Monday, June 10, 2024
ካህን ማነው?
ካህን ማነው?
ካህን የሚለው ግስ ስርወ ቃሉ ዕብራይስጥ ሲሆን ኮሄን כהן (kohen) ከሚለው ቃል የመጣ ነው። አጭር ትርጉሙ "አገልጋይ" ማለት ሲሆን አቅራቢ፣ ሠራተኛ፣ የሚራዳ ማለትንም ያመለክታል። በቅዱስ መጽሐፋችን የመጀመሪያው ካህን የሳሌም ንጉሥ የነበረው፣ ትውልድና ዘር ያልተቆጠረለት መልከጼዴቅ ነበር። (ዘፍ 14:18) እሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነበር። (ዕብ6:20) የመልከጼዴቅ ክህነት በኢየሱስ ክርስቶስ ምሣሌነት የተነገረበት ምክንያት የካህንነት ሹመቱ በነገድ አልተቆጠረም። የኦሪቱ የክህነት ሥልጣን ከሌዊ ነገድ በመወለድ የሚገኝ ቢሆንም ኢየሱስ ግን ሊቀካህን የሆነው ከይሁዳ ነገድ ነው። የኦሪቱ ክህነት ያለመሃላ የሚፀና ቢሆንም የኢየሱስ ክህነት እንደመልከ ጼዴቅ ክህነት በእግዚአብሔር በመሃላ የተረጋገጠ ነው። (ዕብ 7:20—21)
የዚህ ክህነት ዋና ምስጢር በአዲስ ኪዳን ከኢየሱስ በስተቀር በመሃላ እንደመልከ ጼዴቅ ለዘላለም ካህን ነህ ተብሎ የሚሾም ሌላ ካህን የለም ማለትን ያመለክታል። የኢየሱስ የካህንነት ምስጢር ራሱ መስዋእት፣ ራሱ መስዋእት አቅራቢ፣ በአብ የተወደደ መስዋእት ሆኖ በደሙ የዘላለም የኃጢአት ማስተሰሪያ መስዋእት ሆኖልን ስለእኛ ጸንቶ መቆሙን ያረጋግጥልናል።
“እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” (ዕብ 7፥27)
የዚህ በመሃላ የተሾመው ሊቀካህን መስዋእት ወደእሱ የሚመጡትን ነፍሳት ሁሉ የሚቤዥ አንዴ የቀረበ፣ ሕያው የሥርየት መስዋእት ነው።
“ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”(ዕብ 7፥25)
ስለመልከጼዴቅ ከብሉይ ኪዳን የምናነበው ቃል ከአብርሃም ጋር ተገናኝቶ ከመባረኩ በስተቀር በፊት የት እንደነበረ፣ በኋላም ወዴት እንደሄደ የተነገረ ምንም ታሪክ የለም። ይህንን ታሪክ ኢየሱስ ራሱን በዘላለማዊ የማዳን የምልጃው ውስጥ መስዋእት ሆኖ ራሱን ሲገልጥ ብቻ ነው ለማየት የቻልነው። (ዕብራውያን ምዕራፍ 7ን ደግመው ያንብቡ)
ስለዘላለማዊ ሊቀካህን አገልግሎት ስንናገር ይሄንን ሥርዓት ኢየሱስ በራሱ መስዋእትነት የደመደመው ስለሆነ እኛ ክርስቲያኖች ከእንግዲህ ሌላ ምድራዊ ሊቀካህን ዛሬ የለንም። ምክንያቱም የሊቀካህን አገልግሎት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል፣ መካከለኛ አገልጋይ ሆኖ ሥርየትን ማስገኘት ነበር። በኦሪቱ የነበረውን የደም መስዋእት በራሱ ሕያው ሞትና ትንሣኤ ላመኑበት ሁሉ ሥርየትን ስላስገኘ ለክርስቲያን የሚሞትና ቢሞትም ሥርየትን ማሰጠት የሚችል ሰው የለምና ነው። እንኳን ለሌላው የኃጢአት ሥርየት መሆን ይቅርና ራሱን ለማዳን የሚበቃ ማንነት ያለው ሰው በምድር ላይ በጭራሽ የለም። በዚህ ዘላለማዊ ሊቀካህን ሞትና ትንሣኤ ያመንን እኛ በሱ የዘላለም ሕይወትን አግኝተናል።
“እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።”ዮሐ 6፥47
ሌላኛው የክህነት አገልግሎት ያለመሃላ የተሾሙይ የአሮን ዘሮች ነበሩ።
በብሉይ ኪዳን የካህናት ወገን መሆን የሚቻለው ከያዕቆብ ልጆች ሥስተኛ በሆነው ከሌዊ ዘር በመወለድ ብቻ የሚገኝ የአገልግሎት ክብር ነበር።(ዘዳ10:8) ሌዊ ማለት በዕብራይስጥ የተባበረ፣ የተያያዘ፣ የተገናኘ ማለት ነው። ምናልባትም የስሙ ትርጓሜ ከመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ጋር የተያያዘና በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል አገናኝ የሆኑበትን የክህነት አገልግሎት የሚያመለክት ስም ይሆናል። ሌዋውያን የመገናኛው ድንኳን አገልጋዮች ስለሆኑ ከ፲፩ዱ የእስራኤል ነገድ ጋር እንዳይቆጠሩ እግዚአብሔር አዘዘ።
(ዘኁ1:48—49) የሌዋውያን አገልግሎት የምስክሩን ድንኳን መጠበቅ (ዘኁ1:51) ሲንቀሳቀሱ መሸከም (ዘኁ1:53) በማረፊያቸው ደግሞ መትከል ሲሆን አሮንና ልጆቹ ደግሞ የመስዋዕቱን ሥርዓት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማከነወን ነበር። (ዘጸ28:41) በኋለኛው ታሪክ እንደምናነበው ከሌዋውያኑ ወገን የሆኑት አሳፍና ወንድሞቹ ደግሞ በከበሮ፣ በጸናጽል፣ በመሰንቆ ይዘምሩ ነበር። (1ኛ ዜና 15:16—19)
ከክህነት አገልግሎቱ ጋር በተያያዘ ከሌዊ ወገን የሆኑ ካህናት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ልዩ፣ ልዩ የአገልግሎት ድርሻ ነበራቸው። ሕዝበ እስራኤል ሲንቀሳቀስ የመገናኛውን ድንኳን በታዘዘው መሠረት ነቅለው ለሸክም የሚያዘጋጁ፣ የተዘጋጀውን ንዋያተ ቅድሳት ደግሞ የሚሸከሙ፣ በሚያርፉበት ቦታ ደግሞ ከተሸከሙት ተቀብለው በሥርዓቱ ተክለው ለአገልግሎት የሚያዘጋጁ፣ በተተከለው ድንኳን ውስጥ የማስተሰርያ መስዋዕቱን የሚያከናውኑ፣ ተሸክመው ሲሄዱም ሆነ ሲያርፉ በመዝሙርና በመሰንቆ እያሸበሸቡ የሚያገለግሉ መዘምራን ነበሩ። በዚህ የመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ውስጥ ከሌዊ ነገድ የተወለዱት ብቻ በአገልግሎት ተከፍለው በእግዚአብሔር የታዘዙትን አገልግሎት ሲፈፅሙ ኖረዋል። የዚህ ክህነት ባለሙሉ መብት ደግሞ በእግዚአብሔር የተመረጡት የእስራኤል ሕዝቦች ሲሆኑ ከእነርሱም መካከል የሌዊ ዘሮች ብቻ ነበሩ። ከሌዊ ዘሮችም ለድንኳኑ አገልግሎት የተለዩት የአሮን ልጆች ብቻ ናቸው። ስለዚህ፣
1/ በዚህ ዘመን እስራኤላውያን ብቻ ናቸው ለእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች የሚል የአዲስ ኪዳን ትምህርት የለም። ስለዚህ ለተለየ ሕዝብ የተሰጠ የብሉይ ኪዳን የክህነት ሕግ በዚህ ዘመን የለም። አማኞች ሁሉ ካህናት ናቸው።
“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።” ራእይ 5፥9-10
2/ ሌዊ በሌለበት ሌዊ፣ መስዋዕትና ሥርየት አቅራቢው ኢየሱስ በሆነበት ራሱን የተለየ ካህን የሚያደርግ ቢኖር እሱ ምድራዊ ሥርዓት ነው።
እኛ በኢየሱስ ሊቀካህንነት ያመንን ሁላችን ለርስቱ የተለየን በደሙ የተዋጀን ካህናት ነን።
“እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤”
— 1ኛ ጴጥሮስ 2፥9
3/ ሌላ የምድራዊ ሹመት ሊቀካህን ይሁን ካህናት የማያስፈልገን ምክንያት ሁሉም ሰዎች በሞት የሚሸነፉና በኃጢአት የወደቁ ወይም ሊወድቁ የሚችሉ ደካማ ፍጥረቶች ስለሆኑ ነው።
ዕብ 7፣22—23 እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው።
ሥልጣነ ክህነት የሚባል መለኪያና መስፈሪያ የተዘጋጀለት የአገልግሎት መስፈርት በዚህ ዘመን አለ ቢሉ እሱ ከምድራዊ አስተምህሮ የመነጨ እንጂ ከሰማያዊ አገልግሎት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በሰማይም፣ በምድርም ያለን ሊቀካህን አንድ ሲሆን እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ዕብራውያን 8፣ 1—2 ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።
በሊቀካህናችን በኢየሱስ መስዋዕትነት ያመንንና የኃጢአትን ሥርየት ከአብ የተቀበልን፣ እኛ አማኞች ሁላችን በኢየሱስ የተሾመን ካህናት ነን።
“መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።”
— ራእይ 1፥6
ማጠቃለያ፣
ካህን ማነው? ለሚለው ጥያቄ የማጠቃለያ መልሳችን በእስራኤል ዘሥጋ ዘመን ከ12ቱ ነገድ ለሌዊ ብቻ የተሰጠ ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት የዘላለም ሊቀካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን በእሱ ያመን እኛን በደሙ ተቀድሰን የመንግሥቱ ካህናት፣ የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አገልጋዮች ሆነናል።
" ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል"
(ዕብ 12:22—24)