Monday, July 8, 2024

ታቦትና ጽላት ዛሬ የሉም!

ዛሬ ታቦትና ጽላት የሉም! ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በላከው መልእክቱ "ከሚመጣው ቁጣ ትድኑ ዘንድ ራሳችሁን ከጣዖት ወደእግዚአብሔር ዘወር እንዳላችሁ" እያለ የነበሩበትን ከንቱ አምልኮ አራግፈው በመተው እንዴት እንደተመለሱ ሲያስታውሳቸው እናነባለን። ይህንንም አስረግጦ ሲያስረዳ ልትተዉት የሚገባውን እየነገርን፣ ለእግዚአብሔር መታዘዝን እያስረዳናችሁ እንጂ በማባበል ወይም በማቆላመጥ እንዳልነበረ እናንተው ምስክሮቻችን ናችሁ ይላቸዋል። "እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጎምጀት አልሠራንም፤ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም።" (1ኛ ተሰ2:5—6) ይህንን ቃል ዛሬም ያለማቆላመጥ፣ ክብርና ምስጋናን ባለመፈለግ በግልጽ ቋንቋ መናገር ይገባናል። ይኼውም በዚህ ዘመን ከሰማይ በታች ለተለየ ወገን፣ ዘር፣ ትውልድ ወይም በአጠቃላይ የሰው ልጅ ለተባለ የተሰጠ የቀደመችውን የእስራኤላውያን ዓይነት የታቦትና የጽላት ሕግ የለም። አዎ በዚህ ዘመን ትውልድ የሚንበረከክለት፣ የሚሰግድለት፣ ምሥጋናና ውዳሴ የሚቀርብለት፣ እልልታና እምቢልታ የሚነፋለት ታቦትም፣ ጽላትም የለንም! ይልቅስ ዓይናችሁን ሕግን ሁሉ ወደፈጸመው፣ ሕግ ያስከተለው እዳና በደላችንን ቀራንዮ ላይ በሞቱ ጠርቆ ወዳስወገደው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልከቱ። (ቆላስ2:15) ሕግ ካስከተለው ሞት ሕይወት ወደሰጠን ሕያው ታቦታችን ኢየሱስ ተመልከቱ። ይኼን በግልጽ / baldly/ መናገር እውነትን መግለጥ እንጂ ሃይማኖታዊ ስብከት አይደለም። (2ኛ ቆሮ3:3) ምክንያቱም፣ 1/ ታቦትም፣ ጽላትም የተሰጠው ከአህዛብ ለተለየው ለእስራኤል ከሥጋ ነው። (ዘዳ7:6) 2/ ለታቦትም ሆነ ለጽላት የተሰጠ መለኪያ፣ መስፈሪያና ሕግ ዛሬ ላይ የለም። (ዘጸ 25:10—23) 3/ ሙሴ በሰበረው ላይም ይሁን ዳግመኛ በቀረጸው ጽላት ላይ 10ቱን ትዕዛዛት በጣቱ የጻፈው እግዚአብሔር ራሱ ነው። (ዘጸ31:18) (ዘዳ10:4) በእነዚህ ዋና መመዘኛዎች የተነሳ ዛሬ ላይ ታቦትም፣ ጽላትም የለም ብሎ ደምድሞ መናገር ይቻላል። እኛ አለን ብለው የሚከራከሩን ካሉ መልሳችን እሱ ወደእግዚአብሔር የሚደረግን አምልኮ የሚጋርዱ የማመለኪያ አፀዶች ናቸው እንላቸዋለን። (ዘዳ16:21—22) እስራኤሎችም ወደ እግዚአብሔር የሚደረግን አምልኮ የሚያጋሯቸው የማምለኪያ አፀዶችን እየተከተሉ እግዚአብሔርን ያስቀኑ ነበር። የማምለኪያ ቅርጾች፣ ምስሎች፣ ስዕሎች፣ ስግደት የሚቀርብላቸው የሰዎችና የመላእክት ስሞች በሙሉ ከአህዛብ የተወረሱ ሲሆኑ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብን ምሥጋናና ውዳሴ በመጋረድ እነሱም እንዲካፈሉ (share) እንዲያደርጉ በሰይጣን የተፈበረኩ ጣዖታት ናቸው። ለጣዖት አምልኮው መሸፈኛ የሚቀርበው ሞገት እግዚአብሔር ያከበራቸው ስለሆኑ ነው የሚል ቢሆንም ስግደት፣ ምሥጋና፣ ውዳሴ፣ እልልታ፣ ሽብሸባ፣ ቅኔና ዝማሬን አካፍላችሁ ብትሰጡልኝ እኔ በነሱ በኩል እንደደረሰኝ እቆጥርላችኋለሁ ያለበት ጊዜ የለም። አንዳንድ መፍቀሬ ጣዖታት ሰዎች በጻድቅ ስም የተቀበለ የጻድቁን ዋጋ ያገኛል እያሉ አምልኮ አፀዳቸውን ለመከላከል ሲጋጋጡ ይታያሉ። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ የታመነ የእግዚአብሔር ሰው ነበረ ብሎ ማመን ያላየሁትን ጳውሎስ ምስልና ሐውልት ሰርቼ፣ ታቦትና ጽላት ቀርጬ እንድሰግድለት፣ እንድንበረከክለት፣ የዝማሬ፣ የቅኔ ጎርፍ እንዳፈስለት ሊያደርገኝ አይችልም። ምንጩ ያልታወቀው የጳውሎስ ምስል ለክርስቲያን ምኑ ነው? የጳውሎስስ ጽላት መነሻው ከየት ነው? እስራኤሎችን ሲያስቸግር ከነበረው ከማመልከያ አፀድ የሰይጣን መንፈስ የተቀዳ ነው። እግዚአብሔር በእገሌና በእግሊት በኩል የምታቀርቡት ምስጋናና ውዳሴ በተዘዋዋሪ ይደርሰኛልና ቀጥሉበት ሊል የሚችልበት አምላካዊ ባህርይ የለውም። ይልቁንም “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። ”ኢሳ 42፥8 ሲለን እናገኘዋለን። እነዚህ በገበያ ላይ የሚሸጡ የጂፕሰም ምስሎች፣ ቅርጾችና የቀለም ስዕሎችን ግማሽ ክርስቲያኖች እየገዙ ስግደት፣ ጸሎትና ማዕጠንት የሚያቀርቡላቸው ከአምልኮ እግዚአብሔር ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የላቸውም። በአምልኮ ሽፋን የከፍታ ወንበር ላይ የተሰቀሉ ጣዖታት ናቸው። በሰማይ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር እንደተዋጉና ዘንዶውም እንዳልቻላቸው የሚናገረውን የዮሐንስ ራእይ 12:7 መነሻ በማድረግ ጣሊያናዊው ሰዓሊ ጉዊዶ ሬኒ (Guido Reni) በ1635 የሳለውን ስዕል ከገበያ ገዝተው ክርስቲያኖች የሚሰግዱለት፣ በየጥንታውያኑ አብያተ ክርስቲያናት በሱቲ፣ በተንቆጠቆጠ ጨርቅና መብራት በከበረ ቦታ ተቀምጦ፣ ስግደት እየተቀበለ፣ በእጣን እየታጠነ ውዳሴ የሚጎርፍለት ጣዖትን ከማምለክ ውጪ ሌላ ምን ስም ሊሰጠው ይችላል? ጉዊዶ ሬኒ የሰዓሊነት እውቀቱ ያመነጨው እንጂ ከዘንዶው ጋር ስንት የወደቁ መላእክት እንደነበሩና ከሚካኤል ጋር ስንት መላእክት እንደተሰለፉ የሚያውቀው አንዳች ነገር የለም። የወደቀው ባለጡንቻ ወጠምሻው ጥቁር ሰው ሰይጣን መሆኑ ነው? ጥቁር የሆነ ነገርን ሁሉ የሰይጣን መለያ አድርጎ የሰጠው ማነው? የብርሃንን መልአክ ለመምሰል ራሱን መለወጥ የሚችልን ፍጥረት ሁልጊዜም ጥቁር እንደሆነ ማሰብ የእውቀት ጉድለት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እሱም ስዕሉ ወግ ደርሶት በየቤተመቅደሱና ክርስቲያን መሳይ አላዋቂዎች ቤት በክብር ተሰቅሎ እሱም በወደቀበት ስግደትን ይቀበላል። ያ ወደል ወጠምሻ ሰው ወደስዕሉ የሚደረገውን አምልኮ የሚስማማበት ይመስለኛል።
ማጠቃለያ፣ በአዲስ ኪዳን ለእስራኤል ብቻ ተለይቶ የተሰጠው የኪዳኑ ታቦት ዛሬ የለም። "ሥጋና ደሙ የምንፈትትበት ነው" የሚለው ለክህደት የሚቀርብ ምክንያት አምልኮን ከእግዚአብሔር ውጪ ለሌላ በማጋራት ከሚያስከትለው የዘላለም ሞት አያስጥልም። እንደጠረጴዛ እንገለገልበታለን እንጂ እያልክ በፈጠራ ስዕል አሽሞንሙነህ፣ ተሸክመኸው ውጣና ሕዝብን በእልልታና በሆታ፣ እያስጎነበስክ በስግደትና በከንቱ አምልኮ ወደሞት እርድ ንዳው የሚል ፈቃድ የሰጠህ ማነው? ስዕል፣ ምስልና ቅርጽ በየመቅደሱ፣ በየዐውደ በራፉ አስቀምጠህ እያሰገድክበት የገንዘብ መሰብሰቢያ አዚም አድርገህ እንድትጠቀም በልብልህ ላይ ከሰይጣን ውጪ ይሄንን ረቂቅ ተንኮል ያቀበለህ ማንም የለም። ለዚህ ዓይን ያወጣ፣ ከአምልኮ እግዚአብሔር የራቀ ተግባርህ ዋጋ ትከፍልበታለህ። እግዚአብሔር ያጸዳዋል፣ ቆሻሻውን ይጠርገዋል። የኤልዛቤልን ግልሙትና ገፎ እርቃኗን ያስቀረዋል። እግዚአብሔር ከነክርፏቷ የተሸከማት እድሜ ለንስሐ ነበር፣ አሁን ግን ራሱ ወርዶ የገማውን አስወግዶ፣ አዲስ አድርጎ ይሰራዋል!