Wednesday, June 27, 2012

"...መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ" ማቴ. 5፥16

በመምህር ሙሴ ኃይሉ

ምንጭ፤ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መ/ ድረ ገጽ

 መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ማር እንደ ወተት የሚጣፍጠውን ትምህርቱ ለመስተማርና በተለያዩ ምክንያቶች (ተአምራትን ለማየት፣ ምግበ ሥጋን ለመመገብ፣ ሐሰት አግኝተው ለመፈተን...) ከአምስት ገበያ በላይ ሕዝብ ተሰብስበው በተመለከተ ጊዜ ከፍ ወዳለ ተራራ ወጥቶ በወርቃማ አምላካዊ አንደበቱ በተራራማ ስብከቱ ካስተማራቸው የመንፈሳዊነት፣ የሐዋርያዊነት፣ የአገልግሎት፣ የምግባርና የትሩፋት ትምህርት አንዱ ነው፡፡ ይኸው ትምህርት ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያትና በሐዋርያት እግር ሥር የሚተኩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ምዕመናንና ምዕመናትን የሕይወት መርህ በማድረግ እስከ መጨረሻ ህቅታ ድረስ አጽንተው እንዲጠብቁ የተሰጠ የምግባርና የትሩፋት (የሥነ ምግባር) አስተምህሮ ነው፡፡ ብርሃን በተለያዩ ዓይነት የትምህርት ዘርፎች የተለያዩ ትርጉም ቢኖረውም መጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ዕውቀታችን አድርገን ለምናምን ለኛ ግን ብርሃን የእግዚአብሔር የባሕርይ መገለጫው ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት ብርሃን ፈጣሬ ዓለማት፣ ሠራዔ ዓለማት፣ መጋቤ ዓለማት እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለሆነም ብርሃን ሀሉን ያስገኘ፣ ሁሉን የፈጠረ እንጂ በዚህ ዘመን ተገኘ፣ ከዚህ ዘመን በኋላ ያልፋል ተብሎ የማይነገርለት ምሥጢረ መለኮት ነው፡፡ እውነተኛ ዘለአለማዊ ብርሃን እግዚአብሔር መሆኑ ዘመነ መርገም አብቅቶ የዘመነ ምሕረት የምሥራች በተነገረበት ጊዜ ድኅነት ሰጪው፣ አዳኙም ሆነ ድኅነት ተቀባዩ ራሱ የሆነ የባሕርይ ዘለአለማዊ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ (ነባቤ መለኮት) ስለ እውነተኛ ብርሃን ምሥጢር በመጀመሪያ ምዕራፉ ሲጽፍ፡-"...ብርሃን በጨለማ ይበራል ጨለማም አላሸነፈውም፡፡ ...ለሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፡፡ በዓለም ነበረ ዓለሙም በእርሱ ሆነ ዓለሙም አላወቀውም'' (ዮሐ. 1፡1-10) በማለት ጀምሮ የረቀቁ የሥነ መለኮት ትምህርቶችን በምጥቀት ያትታል፡፡


ይህ ማለት አማናዊ ብርሃን እግዘአብሔር መሆኑንና በዚሁ አማናዊ ብርሃንም ሁሉን እንደተገኘ እንረዳለን፡፡ መምህረ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ እውነተኛ አስተምህሮ በግልጽ ሲያስረዳ ማለት እውነተኛ (አማናዊ) ዘለአለማዊ ብርሃን ራሱ "ወልደ አብ ወልደ ድንግል" ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ለደቀ መዛሙርቱና በወቅቱ ለተሰበሰቡት ሕዝብ በግልጽ በአደባባይ አስተምሮአል፡፡ "ደግሞም ኢየሱስ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው" ዮሐ. 8፥12 "በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ" ዮሐ. 12፥36 "የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳላችሁ በብርሃን እመኑ" ዮሐ. 12፥46 እንዲል፡፡ የዓለም ሕዝብ በተለይ ደግሞ ሕግ ተሠርቶላቸው፣ ጽላት ተቀርጾላቸው፣ ነቢያት ተልኮላቸው የነበሩ እስራኤላውያን ሕግን እንጠብቃለን ሲሉ ሕግን እየሻሩና ወደ ራሳቸው (ወደ ሥጋዊ ፍላጎታቸው) ብቻ እየተረጐሙ በኃጢአት ጨለማ ውስጥ ሲኖሩ የጨለማ ጠላት የሆነው እውነተኛ ብርሃን መምጣቱንና ሰዎቹም አለመቀበላቸውን ቅዱስ ዮሐንስ ሲገልጽ፣ "ብርሃን ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነው" (ዮሐ. 3፥19) በማለት ይገልጽልናል፡፡ የመድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንነት ከነቢያት ጀምሮ "በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ በሞት አገርና በጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው" (ማቴ. 4፥14-16) በማለት ሲገልጽ የመጣ ሲሆን ይህንኑ አማናዊ ብርሃን አንቀበልም ብለው ኃጢአት ሳይኖርበት እንደ በደለኛ በብርሃኑ ላይ ማመጻቸውም ነቢያት በመንፈሰ እግዚአብሔር ተመርተው አስቀድመው ተነብየውታል፡፡ "እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምጹ ናቸዉ፡፡ መንገዱን አያውቅም በጐዳውም አይጸኑም" (ኢዮብ.24፥13) እንዲል እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነታዎች መረዳት የሚችለው አማናዊ (እውነተኛ) ብርሃን እግዚአብሔር መሆኑን ነው፡፡ የፀሐይና ጨረቃ እንዲሁም የክዋክብት ተፈጥሮስ? አንዳንድ ሊቃውንት ብርሃንን ሲተረጉሙ የተፈጠረ ብርሃንና ያልተፈጠረ ብርሃን በማለት ይተረጉማሉ፡፡


ያልተፈጠረ ብርሃን እግዚአብሔር ሲሆን የተፈጠረ ብርሃን ደግሞ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ናቸው በማለት ያትታሉ፡፡ ነገር ግን እውነተኛ (አማናዊ) ብርሃን (Absolut light) አንድ እግዚአብሔር ሲሆን ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ደግሞ የዚሁ አማናዊ ብርሃን ነፀብራቆች (Reflecion of Absolut light) ናቸው (ዘፍ. 1፥14-15)፡፡ እነዚህ ብርሃናት የሚያገለግሉት ዘመናትን ለማፈራረቅ፣ ቀንና ሌሊት ለመለየት ትልቁ ብርሃን በቀን ትንሹ ብርሃን ደግሞ በሌሊት ስልጥነው በፈጣሪ ጥበብ የተፈጠረችውን ዓለም በፈጣሪ ቃል ትእዛዝ እስክታልፍ ድረስ ወቅታቸውንና ምህዋራቸውን ጠብቀው ዓለምንና በዓለም ላይ ላሉት ሁሉ ያገለግላሉ፡፡ ፍጥረት የሚባለው "አም ኃበ አልቦ" ካለ መኖር ለመጣ ነገር ሲሆን "ግብር እም ግብር" በፊት ከነበረ (ተፈጠረ) የተፈጠሩት ደግሞ "ግኝት" እንላቸዋለን፡፡ ብርሃንም ሆነ ብርሃናት (ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ከመገኘታቸው አስቀድሞ ብርሃን ይሁን ብሎአልና "ዘፍ.1፡3") ከፈጣሪ ምልዓተ ብርሃንነት ፍጡራንን እንዲያገለግሉለት በፀጋ የሰጣቸው መንፈሳዊ ወይ አምላካዊ ሀብት እንጂ ከሌላ የመጡ ወይም እንደ አዲስ ካለመኖር (from nathingness) የተፈጠሩ ፍጥረቶች ስላልሆኑ ግኝቶች ብንላቸው የተመቸ ነው፡፡ መገኛ ምንጭ እውነተኛ ብርሃን እግዚአብሔር አላቸውና ነው፡፡ ለዚህም ነው የሥነ መለኮት ሊቃውንት ፍጥረት አንድ ቀን ነው (ሰማይና ምድር)፤ ሌላው ግን "ግብር እም ግብር" ከተገኘ የተገኘ ስለሆነ ፍጥረት ሳይሆን ግኝት ነው በማለት የሚያራቅቁት፡፡ ፀሐይ በዓለማዊ ጠበብቶች ወይም ምሁራን ዘንድ የብርሃናት ሁሉ ምንጭ ናት (sun is the source of light) የሚል አስተምህሮ አብዝተው የሚናገሩ ቢሆኑም ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን መጻሕፍተ አምላካውያት መሠረት በማድረግ ፀሐይ የብርሃን ተሸካሚ ናት (sun is the beare of light) የሚል እውነተኛ ትምህርት ተቀብላ ታስተምራለች፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደተገለጸው የብርሃናት ሁሉ መሠረት፣ ምንጭ፣ መገኛ ፀሐይ ሳትሆን ዓለምን ፈጥሮ የሚመግብ ሁሉን ቻይ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነውና፡፡ አባ ሕርያቆስ ዘሀገረ ብሕንሳ በቅዳሴ ማርያም አንቀጹ እንዳለው ወደ መነሻ ርእሳችን እንመለስና ለመጀመርያ ጊዜ ይህን ትእዛዛ የተሰጣቸው ለእነዚሁ ብርሃናት ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን አምላካዊ ትእዛዝ ተቀበለው ሙሉ ለሙሉ የመታዘዝ ሕይወትን ገንዘብ በማድረግ "እንበለ አጽርኦ" ያለ ድካም፣ ያለ መሰልቸት ሁል ጊዜ ከፈጣሪያቸው ለዓለም በፀጋ እንዲያበሩበት የተሰጣቸው ብርሃን በፀጋ እየለገሱ ሥርዓታቸውን ጠብቀው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ "ብርሃናቸውን እያበሩ" ያገለግላሉ፡፡ ግዑዛን ፍጥረታት እያልን የምንጠራቸው እነዚህ የአማናዊ ብርሃን ነፀብራቅ የሆኑ ብርሃናት አምላካቸውን በማመንና በመታመን ዘመን ከተፈጠረ ጀምሮ ይህንን የመታዘዝ ሕይወት ተቀብለው ሲያገለግሉ እነዚህን የፈጣሪ ፀጋ የሆኑ ብርሃናትን ተመልክተን እና ጣዕማቸውን አጣጥመን ሲመሽና ሲነጋ የአምላካችንን ስም በመጥራት እናመሰግናለን፤ ስናመሰግንም እንኖራለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ይህንን የሥነ ምግባር ትምህርት የተነገረ በረድኤትና በቃል፣ በሕግና በትእዛዝ (በመጻሕፍት) ሳይሆን በአካል ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም ሰውም ሆኖ መድነኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ላይ ወጥቶ እርሱን ለሚከተሉ (ለሚያምኑና ለሚታመኑ) ሁሉ መሠረታዊ የሕይወታቸው መሪ እንዲያደርጉት ለደቀ መዛሙርቱና ለተሰበሰበው ሕዝብ ያሰተማረው ትምህርት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት መጽሐፉ በሰፊው ተርጉሞት እንደምናገኘው ይህንን ንፁሕ የወንጌል ቃል ያፈራው በቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሕይወት ላይ ነው፡፡ "ዘርዕ ንጹሕ ዘይፈሪ ውስተ ሥጋሆሙ ለቅዱሳን ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ንፁሕ ዘር በቅዱሳን ሕይወት /ሥጋ/ ላይ 30፣ 60 እና 100 ሆኖ የሚያፈራ አማናዊ ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው" እንዲል /መጽሐፈ ሰዓታት ሞገስነ/፡፡ በመሆኑም ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው አባቶቻችን በሙሉ ብርሃን የሆነውን አምላካቸው በማመናቸውና በመታመናቸው ብርሃናቸው በሰው ፊት አብርቶ በጥቂት ቤተሰብ ብቻ ተወሰና የተመሠረተች ክርስትና በመላ ዓለም እንድትሰበክ ሆነች፡፡ ናቡከደነጾር በኃይል ማርኮ የወሰዳቸውን ሠለስቱ ደቂቅን በአምላካቸው አምነው ስለታመኑ ብቻ ከእምነታቸው ፅናት ተነሰቶ እግዚአብሔርን እንዳመሰገነና የሚቃወማቸው ሁሉ የቅጣት ፍርድ አዋጅ ማወጁ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ በሐዲስ ኪዳንም አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ይህንኑ እውነታ በሕይወታቸው በመተርጐም ብርሃናቸውን ለጨለማው ዓለም አብርተው አልፏል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ፈታኝ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡፡ "ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናል... እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፣ እንጠማለን፣ እንራቆታለን፣ እንጎሰማለን፣ እንከራተታለን፣ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፣ ሲሰድቡን እንመርቃለን ሲያሳድዱን እንታገሳለን ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል" 1ኛ ቆሮ.4፡9-13፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴ መጽሐፉ እንደተረጎመው በሰዎች ላይ ለዘመናት ነግሦ የነበረውን ሞት የሞተው /የተወገደው/ በክርስቶስ ሞት ("ሞተ ከመ ይስዓሮ ለሞት፡- ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ" ቅዳሴ ዘዲዮስቆሮስ/ ስለሆነ ይህን የመነሻ ርእሳችን አስተምህሮ አባቶቻችን ቅዱሳን ሰማዕታት መላ ሕይወታቸውን በመስጠት ደማቸውን በማፍሰስ፣ አጥንታቸውን በመከስከስ፣ አባቶቻችን መናንያንን ደግሞ ጣዕመ ዓለምን ንቀውና መንነው፣ አባቶቻችን መነኮሳት ስለመንግስተ ሰማያት ሲሉ ራሳቸውን ጀንደረባ በማድረግ ምድራውያን መላእክት በመሆን በስውር የተቀበሉት ቃለ ፈጣሪ በአደባባይ መስክረውና አስተምረው ለብዙኃን ማመንና መታመን ምክንያት ሆነው፣ በዓላውያን ፊት የተሰጣቸውን ብርሃን አብርተው አልፏል፡፡ "... እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፣ ተፈተኑ፣ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዘሩ ዓለም አልተገባቻቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጐድጓድ ተቅበዘበዙ" ዕብ. 11፡35-39 እንዲል፡፡ ይህም ሆኖ ቅዱሳን አባቶቻችን ብርሃን ክርስቶስን በልባቸው የእምነታቸውን ፅናት ተመልክቶ በምልዓት ስላበራ የሚመጣ ሥጋዊ ፈተና ሁሉ "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል" /ሮሜ.8፡35/ በማለት መከራው ይበልጥ እያፀናቸው ሄዶ ይኸው ለእኛ ለልጆቻቸው ሕይወታቸውን ሰጥተው ሐዋርያዊ ትውፊቱን ጠብቀው፣ ተዋረዱን አስተካክለው በሥርዓትና በሕግ አጥረው አስረክበውናል፡፡ ከዚህ የምንማረው ይህ አምላካዊ የምግባርና የትሩፋት ትምህርት በዚህ በዘመናት ቀላል በሚባሉ ዓይነት ዘይቤዎች ግን በሕይወታችን ከባድ የሰይጣን ፍላጻ የሚተክሉ እሾሆች አንጥረን በማውጣት ይህንን ትምህርት መተርጎሙ ላይ እጅግ አድርገን ልንተጋ እንደሚገባ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ተገልጋዮች በየደረጃችን በየመዓርጋችን በእምነት የተቀበልነውን ይኸው የልባችን ብርሃን በሚገባና በሕግና በሥርዓት ከሚገባም በላይ በሕገ በትሩፋት አብርቶ በሕይወታችን የዘላለም ሕይወት ወራሾች እንዳንሆን የሚያደርጉ ጥቃቅን የኃጢአት ቀበሮዎችን የክርስቶስ የወይን እርሻ የሆነውን አካላችን ከማርከሳቸው በፊት በንስሐ ልናጠምዳቸውና ከዚያም ለሁሉ ጊዜ ልንጸየፋቸው ይገባል፡፡ በተለይ የሰማይ ከዋክብትን መስለን ጥንግ ድርባችንን ለብሰን የሃይማኖታችን ትምህርት በሚገባ አጥንተን ቤተክርስቲያናችንን በፍቅር ለማገልገል ሌት ከቀን የምንተጋ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ወጣቶች ከእነዚህ የአባቶቻችን የሕይወት ትርጉም ትልቅ ትምህርት ወስደን ያሉንን መንፈሳዊና ማኅበራዊ የበጎ አድርጎት ተልዕኮአችንን እጅግ አሳታፊና ግልጽ በሆነ መልኩ በማስፋትና በማስፋፋት ይህንኑ የቤተ ክርስቲያናችን ተልዕኮ እንቅፋት የሚሆኑ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮችን ደግሞ ተመካክረን በማረምና በማስተካከል ሌሎች ሰዎች የእኛን ሕይወት፣ የእኛን አገልግሎት ወዘተ አይተው ሃይማኖታችንን የሚወዱ፣ አምላካችንን የሚያስመሰግኑ እንዲሆኑ፣ ሕጉም ትእዛዙም ይኸው ስለሆነ በዚህ ረገድ አብዝተን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለው የሕይወት ብርሃን በሌሎች መታየት የሚጀምረው መጀመሪያ በእኛ ውስጥ ማብራት ሲችል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ከከንቱ ውዳሴ ጋር በፍጹም የማይገናኙ ተቃራኒ ነገሮች ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ልጁ መንፈሳዊ ትምህርት ካስተማረው በኋላ አስተማሪ አድርጎ ሲያሰማራው "ይህንን እዘዝና አስተምር በቃልና በኑሮ በፍቅር በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን" /1ኛ.ጢሞ. 4፡11-12/ በማለት መምከሩ ይህንን የጌታችን ትምህርትና የሐዋርያት ሕይወት ልብ ብለን እንድንከተለው ነው፡፡ የብርሃናት አምላክ እግዚአብሔር የተሰጠንን ብርሃን ተጠቅመንበት በዘለዓለማዊ ብርሃን እንድንኖር ያብቃን አሜን፡፡