ዘፍ35፣10-15)፣ ከዳዊት ጋር (ኤር33፣17) ኪዳን አድርጓል። ይህ ኪዳን በዘመናቸው እግዚአብሔርን ለታዘዙበትና ለፈፀሙበት ፍቅር የተነገረላቸው የመኖር ኪዳን እንጂ የአዳምን በደል የሚሽር ወይም ለሰው ልጆች የዘላለም ሕይወትን የሚያስገኝ ኪዳን አልነበረም። “የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትጠብቅ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል።” (ዘዳ 28፥9) እግዚአብሔር የምወደው ልጄ... ያለው ከሰማይ ከወረደው በስተቀር ወደሰማይ የወጣ የለም የተባለለት ባለሙሉ ሥልጣን ዘላለማዊ ሊቀካህን፣ በደሙ በሰማያዊቷ መቅደስ የገባ ኢየሱስ ብቻ ነው። ሞትን አሸንፎ በሞት የተሸነፉትን ሁሉ ከምርኮ ነፃ ማውጣት የቻለ ከኢየሱስ በቀር ማንም የለም። ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልዕክቱ እንዲህ ሲል አስረግጦ ይነግረናል። (ኤፌሶን 4፣8-10) ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው። ይህ ኪዳን፣ አዲስ ኪዳን፣ የሕይወት ኪዳን ይባላል። አብ በአዳም ልጆች ላይ የነበረውን ቁጣ ያበረደበት፣ የተወደደ መስዋዕት፣ በደሙ በኩል ዘላለማዊ የማዳን ሥርየት የተፈፀመበት ኪዳን ይህ ነው። “እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።” ( ዮሐ 6፥47 ) ከዚህ ኪዳን ውጪ እግዚአብሔር ሌላ ኪዳን የለውም። “ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤” (ሮሜ 5፥10) ከዚህ የምሕረትና የይቅርታ ኪዳን ውጪ እግዚአብሔር የተቀበለውና ደስ የተሰኘበት ሌላ ኪዳን የለም ብቻ ሳይሆን ይሄንን ኪዳን ማሟላት የሚችል ከሰው ልጆች መካከል አንድም ሰው አልነበረም። ቢኖርማ ኖሮ ኢየሱስ ሰው ሆኖ መወለድ ባላስፈለገው ነበር። ስለዚህ ለሰው ልጆች የተሰጠ የምሕረት ኪዳን ኢየሱስ ብቻ ነው። ሌላ ኪዳነ ምሕረት የለም! ይህንን ኪዳን የሚተካ፣ ማዳን የሚችል፣ አብ የወደደው መስዋእትና የምወደው ልጄ ያለው ከኢየሱስ በቀር ማንም ስለሌለ ኪዳነምሕረት በማለት በቅድስት ማርያም በኩል ዘላለማዊ ድነት አገኛለሁ በሚል ተስፋ ወደ ማርያም የሚለምን ሁሉ ከሕይወት ኪዳን የጎደለ፣ እግዚአብሔር የሰጠውን የመዳን ኪዳን ያቃለለ ሰው ነው። ድንግል ማርያም ቅድስትና ብፅእት እንጂ እግዚአብሔር አብ የምሕረቴን ኪዳን በሷ በኩል አድርጌአለሁ ብሎ ኪዳን የሰጠበት ሁኔታ የለም።አንዳንዶች በማርያም ጉዳይ ስለጥንተ አብሶ (የቀደመ በደል) እያነሱ ጉንጭ አልፋ ክርክር ሲያደርጉ ይታያሉ። ይሄ የማይረባ ክርክር ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ መምጣት ድረስ ለሰው ልጆች ሁሉ ገነት ተዘግታበት ይኖር ነበር። በገነት የሌለ ሰው ሁሉ በደለኛ ነው። በሕይወት አኗኗሩ ጻድቅና ንፁህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከገነት ውጪ ስላለ በደለኛ ነው። በአጭሩ በኪሩብ የምትጠበቀው ገነት የተዘጋበት የሰው ልጅ ሁሉ በደለኛ ነው። እንዲያውም ብፅእት ማርያም ራሷ ነፍሷ ጌታን እንደምታከብር፣ መድኃኒቷም እንደሆነ እንደዚህ በማለት መስክራለች። “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤” (ሉቃስ 1፥47) እግዚአብሔር የብሉይን (አሮጌውን) ኪዳን ከተመረጡት ከእስራኤላውያን ጋር፣ አዲሱን ኪዳን በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ካመኑት ጋር የሕይወትን ኪዳን አድርጓል። ሌላ ከማንም ጋር የማዳን፣ የሕይወት ኪዳን አላደረገም። “ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐ 14፥6) ኪዳነ ምሕረት ኢየሱስ ነው!

Saturday, November 9, 2024

ስለሸኮናው ድፍንና ቅድ ክርክር መነሻው ከኦርቶዶክስ አጠቃላይ የወንጌል እውቀት ችግር የሚመነጭ ነው!

አባ በርናባስ የተባሉ ሊቀጳጳስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮና በምእመናኖቹም ቅቡል የሆኑና እንደጽዩፍ የሚቆጠሩ የአህያና ተመሳሳይ እንስሳትን ጉዳይ አንስተው በሐዲስ ኪዳን ትምህርት ክልክል እንዳይደሉ ለማብራራት ሞከረዋል። ምሁርና ሊቅ ነኝ ባይ መንጋው የአቡኑን ትምህርት ለመቃወም ከዳር ዳር ለመጮህ አንካሳ ዶሮ አልቀደመውም። ከአፉ ለሚወጣው መራር ቃላት ግድ የሌለው መንጋ ስለአህያ ሥጋ ርኩሰት ለመናገር የቸኮለው የጽድቅ ጉዳይ አንገብግቦት ሳይሆን እንደፈሪሳውያን ሕጋችን ተነካ ከሚል አጉል ተመጻዳቂነት የመነጨ ነው። ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ችግርና ኦርቶዶክስ እንደቤተ ክርስቲያን በውስጧ ሌባና ማጅራት መቺ አመራር፣ በውጪ ደግሞ በሰሜን የትግራይ፣ በመሐል የኦሮሚያ፣ በጎጃም የቅባት ወዘተ ሲኖዶስ እየተባለ ሊበታትናት ጎራ የለየበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ የአህያ ሥጋ ይጣፍጣል! ወይስ ይመራል! ብሎ ለመከራከር መራኮቱ የሚያሳየን ቤተ ክርስቲያኒቱ በአዚም፣ በድንዛዜ ውስጥ እንዳለች አመላካች ይመስለኛል። ከዚህ ድንዛዜ የሚያወጣ ያልተጠበቀ መለኮታዊ ኃይል ካልደረሰላት በስተቀር ቤተክርስቲያኒቱ እንደሥጋ ደዌ በሽታ እየፈራረሰች ማለቋን የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያየ ያስተውላል። የዚህ ታሪክ ጸሐፊ ከ10 ዓመት በፊት ስለቤተ ክርስቲያኒቱ አደጋ በሰፊው ጽፎ ነበር። ይህንን ሊንክ ከፍተው ያንብቡ! 1/ለውጥ አንድ 2/ለውጥ ሁለት 3/ለውጥ ሦስት 4/ለውጥ ዐራት 5/ለውጥ አምሥት ወደተነሳንበት ርዕስ እንመለስ! ለመሆኑ አህያ፣ ፈረስ ወይም አሳማ፣ ሸኮናው ድፍን፣ሸኮናው ቅድ፣ የሚያመሰኳ፣ የማያመሰኳ ይበላል፣ አይበላም ያለው ማነው? ኢትዮጵያ በሲና ተራራ ላይ ኪዳን የተገባላት የኪዳን ሀገር ናት ወይ? ብለን እንጠይቅ። መልሳችን አይደለችም ይሆናል። ኢትዮጵያ ከግብፅ፣ ከሱዳን፣ ከየመን ወይም ከሶሪያ የተለየች የኪዳን ሀገር አልነበረችም፣ አይደለችምም። ሙሴ የሕጉን ኪዳን በሲና ተራራ ላይ ከተቀበለበት አንስቶ በሰሎሞን ቤተመቅደሱ እስከታነፀበት ድረስ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ለ500 አመታት ያህል በጣኦትና በፀሐይ አምልኮ ስር እንደነበረች ታሪክ ይነግረናል። ታዲያ ባልኖረችበትና በሌለችበት ረጅም የእንቅልፏ ዘመን ውስጥ ልክ የብሉይ ኪዳንን ሕግ ተቀብላ ስትተዳደርበት የነበረች አድርጋ ስለሸኮና ድፍንና ቅድ የኦሪት ሕግ ለማውራት የሚጠይቃት የተለመደ ድፍረቷን እንጂ እውቀቷን አይደለም። ሲጀመር ከእግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የተሰጠ የኪዳን ሕግ የለም። ሕግ ሁሉ ለእስራኤል ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እውነት ይህንኑ ነው። “ነገር ግን እናንተን፦ ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ትወርሱአትም ዘንድ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣችኋለሁ አልኋችሁ። እኔ ከአሕዛብ የለየኋችሁ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ።” — ዘሌዋውያን 20፥24 ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በዚህ ኪዳን ውስጥ ነበረች? ኧረ በጭራሽ! በተረትና እንቆቅልሽ PHD ሲኖርህ እንደዘቤ ደፋሩ የሌለህን እውቀትና ማስረጃ በ"ተረቴን መልሱ፣ አፌን በዳቦ አብሱ" ዘዴ ይሆንን ጎጋ ምእመን ታስጨበጭባለህ። ከየት እንደተማረው ባይነግረንም ከዘበነ ለማ በስተቀር የኦሪት ሕግ ለኢትዮጵያ መሰጠቱን ታሪክ አያውቀውም። ንጉሡ ዳዊትም በመዝሙር እስራኤልን ለርስቱ የተመረጠ ሕዝብ እንደነበረ እንዲህ እያለ ሲዘምር እናገኘዋለን። ዳዊት የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆኖ ያውቃል እንዴ? ዳዊት ለርስቱ እግዚአብሔር የመረጠው ሕዝብ ንጉሥ እንጂ የአህዛብ ንጉሥ አልነበረም። አህዛብ ግን ከእግሩ በታች ተቀጥቅጠው የተገዙ ባሪያዎች ነበሩ። መዝ 47፣3-4 አሕዛብን ከእኛ በታች፥ ወገኖችንም ከእግራችን በታች አስገዛልን። ለርስቱ እኛን መረጠን፥ የወደደውን የያዕቆብን ውበት። ኦርቶዶክስ ወንጌል ገና አልገባትም ስንል በማስረጃ ነው። እሷ ግን 2000 አመቴ ነው ብላ እድሜዋን በመቁጠር የእውቀት ሁሉ ጫፍ እንደደረሰች ልትነግረን ትፈልጋለች። እኛ ደግሞ ድንጋይ ውሃ ውስጥ ለሺህ አመታት ስለኖረ ዋና ይችላል ማለት አይደለም እንላታለን። እድሜ ጥሩ ቢሆንም በራሱ ምሉዕና ባለእውቀት ያደርጋል ማለት አይደለም። የግእዝን ብሂል ስላጠኑ ብቻ የእውቀት ጫፍ የደረሱ የሚመስላቸው የተረት አባቶች ከእውነት እንደተፋቱ ዛሬም አሉ። የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ አህያም። አሳማም፣ አንበጣም አይበላም። የማይበላው የተጠቀሱት ፍጥረታት እንደብሉይ ኪዳን ሕግ አትብሉ ስለተባለ ወይም በሐዲስ ኪዳን አስተምህሮ ርኩሳን እንደሆነ እንደተቆጠሩ ስለተማረ ሳይሆን የመብላቱ ባህልና ልምድ ስለሌለው ነው። እኔ አልበላም ማለት የሚበላ ሰው ቢኖር ረክሷል በሚል ኢ-ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ከማነወር ነጻ ሰው ስለሆነ ነው። ወንጌል እንደሚነግረን “የሚበላ የማይበላውን አይናቀው የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፥ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና።” ሮሜ 14፥3 የኦርቶዶክስ መምህራን ነን ባይ ከእውቀት የተፋቱ የተረት አባቶች በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተምታታ መልስ ሲሰጡ ተዉ እንጂ ብሎ የሚከለክላቸው የለም። ተሳስታችኋል ብሎ የሚያርማቸው ስለሌለ እንደፈለጉት እየተረጎሙ ስለ ሸኮና ቅድ፣ ሸኮና ድፍን፣ የሚያመሰኳ፣ የማያመሰኳ እያሉ ያልተሰጣቸውን ሕግ እየጠቀሱ የረከሰና ያልረከሰ ሕዝብ እያሉ ራሳቸውን ከጻድቃን ጎራ፣ የሚበላውን እንደኃጢአተኛ ፈርጀው ፍርድ ሲሰጡ ድንቁርናቸው አይሰቀጥጣቸውም። በሐዲስ ኪዳን ከልማድና ከወግ ካልሆነ በስተቀር የማይበላ ነገር የለም። 1ኛ ጢሞ 4:4-5 እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና። በዘንዶና በፀሐይ ታመልክ የነበረችው የአህዛብ ሀገር ኢትዮጵያ ያልተሰጣትን ሕግ እየጠቀሰች ቅድና ድፍን የምትለው ተረት ተረት ለእስራኤል የተነገረውን ቃል ወደራሷ እየተረጎመች ካልሆነ በስተቀር በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ውስጥ አህዛብ ማነው? ሕዝብስ? ብለን እንጠይቃታለን። “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤” — ዘጸአት 19፥5 ከእስራኤል ውጪ ያለው ሁሉ አህዛብ ይባላል። አህዛብ ደግሞ የኦሪቱ ሕግ የኪዳን ሕዝብ አካል አይደለም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሌላት የኪዳን ሕግ የሚበላና የማይበላ እያለች ስለኮሼር kosher” (כָּשֵׁר) ሕግ መናገር አትችልም። ከተናገረችም ከድንቁርና የተነሳ ነው። ከእስራኤል ውጪ የነበረው አህዛብ ይባላል። የአህዛብ ሀገር ኢትዮጵያ ስለሕግ ማውራት አትችልም። ከሕጉ ውጪ የነበርነውን እኛን አህዛቦችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕጉን ትእዛዛት ሁሉ ፈፅሞ በሐዲስ ኪዳን ሕግ እንደአዲስ ወለደን። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ፣ “እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤” — ሮሜ 9፥4 ካለ በኋላ ከሕግ መሰጠት ውጪ የነበርነውን እኛ አህዛብን ወደአዲሱ የድነት ሕግ እንዴት እንደገባን እንዲህ እያለ ይነግረናል። "የምሕረቱ ዕቃዎችም ከአይሁድ ብቻ አይደሉም፥ ነገር ግን ከአሕዛብ ደግሞ የጠራን እኛ ነን። እንዲሁ ደግሞ በሆሴዕ፦ ሕዝቤ ያልሆነውን ሕዝቤ ብዬ፥ ያልተወደደችውንም የተወደደችው ብዬ እጠራለሁ፤ እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም በተባለላቸውም ስፍራ በዚያ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ ይላል። (ሮሜ9፣24-26) ሕግን የተከተሉ እስራኤሎች ሕግን በመከተላቸው በእምነት ከሚገኘው ጽድቅ ጎደሉ። እኛ አህዛብ ደግሞ በሕግ ከነበረው ሥርዓት ውጪ ስለነበርን በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በማመን ከሚገኘው ጽድቅ የእምነት ተካፋይ ሆንን። "እንግዲህ ምን እንላለን? ጽድቅን ያልተከተሉት አሕዛብ ጽድቅን አገኙ፥ እርሱ ግን ከእምነት የሆነ ጽድቅ ነው፤ እስራኤል ግን የጽድቅን ሕግ እየተከተሉ ወደ ሕግ አልደረሱም።" ሮሜ9፣30-31 ማጠቃለያ፣ ስለሕግ አፈጻጸም ዛሬ ማንም የመናገር መብት የለውም። ፊተኛውን አስረጅቶ ዛሬ በአዲስ ኪዳን ሕግ ውስጥ ነን። የቀደመችቱ ሕግ፣ ሕጉን ያፈረሰ ምን ይሁን ትላለች? በድንጋይ ተወግሮ ይገደል! ኦርቶዶክስ የቀድሞውን ሕግ በግድ እየተገብራለሁ ካለች ስንት ሰው ደብድባ ልትገድል ነው? አባ ባርናባስ ያስተማሩት እንደወንጌል ሕግ ስህተት ባይኖርባቸውም እንደኦሪት ሕግ አስፈጻሚዋ ኦርቶዶክስ አንድ ቀን የማደር መብት ሊያገኙ አይገባም ነበር። ሕጉ ይገደሉ ስለሚል። ዘቤ ለማ ምትክ አልባው የተረት አባት phd በተረት holder፣ ሄኖክ ኃይሌ በተረቱ ብዛት ምእመናን በባዶ ሜዳ ያሰከሩት ዲያቆን፣ መምህራነ ኮኑ በበደወሉ፣ ፊደላተ ዘኈለቁ ኵሉ የተባለላቸው ተረት ጠምጣሚ ሁሉ በማይመለከታቸውና በማያውቁት የኦሪት ሕግ በግድ ነው የሚጮሁት እውነቱን ስለሚያውቁ ሳይሆን ድንቁርናቸውን እንደባለእውቀት ትውልዱ ስላጸደቀላቸው ነው። የእግዚአብሔር መንግስት አሳማ በመብላት አትጠፋም፣ ባለመብላትም አትገኝም። “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።” — ሮሜ 14፥17 እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና። 1ኛ ጢሞ4፣4-5 ስለዚህ በመብላትና ባለመብላት ራሷን ጻድቅ የምታስመስለው ኦርቶዶክስ ከ2000 ዓመት በኋላም ወንጌል ገና አልገባትም። በግሌ አሳማም፣ አህያም አልበላም። አልበላም አልኩ እንጂ የሚበሉት ተኮንነዋል፣ ረክሰዋልም ማለቴ አይደለም። የሚበሉትን አናረክስም፣ የማይበሉትንም ብሉ ብለን አንሰብክም። ወንጌል ስለመብልና መጠጥ አይደለችምና። አባ በርናባስ ያስተማሩት ምንም ስህተት ባይኖርበትም በመንጋ ለሚነዳ ምእመን ይህንን ማስተማር እንደወንጀል ስለሚቆጠር ስለመብልና መጠጡ ትተው መጀመሪያ ስለወንጌል የመዳን ቃል ይስበኩ። ኦርቶዶክሶች ወንጌልን በግእዝም፣በአማርኛም በልዩ ልዩ ቋንቋ ያነቧታል እንጂ አልተረዷትም! የዘሌዋውያን ሕግ እንኳን በኢትዮጵያ በዛሬይቱ እስራኤል የለም። የሌለውን ሕግ እንዴት አድርጋ ነው ኦርቶዶክስ የምትተገብረው? ዘቤ መልስልኝ። ሕጉ ካልተፈጸመ መውገሪያ ድንጋይህን ይዘሃል ወይ? ለነገሩ አንተ ራስህ የቤተክርስቲያኒቱ መርግ ነህ።

Monday, July 8, 2024

ታቦትና ጽላት ዛሬ የሉም!

ዛሬ ታቦትና ጽላት የሉም! ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በላከው መልእክቱ "ከሚመጣው ቁጣ ትድኑ ዘንድ ራሳችሁን ከጣዖት ወደእግዚአብሔር ዘወር እንዳላችሁ" እያለ የነበሩበትን ከንቱ አምልኮ አራግፈው በመተው እንዴት እንደተመለሱ ሲያስታውሳቸው እናነባለን። ይህንንም አስረግጦ ሲያስረዳ ልትተዉት የሚገባውን እየነገርን፣ ለእግዚአብሔር መታዘዝን እያስረዳናችሁ እንጂ በማባበል ወይም በማቆላመጥ እንዳልነበረ እናንተው ምስክሮቻችን ናችሁ ይላቸዋል። "እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጎምጀት አልሠራንም፤ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም።" (1ኛ ተሰ2:5—6) ይህንን ቃል ዛሬም ያለማቆላመጥ፣ ክብርና ምስጋናን ባለመፈለግ በግልጽ ቋንቋ መናገር ይገባናል። ይኼውም በዚህ ዘመን ከሰማይ በታች ለተለየ ወገን፣ ዘር፣ ትውልድ ወይም በአጠቃላይ የሰው ልጅ ለተባለ የተሰጠ የቀደመችውን የእስራኤላውያን ዓይነት የታቦትና የጽላት ሕግ የለም። አዎ በዚህ ዘመን ትውልድ የሚንበረከክለት፣ የሚሰግድለት፣ ምሥጋናና ውዳሴ የሚቀርብለት፣ እልልታና እምቢልታ የሚነፋለት ታቦትም፣ ጽላትም የለንም! ይልቅስ ዓይናችሁን ሕግን ሁሉ ወደፈጸመው፣ ሕግ ያስከተለው እዳና በደላችንን ቀራንዮ ላይ በሞቱ ጠርቆ ወዳስወገደው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልከቱ። (ቆላስ2:15) ሕግ ካስከተለው ሞት ሕይወት ወደሰጠን ሕያው ታቦታችን ኢየሱስ ተመልከቱ። ይኼን በግልጽ / baldly/ መናገር እውነትን መግለጥ እንጂ ሃይማኖታዊ ስብከት አይደለም። (2ኛ ቆሮ3:3) ምክንያቱም፣ 1/ ታቦትም፣ ጽላትም የተሰጠው ከአህዛብ ለተለየው ለእስራኤል ከሥጋ ነው። (ዘዳ7:6) 2/ ለታቦትም ሆነ ለጽላት የተሰጠ መለኪያ፣ መስፈሪያና ሕግ ዛሬ ላይ የለም። (ዘጸ 25:10—23) 3/ ሙሴ በሰበረው ላይም ይሁን ዳግመኛ በቀረጸው ጽላት ላይ 10ቱን ትዕዛዛት በጣቱ የጻፈው እግዚአብሔር ራሱ ነው። (ዘጸ31:18) (ዘዳ10:4) በእነዚህ ዋና መመዘኛዎች የተነሳ ዛሬ ላይ ታቦትም፣ ጽላትም የለም ብሎ ደምድሞ መናገር ይቻላል። እኛ አለን ብለው የሚከራከሩን ካሉ መልሳችን እሱ ወደእግዚአብሔር የሚደረግን አምልኮ የሚጋርዱ የማመለኪያ አፀዶች ናቸው እንላቸዋለን። (ዘዳ16:21—22) እስራኤሎችም ወደ እግዚአብሔር የሚደረግን አምልኮ የሚያጋሯቸው የማምለኪያ አፀዶችን እየተከተሉ እግዚአብሔርን ያስቀኑ ነበር። የማምለኪያ ቅርጾች፣ ምስሎች፣ ስዕሎች፣ ስግደት የሚቀርብላቸው የሰዎችና የመላእክት ስሞች በሙሉ ከአህዛብ የተወረሱ ሲሆኑ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብን ምሥጋናና ውዳሴ በመጋረድ እነሱም እንዲካፈሉ (share) እንዲያደርጉ በሰይጣን የተፈበረኩ ጣዖታት ናቸው። ለጣዖት አምልኮው መሸፈኛ የሚቀርበው ሞገት እግዚአብሔር ያከበራቸው ስለሆኑ ነው የሚል ቢሆንም ስግደት፣ ምሥጋና፣ ውዳሴ፣ እልልታ፣ ሽብሸባ፣ ቅኔና ዝማሬን አካፍላችሁ ብትሰጡልኝ እኔ በነሱ በኩል እንደደረሰኝ እቆጥርላችኋለሁ ያለበት ጊዜ የለም። አንዳንድ መፍቀሬ ጣዖታት ሰዎች በጻድቅ ስም የተቀበለ የጻድቁን ዋጋ ያገኛል እያሉ አምልኮ አፀዳቸውን ለመከላከል ሲጋጋጡ ይታያሉ። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ የታመነ የእግዚአብሔር ሰው ነበረ ብሎ ማመን ያላየሁትን ጳውሎስ ምስልና ሐውልት ሰርቼ፣ ታቦትና ጽላት ቀርጬ እንድሰግድለት፣ እንድንበረከክለት፣ የዝማሬ፣ የቅኔ ጎርፍ እንዳፈስለት ሊያደርገኝ አይችልም። ምንጩ ያልታወቀው የጳውሎስ ምስል ለክርስቲያን ምኑ ነው? የጳውሎስስ ጽላት መነሻው ከየት ነው? እስራኤሎችን ሲያስቸግር ከነበረው ከማመልከያ አፀድ የሰይጣን መንፈስ የተቀዳ ነው። እግዚአብሔር በእገሌና በእግሊት በኩል የምታቀርቡት ምስጋናና ውዳሴ በተዘዋዋሪ ይደርሰኛልና ቀጥሉበት ሊል የሚችልበት አምላካዊ ባህርይ የለውም። ይልቁንም “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። ”ኢሳ 42፥8 ሲለን እናገኘዋለን። እነዚህ በገበያ ላይ የሚሸጡ የጂፕሰም ምስሎች፣ ቅርጾችና የቀለም ስዕሎችን ግማሽ ክርስቲያኖች እየገዙ ስግደት፣ ጸሎትና ማዕጠንት የሚያቀርቡላቸው ከአምልኮ እግዚአብሔር ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የላቸውም። በአምልኮ ሽፋን የከፍታ ወንበር ላይ የተሰቀሉ ጣዖታት ናቸው። በሰማይ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር እንደተዋጉና ዘንዶውም እንዳልቻላቸው የሚናገረውን የዮሐንስ ራእይ 12:7 መነሻ በማድረግ ጣሊያናዊው ሰዓሊ ጉዊዶ ሬኒ (Guido Reni) በ1635 የሳለውን ስዕል ከገበያ ገዝተው ክርስቲያኖች የሚሰግዱለት፣ በየጥንታውያኑ አብያተ ክርስቲያናት በሱቲ፣ በተንቆጠቆጠ ጨርቅና መብራት በከበረ ቦታ ተቀምጦ፣ ስግደት እየተቀበለ፣ በእጣን እየታጠነ ውዳሴ የሚጎርፍለት ጣዖትን ከማምለክ ውጪ ሌላ ምን ስም ሊሰጠው ይችላል? ጉዊዶ ሬኒ የሰዓሊነት እውቀቱ ያመነጨው እንጂ ከዘንዶው ጋር ስንት የወደቁ መላእክት እንደነበሩና ከሚካኤል ጋር ስንት መላእክት እንደተሰለፉ የሚያውቀው አንዳች ነገር የለም። የወደቀው ባለጡንቻ ወጠምሻው ጥቁር ሰው ሰይጣን መሆኑ ነው? ጥቁር የሆነ ነገርን ሁሉ የሰይጣን መለያ አድርጎ የሰጠው ማነው? የብርሃንን መልአክ ለመምሰል ራሱን መለወጥ የሚችልን ፍጥረት ሁልጊዜም ጥቁር እንደሆነ ማሰብ የእውቀት ጉድለት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እሱም ስዕሉ ወግ ደርሶት በየቤተመቅደሱና ክርስቲያን መሳይ አላዋቂዎች ቤት በክብር ተሰቅሎ እሱም በወደቀበት ስግደትን ይቀበላል። ያ ወደል ወጠምሻ ሰው ወደስዕሉ የሚደረገውን አምልኮ የሚስማማበት ይመስለኛል።
ማጠቃለያ፣ በአዲስ ኪዳን ለእስራኤል ብቻ ተለይቶ የተሰጠው የኪዳኑ ታቦት ዛሬ የለም። "ሥጋና ደሙ የምንፈትትበት ነው" የሚለው ለክህደት የሚቀርብ ምክንያት አምልኮን ከእግዚአብሔር ውጪ ለሌላ በማጋራት ከሚያስከትለው የዘላለም ሞት አያስጥልም። እንደጠረጴዛ እንገለገልበታለን እንጂ እያልክ በፈጠራ ስዕል አሽሞንሙነህ፣ ተሸክመኸው ውጣና ሕዝብን በእልልታና በሆታ፣ እያስጎነበስክ በስግደትና በከንቱ አምልኮ ወደሞት እርድ ንዳው የሚል ፈቃድ የሰጠህ ማነው? ስዕል፣ ምስልና ቅርጽ በየመቅደሱ፣ በየዐውደ በራፉ አስቀምጠህ እያሰገድክበት የገንዘብ መሰብሰቢያ አዚም አድርገህ እንድትጠቀም በልብልህ ላይ ከሰይጣን ውጪ ይሄንን ረቂቅ ተንኮል ያቀበለህ ማንም የለም። ለዚህ ዓይን ያወጣ፣ ከአምልኮ እግዚአብሔር የራቀ ተግባርህ ዋጋ ትከፍልበታለህ። እግዚአብሔር ያጸዳዋል፣ ቆሻሻውን ይጠርገዋል። የኤልዛቤልን ግልሙትና ገፎ እርቃኗን ያስቀረዋል። እግዚአብሔር ከነክርፏቷ የተሸከማት እድሜ ለንስሐ ነበር፣ አሁን ግን ራሱ ወርዶ የገማውን አስወግዶ፣ አዲስ አድርጎ ይሰራዋል!