Saturday, February 18, 2012

የቤተክርስቲያን መታደስ!

ክፍል ፪ 


ኦርቶዶክስ ተሃድሶዎች

በአንደኛ ደረጃ ያስቀመጥናቸው ኦርቶዶክስ ተሃድሶዎች በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ የሚያምኑ ሲኖዶሱ ቀኖና ማውጣት እንደሚችል ቀኖናውን መቀበልና ማክበር እንደሚገባ የሚያምኑ ናቸው :: ሆኖም ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያን ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ አለባት በለው ለውጥ የሚናፍቁ ናቸው :: እነዚህ ቡድኖች እንዳይገለሉ የሚፈሩ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ ለውጥ ብታደርግ የተሻለ ትጠናከራለች ብለው የሚያስቡ ናቸው :: ህዝቡን ለመያዝና አብዛኛው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምእመን ንቁ ክርስቲያን ሆኖ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ጉዳዮች ዙሪያ ቀኖናዊ ለውጥ ብታደርግ ጥሩ ነው ብለው የሚናገሩ ናቸው :: በአብዛኛው ጊዜ ፍላጎታቸውን በቀጥታ ባይናገሩም በእውቀት ዳብሯል ብለው ለሚያስቡት ሰው ግን ሃሳባቸውን ይገልጻሉ ::

እነዚህ ቡድኖች እንደ ምሳሌ የሚወስዱት የእህት አብያተ ክርስቲያናትን የአምልኮ ስርአትና ነው በተለይም የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የአምልኮ ስርአት ብዙ ጊዜ ይጠቅሳሉ :: የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትምህርተ ሃይማኖት ደረጃ አንድ ሊባል የሚችል እምነት ያምናሉ በጣም ጥቂት ልዩነቶች ከመኖራቸው ውጭ ዶግማችንና እንዲሁም የቅዳሴው ጸሎት ይዘትም አንድ ሊባል የሚችል ነው :: አብዛኛው ቀኖናቸውም እንዲሁ ይመሳሰላል :: ለምሳሌ የክህነት አሰጣጣቸው፡ የጳጳሳት ስልጣናቸው፡ የቤተ ክርስቲያን አስራራቸውና አከባበራቸው፡ የበአላት ቀናቸው፡ የጾም ጊዜቸው፡ የጾም አጿጿማቸው፡ የንስሃ አገባባቸው እና የመሳሰሉት የሚመሳሰሉ ናቸው ::

በአንጻሩ በማህበር ሆነው በሚያደርጓቸው አምልኮዎች ላይ አንዳንድ ልዩነቶች ይለያያሉ :: አብዛኛዎቹ ልዩነቶች በሚከተሉት ማጠቃለል እንችላለን
1.እነርሱ ላይ የሌሉ እኛ ላይ የሚደረጉ ጸሎቶች
2.እነርሱ ዘንድ የማይከለከሉ እኛ ላይ የሚከለከሉ ስርአቶች
3.እነርሱ የሚያደርጓቸው እኛ የማናደርጋቸው ስርአቶች
4.እኛ የምናደርጋቸው እነርሱ የማያደርጓቸው ስርአቶች

በአብዛኛው የልዩነቶች ምክነያቶች ሊሆኑ የሚችሉ ተብለው የሚጠቀሱ የሚከተሉት ናቸው
1.ኢትዮጵያዊያን ክርስትናን ከመቀበላቸው በፊት ኦሪትን አምነው ይኖሩ የነበሩ መሆናቸው
2.ኢትዮጵያውያን በነጻነት አምልኮተ እግዚአብሔርን ሲፈጽሙ መኖራቸው በአንጻሩ የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ለብዙ አመታት በእስልምና ተጽኖ ውስጥ መቆየትዋ
3.ግብጾች ስርአታቸው ላይ በሲኖዶስ ድንጋጌ መሰረት በቅርብ ጊዜ ለውጥ ማካሄዳቸው
4.የግብጽ ኦርቶዶክስ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፋ አሁን በውስጣዊ መረጋጋት ላይ መሆንዋ ሊቃውንቶችዋ በተለይም ፓትሪያርኳ ቤተ ክርስቲያኒቷን በዘመናዊ መልኩ መምራታቸው ለአዲሱ ትውልድ ስለሃይማኖቱ በቀላሉ ሊያገኘው የሚችል መጻህፍትን መጻፋቸው
እነዚህ ተሃድሶዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ልዩ ልዩ ክፍል አላቸው እነዚህንም እንደሚከተለው እንመለከታለን :

/ እህት አብያተ ክርስቲያናት ላይ ቀለል የሚሉ ስርአቶች እኛም ላይ ተፈጻሚ ይሁኑ ይህንን ያደረገ እንደሚኮነን መነገር የለበትም።


1.ኮፕቶች ጫማ አድርገው ስለሚገቡ እኛም አድርገን ቤተ ክርስቲያን እንድንገባ ቢደረግ ወይም፡ባይደረግ እንኳን ሰው በዚህ እንደሚኮነን ባይሰበክ፣
2.ኮፕቶች ላይ የበአላት ቁጥር ስለሚቀንስ እኛም ጋር ይቀነሱ፡ ወይም በዓላትን ስለማክበር አዲስ ኪዳን ትእዛዝ ሳይሰጥ በዚህ የተነሳ ሰው በዓል ማክበር የግድ እንደሆነ አድርጎ ባይወራ
3.ኮፕቶች የማይጠቀሟቸው እንደ ተአምረ ማርያም ያሉ መጻህፍት እኛ ላይም ከአገልግሎት ቢቀሩ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚጋጨውን ሁሉ ቢታረም፣
4/ ስለነገረ ድኅነቱ ስንናገር በክርስቶስ ማዳን ላይ እንጂ በሌላ መንጠላጠል እንደሚቻል ቢታረም

/ በብሉይ ኪዳን የተከለከሉ እና በቤተ ክርስቲያን በባህልና በስርአት የተከለከሉ ነገሮች ይቅሩ

አንዳንድ ጉዳዮች በብሉይ ኪዳን በግልጽ የተከለከሉ በሌሎች ክርስቲያኖች ዘንድ ክልክል ያልሆኑ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ግን በቀኖና ውስጥ የተካተቱ ወይንም በልማድ የሚደረጉ ጉዳዮች አሉ :: እነዚህን ጉዳዮች ተሃድሶዎች ቀለል ወዳለው መንገድ እንዲሄዱ ይፈልጋሉ :: ለምሳሌ
1.ሴቶች በወር አበባ ጊዜም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳይገቡ መከልከል ያለባቸው ከንጽህና አንጻር ካልሆነ ከርኩሰት መቆጠር የለበትም ይላሉ
2.ስጋዊ ጉዳት የማያመጣ ከሆነና ባህላችን የሚፈቅደው ከሆነ ማነኛውንም ነገር ባርከን መብላትን ቤተ ክርስቲያን አትከለክልም ልማዳችን እንጂ ይላሉ
3.ክርስቲያኖች ተራክቦ ፈጽመውም ቢሆን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳይገቡ መከልከል የለባቸውም ይላሉ።

ሐ ዘመናዊ ከማድረግ ጋር የሚያነሷቸው ጥያቄዎች
1.በኦርጋን መዘመር ይፈቀድ : በኦርጋን መዘመርን ብቻውን ያወጣሁት ብቻውን ስለሚጠቅሱት ነው :: እነዚህ አካላት በስፋት መዝሙርና የሙዚቃ መሳሪያን በተመለከተ በጻፉበት ዌብ ሳይት ላይ እንደጠቀሱት በልዩ ልዩ ጊዜያትም እንደሚናገሩት ኦርጋን በእኛ አርጋኖን ተብሎ ይጠራል ይላሉ :: ይህ ከሌላ ወገን ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው :: በአርጋኖን መዘመርን ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ መዝሙር መሳሪያዎች ባወጣው ቀኖና ላይ ይፈቅዳል ብለው ይከራከራሉ ለዚህም ሐመር መጽሔት የጻፈውን ጽሑፍ እንደ መረጃ አድርገው ያቀርባሉ :: በሌላ በኩል የሓመር ጸሑፍ እንደሚያሳየው /ወይንም ጸሓፊው እንደተረዳው / ኦርጋንና አርጋኖን የተለያዩ እንደሆኑ ነው ::

http://www.ethiopianorthodox.org/churchmusic/musicrelateddoc/synodos%202.pdf
1.በሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎች መዘመር ይፈቀድ : እነዚህ አካላት አሁን ስለሚጠቀሙበት ኦርጋንን በቤተ ክርስቲያን ከቀድሞ ስንጠቀምበት የኖርን ነው ቢሉም ሌሎች ዘመናዊ መሳሪያዎችን መጠቀምም እንዲፈቀድ ይፈልጋሉ :: በእነዚህ መሳሪያዎች መዘመርን የሚፈልጉት ለምን እንደሆነ ሲጠየቁ መልካም ድምጽ ስለሚያሚያወጡና ቤተ ክርስቲያንን ዘመናዊ ለማድረግ ነው ይላሉ :: ከኃጢአት ጋር የሚያገናኘው ሳይኖር እንደዚያ ማሰብ ትክክል አይደለም ይላሉ።

መ ህዝብን ከመያዝ ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች

የሚከተሉት ጥያቄዎች ብዙም ደጋፊ ያላቸው አይሆኑም እንኳን በእኛ ቤተ ክርስቲያን ይቅርና በሌሎች ኦርቶዶክሶችም ዘንድ ጥያቄውን የሚያነሱ ያሉ አይመስለኝም ::ሆኖም አንዳንዶች የሚከተለውን ጥያቄ ሲያቀርቡ ይታያል
1.ከአጽዋማቱ ውስጥ የነነዌ ጾምን ሌላ ስም ብንሰጣት ለምሳሌ የኢትዮጵያ ጾም ብንላትና ስለአንድ ነገር ለምሳሌ ስለሓገራችን እያሰብን በአንድነት የምንጾመው ጾም ቢሆን
2.አጽዋማቱ በመብዛታቸው ብዙው ኦርቶዶክሳዊ እየጾመ አይደለም በመሆኑም የጾሞችን ቁጥር ብንቀንሰውና አብዛኛው ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን እንዲጾም ቢሆን

የጸሓፊው አስተያየት እና እውነታዎች

እነዚህ የቀረቡት ጉዳዮች ትክክለኛነታቸው እና ጠቀሜታቸው ምን ያክል ነው ? ከቤተ ክርስቲያን እምነት ስርአትና ትውፊት አንጻርስ ምን ያክል ጥቅምና ጉዳት አላቸው የሚለውን እንመልከት ::

እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን የራሱ የሆነ ባህልና ስርአቶች አሉት :: እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ በራሱ ይዟቸው የመጣ ትውፊቶች በህዝቡ ዘንድ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ባህሎች አሉት :: ያ ባህል ከሃይማኖቱ ጋር እስካልተጋጨ ድረስ መጠበቁና ለትውልድ መተላለፉ ጠቀሜታ አለው :: ከእኛ ቤተ ክርስቲያን ወጣ ብለን በካቶሊኮች በምስራቅ ኦርቶዶክሶች እንዲሁም በፕሮቴስታንቶች ዘንድ የምናገኛቸው ልዩ ልዩ ባህሎች አሉ :: እነዚህ ባህሎች ደግሞ ለሃይማኖቱ መጠበቅም ጥሩ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ :: የራሳችንን ትተን በሌላ ቤተ ክርስቲያን ያየነውን ሁሉ እናምጣ ማለት ማንነትን አለማወቅ ነው ::

ቤተ ክርስቲያን አብዛኛው ስርአትዋ የተመረኮዘው እግዚአብሔርን ከማክበርና ራስን ዝቅ ከማድረግ አንጻር ነው :: ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያን ጫማ አድርገን እንዳንገባ የከለከለችው በትህትናዋ እና በእምነትዋ ነው :: እምነትዋ በጸሎት ጊዜ እግዚአብሔር አብሮኝ ይኖራል (ማቴ 18:16) ለሰሎሞን የገባውን ቃል ኪዳን እስከዛሬ ያጸናል እግዚአብሔር ወደ ቤተ መቅደሱ ይመለከታል (1ኛነገ 9:3) እግዚአብሔር የሚገለጥበት ቦታ ቅዱስ ነው (ዘጸ 3:5) የሚል ሲሆን ትህትናዋ ደግሞ ቅዱስ የሆነው እግዚአብሄር በረድኤት በሚገኝበት ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዴት ጫማ አድርጌ እገባለሁ ብላ ነው :: ታዲያ ይህ እምነትና ትህትና ዘመኑ ስላደገ ኑሯችን ስለተሻሻለ ጫማ መግዛት ስለቻልን ብንለውጠው ጥሩ ይሆንን ?

በአላት እግዚአብሔር በራሱ ወይንም በወዳጆቹ አማካኝነት ታምራት የተደረገባቸው ቀናት በመሆናቸው መታሰብ ይገባቸዋል :: ለታምራቱ መታሰቢያን አደረገ እንዲል መጽሓፍ (መዝ 111:4):: በአላት የእግዚአብሔርን ቸርነት ምህረት ድል አድራጊነት የቅዱሳንን ተጋድሎ ጽናት መታሰቢያ በረከት የምናስብባቸው ናቸው :: እነዚህ ደግሞ በእምነታችን እንድንጠነክር መልካም እንድናደርግ ፈተናን እንድናልፍ የሚረዱን ናቸው ::

በአንጻሩ በሃገራችን በአል ሲባል በአብዛኛው ስራ ፈትቶ መቀመጥ የሚለውን ነገር የሚያመለክት ነው ::በቋንቋው ራሱ በአል ሲባል ስራ ማቋረጥ እንደማለት ስለሆነ የመንግስት በአል እንዲባል :: በእንግሊዘኛው ቋንቋ የተሻለ ቃል የሚጠቀም ይመስላል ሁለቱን የተለያየ ትርጉም ይሰጣቸዋል :: (Holyday is defined as a day of festivity or recreation when no work is done and Feast is defined as a periodic religious observance commemorating an event or honoring a deity, person, or thing. so they have different meanings)::

ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ስርአት ራሱ የሚከለክላቸው ጥቂት በአላትን ብቻ ነው ቢባልም መጻህፍቱ ግን በአብዛኛው ስራ እንዳይሰራ የሚያዝዙ ናቸው :: ለምሳሌ ታምረ ማርያም 33 በአላትን በእመቤታችን ስም ምንም ስራ እንዳይሰራባቸው ይከለክላል :: ወደ እውነታው ስንመጣ ግን ከተጻፈው 33 በአላት ውስጥ ምን ያክሉ ይከበራሉ ? መጻህፉ የሚያዝዘው እንደ እሁድ ሰንበት እንዲከበር ነው :: ይህ አባባል በሁለት መንገድ ከበድ ያለ ነው :: አንደኛ መከበር ያለበት ምንም ስራ ሳይሰራ እንደ እሁድ ሰንበት ነው ሲል ሁለተኛ ደግሞ ያላከበሩት ደግሞ መወገዛቸውን ይገልጻል :: ወደ እውነታው ስንመጣ ግን እንደ እሁድ ሰንበት በአላቱን እናከብራቸዋልን ? ብሎ እንደ እኔ የሚጠይቅ ሰው ቢኖር በእኔ አስተያየት 5% ኦርቶዶክሳዊ እንደ እሁድ ሰንበት የሚያከብረው ከተገኘ መልካም ነው :: ይህ ከሆነ ደግሞ ከአንባቢው ካህን ጀምሮ ውግዘቱን እየያዝን ወደ ቤታችን እየሄድን ነው ማለት ነው :: ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች በአላት ላይም ቤተ ክርስቲያን የሰራችው ስርአትና ምእመኑ ላይ ያለው የአባበር ስርአት የሚስማማ አይደለም ::

ስለዚህ በአላትን ማሰቡ መታሰቢያነቱ ይቅር መባሉ የሚደገፍ አይደለም አከባበሩን ላይ ግን ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋል :: ስሙንም በአል ከማለት መታሰቢያ ብንለው ጥሩ ግንዛቤ የሚሰጥ ይመስላል :: ቤተ ክርስቲያንም በአላቱን መቀነስ ሳይሆን አከባበሩን የተሻለ ማድረጉ መንፈሳዊነቱን ሳይጎዳ ለምመናንም ሳይከብድ ማክበር ይቻላል :: ካህናቱና ምእመናኑ በመታሰቢያ ቀናት እለት ቤተ ክርስቲያን ሄደው እግዚአብሔርን አመስግነው የቅዱሳንን በረከት ተሳትፈው መመለሱ መቸም ባይቀር ጥሩ ነው :: ብዙዎቹን በአላት ስራ ሳይሰራ ይከበር የሚለው አስተሳሰብ ግን ትንሽ ከበድ ያለ እና እውነታውን ያላገናዘበ ይሆናል ::: በአበይት በአላት ቀን ስራ ባይሰራም ከአከባበራቸው አንጻር የሚያስሄድ ነው :: የሚወስነው አካል መወሰን ይገባዋል።

የምንጠቀምባቸውን መጻህፍት እንቀንስ ጸሎቱ ይቀነስ ስለሚሉት : ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ስለማይጠቀሟቸው እኛም እንተዋቸው የሚለውን ከጸሎቱ አካሄድና ትርጉም ጋር ማየቱ ይጠቅማል። :: ምክነያቱ ደግሞ እኛ የሌሉን እነርሱ ያሏቸው እንዳሉ ሁሉ እኛ ያሉን እነርሱ የሌላቸው መጻህፍት መኖራቸውን መቀበል አለብን :: እነርሱ መጻህፍቱን በልዩ ልዩ ምክነያት አጥተዋቸዋል ወይንም ትተዋቸዋል :: መተውና ማስተካከል የተለያዩ ስለሆነ ሁሉንም በየፈርጁ ማየት ይገባል።
በማጠቃለያ ኦርቶዶክስ ተሃድሶዎች የሚሉት ቤተክርስቲያንን መለወጥ ሳይሆን በአመራሩ ደረጃ ያረጀ፣ ያፈጀውን አካሄድ በዘመኑ ደረጃ ማሻሻል፣ በእምነቱ ይትበሃል ውስጥ ጣልቃ የገባውን ስህተት ማረምና በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ማስተካከል የሚል መንፈስ የያዘ ነው። ዶግማን በተመለከተ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሰፋ ስህተት አለ ብለው አያምኑም። ስህተቱ ትውፊቱንና ባህሉን ከሃይማኖታዊ ዶግማ ጋር በማቀላቀል የነገረ ድኅነትን ጉዳይ መልክ የሌለው አድርጎታል ባዮች ናቸው።
ከቄስ ዘእግዚእነ (cyber Ethiopia.WARKA)