Wednesday, June 6, 2012

ጥያቄ፤ ገነት እና መንግሥተ ሰማያት ልዩነት አላቸውን?


 by Mihretu
ገነት ወይም Garden ቦታ ሲሆን መንግሥተ ሰማያት/Kingdom of God/  ማለት ግን የእግዚአብሔር አገዛዝ ማለት ነው። የሰማያት ወይም የሰማይ መንግሥት ማለት ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት ነው፡፡

በአብዛኛው በማርቆስ ወንጌል "የእግዚአብሔር መንግሥት" የሚለው ቃል ነው በማቴዎስ ወንጌል "መንግሥተ ሰማያት" የተባለው። ትርጉሙም የሰማይ መንግሥት ወይም የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች እንደሚናገሩት፤ ማቴዎስ "የእግዚአብሔር መንግሥት" ከማለት ይልቅ "የሰማይ መንግሥት" ወይም በግዕዙ "መንግሥተ ሰማያት" ብሎ የጻፈበት ምክንያት የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው ለአይሁዶች ስለነበርና አይሁዶች ደግሞ "እግዚአብሔር" የሚለውን ስም ደጋግመው መጥራት ያስቀስፋል ብለው ስለሚያምኑ እንደነበር ይናገራሉ (ምክንያቱም በህግ የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ ይላልና)
ጥቅስ፤
የማርቆስ ወንጌል114-15 ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና። ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ።

የማቴዎስ ወንጌል 417 የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።

የእግዚአብሔር መንግሥት ደግሞ  በደረጃ የምትቀመጥ ቦታ አይደለችም። ነገር ግን የእግዚአብሔር አገዛዝና ፈቃድ የሚፈጸምበት ማለት ነው። ለዚህ ነው በአባታችን ሆይ ጸሎት  "መንግስትህ ትምጣ" ካለ በኋላ ወዲያው "ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን" የሚለው።

ጥቅስ፤
የማቴዎስ ወንጌል 610 ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤

ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ወይም የእግዚአብሔር መንግሥት ማለትም የእግዚአብሔር አገዛዝና ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም እንዲሆን ነው ጸሎቱ የሚያስተምረን። መንግሥት ማለት አገዛዝ ማለት እንደሆነ ሁሉ እኛ ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ሁሉ ፈቃደኞችና የሰይጣንን አሰራር ተቃውመን በቅድስና ለመኖር መወሰናችንን በማወጅ አገዛዝህ በምድር ላይ ይሁን ብለን ስንጠራ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ በምድራችን ላይ እንዲሆን ጠይቀናልማለት ነው። ሰው የእግዚአብሔር አገዛዝ በምድር ላይ እንዲሆን ባለመፈለግ የመንግሥቱ ሰው የመሆን ብቃት ሲጎድለው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው በጎ ፈቃድ ሁሉ ይቀራል። ያኔ የጠላት አሠራር በምድር ላይ መፈጸም ይጀምራል። ረሃቡ፤ጦርነቱ፤እልቂቱ፤ በሽታው፤ስደቱ ሁሉ የሚመጣው የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ የእግዚአብሔር አገዛዝ እንዲፈጸም ለመገዛት ስላልፈለገ ነው።

የእግዚአብሔር ፈቃድ በሚፈጸምበትና የእርሱ ሥልጣን ተግባራዊ በሚሆንበት ሁሉ በዚያ የእግዚአብሔር መንግሥት አለች።


ጥቅስ፤
ሉቃስ ወንጌል 17፤20-21 ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፤ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው።

ኢየሱስ በምድር በተመላለሰበት ጊዜ የእግዚአብሔር አገዛዝ ወይም መንግሥት በእርሱ ይሠራ ስለነበር ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና ብሎ ፈሪሳውያንን ሲነግራቸው እንመለከታለን። በመካከላችሁ የሚለው በልባችሁ ማለት እንዳይደለ ልብ ልንል ይገባል፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ይህን መልስ የመለሰው ለፈሪሳውያን ነው። በመካከላችሁ ናትና የሚለው ኢየሱስ ራሱን ነው። ምንክንያቱም የእግዚአብሔር ሥልጣን አጋንንትን በማውጣት፣ በሽተኞችን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሳት፣ ኃጢአተኞችን ይቅር በማለት በክርስቶስ አማካኝነት በመካከላቸው እየተገለጠች ነበርና።
ጥቅስ
የማቴዎስ ወንጌል 12፤28  እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።
አንዳንዶች «የእግዚአብሔር መንግሥት» በሰማያት ብቻ የምትገኝ የእግዚአብሔር ከተማ አድርገው ያስባሉ። እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ የዛሬ 2000 ዓመት ሐዋርያት የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች ባላሉም ነበር።
ጥቅስ፤
 ማቴ 10፤7 ሄዳችሁም። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ
  የእግዚአብሔር መንግሥት  በኢየሱስ ክርስቶስ  በኩል የሚፈጸመውን የማዳን ሥራ ሰዎች ሁሉ አምነው እንዲቀበሉና እንደፈቃዱ እንዲኖሩ እነሆ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች» እያሉ እንዲሰብኩ ለሐዋርያቱ ነገራቸው እንጂ ያኔውኑ የሚፈጸም የሰማያት ፍርድ ስለመድረሱ አልነበረም። በዚህ ምድር ላይ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የተመላለሰ በሰማያት ባለው የእግዚአብሔር አገዛዝም ከቅዱሳኖች ጋር መኖሪያውን ያደርጋል። ይህም ስለሆነ በዚህ ምድር ላይ «መንግሥትህ ትምጣ» እንላለን። ያም ማለት እንደትእዛዝህና እንደፈቃድህ እንኖራለን ማለት ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት የእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚፈጸምበት ቦታ ስለሆነ። ፈቃዱን ሳንፈጽም «መንግሥትህ ትምጣ» ስላልን ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር ኅብረት እንዲኖረን አያደርግም።
ጥቅስ፤
721 በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።
ታዲያ የእግዚአብሔር መንግሥት ምድርናት?
የእግዚአብሔር መንግሥት ሰው ከሰራው ኃጢአት ሁሉ በንስሐ መታጠብ፤ በአንድያ ልጁ የማዳን ሥራ ማመን፤ ዳግመኛ በኃጢአት ባርነት ላለመያዝ መወሰን፤ በአንድያ ልጁ ፍቅርና ትእዛዛት መኖር ናት። ጌታችን፤ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠን የእግዚአብሔር መንግሥት ይህንን በመፈጸም የምትገለጽ ናት።
ያን ጊዜም «መንግሥትህ ትምጣ» ብለንና «ፈቃድህ በሰማያት እንደሆነ ሁሉ በምድር ትሁን» ስንል በእግዚአብሔር አገዛዝ ሥር ስላለን እግዚአብሔር ለእኛ የፈቀደውና የሰጠውን ኃይል ሁሉ እናገኛለን ማለት ነው። ፈቃዱን ካልፈጸምን ለተሰጠችን መንግሥት ንጹህ ዘር አልሆንም ማለት ነው፤ ያም ቅጣትን ያስከትላል።
ጥቅስ
ማቴ 13፤24 ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች።
በዚህ ዘር ውስጥ ጠላት መጣና እንክርዳድ ዘራ፤ መላእክቱም ባለቤቱ ያልዘራውን ይህንን እንክርዳድ ለመንቀል ፈለጉ፤ ባለቤቱም እስከመከር ድረስ ተውት አለ። በመከርም ስንዴውን ወደጎተራ እንክርዳዱንም ወደእሳት ይጣላል አላቸው።
ክርስቶስ በእኛ ውስጥ የዘራው የሕይወት ቃል ሁሉ መልካም ዘር ሆነ ማለት እንክርዳድ የሌለበት የእግዚአብሔር መንግሥት ዘር ሆንን ማለት ነው።
ባጭሩ ጥያቄውን ለመመለስ፤ ገነት አንድ የተወሰነ ሥፍራ ወይም ቦታ ነው። መንግሥተ ሰማያት የሚለው ቃል ትርጉም ግን በሰማይም፤ በምድርም የእግዚአብሔር ፈቃድና  አገዛዝ የሚፈጸምበት መንግሥት ማለት ነው። ስለዚህ  በሰማይም ይሁን በምድር የእግዚአብሔር ፈቃድ በሚፈጸምበትና የመንግስቱ ሥልጣን በሚገለጥበት ቦታ ሁሉ በዚያ የእግዚአብሔር መንግሥት አለች ማለት ነው።