Friday, February 24, 2012

ለእንዳለ ገብሬ 200ሺህ ተዋጣ!


ቀሪውን 250 ሺህ ብር ሰፋ ባለ መርሐ ግብር ለማሟላት ዕቅድ ተይዟል
በከፍተኛ የልብ ሕመም በመሰቃየት ላይ ላለው ወጣት እንዳለ ገብሬ መታከሚያ በአንድ ቀን መንፈሳዊ አገልግሎት 200 ሺህ ብር ያህል ማሰባሰብ መቻሉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ (ታሪኩን በይበልጥ ለመረዳት፣ ከዚህ ቀደም ሲል ስለ ወጣቱ ችግር ካወጣናቸው ዘገባዎች ጋር ያስተያዩት) ይህንን ያህል ገቢ ሊሰባሰብ የቻለው በአሁኑ ወቅት "ማኅበረ ቅዱሳን" በሚያሳድዳቸው ውድ የሆኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የስብከተ ወንጌልና የመዝሙር አገልጋዮች ባዘጋጁት መንፈሳዊ ጉባዔ ነው፡፡
የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሻላ 17 17 መናፈሻ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ በግል በአድራሻ ጥሪ የተደረገላቸው ሦስት መቶ ያህል ሰዎች ተገኝተው ግማሽ ያህሉን ገንዘብ የለገሡ ሲሆን ቀሪውን ግማሽ መጠን በቃል መግቢያ ሠነድ እንደሚሰጡ ማረጋገጣቸው ታውቋል፡፡ የዕለቱን መርሐ ግብር የመራው መምህር ተረፈ አበራ ሲሆን፣  መምህር ታሪኩ አበራም በበኩሉ የወደቀውን ስላነሳው የደጉን ሣምራዊ ታሪክ ከወንጌል ጋር በማጣቀስ፣ ችግር ላይ የወደቁትን ወገኖች መርዳት ክርስቲያናዊ ግዴታችን መሆኑን ሰፋ ባለ ሁኔታ ትምህርት ሰጥቷል፡፡


በዕለቱ መርሐ ግብር መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ እና መምህር አሰግድ ሣህሉ የየበኩላቸውን መልዕክት ማስተላለፋቸው የተገለጸ ሲሆን ዘማሪ ቀሲስ አሸናፊ ገ/ማርያም፣ ዘማሪት የትምወርቅ ሙላት፣ ዘማሪት ምርትነሽ ጥላሁን፣ ዘማሪት ቅድስት ምትኩ እና ሌሎችም በዝማሬ ያገለገሉበት፣ ጉባዔው የተሳካና የተዋጣለት እንደነበር ታውቋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የታማሚውን ሕይወት ለመታደግ የዚህ ዓይነት ገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በስፋት መዘርጋት እንዳለበት ምዕመናን ያሳሰቡ ሲሆን ዝግጅቱም የተፈለገውን መጠን ያህል ብር ሊሰባሰብ እንደሚችል ያመላከተ ነው ተብሏል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞም፣ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ራሱ በሚመድባቸው አገልጋዮች ተመሳሳይ የገቢ ማሰባሰቢያ መንፈሳዊ መርሐ ግብር በጽ/ቤቱ አዳራሽ ይዘጋጅ ዘንድ ለሥራ አስኪያጁ ለብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፣ እርሳቸውም ዓላማውን እንደሚደግፉ ገልጸው፣ ሆኖም፣ ቀደም ሲል የነበረው ውዝግብ መስመር ባለመያዙ ለመፍቀድ እንደሚቸገሩ አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ፣ አገልጋዮቹ የጀመሩትን የወጣት እንዳለን ሕይወት የመታደግ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልት እንደሚደግፉ አስረድተው፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በሌሎች ሥፍራዎችም አዘጋጅተው ለመታከሚያ የሚሆነውን ድጋፍ ቢያሰባስቡ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡ በውይይቱ ወቅትም ምክትል የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጁ፣ የአስተዳደር መምሪያ ኃላፊውና የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊው መገኘታቸው ታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት አገልጋዮቹ በቅርብ ቀናት ውስጥ ቀሪውን ገቢ ለማሰባሰብ ሰፊ የወንጌል መርሐ ግብር ለመዘርጋት በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኤርትራዊው ተስፋዬ አዳነ እና ሌላ አንድ ናትናኤል የሚባል ግለሰብ የሚገኙበትና በዘሪሁን ሙላቱ የተመራ የጎረምሣ ቡድን ጉባዔውን ለማወክ ወንድወሰን የሚባል ግለሰብ በሚያሽከረክረው መኪና መጥቶ የነበረ ሲሆን ሥፍራው በተጠናከረ የፀጥታ ጥበቃ ሥር የዋለ በመሆኑ የብጥበጣ ሤራውን ሳይፈጽም ወደ መጣበት ለመመመለስ መገደዱን በቦታው የነበሩ እማኞች ገልጸዋል፡፡
ጎረምሶችን በመኪና ይዞ ሲያሽከረክር የነበረው ወንድወሰን ቀደም ሲል በጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት አዳራሽ ሊካሄድ የነበረውን ተመሳሳይ ዝግጅት እንዳይካሄድ የበኩሉን አስተዋፅዖ ያበረከተ ሲሆን፣ መርሐ ግብሩ ለሌላ ጊዜ እንደተላለፈ የሚያሳስበውን ማስታወቂያ ፖስተር የቀደደ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ወንድወሰንን በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች እንደገለጹት ከዚህ በፊት በኮስት ኔት Cost Net (ቁማር) ሰበብ ከሕዝብ ብር አግበስብሶ የዘረፈ ሲሆን ክትትል እንዳይደረግበትም ወደ ደቡብ አፍሪካ ሸሽቶ እንደነበር እና እዚያም በአንዲት ቤተክርስቲያን "አገልጋይ ነኝ"፣ "ክህነት አለኝ" በማለት አጭበርብሮ የቤተክርስቲያንን ገንዘብ መመዝበሩ ታውቋል፡፡ ከጊዜ በኋላም አረሳስቶ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሕንፃ ሥር የኢንተርኔት ቤት ከፍቶ እንደሚንቀሳቀስና "ማኅበረ ቅዱሳን"ን በጥፋት ተልዕኮ እንደሚያገለግል ታውቋል፡፡
"ማኅበረ ቅዱሳን"፣ በአሁኑ ወቅት በቅጥረኞች ዱርዬዎች የቸከና የሠለቸ የብጥብጥ ስልቱን ለማስፋፋት ቢሞክርም፣ የተፈለገውን ያህል ውጤት ሊያስገኝለት ካለመቻሉም በላይ፣ ይህንኑ ተንኮሉን ኅብረተሰቡ በንቃት እያስተዋለው ስለመጣ የፖለቲካ ኪሣራ እየደረሰበት መሆኑ ከየሥፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ በተለይም፣ የወጣት እንዳለ ገብሬ መታከሚያ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እንዳይሳካ በገሃድ ወጥቶ ያደናቀፈ ሲሆን "ስለቤተክርስቲያን ተቆርቁሬ ነው" ቢል እንኳን ወጣቱ የሚደገፍበትን ስልት ራሱ ነድፎ የክርስትና ወጉን በፈጸመ ነበር ሲሉ ታዛቢዎች ነቅፈውታል፡፡ የ"ማኅበረ ቅዱሳን"ን ከንቱ ጩኸት ያስተዋሉ ሰዎች እንደሚሉት ወይ አልረዳ፣ ወይም ደግሞ እንዲረዳ አልተመቸ፣ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ከዚህ ጎግ ወማጎግ ያላቃት ሲሉ የውስጣቸውን ብሶት ተንፍሰዋል፡፡
እግዚአብሔር ለወንድማችን ለወጣት እንዳለ ገብሬ ፈውስን ይስጥልን!!!
እርሱንም ለመታከም የረዱትንና የሚረዱትን ባወጡበት ይተካላቸው!!!
እግዚአብሔር ሁላችንንም ይጠብቀን!!!
አሜን!!!
Posted by Dejeselaam at 2:57 AM (dejeselaam blogspot)