Wednesday, June 6, 2012

ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ/መዝ.136፡1/

                                    ቤተ ጳውሎስ ረቡዕ ግንቦት 29 2004 ዓ.ም.
ለብዙ ጊዜ ዱርዬ ማለት ቀጥተኛ ትርጉሙን፣ ገላጭ ፍቺውን አላውቀውም ነበር፡፡ ዱርዬ ማለት የቆሸሸ ልብስ የለበሰ፣ ሥራ አጥቶ ድንጋይ ላይ የተቀመጠ፣ ለማኅበረሰቡ ስጋት የሆነ ብለን እንፈታው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ያማረ ልብስ የለበሱ፣ ለፕሮቶኮላቸው የሚጠነቀቁ፣ ብዙ ፋብሪካ የተከሉ፣ ብዙ ሥልጣን የተሸከሙ፣ በጌትነት ወንበር ላይ የሚቀመጡ፣ በክብር አልባሳት የተንቆጠቆጡ፣ ወደ ስማቸው ቶሎ የማይደረስ ብዙ ቅጽል ያላቸው፣ ማኅበረሰቡ ተስፋችን ባልቴቶቹ ቀባሪያችን የሚሏቸው … ብዙ ዱርዬዎች አሉ፡፡ ትልቁ ችግራችን ሰውን በልብስ፣ ሰውን በንግግር ችሎታ፣ ሰውን በገንዘብ፣ ሰውን በመዐርግ፣ … መለካታችን ነው፡፡ ሰው በዲግሪ፣ ሰው በኒሻን አይለካም፡፡ የሰው መለኪያው የኑሮ ምርጫው ወይም ቀጥተኛነቱ ነው፡፡ ብዙ የዓለም ክብሮች የታሪክ አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ በአጋጣሚ ግን ቅን መሆን አይቻልም፡፡ ቅንነት ወይም እውነተኛነት ምርጫ ነው፡፡
ዱርዬ ማለት ምን ማለት ነው? አሁንም ፍችውን ማሰስ አለብን፡፡ ዱርዬ ሁሉም ልብስ ልክ የሚሆነው ብዬ በራሴ መዝገበ ቃላት ፈትቼዋለሁ፡፡ ሲዘፍን እንደርሱ ሲዘምር እንደርሱ የሌለ፣ ሲጾም እንደርሱ ሲበላ እንደርሱ የሌለ፣ ሃይማኖታዊ ልብስ ሲለብስ እንደርሱ ሲዘንጥ እንደርሱ የሌለ፣ … ሁሉም ልብስ ልክክ የሚልበት፣ ጎበዝ ተዋናይ እርሱ ዱርዬ ይባላል፡፡ ይህን ፍቺ ያገኘሁት ተጨንቄ ሳይሆን ዓይቼ ነው፡፡ ከስድስት ወር በፊት በአንድ ሠርግ ላይ ተገኝቼ ከሚዜዎቹ አንዱ የማውቀው ሰው ነበር፡፡ ይህ ወንድም ጠበል ሲጠጣ እንደ እርሱ ሥርዓት ያለው ዓይቼ አላውቅም፡፡ ውስኪ ሲጠጣም እንደ እርሱ ጎዝጉዞ የሚጠጣ ያለ አይመስልም፡፡ ታዲያ እዚያ ሠርግ ላይ ትግርኛውን ሲጨፍር፣ ጉራጊኛውን ሲጨፍር ያደጉበት እንኳ እንደ እርሱ አልተዋሐዳቸውም ብል ሐሰት አይደለም፡፡ ታዲያ ልቤ በድንገት፡- “ወይ ዱርዬነት” አለ፡፡ ወዲያው ከሠርጉ ጫጫታ በአሳብ ወጣሁና ዱርዬ ማለት ሁሉም ነገር ልኩ የሆነ፣ ትክክለኛ ማንነቱ ግን ኃጢአት የሆነ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡


ስብከት ሲሰሙ አትንጫጩብኝ የሚሉ፣ ዘፈን ሲሰሙም በዕንባ የሚታጠቡ፣ ቅዳሴ ሲሰሙ አትንቀሳቀሱ የሚሉ፣ ሐሜት ሲመጣ ያለ ቢላዋ የሰውን ሥጋ የሚያወራርዱ፣ የዘማሪ እገሌ አድናቂ ነኝ የዘፋኝ እገሌም አፍቃሪ ነኝ የሚሉ፣ ሁሉ የእነርሱ የሆነ የሚመስላቸው ሁሉ ግን የሌላቸው ብዙ የነፍስ ጎስቋሎች አሉ፡፡ ሁሉም ቀሚስ ልኩ የሚሆንለት ሰው ልክ የሌለው ሰው ነው፡፡
ከቤቴ አጠገብ ይኖር የነበረ አንድ ወጣት ሁልጊዜ ትዝ ይለኛል፡፡ ይህ ወጣት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነው፡፡ ታዲያ እሑድ በመጣ ቁጥር እርሱን ማየት ደስ ይለኛል፡፡ ከወጣትነቱ፣ ከሙሉ ልብሱ ባሻገር በእጁ የሚይዛት አብረቅራቂ መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ መስህብ ሰጥታዋለች፡፡ ያ ወጣት ግን የእሑድ ክርስቲያን ነው፡፡ በማግሥቱ ሰኞ በአደንዛዥ ዕፅ ተይዞ ይታያል፡፡ የሰንበት ክርስትና በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እየተስፋፋ ነው፡፡ ክርስትና ግን ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውጭም ሊኖር ይገባዋል፡፡ በዘመናችን ግን ሃይማኖታዊ ድራማ እየበዛ፣ ክርስቲያኖችም ተዋንያን እየሆኑ ይመስላል፡፡
አንድ አገልጋይ የነበረ ወንድም በማያውቀው ነገር ፖሊስ ይዞት እስኪጣራ በወኅኒ ቤት ማደር ነበረበት፡፡ ይህ ወንድም ሲናገር፡- “ገና ወደ ወኅኒው ቤት ስገባ ይህ አስተማሪው አይደለም; በማለት በአድናቆት ተቀበሉኝ፡፡ የተለየ ቦታ ከሰጡኝ በኋላ ዛሬ ታስተምረናለህ ሲሉኝ ተበሳጭቼ ስለነበር ቆይ ልረጋጋ ተውኝ አልኳቸው፡፡ እነርሱም በመቀጠል ትንሽ ገንዘብ ካለህ ሲሉኝ ከኪሴ አውጥቼ ሃምሳ ብር ስሰጣቸው በደስታ ዘለሉ፣ አንደኛ ደረጃ የሚባለውን ቦታ ለቀቁልኝ፡፡ ከሁሉ የገረመኝ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲል ሁሉም ቆሙ፡፡ ምን ሊያደርጉ ነው ስል የኦርቶዶክስ ዝማሬ መዘመር ጀመሩ፡፡ እንደቆሙ ከምሽቱ አራት ሰዓት ሆነ፡፡ እኔም ልቤ ተነካ፡፡ ለካ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ያሉት እዚህ ነው; ይህን ሊያሳየኝ ነው እግዚአብሔር ወደዚህ ያመጣኝ አልኩኝ፡፡ አራት ሰዓት ሲሆን የጴንጤ መዝሙር ተጀመረ፡፡ አማኞቹም መዝሙሩን እንዲያ የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ መዝሙሩ እስከ እኩለ ሌሊት እስከ ስድስት ሰዓት ቢቀጥልም ድካም የለም፡፡ ከስድስት ሰዓት በኋላ ዘፈን ተጀመረ በጣም ደነገጥኩ፡፡ ከዚያ በኋላ የደከመው እየወደቀ የፀናው እየቀጠለ ስምንት ሰዓት ሆነ” ብሎ አጫውቶኛል፡፡ ይህ ነገር የእስር ቤት ባሕርይ ብቻ አይደለም፡፡ መንፈሳቸው የታሠረባቸው ሰዎችም መገለጫ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ መንፈሳዊነት አማራጭ እንጂ ብቸኛ ምርጫ አለመሆኑ ያሳዝናል፡፡
በየፈረንጅ አገሩ ያሉ ቀሳውስት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የማሳነጽ ወይም የመግዛት ትልቅ ራእይ ያላቸውን ያህል ሰው የማስተማር፣ የማጽናናት ራእይ ግን የላቸውም፡፡ ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ማሰባሰቢያ እየተባለ የዘፈን ምሽት ይዘጋጃል፡፡ ይህንን የተቃወሙ ምእመናን ብዙ መገለል ይደርስባቸዋል፡፡ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የሰውን የምግባር ሕንፃ ማፍረስ ምን ይባላል; በእውነት አምነን፣ በእውነት ዘምረን ምነው በካታኮምብ ውስጥ ምነው በዋሻም ውስጥ በኖርን! አንዳንድ አገልጋይ ነን የሚሉም እንዲህ ያለው ዘፈን አይከለከልም ይላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ የተባለውን ተረት ያስታውሱናል፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ከሚከለክሉ ነገሮች አንዱ ዘፋኝነት ነው፡፡
እነዚያን የባቢሎን ምርኮኞች አንዘምርም ብለው የዘመሩትን እስቲ እንስማቸው፡፡ በኑሮ ውስጥ አንናገርም ብለው የተናገሩ፣ አንዘምርም ብለው የዘመሩ ልባችንን ነክተውታል፡፡ እነዚያ የባቢሎን ምርኮኞች እንኳን በቤተ መቅደስ ሊዘፍኑ በባቢሎንም መዘመርን አልወደዱም። ሁሉ ልካቸው የሆኑ አልነበሩም። ልካቸው መንፈሳዊ ቀሚስ ብቻ ነበረች።
“በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤
ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን፡፡
በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን፡፡
የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን÷
የወሰዱንም፡- የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን፡፡
የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን;
ኢየሩሳሌም ሆይ÷ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፡፡
ባላስብሽ÷ ምላሴ በጒሮሮዬ ይጣበቅ፤
ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ፡፡
አቤቱ÷ በኢየሩሳሌም ቀን የኤዶምን ልጆች አስብ፡-
እስከ መሠረትዋ ድረስ አፍርሱ አፍርሱ ያሉአትን፡፡
አንቺ ወራዳ የባቢሎን ልጅ ሆይ÷
ስለ ተበቀልሽን የሚበቀልሽ የተመሰገነ ነው፡፡
ሕፃናቶችሽን ይዞ በዓለም ላይ የሚፈጠፍጣቸው የተመሰገነ ነው፡፡”
(መዝ. 136÷1-3)።
የምርኮኛ ሕይወት ከባድ ነው፡፡ ምርኮኛ እስረኛ አይደለም፡፡ አገር ጎብኝም አይደለም፡፡ በሰው አገር ላይ ያለ ይግባኝ የሚቀጣ መከረኛ ነው፡፡ እስረኛ በሕግ ይዳኛል፣ ምርኮኛ ግን የሚዳኝበት ሕግ የለውም፡፡ እስረኛ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሎ ይከራከራል፣ ምርኮኛ ግን የሚከራከርበት አንቀጽ የለውም፡፡ እስረኛ ዘመዶቹ አቤት ይሉለታል፣ ምርኮኛ ግን አገሩ የሞተችበት በመሆኑ የሚከራከርለት የለውም፡፡ እስረኛ ከመብቱ በላይ ተጠቅሟል የተባለ፣ ሰርቀሃል፣ ገድለሃል ተብሎ ሌላውን በማጥቃቱ የሚከሰሰ ነው፡፡ ምርኮኛ ግን ተሸንፎ፣ ቆስሎ፣ ሞቶ የሚታሠር ነው፡፡ እስረኛ በአገሩ፣ በመንግሥቱ የሚቀጣ ታራሚ ነው፣ ምርኮኛ ግን ያለ አገሩ ያለ መንግሥቱ የተጋዘ ብሶተኛ ነው፡፡ እስረኛ መታሠሩን የሚያውቀው ፖሊስ ሊሆን ይችላል፣ ምርኮኛ ግን ንጉሡ እያወቀ የታሠረ ነው፡፡ እስረኛ በትንሽ ሹም ተበድሎ ወደ ትልቁ አቤት የሚል ነው፣ ምርኮኛ ግን በትልቁ ሹም ተበድሎ ይግባኝ የሚልበት የጠፋው ነው፡፡ እስረኛ ማኅበራዊ መብቱን የተነጠቀ ነው፣ ምርኮኛ አገሩን የተነጠቀ ነው፡፡ ሁሉም እኩል ያለቅሳሉ እንጂ ከእስረኛ የምርኮኛ ስቃዩ የበለጠ ነው፡፡ እስራኤላውያን በባቢሎናውያን በተማረኩ ጊዜ የደረሰባቸው እንዲህ ነው፡፡
“በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፣ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን” አሉ (መዝ. 136÷1)፡፡ ወንዞች አጠገብ መቀመጥ ትልቅ ደስታ ይሰጣል፡፡ ወንዝ ዳርቻ ቤታቸውን የሚሠሩ እጅግ የደላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ውድ ክፍያ ያለው መዝናኛ ወንዝ ዳርቻ ያለ ቦታ ነው፡፡ እስራኤላውያን ግን በወንዞቹ አጠገብ እየተዝናኑ ሳይሆን እያለቀሱ ነበር፡፡ ጽዮንንም ባሰቧት ጊዜ በዕንባ ይታጠቡ ነበር፡፡ በወንዝ ዳርቻው ውሃ ሳይሆን ዕንባ ይራጩ ነበር፡፡ ለምርኮ በተወሰዱ ዕለት ሁለት ነገሮች ሆነዋል፡፡ ያ ትዝ እያላቸው አነቡ፡-
1.    የዝማሬው ዕቃ ተሰቀለ፡-
“በአኻያ ዛፎችም ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን” ብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ዝማሬ የለንም፣ አገር አልባ ሆነን ዜማ የለንም ብለው መሰንቆቻቸውን ሰቅለው ነበር፡፡
2.   ኤዶማውያን በክፉ ቀን ከፉባቸው፡-
 “አቤቱ÷ በኢየሩሳሌም ቀን የኤዶምን ልጆች አስብ፡- እስከ መሠረትዋ ድረስ አፍርሱ አፍርሱ ያሉአትን” (መዝ. 136÷7)፡፡ ኤዶማውያን የኤሣው ዘሮች ናቸው፡፡ እስራኤል ደግሞ የያዕቆብ ዘሮች ናቸው፡፡ ኤሣውና ያዕቆብ ደግሞ ወንድማማች ናቸው፡፡ ታዲያ ባቢሎናውያን የሩቅ ጠላት ሆነው በመጡ ጊዜ ኤዶማውያን የወዳጅ ጠላት ሆነው ኢየሩሳሌምን እስከ መሠረትዋ አፍርሷት ብለው ተናገሩ፡፡ ከባቢሎናውያን ይልቅ የኤዶማውያን ነገር ልብ ይሰብር ነበር፡፡ “አቤቱ፡- በኢየሩሳሌም ቀን የኤዶምን ልጆች አስብ” አሉ፡፡ የኢየሩሳሌም ቀን ደግ ቀን አልነበረም፡፡ የኢየሩሳሌም የመከራ ቀን ነበር፡፡ ቀኑ ሲከፋ አክባሪዎቻቸው አዋረዷቸው፣ ወንድሞቻቸው ጠላት ያላሰበውን በማሳሰብ ደብዛቸውን አጥፉ ቅሪት አይኑርላቸው አሉ፡፡ ጠላት ሕንጻን ሲያፈርስ፣ የወዳጅ ጠላት ግን መሠረትን ያፈርሳል፡፡
እስራኤላውያን ከቀን በኋላ በባቢሎን ተመችቷቸው ቢኖሩም ኅሊናቸው ግን ምርኮኛ ነበር፡፡ የፈረሰችውን ኢየሩሳሌም፣ የተቃጠለችውን ጽዮንን፣ የቀረውን ያንን የዝማሬ ማዕበል እያሰቡ በትዝታ እሳት ይቃጠሉ ነበር፡፡ ይህን ቃጠሎ የወንዞቹ ብዛት አላቀዘቀዘውም። ባቢሎናውያን የጽዮንን ዝማሬ ያውቁት ነበር፡፡ ምንም ቢማርኳቸው ዝማሬአቸውን መጥላት ግን አይሆንላቸውም ነበር፡፡ ጠላት ሳይቀር የወደደውን ያንን ዝማሬ ኤዶማውያን የቅርብ ዘመዶች ግን እስከ መሠረቱ ይፍረስ ይሉ ነበር፡፡
“የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፡፡ የወሰዱንም የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን፡፡ የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር ላይ እንዴት እንዘምራለን;(መዝ. 136÷3-4)፡፡ ባቢሎናውያን የድል ዝማሬ ቢዘምሩ ያምርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ማርከዋልና። ነገር ግን የምርኮኞቹን ዝማሬ መስማት ይናፍቁ ነበር፡፡ በዓለም ላይ ድል የሚመስለው ድል አይደለም፡፡ ማሸነፍ ሁሉ ማሸነፍ አይደለም፡፡ ያሸነፍናቸው የሚመስሉን የእግዚአብሔር ሰዎች ዝማሬ የሚናፍቅበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ምግብ የማያስመርጥ የረሀብ ቀን ሊመጣ አቃቂር ያወጣንበት ምግብ ሁሉ ምነው በተገኘ ያሰኛል፡፡
እስራኤላውያን አሁን ከትካዜአቸው ወጥተው ቢዘምሩ የማረኳቸውን ይማርኩ ነበር፡፡ በሥጋ የማረኳቸውን በመንፈስ ይማርኩ ነበር፡፡ የሚበልጥ ማሸነፍ ያለው ከትካዜ ወጥቶ ብዙ በመሥራት ውስጥ ነው፡፡ ወሬ ጆሮን፣ ሥራ ሕይወትን የመግዛት አቅም አለው፡፡
ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን
“በሰሜን ወገን በመልካም ስፍራ የቆመ የምድር ሁሉ ደስታ የጽዮን ተራራ ነው”         (መዝ. 47÷2) ተብሎ እንዳልተዘመረ አሁን ግን ጽዮንን ባሰቡ ጊዜ አለቀሱ፡፡ ጽዮን የሕግ መውጫ፣ የሥርዓት ቤት የነበረችው ሕግ አልባ፣ ደፋር የሚያስተዳድራት እንደሆነች ባሰቡ ጊዜ አለቀሱ፡፡ ጽዮንን ባሰቧት ጊዜ ያለቀሱት ፍርድ አዋቂ ንጉሥ፣ ፍቅር አዋቂ ካህን፣ ትምህርት አዋቂ ነቢይ፣ ቅኔ አዋቂ ዘማሪ፣ ምሥጢር አዋቂ ሊቅ በመጥፋቱ ነው፡፡ ጽዮንን ባሰቧት ጊዜ ያለቀሱት የቊርጥ ቀን ልጆቿ ከምድሯ ተፈናቅለው ኤዶማውያን እነ ሆድ አምላኩ እነ ሠያጤ እግዚኡ እንደተቆጣጠሯት ባሰቡ ጊዜ ነው፡፡ ጽዮንን ባሰቡ ጊዜ ያለቀሱት የአምልኮው ስፍራ መቅደሱ ፈርሶ፣ ክብር ለእስራኤል አምላክ፣ ቅኔ ለታላቁ ጌታ መሆኑ ቀርቶ ሰው ሰውን እያወደሰ የሚኖርባት መሆኑን ባሰቡ ጊዜ ነው፡፡ ጽዮንን ባሰቧት ጊዜ ያለቀሱት ለዝማሬ የሚቀጣጠሩበት፣ ለአምልኮ የሚወጡበት፣ በኅብረት የሚቀድሱበት ቀን በመቅረቱ ነው፡፡
ጽዮንን ባሰቡ ጊዜ ያለቀሱት አስተማሪ ነቢይ፣ መካሪ ካህን፣ በቅን የሚፈርድ ንጉሥ የሌለባት፣ መዋቅሯ ከባቢሎን ሥጋዊ መዋቅር እንኳ ያነሰ መሆኑን ባሰቡ ጊዜ ነው፡፡
እናንተስ ጽዮንን ባሰባችሁ ጊዜ ታለቅሱ ይሆን; ለማልቀስም ጉልበት ይጠይቃልና ጉልበት ካላችሁ ለጽዮን አልቅሱ፡፡ ከውሽሞቿ ሳይሆን ከባሏ እንዲያፋቅራት፣ ልጆቿ ወደ ቅጥሯ እንዲመለሱ፣ የእርቅና የሰላም ቀን እንዲታወጅባት፣ መቅደሷ እንደገና እንዲሠራ፣ ቅጥሯ እንደገና እንዲገነባ ለጽዮን አልቅሱ! ምሕረቱ ብዙ የሆነ ጌታ ዕንባን ተሻግሮ አይሄድምና አልቅሱ። እግዚአብሔር መልስ አለው፡፡