Wednesday, February 29, 2012

ዳንኤል ክብረት፣ ዘበነ ለማና ምህረተአብ ሃዋሳ ላይ ለመስበክ መመሪያ አይፈቅድላቸውም!

 የአቡነ ገብርኤል የገጽታ ግንባታ ተግባር!

የተሰደዱት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ጉባዔውን ለማደናቀፍ ምንም ዓይነት ዕቅድ እንደሌላቸው አስታወቁ

በሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ከመጪው የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ መንፈሳዊ ጉባዔ ሊዘጋጅ እንደሆነ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ስምዓ ጽድቅ ተከፋይ ዐምደኛ መልአከ ብርሃን ይትባረክ ታጠቅ ድምፅ ማጉያ ይዘው በሹሽሹክታ ለሕዝብ መናገራቸውን መግለጻችን ይታወሳል፡፡  በሀዋሳ ዳቶ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ለእመቤታችን በዓለ ንግሥ ለተሰበሰበው ሕዝብ ዳንኤል ክብረት፣ ዘመድኩን በቀለና ዘማሪ ቴዎድሮስ ዮሴፍ ሄደው እንደሚያስተምሩ መናገራቸውን ጭምር መግለጻችን አይዘነጋም፡፡ ሆኖም አሁን በደረሰን መረጃ ሄደው የሚያስተምሩት መ/ር ዘበነ ለማ ከአሜሪካ፣ ዳንኤል ክብረት፣ መ/ር ምሕረተአብ አሰፋ፣ ዘማሪ ቴዎድሮስ ዮሴፍና ሌሎችም ስማቸው ያልተገለጹ ሰዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ የመ/ር ዘበነ ባይታወቅም ዳንኤል ክብረት ከፍተኛ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አመራር፣ እንዲሁም መ/ር ምሕረተ አብ አሰፋ የ"ማኅበሩ" አባልና ደጋፊ በመሆናቸው ሄደው ለማስተማር ቀደም ሲል የተላለፉ መመሪያዎች እንደማይፈቅዱላቸው ታውቋል፡፡ እነዚህም:-
  1. ክቡራን የመንግሥት ሚኒስትሮች በታዛቢነት በተገኙበት አቡነ ገብርኤል ራሳቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ሆነው መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም በተካሄደው የሠላም ጉባዔ የወሰኑትና የፈረሙበት "ማኅበረ ቅዱሳን" በማናቸውም የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ ጥቅምት 6 ቀን 2002 ዓ.ም በቁጥር 44/70/2002 መመሪያ ወጥቷል፡፡
  2. የሀዋሳን ግጭት ለማብረድ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የተመራው አጣሪ ቡድን ያቀረበው ሪፖርት ግጭቱ የተከሰተው ተስፋ ኪዳነ ምሕረትና ፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ማኅበር እና "ማኅበረ ቅዱሳን" ባስነሱት ሁከት መሆኑን ይገልጽና ተስፋ ኪዳነ ምሕረት ማኅበርን ጨምሮ "ማኅበረ ቅዱሳን" እንደማንኛውም ተቋምና ግለሰብ አስቀድሶና ተገልግሎ ከመውጣት በስተቀር በቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡና በዐውደ ምሕረት ላይ እንዳያስተምሩ፣ የካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም በቁጥር 92/54/2003  ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት መመሪያ ተላልፏል፡፡
  3.  የተሰደዱት የሀዋሳ ምዕመናን፣ ምዕመናትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እንዲከበርና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ለ"ማኅበረ ቅዱሳን" ወግነው ባደረሱት የመልካም አስተዳደር በደል ሳቢያ ከሀገረ ስብከቱ እንዲነሱ ባካሄዱት የአንድ ዓመት ከ8 ወራት የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ መሠረት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልዓተ ጉባዔ ስብሰባ ተጠርቶ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ሌላ አጣሪ ኮሚቴ ለአራተኛ ጊዜ ወደ ሥፍራው እንዲላክና ችግሩን አጥንቶ ለግንቦት 2004 ዓ.ም እንዲያቀርብ ወስኗል፡፡ እስከዚያው ድረስም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሁሉንም ልጆች አቅርበው አስማምተውና አቻችለው በአባትነትና በልጅነት ስሜት ሠላም እንዲያሰፍኑ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ታህሣሥ 26 ቀን 2004 ዓ.ም በቁጥር ል/ጽ/200/27/04 መመሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ይህ ብቻም አይደለም፤ መምህር ዘበነ ለማ የሚንቀሳቀሱት በሀገር ውስጡ ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ስላልሆነና ውጭ ሀገር ባለው ሲኖዶስ በመሆኑ የቤተክርስቲያናችን ዕውቅና የላቸውም፡፡ ዳንኤል ክብረትና መ/ር ምሕረተአብ አሰፋ ወደ ሀዋሳ ሄደው የሚያስተምሩ ስለመሆናቸው የጠቅላይ ቤተክህነትና የስብከተ ወንጌልና ሐዋሪያዊ ተልዕኮ መምሪያ ፈቃድ የላቸውም፡፡ ስለዚህ፣ ሦስቱም ሰባኪዎች "ሕገወጥና ፈቃድ የሌላቸው አጉራ ዘለል ሰባኪዎች በየሀገረ ስብከቱ ሄደው እንዳያስተምሩ" የወጣው መመሪያ እንደሚግዳቸው ታውቋል፡፡


በሌላ በኩል አቡነ ገብርኤል ሕግና መመሪያን በመጣስ የሀገረ ስብከቱንና የአጥቢያ ቤተክርስቲያናትን መዋቅሮች ከላይ እስከታች በግጭቱ ወቅት ድንጋይ አንስተው ይደባደቡ በነበሩት የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት በመሰግሰግ ገሃድ የወጣ ግጭት አባባሽ ተግባር ፈጽመዋል፤ እየፈጸሙም ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ ለዓላማቸው ከጎናቸው ያልቆሙትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የክህነት ሥልጣን ያላቸውን አገልጋዮች አባረዋል፣ ከደመወዝና ከደረጃ ዝቅ አድርገው አስቀምጠዋል፣ አዛውረዋል፤ በጋጠወጥነትና በተደጋጋሚ የዲስፕሊን ችግር የታወቁ ካህናትን ከየተዛወሩበት አምጥተው በዙሪያቸው ኮልኩለዋል፡፡ "ለቤተክርስቲያን ሀብታሞቹ ናቸው ያሏት" በማለት፣ ድኆችን ከቤተክርስቲያን በማራቅ እፍኝ የማይሞሉ ጥገኛ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎችን አቅፈው ይዘዋል፡፡

አሁን ደግሞ፣ በእነዚህ ሕገወጦች ታጅበው በ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሰባክያንና ዘማርያን ከየካቲት 23 እስከ 25/2004 ዓ.ም መንፈሳዊ ጉባዔ ለማካሄድ በመዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡  የጉባዔው መዘጋጀት ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ አንደኛው "ማኅበረ ቅዱሳን" በሀዋሳ ዐውደ ምሕረት ላይ ቆሞ እንዳያስተምር የተላለፈውን መመሪያ የሚጥስ ነው፡፡ ሁለተኛው የ"ማኅበረ ቅዱሳን" መጥቶ እንዳሻው መፏለልና ሕዝብ የሚፈልገው እንዳያገለግል ማገድ ሕዝብን መከፋፈልና ግጭቱን ማባባስ ነው፡፡ ሦስተኛ፣ በሕገወጥነት መመሪያን በመተላለፍ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያን መዋቅሮች ውስጥ ለተሰገሰገው የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሠራዊት ሕጋዊ ሽፋንና ዕውቅና መስጠት ነው፡፡

ይህ በእንዲሀ እንዳለ አቡነ ገብርኤልና እፍኝ የማይሞሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴ አጃቢዎቻቸው ለስማቸው የመልካም ገጽታ ግንባታ ሌት ተቀን በመሯሯጥ ላይ መሆናቸውን ዘጋቢዎቻችን ገልጸውልናል፡፡ በተለይም "ለገብርኤል ገብርኤል መጣለት" ዶክቶር!! ዶክቶር!! ምሁር!! ምሁር!! እየተባባሉ መሞጋገስ፣ ስለ ራስ ክብርና ሞገስ ማውራት የተለመደ የዐውደ ምሕረት ላይ ትዕይንት እየሆነ መምጣቱን ምንጮቻችን አስታውቀዋል፡፡

አቡነ ገብርኤል በሲኖዶስ ፊት ሲሆን የተከፈለ፣ የተሰደደ ሕዝብ የለም ብለው እየዋሹ፣ ሀዋሳ ደግሞ ሲሄዱ የተሰደደውን ሕዝብ በጋራ እንዳይጸልይና የራሱን የወንጌል መርሐ ግብር ዘርግቶ ቃለ እግዚአብሔርን እንዳይከፈል፣ ሕዝብ እንዲታሰርና እንዲገላታ ለየፖሊስ ጣቢያውና ለየቀበሌው በመጻፍ፣ የፍትሕና ፀጥታ ቢሮዎች የግል ቢሮዎቻቸው እስኪመስሉ ድረስ ጠዋት ማታ በአካል የሚመላለሱ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከዚህም በላይ በስደት ላይ ያለው ሕዝብ እዚህ ግባ የማይባልና ተሃድሶ እንደሆነ አቡነ ገብርኤልን የሚያክል ትልቅ ሰው ዓይኑን በጨው አጥቦ ሲዋሽ እጅግ እጅግ የሚያሳፍር ነው ተብሏል፡፡ እርሳቸው ነገ ጠባ ወንጌል ከመስበክ ይልቅ የተለያዩ የማንቋሸሽና የስድብ ቋንቋዎችን በመጠቀም፣ የማጥላላት ዘመቻውን እየመሩ ሲሆን ሌሎችም ዲያቆናትና የቅኔ መምህር ነን ባዮች ዱካቸውን ተከትለው መሳደብ የየዕለቱ ተግባራቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች እንደታዘቡት፣ እነአቡነ ገብርኤል ትክክለኛ ችግራቸውን ፈትሸው ዕርቅና ሠላም በማውረድ ፈንታ በእልህ መንገድ ተጉዘው የመረጡት የብጥብጥና የክፍፍል ተልዕኮ ለመንግሥት፣ ለሕዝብ ወይም ለቤተክርስቲያን ለማንኛቸው ይጠቅም እንደሆነ ዞር ብለው ማሰላሰል አልቻሉም ይላሉ፡፡

የከተማው ሕዝብ ማን ምን እንደሆነ እውነቱን አብጠርጥሮ የሚያውቅ በመሆኑ በውሸታቸው እየተሰላቸ ያለሰዓቱ ከቅዳሴ አቋርጦ በመውጣትና ጉባዔያቸውን ባዶ በማድረግ ወደየቤቱ የሚሄድ መሆኑ ታውቋል፡፡


የቅጥር ግቢው ጭር ማለት ያሳሰባቸው አቡነ ገብርኤልና ሥራ አስኪያጁ ቢሳካላቸው እነ መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ፣ መ/ር አሰግድ ሳህሉ፣ ቀሲስ መ/ር ተስፋዬ መቆያ፣ መ/ር ገ/ሚካኤል፣ መ/ር አድነው፣ መ/ር ተረፈ አበራ፣ ዘማሪት ምርትነሽ ጥላሁን፣ ዘማሪት ዘርፌ ከበደ፣ ዘማሪት የትምወርቅ ሙላት፣ ዘማሪት ቅድስት ምትኩ፣ ዘማሪት ለምለም ከበደ፣ ዘማሪት ወርቅነሽ፣ ዘማሪት ሠላማዊት፣ ዘማሪት ጽጌረዳ ግርማ፣ ቀሲስ ዘማሪ  አሸናፊ ገ/ማርያም፣ ዘማሪ ዲ/ን ትዝታው ሳሙኤል፣ ዘማሪ እንግዳወርቅ በቀለ፣ ዘማሪ ፈቃዱ አማረ፣ ዘማሪ ዳግማዊ ደርቤ፣ ዘማሪ ዕዝራ፣ ዘማሪ ሀብታሙ ሽብሩ፣ ልዩ ልዩ የመዝሙር መሣሪያ ተጫዋቾች እና ሌሎችም ስማቸውን ዘርዝረን የማንጨርሰው ውድ የቤተክርስቲያኒቱ ሰባክያንና ዘማርያን ልጆች ሲያገለግሉ እንደነበረው ጊዜ ቅጥር ግቢው ሞልቶ ተርፎ ወደ አደባባይ እስኪፈስ በሕዝብ ለማጨናነቅና "ይኸው ሕዝቡ በአንድነት እያመለከ ነው" ለማሰኘት ልዩ ልዩ ስልቶችን ነድፈዋል፡፡  

ከእነዚህ ስልቶች አንዱ መ/ር ዘበነ ለማን ከአሜሪካ በማምጣት በተለይም ዳንኤል ክብረት ቢመጣ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አራቱ ካምፓሶችና ከከተማው እንዲሁም ከአካባቢው አቅራቢያ ወረዳዎች የማኅበረ ቅዱሳንን ሠራዊት ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦ በማግተልተል ቪዲዮ በማስቀረጽና በግንቦቱ ሲኖዶስ "ይኸው ሕዝቡ በደስታና በአንድነት እያመለከ ነው፡፡ አቡነ ገብርኤል ሕዝቡን ወደ አንድነት ያመጡ የሠላምና የወንጌል አባት ናቸው፤ ይህንን መረጃ ተመልከቱ" ብሎ የቪሲዲ ማስረጃ ለማጠናቀር ነው ተብሏል፡፡

ይህ ብቻም አይደለም ትላልቅ ፖስተሮችን በከተማዋ ልዩ ልዩ ቦታዎች በመለጠፍ፣ አነስ ያሉ ፖስተሮችን በየንግድ ቤቱና በየባጃጁ በመለጠፍ እንዲሁም የንስሐ አባቶች ወደ የንስሐ ልጆቻቸው ሄደው በነቂስ እንዲወጡ መቀስቀስ እንዳለባቸው ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት የከተማዋ ሕዝብ እንደማይወጣ ስለሚታወቅ የአጥቢያ ነዋሪዎችን አስመስሎ አጥቢያውን የማይወክሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችንና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሠራዊትን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለማዋል መሆኑን ውስጥ ዐዋቂ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በስደት ላይ የሚገኙት የሀዋሳ ሰንበት ት/ቤት አባላት ጉባዔውን ለማደናቀፍ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ ተደርጎ በአንዳንድ ብሎጎችና ፌስቡኮች የተሠራጨው ዘገባ ትክክል እንዳልሆነና እነርሱንም እንደማይመለከት ወደ ሀዋሳ ደውለን ያነጋገርናቸው ልዩ ልዩ አባላቶቻቸው አረጋግጠውልናል፡፡ የዚህ ዘገባ ምንጩና ዓላማው ምን እንደሆነ አልገባንም ያሉት እነዚህ ወገኖች፣ "ማኅበረ ቅዱሳን" ሆን ብሎ ራሱ ያሠራጨው ሐሰተኛ ዘገባ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል፡፡

አባላቱ እንደሚሉት፣ "እነአቡነ ገብርኤል የራሳቸው ጥላ እያስበረገጋቸው፣ ዘወትር በዓል በመጣና ጉባዔ በተዘጋጀ ቁጥር የተሰደዱት ምዕመናን፣ ምዕመናትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በኃይል ሊያስወግዱን ነው፣ ሊረብሹን ነው፤ ስለዚህ እሠሩልን፣ ደብድቡልን እያሉ የፍትሕና የፀጥታ ክፍሎችን በስልክ፣ በደብዳቤ እና በአካል መወትወት ልማዳቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ታላላቅ በዓላትን አሳልፈናል፤ እስካሁን የደረሰባቸው ነገር የለም፤ ለወደፊቱም እግዚአብሔር ስለዋጋቸው ከሚከፍላቸው በስተቀር በእኛ ዕቅድና ፍላጎት የምናደርገው ነገር የለም" ብለዋል፡፡

"ጉባዔው ፍጹም ሕገወጥ እንደሆነ ብናውቅም ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ መንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤትና ስብከተ ወንጌልና ሐዋሪያዊ ተልዕኮ መምሪያ የሚያደርጉትን ከመጠበቅና አቡነ ገብርኤል የሚያካሄዱትን ሥርዓተ አልበኝነት ከምንታዘብ በስተቀር ምን ልናደርግ እንችላለን"? ብለው ጥያቄን በጥያቄ መልሰዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የዝግጅት ክፍላችን፣ "ከቤተክርስቲያን ተገንጥላችሁ፣ የራሳችሁን ሌላ እምነት እየተከተላችሁ ነው የሚባለው ምን ያህል እውነት ነው" ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄም ሁሉም አንድ ዓይነት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ "ይህ የሰይጣን ወሬ ነው፤ ከቤተክርስቲያን ተለይተን የወጣነው ተገንጥለን ሳይሆን በአቡነ ገብርኤል አዛዥነት ባጅ የተለጠፈላቸው የማኅበረ ቅዱሳን ሠራዊትና ጥቅመኛ ፖሊሶች ድብደባ ስላበዙብንና ለማስቀደስ ብቅ ስንልም እየተጠቋቆሙ ስለሚያሲይዙን ነው፡፡ ስለዚህ፣ በስደት ላይ የምንቆየው፣ ሁላችንንም ኑ ልጆቼ የሚለን፣ በጎቹን፣ ጠቦቶቹንና ግልገሎቹን በትጋት የሚጠብቅ አባት እረኛ  እስኪመደብልንና ዕርቀ ሠላም እስኪወርድ ድረስ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ጥሞና ያለበት ጾምና ጸሎት ይዘን በጋራ የወንጌሉን ቃል እየተማማርን ነው፡፡  ወደተለያዩ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት እየሄድንም እናስቀድሳለን፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ላይ ያለን እምነት በጥልቅ አለት ላይ እንደተመሠረተ ግንብ ነው፡፡ ነፋስ መጣ ገፋውም ሊወድቅ አልቻለም፡ ይኸው እስከዛሬ ጸንተናል" በሚል ጠንካራ መንፈስ መልሰውልናል፡፡ dejeselaam blog