Friday, June 22, 2012

ካስቀኑት ያልቀረ እንደዚህ ነው ማስቀናት!!

 
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በተ/ሃይማኖት ስም ስለሚጠሩ ሦስት ሰዎች ማንነትና ምንነት በሰፊው ጽፈው አኑረውልናል። የትኛው ተ/ሃይማኖት የጻቅድነትን ስያሜ፤ ከማን እጅ እንደተረከበና ይኸው ጥሪ በዘር ማንዘሮቹ በርስትነት ተይዞ እንዲቆይ በግዝት እንዲጸናና ዜና ታሪኩ በመላው ኢትዮጵያ በሰፊው እንዲናኝ ስላስደረገው ተ/ሃይማኖ ማንነት ፤ አፍ በሚያስይዝ ጽሁፍ ስውሩን ደባ አጋልጠው ለትውልድ በማስረዳታቸው ይህም አለ እንዴ? ብለን እንድንገረም ካደረጉን ቆይቷል።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ስለሰውዬው ማንነት በነገሩን ወቅት ይህም አለ እንዴ? ብለን ዝም ከማለት ወይም የምንወደው ጻድቅ ተነካብን ብለን ከማኩረፍ ይልቅ ስለነገሩን ታሪክ እንዴትነት ፤የእውነተኛውንና  የጻድቁን ተ/ሃይማኖትን መንፈሳዊ ገድል  ስለቀማው  ሰው ማንነት፤ በማወቅ ብቻ ሳንወሰን ያንን መነሻ አድርገን ሌሎችን መረዳቶችም  እንድናገኝ ዓይናችን በመግለጣቸው ጭምር አመስግነናቸዋል።  ድሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ብዙ የምንታመንበት፤ ዘወትር የምንደግመው፤ ሰውነታችንን የምናሻሽበት፤ የጸሎት መጽሐፋችን የነበረውንም  የገድል መጽሐፍ እንድንመረምር እድል አስገኝተውልናል።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ከታሪክ ጭብጥ ተነስተው ስለገለጿቸው፤ ስለሦስቱ ተ/ሃይማኖቶች ማንነትና ታሪክ ወደፊት ለማቅረብ እንሞክራለን። ለዛሬው ግን ለርእሳችን ወደመረጥነው ጉዳይ እናመራለን።
እግዚአብሔር በቅዱሳኖቹ እጅ ድንቅን አድርጓል። ፊትም፤ ዛሬም፤ ወደፊትም ይሰራል። ይህ ግን የሚያስደንቀውና የሚያስገርመው ሥራ የቅዱሳኖቹን ኃይል ሳይሆን ኃይሉን በእነሱ የገለጸ የእግዚአብሔርን ከሃሌ ኩሉነት/ ሁሉን ቻይነት/ የሚነገርበት ዜና  ነው። ይህንን እግዚአብሔር በቅዱሳኖች አድሮ የመሥራት ኃይሉን ቅዱስ ጳውሎስ በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ሲገልጽልን፤  በኢቆንዮን ከተማ ውስጥ ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ እግሩ የሰለለች ሆና የተወለደ በልስጥራንም በተባለ ስፍራ አንድ ሰው በፈወሰ ጊዜ፤ ህዝቡ ተገርሞ አማልክት ከሰማይ ሰው ሆነው ወርደዋል በማለት መስዋእት ሊያቀርቡላቸው በወደዱ ጊዜ እንዲህ አለ።
«ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ እንዲህም አሉ። እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው። ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም። ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው» የሐዋ 14፤ 14-18

ጳውሎስ ስላደረገው ድንቅ ነገር የምሥጋና መስዋእት የተገባው በእሱ እጅ ይህንን ያደረገ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነና እንዳለፉት የአህዛብነት ዘመን በገዛ የአምልኰ ጎዳናቸው መሄድ እንዳይገባቸው፤ የእነሱን ምስክርነት እንዲቀበሉ አድርጎ  በጭንቅ እንዳስተዋቸው በወንጌል ተጽፎልን ተቀምጧል።
በየትኛውም ዘመን በእግዚአብሔር እጅ ስለተደረገው ድንቅ ነገር ቅዱሳን ምሥጋናንና መስዋእትን ከእግዚአብሔር ጋር ሲጋሩ ወይም እኩል ሲካፈሉ አልታየም። ቅዱሳን በእነሱ ስለተደረገው ነገር ሕዝቡ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ፤ እንዲያመልኩ እንጂ በምትኩ ራሳቸው እንዲመሰገኑ፤ እንዲመለኩ ሲያደርጉ አይታወቅም። አላውያን ነገሥታት ወይም ጣዖት አምላኪያን ካልሆኑ በስተቀር። አንዳንድ ክርስቲያኖች  የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆኑ ባለመቁጠር  ዛሬ እንደምናየው « እኔ የተክልዬ ልጅ፤ የድንግል ባሪያ፤ አርሴማ ጠበቃዬ፤ ዜና ማርቆስ ከለላዬ ወዘተ  በሚል ክህደት በእግዚአብሔር ምትክ ልዩ ልዩ መጠጊያና መጠለያ በማዘጋጀት እንደኢቆንዮን ከተማ ሰዎች ጳውሎስ የከለከውን መስዋእት ለማቅረብ ሲደፍሩ መመልከት ልብሳችን አልፎ ልባችንን የሚያስቀድድ ድርጊት ነው።
ጳውሎስ ይህንን የዝሙት አምልኰ እንዲህ ብሎታል።
«ይህንም እላለሁ። እያንዳንዳችሁ፤ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ። ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን?» 1ኛ ቆሮ 1፤ 12-13
የዝሙት አምልኰ የምንለው ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ በአንዱ ሙሽራና ራስ በሆነው፤  በክርስቶስ ጸንተው እንዳይኖሩ ከዚህም፤ ከዚያም ጋር ሙሽራዬ፤ ጠበቃዬ፤ከለላዬ እያሉ  ሰዎች የአምልኰ ዝሙታቸውን ያለገደብ የሚፈጽሙትን በመደዴ ሲፈጽሙት ስንመለከት ነው።
ከዚህ ውስጥም  ከላይ በመግቢያችን ላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው ከሦስቱ ተ/ሃይማኖት በአንዱ ላይ በጽሁፍ ስለተቀመጠው የአምልኰ ዝሙት እንመልከት።
ገድለ ተ/ ሃይማኖት ምዕራፍ 2 ቁጥር  16
«ይህ መማጸኛችን፤ ይህ አስተማሪያችን፤ ይህ መድኃኒታችን፤ ይህ አለኝታችን፤ ይህ ነጻ አድራጊያችን፤ ይህ የመንግሥተ ሰማይ ፈለማችን፤  ይህ በታረዝን ጊዜ ልብሳችን፤ ይህ በተራብን ጊዜ እውነተኛ ምግባችን፤ ይህ በተጠማን ጊዜ እውነተኛ መጠጣችን፤ ይህ በደከምን ጊዜ ምርኩዛችን»
ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ ላይ የተጻፈውን አይቶ ቢሆን ኖሮ በእነዚህ በዘመናችን  ኢቆንያውያን ላይ ልብሱን በመቅደድ ብቻ የሚያበቃ  እንደማይሆን መገመት አይከብደንም። በአንድ በበልስጥራን ሰው መዳን ክብሩ የእሱ እንዳልሆነ  ጮኾ የተናገረው ቅዱስ ጳውሎስ፤  ለተ/ሃይማኖትን የቀረበው ዓይነት የምስጋና መስዋእት ዓይነት  «አንተ  አለኝታችን፤ መድኃኒታችን፤ ነጻ አድራጊያችን፤ ልብሳችን፤ ጉርሳችን፤ መጠጣችን፤ ምግባችን ነህ» ቢባል ምን ይል ይሆን?  
ዘማውያን አምላኪዎች ግን ለዚህ ደንታ የላቸውም። በዚሁ ዓይነት ምሥጋና ጳውሎስም፤ ኬፋም፤ ኢየሱስም፤ እግዚአብሔር አብም፤ ማርያምም ሁሉም ቢመሰገኑ ምንም ችግር የለውም የሚሉ ይመስላሉ። ምክንያቱም እኔ የማደርገውንና፤ እኔ ከማደርገው በላይ ታደርጋላችሁ ብሏልና ይሉናል። እግዚአብሔር ማድረግ የማይችለውና ፤ ቅዱሳን ማድረግ የሚችሉት ምን ይሆን? ዐውደ ምንባቡን ዝርው አድርጎ በመተርጎም ብዙ እግዚአብሔር እንዳለ ወይም ቅዱሳን ሁሉ እግዚአብሔሮች እንደሆኑ ማሰብ ከክርስቲያናዊ ኅሊና የሚመነጭ አይደለም። ጳውሎስ እኛ ስላደረግነው እግዚአብሔርን አመስግኑ ያለው ስህተት ነበር። ራሱ እግዚአብሔርን መሆን ችሏልና ማለት ነው እንደሰዎቻችን አባባል። ይህ አስተምህሮ ከመንፈስ ቅዱስ የተገኘ ሳይሆን በእግዚአብሔር አሠራር ላይ በጠመመ ቃል አንድም ብሎ የሌለ ፍቺ ቆፍሮ ያመጣው ጠላት መሆን አለበት።
1/ መማጸኛችን ማለት ምን ማለት ነው?
በብሉይ ኪዳን ሰዎች የሚማጸኑባቸው ከተሞች ነበሩ። እነዚህ የመማጸኛ ከተሞች ለሁለት ወገን የተፈቀዱ ናቸው። በአንድ በኩል ሰው ለገደሉ ሌዋውያን ካህናትና በሌላ በኩልም ተራው ሕዝብ ሁሉ ከፍርድ በፊት ተበቃዩ እንዳይገድለው ራሱን የሚያስጠልልበት ከተማ ሆኖ ያገለግል ነበር።
«በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንት ለዩ። ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹም ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ»   ዘኁ 35፤11-12
የአዲስ ኪዳኑ የመማጸኛ ከተማ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አዳምና ልጆቹ ወንጀለኞችና የሞት ፍርድ የተገባን መጻተኞች ሆነን ሳለ ከዚህ ሞት ያዳነን፤ የሚያስተማምን  ዋስትና ያለው መሸሸጊያ ከተማ የሆነን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።
ኢየሱስ  የመሸሺያ ከተማችን ራሱ ስለመሆኑ እንዲህ አለን።
ዮሐ 14«በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና»
ስፍራ ላልነበረን፤ መኖሪያችን ለተበላሸ፤ የሚያስጠጋን ለጠፋ፤ እግረ አጋንንት ሲጠቀጥቀን ለነበርነው ለእኛ ለመጻተኞቹ  የመማጸኛ ከተማችን ማነው? ቢባል ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ትክክለኛው መልስ። ዘማውያን አምላኪዎች ግን የለም ካንተ ሌላም አለ፤ እሱም ተ/ሃይማኖት ነው! ይሉናል። ተ/ሃይማኖት መማጸኛችን ሲሉ አያፍሩም። ጳውሎስ ዛሬ አብሮን ኖሮ አንተ የመማጸኛ ከተማችን ብንለው አዎን!  ብሎ ይቀበለን ይሆን? በፍጹም !!!
2/ መድኃኒታችን
ከሁሉም የዝሙት አምልኰ ሁሉ የከፋው ይህኛው ነው። ያለምንም ተጨማሪ ማብራሪያ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ሳለ ተ/ሃይማኖት መድኃኒታችን ብሎ መናገር ክህደትና ኑፋቄ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳን በበልስጥራን ሰው በፈወሰ ጊዜ መድኃኒታችሁ እኔ ነኝ አላለም። ምክንያቱም ጳውሎስ ለኃጢአተኞች ሲል አልተጠመቀም፤ አልተሰቀለምም። የሰው መድኃኒትነት ምድራዊና ደካማ እንጂ ፍጹም ስላልሆነ ለክርስቲያኖች ተ/ሃይማኖት መድኃኒታችን ማለት ስህተት ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ የማዳን ሥራ ላይ ጣልቃ የገባ አደገኛ ክህደት ነው። ይህንን የሚሉ ሊወገዙ ሲገባ፤ ይህንን ማለት ትክክል አይደለም ያሉ ሲወገዙ ማየት ሰይጣን ድሩን እንዴት እንዳደራ የሚያሳይ ነገር ነው። እስከ ጊዜው እንጂ፤ እውነት የሚገለጥበት ሰዓት በመድረሱ የእውነትን ጭራዋን ቢሸፍኑ አናቷ ብቅ ይላል፤ አናቷን ቢሸፍኑ፤ ጭራዋ ብቅ ማለቱ እየታየ ነው። ይህንን የሚያዘገይ ካልሆነ ሸፍኖ የሚያስቀረው ምንም ኃይል እንደሌለ አስረግጠን እንናገራለን። ንጽናህ ንስቲተ!

ሉቃ 211 ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።
ዮሐ 442 ሴቲቱንም። አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር።
ሐዋ 531  ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።
ፊልጵ 320 እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤
1 ዮሐ 414 እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን።
ከብዙው በጥቂቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ ተ/ሃይማኖት መድኃኒታችን የሚሉ ከየት የተገኙ መናፍቃን ናቸው?
3/ ነጻ አድራጊያችን
ነጻ መውጣት ምን ጊዜም ነጻ መሆን ካለመቻል ጋር የተያያዘ ነው። ተበዳሪ የአበዳሪ ባሪያ ስለሆነ ነጻ ሰው አይባልም። ሰው ጉልበቱን፤እውቀቱን ቢሸጥም ለሸጠለት ሰው ባሪያ ነው። ለመሸጥ ከተስማማበት ሰዓት መቀነስም ፤ ማስቀረትም አይችልም። ብዙ የሥጋዊ ኑረት የባርነት መገለጫዎች አሉ። ከዚህ የሚበልጠውና የሚከፋው መንፈሳዊ ባርነት ነው። በመንፈሳዊ ባርነት ሥር የወደቁ ሰዎች ራሳቸውን ወይም ልጆቻቸውን ለመስዋእት ያቀርቡ እንደነበር ታሪክ ይናገራል። በመንፈሳዊ ባርነት ሥር የተያዙ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላካቸው ሲሉ ይገርፋሉ፤ ደማቸውን ያፈሳሉ፤በብዙ ሥቃይ ውስጥ ያኖራሉ። ነገር ግን ይህንን መንፈሳዊ ባርነት ቢያደርጉም የነፍሳቸው ነጻነት ማወጅ አይችሉም። አንድም ማረጋገጫ የላቸውም፤ ሊያቀርቡም አይችሉም።
ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ያላቸው መንፈሳዊ ነጻነት ራሳቸው መስዋእት በማቅረብ የተረጋገጠ ሳይሆን ነጻ ለማውጣት በሚቻለው፤ ሞት ይዞ  ባላስቀረው፤ ይልቁንም ሞት ለሚገባቸው  ሁሉ ራሱ ነጻ አውጪ ሆኖ በተሰዋው በኢየሱስ ክርስቶስ የተረጋገጠ ነው።
«በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ» ገላ 5፤1
በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና        ሮሜ 8፤2
መማጸኛችን፤ መድኃኒታችንና ነጻ አድራጊያችን፤ ተ/ ሃይማኖት ነው የሚሉ ሰዎች ገና የኢየሱስ ክርስቶስ የተሻለውና የበለጠው ድኅነት ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው። መቼም ትንሽና ትልቅ ወይም የጎደለውና የሚጨመር ድኅነትና ነጻነት በክርስቶስና በተ/ሃይማኖት መካከል ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ክርስቶስ ያልጨረሰው ተ/ ሃይማኖት የሚሞላው ወይም የክርስቶስ አስተማማኝነት ስለጎደለው የተ/ሃይማኖት መጠባበቂያ የሚያስፈልገው ክርስቲያን ሳይሆን መናፍቅና በዝሙት አምልኰ የተለከፈ ብቻ የሚከተለው ነው። ሰው አንዱንና የተሻለውን  መተማመኛ እንጂ ይህም፤ ያም አይቅርብኝ ብሎ በአይን አዋጅ ምኞት ሁሉንም ለማግኘት አይሰክርም። ከሙሽራው ውጪ ሙሽራ ያስቀመጡ ዘማውያን ግን እንደዚያ ያደርጋቸዋል።
ስናጠቃልል ለሰው ልጆች አለኝታ፤ ነጻ አድራጊ፤ መጠለያ፤ መጠጊያ፤ ቢራቡ ምግብ፤ ቢታረዙ ልብስ፤ ቢጠሙ መጠጥ፤መድኃኒትና ሕይወት እግዚአብሔር አምላክ ብቻ ነው። ቅዱሳን አገልጋዮች ናቸው እንጂ ፈጣሪዎች አይደሉም፤ ይህን ማድረግ አይችሉም።
ዘማውያን አምላኪዎች ግን የለም! አምላክ ዘበጸጋ ስለተባሉ  እነ ተ/ሃይማኖትም አምላክ ሆነው ሊያገለግሉና ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት፤ ለታረዘ ልብስ፤ ለተራበ ምግብ፤ለተጠማ የህይወት ውሃ፤ በሲኦል ላለ ነጻ አድራጊና የመንግሥተ ሰማይ መንገድ ሆነው መስራት ይችላሉ ይሉናል። በአጭሩ ሲቀመጥ  ተ/ሃይማኖት እግዚአብሔር መሆን ይችላሉ ነው ነገሩ። እንዴት ሆነው ለዓለሙ መድኃኒት ይሆናሉ? ለማንስ ቤዛ ሆነው በመድኃኒትነታቸው ያድናሉ? እንዴትስ አድርጎ ቢራብ ምግቡ፤ ቢጠማ መጠጡ ይሆናሉ? ነጻ አድራጊና የመንግሥተ ሰማይ ርስት ይሆናሉ? ይህንን ማድረግ ከቻሉ የክርስቶስ ሥራ ምን ሊባል ነው? ብንል መልሳቸው ዝም ብለህ መቀበል ነው እንጂ ይህንን መጠየቅ ምንፍቅና ነው ይሉናል። መናፍቁ፤ እውነት ተናጋሪውን መናፍቅ ሲል አይገርምም?
 ማስቀናታችሁ  ያልቀረ እንደዚህ ነው እንጂ!!! ምክንያቱም  እግዚአብሔርን በመለኮታዊ ስልጣኑ አብዝቶ ማስቀናት፤ መናፍቃኑን ቶሎ እንዲወገዱ ያደርጋልና ነው!